አስቀድሞ መወሰን ማለት ምን ማለት ነው? አስቀድሞ የመወሰን ሃሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው?

ሮሜ 8፡29-31 የሚከተለውን ይላል፣ ‘‘ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው። እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?’’ ኤፌሶን 1፡5 እና 11 ደግሞ የሚከተለውን ያስነብበናል፣ ‘‘በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን። … እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ፥ አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን።’’ በርካታ ሰዎች ስለአስቀድሞ መወሰን አሉታዊ አስተያየት አላቸው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ፍቺው ካልሆነ በቀር አስቀድሞ መወሰን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሃሳብ መሆኑ ብዙ አከራካሪ አይደለም።

አስቀድሞ መወሰን የሚለው ቃል proorizo ከሚለው የግሪክ ቃል የተወሰደ ሲሆን የቁም ትርጉሙም ‘ቀደም ብሎ መወሰን’ ማለት ነው። ይህ ቃል፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ የተወሰኑ ነገሮች ባሉበት ሁኔታ እንዲሆኑ እንደወሰነ ያሳያል። ከላይ በቀረቡት ጥቅሶች መሰረት፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንዲሆኑ የወሰናቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? በ ሮሜ 8፡29-30 መሰረት፣ የተወሰኑ ሰዎች የልጁን መልክ እንዲመስሉ፣ እንዲጠሩ፣ እንዲፀድቁ፣ እና እንዲከብሩ እግዚአብሔር አስቀድሞ ወስኗል። እግዚአብሔር የተወሰኑ ሰዎች እንዲድኑ አስቀድሞ ወስኗል። በበርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ውስጥ አማኞች በክርስቶስ እንደተመረጡ እናነባለን (ማቴዎስ 24፡22፣31፤ ማርቆስ 13፡20፣ 27፤ ሮሜ 8፡33፣ 9፡11፣ 11፡5-7፣ 28፤ ኤፌሶን 1፡11፤ ቆላሲያስ 3፡12፤ 1ተሰሎንቄ 1፡4፣ 1ጢሞቴዎስ 5፡21፤ 2ጢሞቴዎስ 2፡10፣ ቲቶ 1፡1፤ 1ጴጥሮስ 1፡1-2፣ 2፡9፤ 2ጴጥሮስ 1፡10)። አስቀድሞ መወሰን፣ እግዚአብሔር በሉአላዊነቱ የተወሰኑ ሰዎች እንዲድኑ መምረጡን የሚናገር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዶክትሪን ነው።

በዚህ ዶክትሪን ላይ አስቀድሞ የሚነሳው መከራከሪያ፣ ‘ፍትሃዊ አይደለም’ የሚለው ነው። እግዚአብሔር የተወሰኑትን መርጦ ሌሎቹን እንዴት ይተዋል? እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለብን ትልቅ ቁም ነገር ቢኖር ማናችንም ብንሆን የመዳን መብት የሌለን መሆኑን ነው። ማናችንም መዳንን እንደመብት ልንጠይቅ ሕጋዊ መሰረት የለንም። ምክንያቱም ሁላችን ሃጢአትን አድርገናል (ሮሜ 3፡23)፣ በዚህም ምክንያት የሚጠብቀን ዘላለማዊ ቅጣት ብቻ ነው (ሮሜ 6፡23)። እናም፣ ከፊላችንን አይደለም ሁላችንንም ወደ ገሃነም እሳት ቢሰደን እግዚአብሔር ፍጹም ፍታዊ ያደርገዋል። ፍትህ ተገቢውን ውሳኔ ማግኘት ማለት ነውና። ሆኖም ግን እግዚአብሔር የተወሰኑትን ለማዳን መረጠ። እግዚአብሔር በዚህ ምርጫ ውስጥ ባልተካተቱት ሰዎች ምክንያት ኢፍታዊ አይሆንም። ምክንያቱም ያሉበት ቦታ የሚገባቸው ነውና። እግዚአብሔር የተወሰኑትን ለማዳና ያደረገው ሉአላዊ ምርጫ በተቀሩት ላይ ያለውን ኢፍታዊነት አያሳይም። ማንም ሰው ከእግዚአብሔር አንዳች መልካም ነገር የማግኘት መብት የለውም። አንዳች ባለማግኘቱም በእግዚአብሔር ላይ ቅሬታ ማሰማት አይችልም። አንድ ሰው ከ20 ሰዎች መካከል መርጦ ለ5ቱ ብቻ ገንዘብ ቢሰጥ፣ የተቀሩት 15ቱ ይበሳጩ ይሆን? ሊበሳጩ ይችሉ ይሆናል። ለመበሳጨት ሕጋዊ መብት ይኖራቸው ይሆን? ፈጽሞ። ለምን? ለጋሹ የማናቸውም እዳ የለበትምና። ሰውየው ያደረገው አንድ ነገር ቢኖር ለተወሰኑቱ ሰዎች ለጋስ ለመሆን መወሰኑ ነው።

እግዚአብሔር የሚድኑትን የሚመርጥ ከሆነ፣ በገዛ ፈቃዳችን መርጠን በክርስቶስ ለማመን የምንወስነውን ውሳኔ ከንቱ አያደርገውምን? መጽሐፍ ቅዱስ ምርጫ እንዳለን ይናገራል – በክርስቶስ የሚያምን ሁሉ ይድናል (ዮሐንስ 3፡16፤ ሮሜ 10፡9-10)። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በእርሱ የሚያምኑትን እና ፈቃዱን የሚሹትን ሰዎች እንደሚጥላቸው አይናገርም (ዘዳግም 4፡29)። በእነዚህ ሁለት ሃሳቦች መካከል አንድ የምናስተውለው መለኮታዊ አሰራር አለ። ይህም የእግዚአብሔር አስቀድሞ አማኙን የመሳብ ስራ (ዮሐንስ 6፡44) ግለሰቡ አምኖ ለመዳን ከሚያደርገው የግል ውሳኔ ጋር (ሮሜ 1፡16) መለኮታዊ አብሮነት እንዳላቸው።

እግዚአብሔር የሚድኑትን አስቀድሞ ወስኗል የሚለውና ለመዳን ክርስቶስን መምረጥ ይኖርብናል የሚሉት ሁለቱም ሃሳቦች ውሁድ እውነታዎች ናቸው። ‘‘የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም’’ (ሮሜ 11፡33)።

አስቀድሞ መወሰንና መመረጥ፣ አስቀድሞ ከመታወቅ ጋር ያላቸው ዝምድና ምነድን ነው?

እግዚአብሔር ሁሉን አስቀድሞ በማወቁ፣ አስቀድሞ የወሰናቸውን እና የመረጣቸውን ሰዎች በዚህ እውቀቱ ላይ ተመስርቶ መምረጥ ይችል ነበር። ነገር ግን የአስቀድሞ ውሳኔውም ሆነ ምርጫው ስለእነዚህ ሰዎች ባለው የአስቀድሞ እውቀቱ ላይ የተመሰረተ አይደለም። በቀላል ቁጥር የማይገመቱ ክርስቲያኖች በዚህ መንገድ ያምናሉ፤ አመለካከቱም የአርሜናውያን አስቀድሞ ውሳኔ አመለካከት በመባል ይታወቃል። የዚህ አመለካከት ችግር መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አስቀድሞ መወሰን፣ መመረጥ እና አስቀድሞ መታወቅ ከሚናገረው ጋር አብሮ የማይሄድ መሆኑ ነው። እግዚአብሔር ይህን ምርጫ ያደረገው ስለ መረጣቸው ሰዎች መጪ ዘመን አስቀድሞ በማወቁ ላይ ተመስርቶ አለመሆኑን ለመገንዘብ፣ እግዚአብሔር የተወሰኑ ሰዎችን ለድነት የመረጠበትን ወይም የወሰነበትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክንያት መገንዘብ ይኖርብናል።

ኤፌሶን 1፡5 እንዲህ ይላል፣ ‘‘በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን።’’ በዚህ ጥቅስ መሰረት፣ እግዚአብሔር እኛን አስቀድሞ የወሰነበት ምክንያት እኛ የሰራነው ወይም የምንሰራው ስራ ሳይሆን በጎ ፈቃዱና የገዛ ደስታው ነው። ሮሜ 9፡15-16 ደግሞ እንዲህ ይላል፣ ‘‘ለሙሴ፡- የምምረውን ሁሉ እምረዋለሁ ለምራራለትም ሁሉ እራራለታለሁ ይላልና። እንግዲህ ምሕረት ለወደደ ወይም ለሮጠ አይደለም፥ ከሚምር ከእግዚአብሔር ነው እንጂ።’’ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እንዲህ ይላል፣ ‘‘ለሙሴ፣ የምምረውን እምረዋለው፣ ለምራራለትም እራራለታለው ይላልና። እንግዲህ ይህ ከሰው ፍላጎት ወይም ጥረት ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር ምህረት የተነሳ ነው።’’ ስለያዕቆብና ኤሳው በሮሜ 9፡11 ‘‘ልጆቹ ገና ሳይወለዱ፥ በጎ ወይም ክፉ ምንም ሳያደርጉ፥ ከጠሪው እንጂ ከሥራ ሳይሆን በምርጫ የሚሆን የእግዚአብሔር አሳብ ይጸና ዘንድ፥ …’’ የሚል ተጽፎ እናነባለን። በኤፌሶን 1፡11 ላይ ደግሞ፣ ‘‘እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ፥ አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን።’’ በእነዚህና በሌሎች በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ የምናነበው ነገር፣ አስቀድሞ መወሰን ወይም መመረጥ እኛ ባደረግነው ወይም ወደፊት በምናደርገው ተግባር ላይ የተመሰረተ አለመሆኑን ነው። እግዚአብሔር ሕዝቦችን ከነገድ እና ከቋንቋ ለመንግስቱ የመረጠው በገዛ ሉአላዊ ፈቃድ ላይ ተመስርቶ ነው። እግዚአብሔር እነዚህን ሕዝቦች ከነገድ እና ከቋንቋ ለመንግስቱ የመረጠው ገና አለም ሳይፈጠር በፊት (ኤፌሶን 1፡4)፣ በገዛ ሉአላዊ ፈቃዱ ላይ ተመስርቶ እንጂ የወደፊቱን ስለሚያውቅ፣ ወደፊት በሚያደርጉት ተግባር ላይ ተመስርቶ አይደለም።

ሮሜ 8፡29 ‘‘አስቀድሞ ያወቃቸውን … አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤’’ ይል የለምን? ይህ ማለት አስቀድሞ መወሰን በእግዚአብሔር አስቀድሞ ማወቅ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ አያሳይምን? መልሱ፣ አዎ አስቀድሞ መወሰን በእግዚአብሔር አስቀድሞ ማወቅ ላይ የተመሰረተ ነው። ችግሩ አስቀድሞ ስለማወቅ የምነሰጠው ትርጉም የተዛባ መሆኑ ነው። የእግዚአብሔር አስቀድሞ መወሰን፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ በማወቅ ችሎታው ላይ የተመሰረተ ነው የሚለው ሃሳብ፣ እግዚአብሔር ሊያድናቸው የወሰናቸውን ሰዎች የመረጠው መፃኢ ጊዜያቸውን ካየ በሁዋላ እና ማን ወንጌልን እንደሚቀበል እና እንደማይቀበል ጋረጋገጠ በሁዋላ ነው ወደሚል ትርጉም የሚወስደን ከሆነ ከላይ ካየናቸው የእግዚአብሔር የምራጭ ምክንያቶች ጋር እንቃረናለን።

ስለሚድኑ ሰዎች የዮሐንስ ወንጌል 10፡26 የሚለውን እንይ። ኢየሱስ ስለ ሚቃወሙት ሰዎች ሲናገር እንዲህ አለ፣ ‘‘ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም’’። በዚህ ጥቅስ መሰረት ሰዎች የሚያምኑት የእግዚአብሔር በግ ስለሆኑ ነው። እግዚአብሔር እነዚህን ሰዎች ለድነት የመረጣቸው አንድ ቀን በሚያደርጉት የማመን ውሳኔ ምክንያት ሳይሆን ገና ሳይፈጠሩ በክርስቶስ የራሱ ልጆች እንዲሆኑ አስቀድሞ ስለመረጣቸው ነው። አንዱ አምኖ ሌላው የማያምንበት ምክንያት አንደኛው በእግዚአብሔር አስቀድሞ ልጁ እንዲሆን ስለተመረጠ እና ሌላው ደግሞ ስላልተመረጠ ነው።

3 thoughts on “አስቀድሞ መወሰን ማለት ምን ማለት ነው? አስቀድሞ የመወሰን ሃሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው?”

    1. ሰላም ላንቺ ይሁን አባይነሽ፣

      ስለ አስተያየትሽ እና ባርኮትሽ ምስጋናዬ የላቀ ነው። በትምሕርቱ መጠቀምሽን ማወቄ ደግሞ ይበልጥ እንዳገለግል ያበረታታኛል።
      ሌሎች መንፈሳዊ ጥያቄዎች ካሉሽ በጥያቄዎችሽ ላይ በመመስረት ትምሕርቶችን አዘጋጅቼ ድረ-ገጹ ላይ ለመጫን ወይም በግል ኢ-ሜይል አድራሻሽ ለመላክ ዝግጁ ነኝ።
      ጌታ ይባርክሽ

      አዳነው ዲሮ
      ትምሕርቶች ዝግጅት ክፍል ሃላፊ
      tsegaewnet@gmail.com
      https://tsegaewnet.wordpress.com/

Leave a Reply to tsegaewnetCancel reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading