የዘላለም ሕይወትን የማገኘው እንዴት ነው?
የዘላለም ሕይወትን እንዳገኝ የየትኛው ቤተ ክርስቲያን አባል መሆን አለብኝ የሚል ጥያቄ ያስጨንቆታል? የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ከእኔ የሚጠበቀውስ ምን ይሆን በሚል ሃሳብ ተወዛግበው ያውቃሉ? እርሶ ሃጢአተኛ በመሆኖ እና እግዚአብሔር ደግሞ ፍጹም ፃድቅ ስለሆነ የዘላለም ሕይወት ሊደረስበት የማይቻል እና የተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚያገኙት እንደሆነስ አስበው ያውቃሉ? ከእነዚህ ጥያቄዎች አንዱ የሚመለከትዎ ከሆነ ምላሹን እነሆ።
የዘላለም ሕይወት የሚለው ሃሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ38 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ባለው አገባብ (አውድ) መሰረት የዘላለም ሕይወት ማለት የሰው ልጅ በሰማያዊ ስፍራ በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ በተድላና በደስታ የሚኖረውን ቁጥር አልባ የሕይወት ዘመን ያመለክታል።
የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ላይ ካመፀበት ወቅት (ዘፍጥረት 3፡6) ጀምሮ፣ በሰራው ሃጢአት ምክንያት የተፈረደበትን ሞት (ሮሜ 6፡23) እየጠበቀ፣ ሕይወቱ ከስጋው የምትለይበትን ቅንጭብጫቢ እድሜዎች እየቆጠረ፣ በተስፋቢስነት የሚኖር ምስኪን ፍጥረት ነው። ከዚህ ውድቀት በኋላ የሰው ልጅ የሃጢአት ባሪያ ሆነ። ይህንን እውነት ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይገልፀዋል ‘‘ኢየሱስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው።’’ (ዮሐንስ 8፡34፤ ሮሜ 6፡17-18፤ ሮሜ 6፡20)።
የእግዚአብሔር ልጅ በመሆን ከዚህ እስራት የተፈታ ካልሆነ በቀር የሃጢአት ባሪያ የሆነ ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ደርሻ እንደማይኖረው የእግዚአብሔር ቃል በሚከተለው መንገድ ማስረጃ ይሰጠናል፣ ‘‘ባርያም ለዘላለም በቤት አይኖርም፤ ልጁ ለዘላለም ይኖራል’’ (ዮሐንስ 8፡35)።
መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ የሃጢአት ባርያ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ ለምን የሃጢአት ባሪያ እንደሆነም ይነግረናል። የሃጢአት ደራሲ ዲያብሎስ ነው (1ዮሐንስ 3፡8)። ሃጢአትን ያደረግነው በዚህ እርኩስ ፍጥረት ስር ስለተገዛን እነደሆነ ዮሐንስ በቁጥር 8 ላይ ይነግረናል። በዚህ መሰረት የሰው ልጅ የሃጢአት ባሪያ የሆነው በቅዱስ አምላኩ ትዕዛዝ ላይ አምጾ የዲያብሎስን ውሸት ለማድመጥ በመረጠ ወቅት (ዘፍጥረት 3፡1-8) እንደሆነ እንረዳለን።
የዘላለም ሕይወት ማለት ከዚህ ባርነት ነፃ መውጣት ማለት ነው። የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት እነማን ናቸው ብሎ መጠየቅ በሌላ አነጋገር ከዚህ እስር እና ባርነት ነፃ የሆኑት እነማን ናቸው ማለት ነው።
በዚህ ባርነት ውስጥ ያለ ሰው የሚያፈራው መልካም ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት አፀያፊ ነው (ሮሜ 8፡8)። የሚያፈሩት ፍሬ፣ የልጅ ሳይሆን የባሪያ ፍሬ ነውና በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ሊኖረው አይችልም። ከባርነት ሳይወጡ፣ በሃይማኖተኝነት በመነሳሳት፣ መልካም ስራ በመስራት፣ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት መሞከር ይቻላል። ሙከራው ግን ፍሬ ቢስ ነው። እግዚአብሔር በዚህ ደስ አይሰኝምና። የዘላለም ሕይወት የስራ ጉዳይ ሳይሆን የተፈጥሮ ጉዳይ ነው። የፍሬ ጉዳይ ሳይሆን የዛፍ ጉዳይ ነው። ከእሾህ ዛፍ የበለስ ፍሬ እንደማይቆረጥ ሁሉ ከአጣጥ ቍጥቋጦም የወይን ፍሬ አይለቀምም። ሁለቱንም አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር፣ ፍሬ ማፍራቸው ነው። የሚያለያያቸው ደግሞ የፍሬው አይነት ነው። በዲያብሎስ እና በሃጢአት ባርነት ስር ያለ ሰውም ሆነ ነፃ የወጣ፣ ሁለቱም ፍሬ ያፈራሉ። ስራ ይሰራሉ። ጥያቄው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው ፍሬ የቱ ነው የሚለው ነው። በባርነት ስር ሆነው እግዚአብሔር በፍሬያችን ደስ በማሰኘት የዘላለም ሕይወት እናገኛል ስለሚሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ መልዕክት አለው፣ ‘‘በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም’’ (ሮሜ 8፡8)። መጀመሪያ ፍሬው ሳይሆን ግንዱ መቀየር አለበት። ግንዱ ከተቀየረ ፍሬው መልካም ይሆናል። ስለዚህ የዘላልም ሕይወት ከተፈጥሯችን እንጂ ከመልካም ምግባሮቻችን ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። የግንድ ለውጥ ያደረገ፣ (የተፈጥሮ ለውጥ ያደረገ) የግንዱ ሕይወት ውጤት የሆነውን ፍሬ ማፍራቱ አይቀርምና።
በዚህ ምድር ላይ አፋቸውን ሞልተው ‘‘እግዚአብሔር የለም’’ የሚሉ ነገር ግን በሕይወታቸው በሚያደርጉት ሰናይ ምግባር አለምን ያስደመሙ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ታሪክ ለሚያገላብጥ እና አካባቢውን በትኩረት ለሚቃኝ ሰው እንግዳ ነገር አይደለም። እነዚህ ሰዎች በሚያደርጉት ልግስና፣ ታማኝነት፣ ታታሪነት በርካታ ተከታዮችን ለማፍራት የቻሉ መሆናቸውንም መዘንጋት የለብንም። አንዳንዶቹ ስለያዙት መልካም አላማ መሳካት ሲሉ ራሳቸውን ለሞት አደጋ እንኳ አሳልፈው ሰጥተዋል፣ እየሰጡም ነው። የዘላልም ሕይወት ጉዳይ የተፈጥሮ ጉዳይ ሳይሆን የመልካም ምግባር ጉዳይ ቢሆን ኖሮ እነዚህን ሰዎች በመንግስተ ሰማይ ባገኘናቸው ነበር። በዚህ ምድር ላይ ላበረከቱት መልካም ተጽዕኖ አክብሮት ቢኖረኝም፣ የዘላለም ሕይወት ተካፋዮች ስለመሆናቸው ግን ተስፋ ልንሰጣቸው አልችልም። ስለዚህ ስለዘላለማዊ ሕይወት ተገቢው ጥያቄ – ‘‘ምን ሰርቻለው?’’ ሳይሆን፣ ‘‘ከዚህ የዲያብሎስ እስራት ተፈትቻለው ወይ?’’፣ ‘‘ከሃጢአት ባርነት ነፃ ወጥቻለው ወይ’’፣ ‘‘ባሪያ ሳይሆን ልጅ ሆኛለው ወይ?’’ የሚለው ይሆናል።
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅ የሚያስፈልገውን አርነት የሚያውቅ አምላክ ነውና በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ይህንን የአርነት ስብከት መስበክ ጀመረ። ለዚህ የኢየሱስ ስብከት፣ ትምህርቱን የተቃወሙ አንዳንድ አይሁድ የሰጡትን ምላሽ እንመልከት። ኢየሱስም፣ ‘‘እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው። እነርሱም መልሰው። የአብርሃም ዘር ነን ለአንድም ስንኳ ከቶ ባሪያዎች አልሆንም፤ አንተ፣ አርነት ትወጣላችሁ እንዴት ትላለህ? አሉት። ኢየሱስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው። ባርያም ለዘላለም በቤት አይኖርም፤ ልጁ ለዘላለም ይኖራል። እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ። …እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ’’ (ዮሐንስ 8፡32-44፣)።
የዘላለም ሕይወትን የሚሰጥ ማን ነው?
የዘላለም ሕይወት ከእግዚአብሔር የሚሰጠን እና እኛ የምንቀበለው ውድ ስጦታ ነው። የሰው ልጅ በራሱ ማንነት እና ጥረት ሊያገኛት ስላልቻለ፣ እግዚአብሔር እንዲሁ በነፃ፣ ለሚቀበላት ሁሉ ሊሰጣት ወዷል። በዘላለም ሕይወት ውስጥ የእግዚአብሔር ድርሻ መስጠት ሲሆን የእኔ እና የእርሶ ድርሻ ደግሞ በእምነት መቀበል ነው።
የዮሐንስ ወንጌል 10፥28 ‘‘እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም።’’
የዮሐንስ ወንጌል 17፥1-2 ‘‘ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ወደ ሰማይ ዓይኖቹን አነሣና እንዲህ አለ፦ አባት ሆይ፥ ሰዓቱ ደርሶአል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ፥ በሥጋም ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠኸው፥ ለሰጠኸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ ልጅህን አክብረው።’’
1ኛ የዮሐንስ መልእክት 2፥25 ‘‘እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው።’’
1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፥11 ‘‘እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው።’’
ወደ ሮሜ ሰዎች 6፥23 ‘‘የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።’’
የዮሐንስ ወንጌል 5፥39 ‘‘እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤’’
የዘላለም ሕይወት ያላቸው እነማን ናቸው?
ከዚህ የሃጢአት ባርነት ነፃ የሚያወጣኝ ማን ነው? ከዲያብሎስ አገዛዝ የሚታደገኝ ማነው? ማነው ይህን አጋንንታዊ አሮጌ ተፈጥሮ ሽሮ የእግዚአብሔር ልጅ የሚያደርገኝ? ማነው የዘላልም ሕይወት የሚሰጠኝ? መልሱ አጭር ነው፣ ኢየሱስ ብቻ። ይህ የኔ አስተያየት አይደለም። የዘላለም ሕይወት የሚለው ቃል ተጠቅሶ በምናገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ሁሉ የዚያ ስጦታ ምክንያት ኢየሱስ እንደሆነ ይናገራል።
የዘላለም ሕይወት ያላቸው ከሃጢአት ባርነት ነፃ የወጡ ናቸው። ‘‘አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው’’ (ወደ ሮሜ ሰዎች 6፥22)። ከዚህ ሞት እና ሃጢአት ባርነት ነፃ ለመውጣት ነፃ አውጪ ያስፈልጋል (ሮሜ 8፡2)። ያ ነፃ አውጪ ኢየሱስ ነው (ዮሐንስ ወንጌል 8፡36፤ 1ዮሐንስ መልዕክት 3፡8፤ ሉቃስ 4፡17-20)። ከዚህ ባርነት በመልካም ምግባሮቻችን ማምለጥ የምንችል ቢሆን ኖሮ የኢየሱስ ነፃ አውጪነት ባላስፈለገም ነበር። ከዚህ ባርነት ነፃ የሚያወጣን ክርስቶስ እንደሆነ ካመንን የዘላለም ሕይወት የእኛ ናት።
የዘላለም ሕይወት ራሱ ኢየሱስ ነው። ‘‘የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው’’ (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፥20)። የዘላለም ሕይወት የሚገኘው በኢየሱስ ውስጥ ነው፣ ‘‘እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው’’ (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፥11)። ይህን ዘላለማዊ ሕይወት፣ ኢየሱስን ስንቀበል ገንዘባችን (የራሳችን) እናደርጋለን። የዘላለም ሕይወት ያላቸውም ኢየሱስ ያላቸው ብቻ ናቸው። የዘላለም ሕይወት፣ ኢየሱስ በሌለበት የለችምና ኢየሱስ የሌለው የዘላለም ሕይወት የለውም፣ ‘‘ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም’’ (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፥12)።
ይህ ሕይወት ያላቸው – የዚህ እምነት ተከታይ ናቸው፣ ወይም ረጅም ዘመን የቆየው የዚህ እምነት አባላት ናቸው፣ ወይም፣ ባማረ እና በተዋበ ካቴድራል ውስጥ እግዚአብሔር የሚያመልኩት የዚህ እምነት ተከታዮች ናቸው፣ ወዘተ አይልም። ይህ ሕይወት ያላቸው ልጁ ኢየሱስ ያላቸው ሁሉ ናቸው። እናም የትኛውን እምነት ብከተል ነው የዘላልም ሕይወት ያለኝ የሚል ጭንቀት ካለብዎ፣ መልሱ አጭር ነው በስጋ የተገለጠውን (1ጢሞቴዎስ 3፡16)፣ ሰውም (ማቴዎስ 16፡13) እግዚአብሔርም (ዮሐንስ 1፡1፤ 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፥20) የሆነውን ለእርሶ ሃጢአት ቤዛ የሆነውን የሞተውን ከዛም በ3ኛው ቀን ከሙታን መካከል የተነሳውን ኢየሱስን የሚያምኑ እና ቃሉን የሚከተሉ (ዮሐንስ 5፥24) ከሆኑ የዘላልም ሕይወት እንዳሎ መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥሎታል። ቅዱሱ መጽሐፍ ካረጋገጠልዎ፣ የሰው ማረጋገጫ የግድ አያስፈልጎትም። የምሁራን፣ የሊቃውንት፣ የጳጳሳት፣ የፓስተሮች ይሁንታ አያሻዎትም። እርሱ ካለ፣ አለ ነው። የእርሶ ድርሻ፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም እንዳለችው አሜን፣ ‘‘እንደ ቃልህ ይሁንልኝ’’ (ሉቃስ 1፡38) ማለት ብቻ ነው።
የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የእኔ ድርሻ ምንድን ነው?
አንድ ነገር ለማግኘት ልፉት እና ድካም ግድ በሆነባት አለም ውስጥ፣ በፀጋ ስለተገለጠው የእግዚአብሔር ነፃ ስጦታ ማውራት እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል። በመልፋት እና በመድከም የላቡን ዋጋ በመቀበል ለኖረ ሰራተኛ፣ ነፃ ስጦታ ድካሙ ካስገኘችለት በላይ ደሞዝ እንዳላት ቢነገረው ዜናውን የጅል ወሬ አድርጎ መቁጠሩ የሚጠበቅ ነው። እግዚአብሔር ግን ይህንን የአለም ጥበብ እና ስርአት ሊያዋርድ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ያድን በጎ ፈቃዱ ሆነ (1ቆሮንቶስ 1፡19-21)። ያለስራ ሃጢአተኛውን በሚያፀድቅ ያመነን ሰው እግዚአብሔር በዘላለም ሕይወት ሊያኖር ቢወድ (ሮሜ 4፡5)፣ እንዲህ አይሁን ለማለት እኛ ማን ነን? በውስጣችሁ ያለው ግንድ (የወደቀው ተፈጥሯችን ማለት ነው) የሞተ ስለሆነ የምታፈሩትም ፍሬ የሞተ ነውና በእናንተ ስራ አልከብርም። መልካም ምግባራችሁ ሳይቀር የመርገም ጨርቅ ስለሆነ በፊቴ አስነዋሪ ነው። በመሆኑም የገዛ እጄ መድሃኒት አዘጋጅታለች። በእኔ ስጦታ እንጂ በእናንተ ስራ የዘላለምን ሕይወት አታገኙም (ኤፌሶን 2፡8-9) ቢል፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚከራከር ማን ነው? የዘላለም ሕይወት እግዚአብሔር በላከው በኢየሱስ ለሚያምኑ እና ቃሉን ለሚከተሉ ሁሉ የተዘጋጀች ነፃ ስጦታ ነች። የሚቀበላት ያገኛታል፤ የሚያቃልላት ወይም በሌላ መንገድ ሊያገኛት የሚሻት ሁሉ ያጣታል። የዘላለምን ሕይወት መቀበል የሚሹ ሰዎች ድርሻ ምን እንደሆነ ከዚህ በታች በቀረቡት ጥቅሶች ውስጥ እንመልከት፡-
የዮሐንስ ወንጌል 3፥14-15 ‘‘ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል።’’
(የዮሐንስ ወንጌል 3፥16) ‘‘በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።’’
ለዘላለም ሕይወት ተዘጃግተዋል? እንግዲያው በሐዋሪያት ዘመን እንደነበሩ ብልህ ሰዎች ያድርጉ። ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች ምን አደረጉ? ‘‘አሕዛብም ሰምተው ደስ አላቸው የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፥ ለዘላለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ’’ (የሐዋርያት ሥራ 13፥48)።
የዮሐንስ ወንጌል 3፥36 ‘‘በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።’’
የዮሐንስ ወንጌል 6፥40 ‘‘ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።’’
የዮሐንስ ወንጌል 6፥47 ‘‘እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።’’
የዮሐንስ ወንጌል 17፥3 ‘‘እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።’’
1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 1፥16 ‘‘ስለዚህ ግን፥ የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ፥ ምህረትን አገኘሁ።’’
ቲቶ 3፡6-7 ‘‘ያን መንፈስም፥ በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው።’’
1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1፥2 ‘‘ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤’’
1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፥13 ‘‘የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ።’’
የዮሐንስ ወንጌል 5፥24‘‘እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።’’
የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ሌሎች አማራጭ መንገዶች ይኖሩ ይሆን?
ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርሰው መንገድ አንድ ነው። እርሱም ኢየሱስ ነው (ዮሐንስ 14፡6)። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ መንገድ እንዲህ ይላል፣ ‘‘ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ’’ (ይሁዳ 1፡21)።
ይህንን ዘላለማዊ ሕይወት በራሴ መንገድ ለማግኘት እጥራለው፣ ወደዚህ ዘላለማዊ ሕይወት የሚያደርሱ ሌሎች አማራጭ መንገዶች አሉኝ፣ ሃይማኖቴ የዘላለም ሕይወት መንገዴ ነው፣ ወዘተ ብለን ይህን ሕይወት ለምንገፋ ሐዋሪያው ጳውሎስ እና በርናባስ የሚከተለውን ይመክሩናል፣ ‘‘ጳውሎስና በርናባስም ገልጠው፣ የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ከገፋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንዳይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን፥ እነሆ፥ ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን’’ (የሐዋርያት ሥራ 13፥46)።
በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ሌላ አማራጭ የሚፈልግ ደግሞ የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ ይሆናል፣ ሕይወትንም አያይም። ‘‘በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም’’ (የዮሐንስ ወንጌል 3፥36)።