ፀሎት ምንድን ነው? ፀሎት ምን ምን ያካትታል?

ፀሎት አፅናፈ አለምን ከፈጠረና ከሚቆጣጠር፣ እንዲህ ታላቅ ሆኖ ሳለ ደግሞ ዝርዝርና ትናንሽ በሆኑ የሕይወታችን ክፍሎች ውስጥ ሳይቀር ድርሻ እንዲኖረው ከሚሻ የፍቅር አምላክ ጋር የምናደርገው ጥልቅ ውይይት ነው፡፡

እግዚአብሔርን መቅረብም ሆነ ማነጋገር የምንችለው በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ በኩል ብቻ ነው። የትኛውም መልካም ስራችን ቅዱሱ እግዚአብሔር ፊት ሊያቀርበን እንደማይችል መረዳት ይኖርብናል፡፡ በፀሎት ወደዚህ ቅዱስ አምላክ  ፊት መቅረብን እንደ ታላቅ እድል መቁጠር ይኖርብናል፡፡

በየትኛውም ውይይት ላይ እንደተለመደው፣ መስማት የውይይት ትልቁ ክፍል ነው፡፡ እግዚአብሔር በልቤ ሲናገር ወይም አንድ አዲስ ነገር ሲገልጥልኝ በማሰላሰልና በማድመጥ ጊዜውን መጠቀም ይኖርብኛል፡፡ እግዚአብሔር ዘወትር ከእርሱ አንዳች ነገር እንደ ምንጠብቅ ሆነን እንድንኖር ይወዳል፡፡

እግዚአብሔር ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚፈልጋቸውን ነገሮች ቅድሚያ መስጠት፣ ለእግዚአብሔር  ያለንን ክብርና  የሚገባውን ትክክለኛ  ስፍራ መስጠታችንን የምናረጋግጥበት አንዱ  መንገድ  ነው፡፡ ይህን ለማድረግ፣ ትራፊውን ጊዜያችንን፣ ትራፊውን ጉልበታችንን እና ትራፊውን የኛ የሆነውን ነገር ከመስጠት ወጥተን ምርጥ የምንለውን ነገራችንን ለእርሱ የማቅረብ ልምምድ ውስጥ መግባት ይጠበቅብናል፡፡

ሀ. ከእግዚአብሔር ጋር ያለኝ የውይይት (የፀሎት) ጊዜ መጠን- በሚኖረኝ የልብ ዝግጅት፣ ቅድሚያ  ስለ ምሰጣቸው ነገሮች ባለኝ እውነተኛ ግምገማ እና ስለ እርሱ ግርማ ባለኝ እውቀት መጠን እየጨመረ ይሄዳል፡፡

መዝ. 5፡3 (አ.መ.ት.) እግዚአብሔር ሆይ፤ በማለዳ ድምጼን ትሰማለህ፤ በማለዳ ልመናዬን በፊትህ አቀርባለሁ፤ ፈቃድህንም በጥሞና እጠባበቃለሁ፡፡

መዝ. 37፡7 (አ.መ.ት.) እግዚአብሔር ፊት ጸጥ በል፤ በትዕግሥትም ተጠባበቀው፤ …

መዝ. 119፡147 (አ.መ.ት.) ትረዳኝ ዘንድ ጎሕ ሳይቀድ ተነስቼ እጮኻለሁ፤ ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ኢሳ. 50፡4 … ማለዳ ማለዳ ያነቃኛል፣ እንደ ተማሪዎችም ትሰማ ዘንድ ጆሮዬን ያነቃል፡፡

ለ. ፀሎት እግዚአብሔርን ማድነቅ፣ ማመስገን እና መባረክን ያካትታል፡፡

መዝ. 145፡2-3 በየቀኑ ሁሉ እባርክሀለሁ፣ ስምህንም ለዘላለም ዓለምም አመሰግናለሁ፡፡ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፣ እጅግም የተመሰገነ ነው፣ ለታላቅነቱም ፍፃሜ የለውም፡፡

መዝ. 146፡1-2 ሃሌ ሉያ ነፍሴ ሆይ እግዚአብሔርን አመስግኚ በሕይወቴ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ በምኖርበት ዘመን ሁሉ ለአምላኬ እዘምራለሁ፡፡

ዳን. 6፡10 ዳንኤልም ፅህፈቱ እንደ ተፃፈ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ የእልፍኙም መስኮቶች ወደ ኢየሩሳሌም አንፃር ተከፍተው ነበር ቀድሞም ያደርግ እንደ ነበር በየዕለቱ ሶስት ጊዜ በጉልበቱ ተንበርክኮ በአምላኩ ፊት ፀለየ አመሰገነም፡፡

ኤፌ. 5፡19-20 በመዝሙር እና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በእርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ፣ ሁልጊዜ ስለሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለሁሉ አመስግኑ፡፡

ፊሊ. 4፡6-7 በነገር ሁሉ በፀሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ፡፡ አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁን እና አሳባችሁን በክርስቶስ ይጠብቃል፡፡

ቆላ. 4፡2-4 ከማመስገን ጋር በፀሎት እየነቃችሁ ለእርሱ ትጉ፤ …

1ተሰ. 5፡16-17 ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፣ ሳታቋርጡ ፀልዩ፣ በሁሉ አመስግኑ፣ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና፡፡

ሐ. ፀሎት መናዘዝ፣ መታረቅን እና ሌሎችን ይቅር ማለትን ያካትታል፡፡

መዝ. 32፡5 ኃጢአቴን ላንተ አስታወቀሁ፣ በደሌንም አልሸፈንሁም፣ ለእግዚአብሔር መተላለፌን እነግራለሁ አልሁ፣ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውክልኝ፡፡ (መዝሙር 66፡18 ይመልከቱ)

ምሳሌ 28፡13 ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምህረትን ያገኛል፡፡

ማቴ. 5፡23-24 እንግዲህ መባህን በመሰዊያላይ ብታቀርብ በዚያም ወንድምህ በአንተ ላይ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ በዚያ በመሰዊያው ፊትመባህን ትተህ ሂድ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ፡፡

ማር. 11፡25 ለፀሎትም በቆማችሁ ጊዜ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት፡፡

ሮሜ. 12፡18 ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ፡፡

1ዮሐ. 1፡9-10 በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከአመፃም ሁሉ ሊያነፃን የታመነና ፃድቅ ነው፡፡

መ. ፀሎት ልመናዎችን፣ ስለ ግል ፍላጎቶቻችን ጥያቄዎች ማቅረብንም ያካትታል፡፡

ማቴ. 6፡5-8 … አንተ ግን ስትፀልይ ወደ እልፍኝህ ግባ፤ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ፀልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል፡፡ አህዛብ በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትፀልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ፡፡ ስለዚህ አትምሰሉአቸው ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና፡፡

ማቴ. 6፡25-34 … ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል …

ያዕ. 1፡5 ከእናንተ ማንም ጥበብ ቢጎድለው ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን ለእርሱም ይሰጠዋል፡፡

ሠ. ፀሎት ምንም እንኳን የማይቋረጥና የሁል ጊዜ ግንኙነት ቢሆንም ለእርሱ የሚሆን የተለየ ሰዓት ሊኖረው ይገባል፡፡

መዝ. 55፡17 በማታና በጠዋት በቀትርም እናገራለሁ፣ እጮኸማለሁ፣ ቃሌንም ይሰማኛል፡፡

መዝ. 119፡62 ስለ ፅድቅህ ፍርድ በእኩለ ሌሊት አመሰግንህ ዘንድ እነሳለሁ፡፡

መዝ. 119፡164 ስለ ፅድቅህ ፍርድ ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሀለሁ፡፡

ዳን. 6፡10 ዳንኤልም ፅህፈቱ እንደ ተፃፈ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ፣ የእልፍኙም መስኮቶች ወደ ኢየሩሳሌም አንፃር ተከፍተው ነበር፣ ቀድሞም ያደርግ እንደነበር በየዕለቱ ሶስት ጊዜ በጉልበቱ ተንበርክኮ በአምላኩ ፊት ፀለየ፣ አመሰገነም፡፡

ሮሜ. 12፡12 በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ፤

1ተሰ. 5፡17 ሳታቋርጡ ፀልዩ፤ …

በ 1ተሰ. 5፤17 ላይ የተሰጠ አስተያየት፡ #የማያቋርጥ ፀሎት፣ በሚቻል ወቅት ሁሉ የሚደረግ ቀጣይነት ያለው ፀሎት ማለት እንጂ አንድም ጊዜ የማይቆም ማለት አይደለም፡፡ ጳውሎስ ይህንን ጉዳይ ያነሳው ያለማቋረጥ ሃሳብን ለእግዚአብሔር ማስገዛት ፈታኝ በሆነበት የዕለት ተዕለት ሕይወታችን፣ በተቻለ መጠን ያለማቋረጥ ከእግዚአብሔር ሕብረት ስር የመሆንን አስፈላጊነት ለመግለፅ ነው፡፡

ረ. ፀሎት ምልጃንና ስለሌሎች ሰዎች ፍላጎቶች መፀለይን ያካትታል፡፡

2ቆሮ. 1፡8-11 በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን፣ ወንድሞች ሆይ፣ ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና፤ ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤ አዎን፣ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፣ እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር። እርሱም ይህን ከሚያህል ሞት አዳነን፣ ያድነንማል፤ እናንተም ደግሞ ስለ እኛ እየጸለያችሁ አብራችሁ ስትረዱን፣ በብዙ ሰዎች በኩል ስለ ተሰጠን ስለ ጸጋ ስጦታ ብዙዎች ስለ እኛ ያመሰግኑ ዘንድ፣ ወደ ፊት ደግሞ እንዲያድን በእርሱ ተስፋ አድርገናል።

ኤፌ. 6፡18-20 በፀሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ፀልዩ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመፅናት ሁሉ ትጉ ደግሞ የወንጌልን ምስጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለእኔ ለምኑ ስለ ወንጌልም በሰንሰለት መልዕክተኛ የሆንሁ መናገር እንደሚገባኝ ስለእርሱ በግልጥ እናገር ዘንድ ለምኑ፡፡

ቆላ. 4፡12 ከእናንተ የሆነ የክርስቶሰ ባሪያ ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብችኃል፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ተረድታችሁ ፍፁማን ሆናችሁ እንድትቆሙ ሁል ጊዜ ስለ እናንተ በፀሎቱ ይጋደላል፡፡

 

5 thoughts on “ፀሎት ምንድን ነው? ፀሎት ምን ምን ያካትታል?”

Leave a Reply

%d bloggers like this: