እውን እግዚአብሔር አለ?

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እግዚአብሔር እንዳለ ያምናሉ፡፡ ጥቂቶች ማስረጃ አለን ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ እግዚአብሔር እንዳለ በማስረጃ አረጋግጠህ ታውቃለህ? በውኑ የእርሱ መኖር በሳይንስ ሊረጋገጥ ይችላልን? አንተን ራስህንና አለማትን አንድ ድንቅ አዕምሮ እንዲፈጠራቸው በእርግጠኝነት ታውቃልህ? ወይስ ይህ ጉዳይ በእምነት ብቻ ሊቀበሉት የተገባ ነው ብለህ ትደመድማለህ? እስቲ ይህን ጥያቄ እንዳስ፡፡

ሰዎች በእግዚአብሔር መኖር ጥያቄ ላይ መከራከር ከጀመሩ ብዙ ሺ አመታት ነጉደዋል፡፡ ብዙዎቹ ታዲያ የእግዚአብሔርን መኖር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ማረጋገጥ ይቻላል ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ይህ የሰው ልጆች ትልቅ ጥያቄ፣ በረቂቅ ፍልስፍና (abstract philosophy) እና በ ሜታፊዚካል (metaphysical) አስተምህሮቶች ውስጥ ምላሽ ያገኛል የሚል ሰፊ ግምት ይሰጣሉ፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ፣ ማለትም የአግኖስቲክስ /agnostics/ ትምህርት አራማጆች፣ እግዚአብሔር መኖሩን እርግጠኛ የሚያደርገን ነገር ፈፅሞ የለም ይላሉ፡፡ የተቀሩት ደግሞ “የእግዚአብሔር አለ” መለኮተ ትምህርተ ከልጅነታቸው እንደ ተረት የሰሙ ናቸው፤ አልያም ጥያቄው የማይሞቃቸውና የማይበርዳቸው ለዘብተኞች ናቸው፡፡

መጽሐፍ ቅዱሳችን በእግዚአብሔር መኖር ላይ የሚጠራጠሩትንና በድፍረት ‹የለም› ለሚሉትን አንድ ስም ይሰጣቸዋል – ሞኞች፡፡ “ሰነፍ በልቡ፡- አምላክ የለም ይላል” መዝ. 14፡1፡፡ ይህ ጥቅስ በ መዝ. 53፡1 ላይም ተደግሞ እናገኘዋለን፡፡ ይህ ፅሁፍ እግዚአብሔር ለምን እነዚህን ሰዎች “ሞኞች” እንደሚላቸው ይመረምራል፡፡

በጽሑፉ አቅራቢ እምነት ከዚህ በታች ስለ እግዚአብሔር መኖር በሳይንስ አንፃር በአስረጂነት የተቀመጡ ታሪኮች፣ አንዳንዶችን ይህንን ጥያቄውን ዳግመኛ እንዳያነሱት ያደርጋቸዋል፤ እየወላወሉ ያሉ ሌሎችን ደግሞ ያፀናል፡፡ በመጀመሪያ አንዳንድ ባህላዊ ማስራጃዎችን እንዳስሳለን፡፡ በመቀጠልም ከሳይንስ ማህደር የሥነ ሕይወት (biology)፣ የጠፈር ሳይንስ (astronomy)፣ ኬሚስትሪንና ሒሳብ ማህደሮችን እናገላብጣለን፡፡

ስነፍጥረት ወይስ የዝግመታዊ ለውጥ ፍልስፍና (evolution)

የእግዚአብሔር መኖርና አለመኖር ጥያቄ ሲነሳ አብሮ ሊነሳ የሚገባ አንድ ተዛማጅ ሀሳብ አለ፡፡ ይህም ሀሳብ -ሕይወት በምድር ላይ የተገኘው ድንገት፣ በእድል ነገር ግን በዝግመታዊ የለውጥ ስርዐት ነው ወይስ በአንድ ልዩና ታላቅ አካል ፈጣሪነት? በሌላ አነጋገር በምድራችን ላይ የሚገኙ ፍጥረታት፣ የዝግመታዊ ለውጥ አርበኞች (evolutionist) እንደሚሉት የሚሊዮን አመታት የዝግመታዊ ለውጥ ገፀ በረከቶች ወይስ “ይሁን” የሚለው የእግዚአብሔር ስልጣናዊ ቃል ፍሬዎች?

አንድ በዚህ በዝግመታዊ የለውጥ ሳይንስ ላይ ለ ሁለት አመት ተኩል ጠለቅ ያለ ጥናት ያደረገ ሰው ዴቪድ ሲ. ፓክ (David C. pack) በጥናቱ መባቻ ላይ እንዲህ አለ፡፡ “የዝግመታዊ ለውጥ ሳይንስን መቀበል እግዚአብሔር አለ በሎ ከማመን የበለጠ እምነት ይጠይቃል” ሲል በዝግመታዊ ሳይንስ ንድፈ ሃሳቦች ውስጥ ያሉትን ሕፀፆች ወይም ግጭቶች (fallacies) ለማስቀመጥ ሞክሯል፡፡

ምናልባት ብዙዎች ይህ ሳይንስ እንደ 1 + 1 = 2 ስሌት ከህፀፅ የፀዳ፣ የተረጋገጠና የፀና የመላምት መሰረት ያለው አድርገው ያስቡት ይሆናል፡፡ ሆኖም የዝግመታዊ ለውጥ ሳይንስ እንደሌሎች ንድፈ ሃሳቦች ሁሉ ከራሱና ከሌሎች የሳይንስ ሕጎች ጋር የሚጣረስበት ነጥቦች ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ይህንን ‘ሳይንስ’ ነው እንግዲህ ብዙዎች ስለ ፍጥረት ለሚነሱ ጥያቄዎች እንደ ማጣቀሻ ዶሲያቸው የሚቆጥሩት፡፡ በነገራችን ላይ፣ በኔ እምነት በሳይንስ አንፃር፣ ሊረጋገጡ (proof) የማይቹሉ እሳቤዎች ሁሉ ከእምነት የተለየ ጎራ ሊሰጣቸው አይችልም፡፡ የዝግመታዊ ለውጥ ሳይንስ የፍጥረት መጀመሪያን እሳቤ በሳይንስ ላቦራቶር ውስጥ ቀምሮ ሊያስጨብጠን፣ ሊያስዳስሰን ወይም ሊያስነካን አይችልም፡፡ ሳይንሱ እሳቤዎቹን ከመላምት ይጀምርና ከዛ በመቀጠል ለሆኑት የዝግመታዊ ለውጥ ክስተቶች ማስረጃ ሊያስቀምጥ ይሞክራል፡፡ ያም ሆነ ይህ መነሻው መላምት ነውና የአንድ እምነት ክፍል ከመሆን ዘሎ ሙሉ በሙሉ የሳይንስ አካል ነው ለማለት አልደፍርም፡፡

ስለ ዝግመታዊ ሳይንስ ተጣርሶዎች በሌላ ጊዜ እንደምመለስበት በመግለፅ ወደተነሳው ሃሳብ እመለሳለሁ፡፡

እምነትና ማስረጃ

በአንድ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ እምነት ትልቅ ትርጉም ያለው መለኮታዊ ስጦታ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኝ እርሱንም ሊያውቅ የሚወድ ቢኖር የእግዚአብሔር መንፈስ አንድ ምክር ይለግሰዋል፡- ያለ እምነት (እግዚአብሔርን) ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና ዕብ. 11፡6፡፡ እምነት ለክርስቲያን ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ እንደውም ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት ከቶ አይሞከርም፡፡

የትኛው አምላክ

ሐዋርያው ጳዉሎስ በ 1ቆሮ. 8፡5-7 እንዲህ ሲል ጽፏል፡- መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ ነገር ግን በሰማይ ሆነ በምድርም ሆነ አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለንነገር ግን ይህ እውቀት በሁሉ ዘንድ አይገኝም፡፡

ሃይማኖቶች ፍጥረታዊ ከሆኑቱ – ከድንጋይ፣ ከእንጨትና ከሌሎች ግዑዛን የሆነ ብዙ አማልክት ለራሳቸው አበጅተዋል፡፡ ስርዐትና ወግ ቀርጸውላቸውም ያመልኳቸዋል፡፡ ያስገርምዎ ከሆነ፣ ጥንታዊያን ግሪኮች 30,000 የሚያህሉ የፈጠሯቸውን ‹ፈጣሪዎች› ያገልግሉ እንደነበረና በዚህ ዘመን የሚኖሩ ሂንዱዎች ደግሞ ከ 5 ሚሉዮን በላይ ለሚሆኑ አማልክት እንደሚያጥኑ ልንገርዎ፡፡ ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር እነዚህ ሰዎች አማልክቶቻቸውን የሰሩበትን ቁስ (malerial) የፈጠረ መሆኑ የሚገልጥ እውቀት፣ ጳዉሎስ እንዳለው በሁሉ ዘንድ አይገኝም፡፡

የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር በዚ የምሪት መጽሐፍ ለመተዳደር ፈቃዳቸውን ላሳዩ ሁሉ የሰላም፣ የደስታ እና የተትረፈረፈ ሕይወት መንገድን ጠቁሞበታል፡፡ ይህን በመጠቀም የሰው ልጅ ከተጋረጠበት የግርግር፣ የወከባና የጥርጥር ክፋቶች መዳን ይችላል፡፡ ሆኖም ብዙ ባወቀ ቁጥር ብዙ መጠየቅ ባሕሪው የሆነ አዕምሮ ይህንን ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል፡- ‹መፅሐፍ ቅዱስ ሊረጋገጥ የሚችል የስልጣን መፅሐፍ ነውን?› መልሴ ‹መጠርጠሩስ› ነው፡፡ ሆኖም የዚህን ምላሽ ለማግኘት የሚረዳዎትን ውይይት ሌላ ጊዜ እንደምመለስበት ቃል ገብተቼ አሁን ወደተነሳሁበት ሃሳብ ልመለስ፡፡

ሳይንስ ምን ይለናል?

አንተ አማኝ ሆይ ሳይንስ እግዚአብሔር አለ ብዬ ያመንኩበትን እምነቴን በማስረጃ ውድቅ disprove ያደርጋል ብለህ አትስጋ፡፡ በእርግጥ ብዙ የዘርፉ ጠበብት ሳይንስ የእግዚአብሔር መኖርን ማረጋገጥም ሆነ መካድ የሚችልበት መሠረት የለውም ይላሉ፡፡ ይህንን ሊያደርግ እንኳ ቢሞክር የዘመናችን ታዋቂ የእግር ኳስ ተጨዋች ተጠቅሞበት ስለማያውቀው አንድ መገልገያ ተአምራዊ ጠቀሜታ በማስታወቂያ አማካኝነት ሞግቶና አሳምኖ የምርቱ ተጠቃሚዎች ሊያደርገን ከሚያደርገው ደካማ የማስታወቂያ ጥበብ ተለያይቶ ሊታይ አይችልም፡፡ ሆኖም በዚሁ የሳይንስ መለኪያም ቢሆን እንኳ እግዚአብሔር የራሱን መኖር ከማሳወቅ አልከለከለም፡፡ እንደውም መማር ላልለገመ አዕምሮ ከዚሁ ጎራ የእዚአብሔርን መኖር ጮኸው የሚናገሩ ብዙ ማስረጃዎችን መቁጠር ይቻላል፡፡

አስቀድሜ ከላይ እንደገለጥኩት እግዚአብሔር በእምነታችን ደስ ይሰኛል፡፡ ስላልታየውና ስላልተዳሰሰው፣ ስላልተሰማውና ስላልተሸተተው ነገር ሁሉ ማስረጃ ስንፈልግ መኖር አለብን የሚል አስተምህሮ የለኝም፡፡ ይህን የማድረግ ጊዜና አቅሙም የለምና፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል ከእውቀት ከፍለን እናውቃለን 1ቆሮ. 13፡9፣ ስለዚህ ተፈጥሯዊ ለሆኑት የስሜት ሕዋሶቻችን ማስረጃን ስንመግብ መዋልና ማደር የለብንም፡፡ ይህን ብናደርግ ነገም ከነገም ወዲያ ይህ ጥያቄ ማብቂያ ሳይኖረው ይቀጥላል፡፡

ይህ ማለት ግን ማስረጃ መፈለግን መጽሐፍ ቅዱሳችን ፈፅሞ ይቃወመዋል ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ እምነታችን ጭፍን እንደሆነ ለሚመስላቸው ሁሉ ሊረዳቸው ቢችል፣ ራሳቸው ከሚጠቅሱት ማህደራቸው እግዚአብሔር መኖሩን ለመግለፅ ከበቂ በላይ ማስረጃዎችን እነሆ ብንል ክፋቱ አልታይህ ቢለኝ እንጂ፡፡ ምን ያህል ከምለው ጉዳይ ጋር እንደሚዛመድ ባላውቅም በአንድ የታሪክ አጋጣሚ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመረጣቸው ሐዋሪያት መካከል ትንሳኤውን ለመቀበል የከበደው ሰው ተገኘ፤ ስሙም ቶማስ ይባላል፡፡ ባጭሩ ይህ ሰው ማስረጃ ፈለገ፡፡ የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ፤ ጣቴንም በችንከሩ ምልክት ካላገባሁ፣ እጁንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም አለ (ዮሐ. 20፡25)፡፡

ኢየሱስ ደግሞ ከስምንት ቀን በኃላ ቶማስ በነበረበት ወቅት ራሱን ገለጠ፡፡ ቶማስንም እንዲህ አለው፡- “ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው” ዮሐ. 20፡27፡፡ እዚህ ላይ ኢየሱስ የቶማስን የማስረጃ ጥያቄ ሲመልስ እንመለከታለን፡፡ ሆኖም ይህን ማስረጃ ሳይጠይቁ የሚያምኑ ብፁዓን መሆናቸውንም ሳይነግረው አላለፈም (ዮሐ. 20፡29)፡፡ ኢየሱስ ማስረጃ መስጠቱን አልከለከለም፣ ቢሆንም አላሞገሰም፡፡ ምክንያት ቢሉ እርሱን ደስ የሚያሰኘው እምነት ነውና (ዕብ. 11፡6)፡፡ ጳዉሎስ በ (1ተሰ. 5፡21) ላይ ሁሉን ስለመፈተን ክርስቲያኖችን ሲመክር እናያለን፡፡

የመጀመሪያው የቴርሞዳይናሚክስ ሕግ (The First Law of Thermodynamics)

የመጀመሪያው የቴርሞዳይናሚክስ ሕግ እንዲህ ይላል “ማተርና ሐይል አይፈጠሩም አይጠፉም (Matter & energy can be neither created nor destroyed)፡፡ በዚህ መርህ መሠረት በማተር ወይንም ሀይል ላይ ለውጥን ለማምጣት የሚችል አንዳች ተፈጥሯዊ ሂደት የለም፣ ሊኖርም አይችልም፡፡ ይህ ማለት አዲስ ማተር ወይም ሀይል ካለመኖር ወደመኖር ሊመጣ አይችልም፤ ከመኖር ወደ አለመኖርም ሊሸጋገር አይችልም፡፡ የሳይንስን ማዕድ እየጨለፍን እንደሆነ ልብ ይልዋል፡፡ በዚህ መሰረት ማንኛውም ኢ-አማኝ “ጠፈር (universe) ወደመኖር የመጣው ከምንም ነገር ነው ቢል ከዚህ ሳይንስ ሕግ ጋር መጣረሱ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ስንጠቀልለው ይህ የሳይንስ ሕግ በግልፅ፣ ጠፈርና በውስጧ የሚገኙት ማተር እና ሀይል ከምንም ሊገኙ የሚችሉ ሳይሆኑ ጅማሬና ምክንያት እንዳላቸው ያመለክተናል፡፡

ሁለተኛው የቴርሞዳይናሚክስ ሕግ (The Second Law of Thermodynamics)

ሁለተኛዉ የቴርሞዳናሚክስ ሕግ በአጭሩ ሲጠቃለል እንዲህ ይላል፡- ማናቸውም ነገሮች ወደፍፃሚያቸው ያመራሉ (everything moves toward disorder)፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆነ በምሳሌ እንመልከት፡፡

አስተዉሉ! በዝግመታዊ ለውጥ ጋሽአጃግሬዎች ፍልስፍና፡- ማናቸውም ነገሮች ያለማቋረጥ ይበልጥ ወደ ላቀና ይበልጥ ወደተወሳሰበ ስርዐት (order) ያድጋሉ፣ ያመራሉ ወይም ይለወጣሉ፡፡ በሌላ ቋንቋ ነገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሉ እንጂ እየወረዱ (እያሽቆለቆሉ) አይሄዱም፡፡

በማሞቂያ ማሽን ላይ በ150 ዲግሪ ፋራናይት እየሞቀ ያለ ውሃ፣ ማሞቂያ ማሽኑ ስራ ሚያቆም የውሃው ሙቀት ከመጨመር ይልቅ መቀነስ ይጀምራል፡፡ ሙቀቱ ከመጨመር ይልቅ መቀዝቀዝ ይጀምራል፡፡ በኮረብታ ላይ ኮስ ብታስቀምጥ ቁልቁል ይወርዳል እንጂ ሽቅብ አይወጣም፡፡ አንድን ስራ ለመስራት ጥቅም ላይ የዋለ ሃይል (ጉልበት) ከመጥቀም ወደ አለመጥቀም ይጓዛ፡፡ ከከፍተኛ ወደ ሙጣጭ ብሎም ምንም ይሸጋገራ፡፡

ይህ ጉዳይ ከምናወራው የፍጥረት ጉዳይ ጋር ሲዛመድ፣ ሁለተኛው የቴርሞዳይናሚክስ ሕግ፡- ጠፈር (universe) ወደ አለመኖር ይጓዛል፡፡ ወደመጠቅለል ይፈጥናል (It moves towards disorder)፡፡ እንጂ ፈፅሞ ወደተሻለ ስርዐት፣ ወደ በለጠ ውስብስብነት አያዘግምም፡፡ ይህ እንግዲህ የ 2ተኛ የቴርሞዳይናሚክ ሕግ ነው፡፡

ይህ ሕግ ከዝግመታዊ ለውጥ አራማጆች (evolutionist) እሳቤ ጋር በግልፅ እንደሚላተም ልብ ይሉዋል፡፡ ይህንን ሀቅ የዝገምታዊ ለውጥ አራማጆቹም ሳይቀር በይፋ እንዲ ሲሉ ገልፀውታል፡- የዝገምታዊ ለውጥ መላምት እና የ 2ተኛው ቴርሞዳይናሚክስ ሕጎች በፍፁም አብረው ሊሄዱ የማይችሉ ናቸው፡፡

ኦልደስ ሄክስሊ ሲናገር፡- “ነገሮች ወደተሻለና ወደ ተወሳሰበ ስርዐት ያዘግማሉ’’ በሚለው የዝገምታዊ ለውጥ እሳቤ እና ‘’ነገር ሁሉ ወደፍፃሜው ለመድረስና ለመጠቅለል ይጓዛል’’ በሚለው የ 2ተኛው ቴርሞዳይናሚክስ ሕግ መካከል ግልፅ ግጭት ይስተዋላል ይላል፡፡ ሆኖም የ2ተኛው ቴርሚዳይናሚክስ ሕግ ከዝገመታዊው መላምት ይልቅ በብዙ መመዘኛዎች ብዙዎችን የሚያስማማ እሳቤ ነው፡፡” (ምንጭ፦morris, Henry M. The Twi light of Evolution, Grand Rapids: Baker Book House, 1967, p.35).

ይህ ብዙዎችን ሳይንቲስቶች የሚያስማማ የቴርሞዳናሚክስ ሕግ የዝግመታዊዉ ለውጥ መላምት አራማጆች ራሳቸውን እንዲጠይቁ የሚያደርግ መሆኑን አንባቢ ልብ ይበል።

የፍጥረት ማስረጃዎች

አሁን ከላይ ባነሳናቸው ሳይንሳዊ እሳቤዎች ግጭት መሃል የጨለፍነው አንድ እውነት አለ፤ ይህም – ፍጥረት ከምንም ተነስቶ ወደ አለመኖር የከተመ ሳይሆን አንድ ፈጣሪ እንዳለው። የሚቀጥሉት አንቀፆች ስለፍጥረት አስደናቂ ማስረጃዎችን ጀባ ይሏችኋል፡፡

የዝግመታዊ ለውጥ መላምት ያለምንም ሕፀፅ በሳይንሱ አለም ሞገስ ያገኘና ሲያገኝ የሚኖር የዳርዊን ምትሀታዊ የፈጠራ ውጤት እንደሆነ የሚያምኑ በአገራችን ጥቂት እንዳልሆኑ እገምታለሁ፡፡ ሆኖም ይህ እሳቤ እርስ በእርስ በሚጠረሱ በርካታ እሳቤዎች የተሞላ መሆኑን ሳስገነዝብዎ ለአንድ አላማ ነው፡፡ ስለፍጥረት መገኘት ዳርዊን የቀመረልዎ ቀመር እርስ በእርሱ የተምታታና በሌሎች መሰረታዊ የሳይንስ ሕጎች እንኳ ሊደገፍ የማይችል የፈጠራ ሃሳብ መሆኑን ተገንዝበው፣ ሳይንስ ያረጋግጠው ካልሆነ በስተቀር በማስረጃ አስደግፎ ሊሽረው የማይችለውን ሃቅ፡- እርሱም ፍጥረት በፈጣሪ እንደመጣ ተቀብለው ሕይወት እንዲሆንልዎ፡፡

የዝግመታዊ ለውጥ መላምት ደግሞ ደጋግሞ ሊያስረዳን የሚሞክረው ጉዳይ አለ፡፡ ፍጥረት እንዴት በዝገምታዊ ሂደት ውጤት ሕይወት ከሌለው ግዑዝ እና ተራ ነገር ወደ እጅግ ዉስብስብ ሕይወት ወዳለው ቅርፅ መለወጡን፡፡

በዝግመታዊ ለውጥ መላምት ውስጥ ባሉ የተለያዩ ንዑሳን እሳቤዎች መካከል የሚስተዋለው ግጭት ዋነኛ ምክንያት እያንዳንዱ ንዑሳን እሳቤዎች እርስ በእርሳቸው መላና ውል በሌላቸው አመክንዮ (logic) የተጎነጎኑ መሆናቸው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ለአብነት ከዚሁ እሳቤ መንደር እንቃርም፡፡ “ብዙ የዝመታዊ ለውጥ ምሁሮች የሰው ልጅ በኬሚካላዊ ተፈጥሮው (ይዘቱ) 99 በመቶ ከጦጣ ጋር ሲመሳሰል በደም እርጥበት ምርምር ውጤቶች ደግሞ (Blood precipitation tests) ቺምፓንዚ የቅርብ ዘመዳችን ይሆናል፡፡ እነሱ እዚህ ሊያቆሙንና የእውር ድንብር ሊመሩን ወደፈለጉት – የጦጣ ዘመድህ ቺምፓንዚ አጎትህ – ማጠቃለያ እንድንደርስ ይወዳሉ፡፡ እኛ ደግሞ እስቲ እነሱ ወደጀመሩት፣ ግን ሊቀጥሉት ወዳልፈለጉት የላቦራቶር ምርምር ውጤቶች ዜና ለአፍታ ጎራ እንበል፡፡

በኮሌስትሮል መጠን ቴስት የቅርብ ዘመዳችን ማን ቢሆን መረጡ? የሚመርጡት መሆኑን እየተጠራጠርኩ ልንገርዎ፤ ዘመድዎ ጋርተር የተባለው እባብ ነው፡፡ የእንባ ኢንዛይም ኬምስትሪ ደግሞ ዶሮን የቅርብ ስጋ ዘመዳችን እንደሆነ ይናገራል፡፡ በሌላ የደም ኬሚስትሪ ቴስት ውጤት ደግሞ ቢያምኑም ባያምኑም የቅርብ ዘመዳችን የቅቤ ባቄላ አደንጓሬ (the butter bean) ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ምንጭ፡-(Morris, Henry M., The Twilight of Evolution, Grand Rapids: Baker Book, 1967).

የሕይወት ውስብስብነት

ሁላችንም በተንቀሳቃሽ ፊልም አልያም በአካል ከፍተኛ ፍንዳታዎችን ሰምተናል፤ አይተናል፡፡ እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡፡ ከነዚህ ፍንዳታዎች በኃላ ፍንዳታዎቹ ያስከተሏቸው ስርዐት ያለው ውጤት ተመልክታችሁ ታዉቃላችሁ? እንበልና የፍንዳታው የፈጠረው ምርጥ ስርዐት፣ ፍንዳታው የፈጠረው ውብ ነገር? መልሳችሁ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አይሳነኝም፡፡ ፍንዳታ ስርዐት አልባነትን ከማስከተል ሌላ ምን ሊፈይድ፤ ፍንዳታ ያነን ነገር ወደ አለመኖር ከማሻገር የዘለለ ምን ሊያመጣ፡፡ በቃ ይኸው ነው፤ ከባድ ፍንዳታ፤ ቀጥሎ ቀውስ፣ ፍርስራሽ፡፡ ሌላ ምን ሊሆን፡፡ ይህ ጉዳይ በዚ አያበቃም ይህ መንደርደርያ ለማሰብ ወደሚከብደኝና ብቻዬን ፈገግ ወደሚያሰኘኝ ፍልስፍና መንደር ጎራ ያደርገናል፡፡

የቢንግ ባንግ መላምት/Binbang theory ይሰኛል፡፡ የታላቅ ፍንዳታ መላምት መሆኑ ነው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሲቀበሉት በኩራት ነው፡፡ በፍጥረት ጉዳይ ላይ በአንድ ወቅት ከአንድ ኢ-አማኝ አውሮፓዊ ጋር ባደረኩት ቆይታ ይህንን ኩራት ተመልክቼዋለሁ፡፡ እስቲ ይህ ጉዱይ እናንተን ያኮራ ይሆን ያሸማቅቅ ለማየት ወደማዕዱ እንዝለቅ፡፡

እስቲ ከዚ በታች፣ ፍንዳታ – በዙሪያችን የምናየውን እና እኛን የመሰለ ግሩም ፍጥረት ለመፍጠር ያለውን የእድል ሂሳብ (probability) አስመልክቶ ከአንድ ምሁር የተሰጠ አስተያየት እንመልከት፡፡

ምሁሩ ዶክተር ራንግአንታን ይባላሉ፡፡ እኔ ይላሉ እኚ ሰው፤ “እኔ፣ ሕይወት የታላቅ ፍንዳታ ውጤት ነው የሚለውን መላምት፣ ከአንድ የማተሚያ ቤት ቃጠሎ ውስጥ አንድ ጥሩ መዝገበ-ቃላት ማግኘት ተቻለ ከሚለው የቅዠት ሃሳብ ለይቼ አላየውም፡፡” ሲሉ የዚህን ፍልስፍና ስር አልባ አመክንዮ ገልፀዋል፡፡ (ምንጭ፡ Origins?, P.15).

ሌላው ሳይንቲስ፣ ሰር ፍሬድ ሆይል፣ እንግሊዛዊ አስትሮነመር እና የካምብሪጅ ዮኒቨርሲቲ አስትሮኖሚ ፕሮፌሰር፣ በታላቅ ፍንዳታ ምክንያት ሕይወት ሊፈጠር ይችላል የሚለውን መላምት ሲተቹ እንዲ ይላሉ፡-“ በዚ መልክ ሕይወት ሊገኝ ይችላል ብሎ ማሰብ በቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች መካከል የነፈስ ከባድ አውሎንፋስ ተረፈ ምርቶቹን አላትሞና አጋጭቶ ሲያበቃ አንድ ቦይንግ 747 አውሮፕላን እነሆኝ ሊል ይችላል ብሎ ከማሰብ የተሻለ ነው ብይ አላየውም” ብለዋል፡፡ (ምንጭ፡ Nature, vol. 294, Nov.12, 1981, “ Honye on Evolution,” p.105).

አስደናቂ ሕዋሶች (cells) እና የውስብስብነት የመጨረሻ ደረጃ (Irreducibil complexity)

ወደ ትንታኔ ሐሳብ ከመግባቴ በፊት “የውስብስብነት የመጨረሻ ደረጃ” የሚለውን ሃሳብ ግልፅ ማድረግ ይጠበቅብኛል፡፡ ይህንን ሃሳብ ለመረዳት ምሳሌ መውሰዱ የተሻለ አማራጭ ይመስለኛል፡፡

ሁላችንም የአይጥ ወጥመድ እናቃለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ቢያንስ አንድ አጥምደን አልያም ሲጠመድ አይተን ይሆናል፡፡ ወጥመዱ የተፈበረከበትን ተግባር ሳያስተጓጉል፣ ከተሰራበት አካል አንድ አጉድሉ ብትባሉ የቱን ትፈቱ ይሆን? ምላሾቹ፡- “ሁሉም አካላት ወጥመዱ የተሰራበትን አላማ ለማሳካት አስፈላጊዎች ናቸው” እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ የወጥመዱን ውስብስብነት ከዚ በተሻለ መቀነስ አትችሉም፡፡ ይሄ የመጨረሻ ደረጃ ውስብስብ አካል ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ከላይ በርዕሱ የሰፈረውን የመጨረሻ ደረጃ ውስብስብነት ሃሳብ ያስረዳል። እንዲሁ፣ አንዳንድ ሕይወት ያላቸው አካላት ካሉበት የዉስብስብነት ደረጃ ዝቅ እንዲሉ ለማድረግ መሞከር፣ የወጥመዱን አንድ አካል አጉድሎ አይጥ በአግባቡ እንዲያጠምድ ለማድረግ እንደመሞከር የማይቻል ተግባር ነው፡፡ አንዱን አካላቸውን አጎደልን ማለት አጠቃላይ የአሰራራቸውን መዋቅር አናጋነው ማለት ይሆናል፡፡ በአጭሩ በሕይወት ያሉበት ደረጃ፣ የመጨረሻው የውስብስብነት ደረጃ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ የመጨረሻ ደረጃ ውስብስብ መዋቅር በሂደት የሚገኝ (የሚፈጠር) አይሆንም፡፡ ከነሱ በታች ዝቅ ያለ የውስብስብነት ደረጃ ስለሌላ ኢቮልቭ (evolve) ሊያደርጉ አይችሉም። በሕይወት ለመኖር አንዳች ነገራቸው ሳይጎድል ባሉበት ሁኔታ መገኘት (መኖር) አለባቸው፡፡ ምክንያት ቢሉ የሕልውናቸው መዋቅር ይህና ይህ ብቻ ነውና፡፡ ከዚ አንዱ ቢጎድል፣ እነሱ የሉም፡፡

ሕይወት፣ ሕይወት ሰጪን ይሻል

አሁን በዚች ምድር ላይ የምናያቸው ፍጥረታት ከየት ተገኙ? እንዴት እዚ ተገኙ? መፅሐፍ ቅዱሳችን በስድስቱ ቀኖች ተፈጠሩ ይለናል ዘፍ 1፡፡ ይህ እውነት ነው? ወይስ ሕይወት ወደመገኘት፣ ወደመታየት የመጣው በራሱ ነው?

ሁሉም የመጀመሪያ አመት የሥነሕይወት ሳይንስ (Biology) ተማሪዎች የሚያዉቁት የባዮጄነሲስ ሕግ (The law of Bioginesis) ምን እንደሚል እንይ፡፡ ልብ አርጉ አሁን እያወራሁት ያለው እምነት ሳይሆን ሳይንስ ነው፡፡ ይህ ሕግ እንዲህ ይላል፡፡ የማንኛውም ሕይወት አስደማሚ ንድፍ ከእርሱ ቀድሞ ከነበረ ሕይወት ይገኛል፡፡ በአጭሩ ሕይወት ከሕይወት ይገኛል ማለታቸው ነው፡፡ እንግዲህ ይህ የባዮጄነሲስ ሕግ ከዝግመታዊ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ጋር እንዴት እንደሚላተም አስተውል፡፡ ምክንያት ቢሉ፡- የዝግመታዊ ለውጥ መላምት ሕይወት ከቢሊዮን አመት በፊት በጠፈር ላይ ባልታወቀ ምክንያት በተፈጠረ ከፍተኛ ግጭት ምክንያት ተፈጠረ ብሎ ያምናልና፡፡ ያምናልና የሚለው ቃል ላይ ያስመርኩበት ምክንያት አለኝ፡፡ ይህ መላምት ሳይንስ ሊባል የማይችል እንደሆነ ልብ እንዲሉ ነው፡፡ በአጭሩ አንዳንድ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ብዬው ልለፍ፡- የዝግመታዊ ለውጥ መላምት “ሳይንሳዊ” እምነት ነው፡፡

እነዚህ የስነ-ሕይወት ሳይንቲስቶች፣ በእንስሳት አሀዱ (ረቂቅ) ህዋስ (protozoa) እና በእፅዋት አሀዱ (ረቂቅ) ህዋስ (bacteria) ላይ ያደረጉትጥናት ማጠቃለያ የሚለው አንድና አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ይህም፣ የሕይወት ምንጭ ሕይወት ብቻ ነው፡፡ አለቀ፡፡ እንግዲህ በመረጃ የተደገፈውና በቤተሙከራ የተረጋገጠው ሳይንስ መጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ከሰፈረው እውነት ጋር አልተጋጨም፡፡ የዝግመታዊ ለውጥ መላምት ከእምነታችን ጋር ብቻ ሳይሆን ከሳይንስም ጋር የሚጋጭ ጭፍን መላምት እንደሆነ አንባቢዎቼ ልብ እንዳሉ ላሳስብና ወደ ጀመርኩት ሃሳብ ላዝግም፡፡

‘አንድ ሕዋስ (cell) ቀድሞ ከነበረ ሌላ ሕዋስ ብቻ ይገኛል’፣ የሚለው ማጠቃለያ የቤተ-ሙከራቸው ውጤት በመሆኑ የስነ-ሕይወት ተመራማሪዎች፣ በኩራት ይናገሩታል፡፡ ለምን ይሆን? በማይከፋፈል የመጨረሻ ቅርፅ ወይም ደረጃ ላይ ያሉ ሕዋሶች ከምትገምቱት በላይ ውስብስብ ናቸው፡፡ ለአብነት “በራሱ መኖር የሚችለው የመጨረሻው ተራ (ቀላል) ሕይወት ያለው የ prokagote bacteria ሕዋስ ለአይምሮ የሚደንቅ ውስብስብ ተፈጥሮ አለው፡፡ ይህ ውስብስብነቱ ከመንኮራኩር ቴክኖሎጂ ጋር ሲነፃፀር፣ ይህን ዘመነኛ የጠፈር ቴክኖሎጂ ተራና ምናምንቴ ያደርገዋል፡፡” (ምንጭ፡ Darwin on Trial, Philip Johnson, p.102)

ቀጥለን የምንመለከተውም ምንጭ የሕዋስን ውስብስብነትንም ሆነ መገኛ ምንጭ በማስረዳት ረገድ እላይ ካነሳነው ሃሳብ ያልተናነሰ ፋይዳ አለው፡፡ “አንድ ሕዋስ በሕይወት ለመኖር የተለያዩ አገልግሎትን የሚሰጡት አካሎቹ (ክፍሎቹ) ሁሉ በአንድነት ያስፈልጉታል (ትርፍ አካል የለውምና)። እንግዳውስ ሕይወት በዝግመታዊ ለውጥ ተገኘ ካልን- በቢሊዮን የሚቆጠሩ የአንድ ሕዋስ የተለያዩ ክፍሎች በአንድ ጊዜ እና በአንድ ቦታ በሕይወት መገኘት አለባቸው፡፡ ይህ ብቻ አይበቃም፡፡ እነዚህ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አካላት ሕዋሱን ለማስገኘት በአንድ መንገድ ብቻ መደራጀት (መዋቀር) አለባቸው፡፡” (ምንጭ፡ Origins?, Ranganathan, B.G., p. 15)

እንግዲህ በሳይንሱ መሰረት ይህ ሕዋስ በቢሊዮን የሚቆጠሩ አስፈላጊ ክፍሎቹ በተመሳሳይ ጊዜና በአንድ ቦታ በአንድነት መገኘት ካልቻሉ ሕዋሱ ሕይወት የለውም፡፡ በዝግመት አካሎቹ መፈጠር አይችሉም ማለት ነው፡፡ በአጭሩ የዝግመታዊ እድገት መላምት ለዚ የመጨረሻ ደረጃ የሕይወት አካል መፈጠር ፋይዳ የሌለው መላምት ነው፡፡ አንባቢ ልብ ይበል እስካሁን ያወራነው ስለመጨረሻው ረቂቅ (አሃዱ) ሕዋስ አፈጣጠር ውስብስብነት ነው፡፡ ስለከፍተኛ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ውስብስብነት ምን ሊመስል እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ይቻላል፡፡ የዝመታዊ ለውጥ አራማጆች፣ በአንድ ወቅት ድንገት፣ ባልታወቀ ምክንያት፣ ተከስቶ ይሆናል በሚሉት ግጭጥ ተፈጥሯል የሚሉን ይህንን ውስብስብ የሕይወት ሥርዐት መሆኑን አንባቢ ልብ ይበል፡፡

አስደማሚው የሰው ልጅ ጭንቅላት/አእምሮ

ቆም በልና አስብ፡፡ በዙሪያህ ያለውን ፍጥረት በአንክሮ ተመልከት፡፡ ምድርን ሰማይንም በጥሞና አስተውል፡፡

እስቲ እልፍ አእላፋት የሆኑትን ፈለኮች (planets)፣ ከዋክብት፣ ጋላክሲዎች ለማስተዋል ሞክር፡፡ በቀለም፣ በቅርፅ፣ በመጠን፣ በውበትና የቆይታ ዘመናቸው እጅግ የተለያዩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዕፅዋት ዝርያዎችን ተመልከት፡፡ ከቃል ይልቅ ዝምታ ይገልፃቸው ካልሆነ ሌላ በምን መልክ ትተርካቸዋለህ!

እስቲ ስለምግብ ጥቂት ብዬ ልለፍ በምድራችን ላይ ያለው የምግብ አይነት ሕፀፅ በማይወጣለት አስገራሚ ስርዐት ተዋቅሮ ለእንስሳት አልያም ለዕፅዋት ቀርቧል፡፡ የሰው ልጅ በዚ ስሕተት የለሽ የምግብ ስርዐት ውስጥ እጁን አስገብቶ “ላሻሻል” ሲል የፈጠረው ውጥንቅጥ ከማንም የተሰወረ አይደለም። የዘረመል ምህንድስና እያደረሰ ያሰውን ቀውስ ልብ ማለት ብቻ ለዚህ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ የሰው ልጅ እጁን ሰብስቦ እግዚአብሔር የፈጠረለትን ብቻ ቢመገብ ከምግብ ጋር በተያያዘ የሚመጡ በሽታዎችን ደጅ በላንኳኳ፣ እነሱም ደጅ ደፍተው ዝለቅ ባላሉት ነበር፡፡

እጽዋት ለሰው ልጅ ምግብነት እስከሚደርሱበት ድረስ የሚያደርጉት የእድገት ጉዞ ተአምራዊ በሆነ ውስብስብነት የተሞላ ሂደት ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ጥልቅ ያልሆነ ገለፃ ለመስጠት እንኳ የራሱ የሆነ መፅሐፍ ማዘጋጀት ግድ ይላል፡፡

አሁን ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነፍሳትን ጨምሮ በርካታ የእንስሳት ፍጥረትን አስተውል፡፡ እነዚህ ደግሞ ከእፅዋቱ አለም በተለየ መልኩ አስገራሚና አስደማዊ ተፈጥሮአዊ ባሕሪ አላቸው፡፡ ጭብጤ ምንድን ነው? እነዚህ ነገሮች የቱንም ያህን አስገራሚና አስደማሚ ቢሆኑም የሰውን ጭንቅላት/አእምሮ ግን ፈፅሞ ሊተካከሉት አለመቻላቸው የትንታኔዬ ጭብጥ መሆኑ ይሰመርልኝ፡፡ ማንም ይህንን እውነት አይጠራጠርም፡፡

የሰው ልጅ የፈጠራ ችሎታ ውሱንነት

የሰው ልጅ ምን መስራት ችሏል? በጠቀሜታቸው ሰፊ ቦታ ያላቸውና ውስብስብ የሆኑ እንደ ስልክ፣ መኪና፣ ባቡር፣ አውሮፕላን፣ ኮምፒውተር፣ የፋክስ ማሽን፣ መንኮራኩር ወዘተ፡፡

የእነዚህ ድንቅ ፈጠራዎች ባለቤቶች አንድ ውሱንነት አላቸው፡፡ እነሱ ብቻ አይደሉም ማንም ሰው ቢሆን የሰው ጭንቅላት (አዕምሮ) መስራት አይችልም፡፡ ማንም ሰው የሰራው ነገር ሁሉ ከሰው ያነሰ ነው፡፡ እስቲ ሰው ሰርቶት ካበቃ በኋላ ከሰው በላይ የሆነ አንድ ነገር ጠቁሙኝ፡፡ አንድም ነገር ልናስብ እንደማንችል አልጠራጠርም፡፡

እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ላንሳልህ አንተንና አዕምሮህን ማን ፈጠረ? ዳዊት (መዝ 139፡14) ያለውን ምስክርነት ልጥቀስልህ ወይስ የዳርዊንን መላምት? ዳርዊን ያለውንማ አየንኮ፡፡ እስቲ ዳዊት ምን አለ? “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለው።” ለራስህ እውነተኛ ሁን። እውን ካንተ የሚያንስ አንድ ግዑዝ አካል ድንገት፣ ባልታወቀ ሁኔታ አንተን ፈጠረህ? ወይስ ካንተ የበለጠ አምላክ ሰራህ? የትኛውን ማመን እንደሚከብድህ አንተ ታውቃለህ?

ሆኖም አንድ ነገር ልምከርህ፡- ይህ ባንተ ውስጥ ያለው ታላቅ የፈጠራ ብልህነት፣ አመክንዮ፣ ምክኒያታዊነት፣ ሃሳብ፣ ፈቃድ፣ ፍላጎት፣ ቅልጥፍና፣ ወዘተ ባንድ ወቅት ምናልባት በተከሰተ ያልታወቀ ግጭት ምክንያት የተፈጠረ ነው ብለህ ራስህን አትስደብ፡፡

እስቲ አንድ እርምጃ ወደፊት እንሂድ

መለስ በልና ቀደም ብለን የተናጋገርንባቸውን ጉዳዮች አስባቸው ስለ ጠፈርና በውስጡ ስላለው ነገር፡- ስለ ከዋክብት፣ ስለፈለኮች፣ ስለጋላክሲዎች፣ ስለተክሎች፣ ስለ እንስሳት፣ ስለ ሰዎችና ስለሰዎች አእምሮ፡፡

ሁሉን ለመፍጠር የምትችል እንደሆንክ ራስህን ለአንድ አፍታ አስብ፡፡ በእውነት እንዲህ አይነት ውበት፣ ግርማ፣ ብዛት፣ የምህንድስና እወቀትና ምጥቀት የተጎናፀፈ ፍጥረት የምትፈጥር ይመስልሃል? ማንም ሳይረዳህ መሆኑን አትዘንጋ፣ የምትገለብጠው ወይም የምታገናዝብበት ሕግ/ደንብ ሳይኖርህም ጭምር፡፡

እያንዳንዳቸው በአማካይ 100 ቢሊዮን ከዋክብት ያሏቸው ከ 1 ትሪሊየን በላይ ጋላግሲዎችን ዲዛይን ማድረግ ትችል ይሆን? ምንም ማገናዘቢያ ሳይኖርህ፣ ከምንም ተነስተህ፣ ብርሃንን ከፈጠርክ በኋላ 186,000 ማይልስ በሰከንድ እንዲሮጥ ልታዘው ታስብ ይሆን? ድምፅንስ ፈጥረህ በሰዓት 660 ማይልስ እንዲጓዝ ትወስነው ይሆን? ለሳይንስ የታወቁትን አቶሞችንና ንዑስ አቶሞችን ታበጃቸው ነበር? እነዚህን አቶሞች ወደ ውስብስብ ሞሎኪውሎች በመቀየጥ ለቁጥር አታካች የሆኑ ተግባራት እንዲከውኑ ታዛቸው ይሆን? እርስ በእርሳቸው ተደጋጋፊ ከመሆናቸው በላይ በዕፅዋት አለም ውስጥም ጭምር ይህንን ባሕሪ በተግባር የሚገልጡ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ እንስሳትን ምንም አይነት ኮድ ሳትኮርጅ ትፈጥር ይሆን? ለነዚህስ የሚሆን አስፈላጊውን የምግብ አይነት ሁሉ ታበጅላቸው ይሆን? እንዲህ እያልኩ ልከርም እችላለሁ፡፡ ሆኖም የምጓዝበትን መንገድ ጫፍ አይተኸው እንደሁ፣ እዚ ላይ ላቁም፡፡

አንተና የአንተ አእምሮ በነሲብ በሆነ እድል ምክንያት ካለመኖር ወደመኖር መቷል ብለህ ራስህን እንዳትሰድብ እንደመከርኩህ ሁሉ እነዚህ አስገራሚና እጅግ ውስብስብ የሆኑ ፍጥረታት ሁሉ በድንገትና በእድል ተገኝተዋል ብለህ ፈጣሪን እንዳትሰድብ ልምከርህ፡፡ ሞኞች ይህን ብለው ከሆነ አንተ ይህን የሞኝነት መንገድ ልትከተል አይገባህም፡፡ በማስተዋል ከመረመርክ የእግዚአብሔርን መኖር ለማረጋገጥ መጽሐፍ ቅዱስን መጥቀስ ግድ አይልም፡፡ የተገለጠው ፍጥረት እርሱን በግልጥ ይሰብካሉና፡፡ በሳይንስ ርዕስ ስር ምክንያትንና አመክንዮን መሰረት በማድረግ እያወራን እንደሆነ ለአፍታ እንዳትዘነጋ ደግሜ ላስታውስህ፡፡ አምክንዮአችንም ሆነ ምክንታችን የእግዚአብሔርን መኖር በግልፅ ከማወራት ሌላ ተቃርኖ እንደሌላቸው ማጠቃለል የምንችልበት ደረጃ የደረስን ይመስለኛል፡፡

እንግዲህ ልብ በል፡፡ የዳርዊን ዝግመታዊ ለውጥ መላምት፣ ሳይንስ አይደለም፤ መላምት እንጂ፡፡ የዳርዊን መላምት፣ ሳይንስን ሳይንስ ሚያሰኙ ተጨባጭ ማስረጃዎች (empirical evidence) የማያሟላና በግምት የተሞላ እሳቤ ነው፡፡ ዳርዊን ራሱ ሲናገር ያሰብኩት ሃሳብ “ቅዠት ይሆን….” ብሎ በመላ ምቱ ይጠራጠራል፡፡ ይህን ሃሳብ በሞኝነት መቀበል ምርጫህ ከሆነ ልቤ በጣም ያዝንልሃል፡፡

የቅሬተአካል መዝገብ ክፍተት (missing link)

የዝግመታዊ ለውጥ አራማጆች ለመላምታቸው ደግመውና አበክረው እንደማስረጃ የሚያቀርቡት የቅሬተ-አካል ስብስቦችን ነው፡፡ በእውኑ ይህ ማስረጃ አለ ይሆን? በውኑ እነዚህ አጥንቶች የሰው ልጅ በዝግመታዊ ለውጥ መምጣቱን ያስረዱ ይሆን? የሳይንሳዊው መዝገብ ሃቅ ምን ይላል? አስታውሱ አሁን የምንፈልገው እዉነታዎችን፣ ማስረጃዎችን እንጂ መላምቶችንና እምነቶችን አይደለም፡፡

የአንድ እውቅ ቅሬተ አካል አጥኚ አባባል እነሆኝ፡፡ ዶክተር ኮሊን ፓተርሰን ይሰኛሉ፡፡ በእንግሊዝ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም አንጋፋ የቅሬተ አካል ተመራማሪ ናቸው፡፡ የቅሬተ አካል ችግርን አስመልክቶ ለ ሰንደርላንድ በፃፉት ደብዳቤ እንዲ ይላሉ፡-“የዝግመታዊ ለውጥ ሽግግርን በተመለከተ በሰጠኸው አስተያየት ቀጥተኛ የሆነ ማስረጃ ለማቅረብ ያለውን ውሱንነት ሙሉ በሙሉ የምቀበለው ነው፡፡ በእጃችን ካለው በተጨማሪ የማውቀው በህይወት ያለ ማስረጃ ወይም በቅሬተ አካል ማስረጃነት ሊጠቀስ የሚችል ነገር ቢኖር፣ ባካተትኩት ነበር … እናም ጎልድና የአሜርካ ሙዚየም ሰዎች ‘የሽግግር ቅሬታ ማስረጃዎች የሉም’ ብለው የሚያነሱትን ሙግት መቃወም እጅግ ከባድ ነው፡፡ ማናችንም ብንሆን ሽንጣችንን ገትረን የምንከራከርበት እንዲህ ያለው አስረጅ ቅሬተ አካል የለምና”።

ጥቂት ቅሬታዎች

በ1920 እ.ኤ.አ በምእራብ ኔብራስካ አንድ ጥርስ ተገኘ፡፡ በርካታ ሳይንቲስቶች ይህንን ክፍተት (missing link) ሊሞላ የሚችልና የሰው ልጅ በዝግመታዊ ለውጥ ሂደት መገኘቱን የሚያስፈዳ ግኝት ሲሉ አወደሱ፡፡ ጥርሱ ሰው እንዲመስል ከተበጀ በኋላ በተገኘበት ቦታ ስያም ተሰጠው፡- “የኔብራስካ ሰው”፡፡

ግኝቱ፣ የዝግመታዊ ለውጥ አራማጆችን ጮቤ ያስረገጠ ታላቅ ዜና ነበር፡፡ ሆኖም ብዙ ሳይቆይ አንድ አሰቂኝ ነገር ተፈጠረ፡፡ ከአምስት አመት በኋላ አንድ ሰው ስለተገኘው ጥርስ የአንድ ገበሬን አስተያየት መጠየቅ ፈለገ፡፡ ምላሹም ጥርሱ “የኣሳማ ጥርስ” ነው የሚል ነበር፡፡ ጥርሱ በተገኘበር አካባቢ በተደረገው ተጨማሪ ጥናት የተገኙት ቀሪ ቅሪት አካሎች የገበሬውን አስተያየት የሚያረጋግጡ ሆነው ተገኙ፡፡

የዝግመታዊ ለውጥ አራማጆች ያለውን የሽግግር ለውጥ ክፍተት ለመሙላት በማስረጃነት የሚያቀርቡት ብዙ ጊዜ አጥንት ወይም የአጥንት ስብርባሪዎችን ነው፡፡ አንድ ሰው ጥቂት ስብርባሪ አጥንቶች ያገኛል፡፡ በመቀጠል የተራቀቁ አርቲስቶች ክፍተቱን በመሙላት ሰው እንዲመስል የበኩላቸውን ሙያዊ ሚና ይወጣሉ፡፡ በመቀጠል ስም ይወጣለትና የሚታይ የዝግመታዊ ለውጥ ማላምት ማስረጃ ይባል፡፡

በአንድ ወቅት “Orce Man” የተባለውና መጨረሻ የአህያ የራስ ቅል መሆኑ የተረጋገጠው፤ በአንድ ወቅት “Ramapithecus Man” የተባለውና መጨረሻ የዝንጀሮ የራስ ቅል መሆኑ የተረጋገጠው፤ እንዲሁም የኒያደርታል ሰው ከፊል ጦጣ ከፊል ሰው የሆነ የሽግግር ወቅት እንስሳ ሳይሆን በሪኬት በሽታ ምክንያት እግሮቹ የተንሻፈፉ bow-legged የሆነ ሰው መሆኑ መረጋገጡ የዚህን መላምት ቀልደኛ ሃሳቦች ይበልጥ ይፋ የሚያወጡ ናቸው፡፡

ከዚህ በታች የቀረቡት የሳይንቲስቶች አባባል የዝግመታዊ ለውጥ መላምት አራማጆች ሃሳብ ምን ያህል እርባና ቢስ መሆኑን ጮኸው ያሳብቃሉ።

ዶክተር ቲም ዎይት፣ የካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ አንትሮፖሎጂስት፣ በርክሌይ፣ New scientise, ኤፕሪል 28, 1983, p. 199 እንዲህ ይላሉ፡- “ከአምስት ሚሊዮን አመት በላይ ያስቆጠረና የሰውን የደረት ክፍል ከትከሻው ክፍል ጋር ከሚያገናኙ ሁለት አጥንቶች አንዱ እንደነበረ ሲነገርለት የቆየው ቅሬተ አካል (collarbone) በመጨረሻ የዶልፊን የጎድን አጥንት ሆኖ መገኘቱ… የብዙ አንትሮፓሎጂስቶች ችግር የሰው ቅሬታ አካል ለማግኘት ካላቸው መጠን ያለፈ ጉጉት የተነሳ፣ የተገኘ አጥንት ሁሉ የሰው መሆን አለበት የሚል መደምደሚያ ላይ ፈጥነው መድረሳቸው ነው፣” ሲሉ የዚህን መላምት በውጥረት የተሞላ አካሄድ አጋልጠዋል።

ሌላ በፊዚክስ የዜና መፅሔት ላይ የቀረበ ፅሁፍ እንመልከት፡- “በእውነቱ ከሆነ የዝግመታዊ ለውጥ መላምት ሳይንሳዊ ሐይማኖት ሆኗል፤ ብዙ ሳይንቲስቶች በሐይማኖቱ አምነዋል የቀሩት ደግሞ ሃሳባቸው እርሱን እንዲመስል እያስገደዱት ይገኛሉ፡፡” (H.s. Lipson, FRS, Prof. Df physics, Univ. of Manchester, UK, ‘A Physicist Looks at Evolution, ‘physies Bulletion, Vol. 31, 1980, P. 138)

የዝግመታዊ ለውጥ “ሳይንሳዊ” ሐይማኖት ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ በዝግመታዊ ለውጥ ሂደት ተገኝቷል ብሎ ያምናል፤ ያረጋግጣል አልወጣኝም፡፡ ይህ ማለት አሁን በምንኖርበት አለምም ጭምር በዚ የለውጥ ሂደት ላይ የሚገኙ ሕይወት ያላቸው ነገሮች አሉ ማለት ነው። አልያም ቅሬታቸውን ማግኘት እጅግ ቀላል ይሆን ነበር ማለት ነው፡፡ በቀላሉ በምሳሌ ላስቀምጥላችሁ፡፡ የሰው ልጅ ለሱ የቅርብ “ዘመድ” ከሆነው ጦጣ ነው ኢቮልቭ ያደረገው ይሉናል፡ እንግዲህ እንዲህ የሚሉት አማኞች የጦጣነት ዘመናቸውን አጠናቀው ሰው መሆን የቻሉ እድለኞች ናቸው ብለን ብናስብ፣ በመላምቱ መሰረት እነሱ ወደደረሱበት የሰውነት ደረጃ ለመድረስ እድሜ ያላደላቸው በሰውና በጦጣ ዝርያ መካከል የሚገኙ ሰው መሰል ጦጣዎች (ከፊል ሰው ከፊል ጦጣ) በአሁኑ ሰአት በአለማችን በብዛት መገኘት ነበረባቸው፡፡ ሆኖም እነዚህ ከፊል አንዱን ከፊል ግሞ ሌላውን የሚመስሉ እንስሳት ይህ የዝግመታዊ ለውጥ ሃይማኖት ከተጠነሰሰበት ወቅት ጀምሮ አልታዩም፤ ከዛም በፊት የሉም፡፡ አይናችሁን ጨፍናችሁ ይህንን እመኑ ብለው ቢያግባቡን፣ መልሳችን መሆን ያለበት ሳይንቲስት ነኝ እያልክ ማስረጃ አቅርበህ ከማስረዳት ይልቅ ለምን እንዳምን ታስገድደኛለህ ነው፡፡ ይህንን እውነታ ደግሜ ላረጋግጥላችሁ፡- በቅሬተ አካል ምርምር ውስጥ እስከ አሁን ድረስ አንድም ይህንን የሂደት ቅርፅ ክፍተት ሊያስረዳላቸው የሚችል ማስረጃ በቅሬታ አካል ሬከርድ ውስጥ ማግኘት አልቻሉም፡፡ ምንም ተጨባጭ ማስረጃ የለም።

የዚህ “ሳይንሳዊ” ሃይማኖት አራማጆች (የዝግመታዊ ለውጥ ፋናወጊዎችን) ማለቴ ነው፡- ምንም እንኳ “አሣ፣ በየብስና በውሃ ውስጥ ወደሚኖር እንስሳ (amphibian) ለመለወጥ 50 ሚሊዮን አመት የዝግመት ለውጥ ማሳለፍ አለበት” ይበሉ እንጂ፣ በዚ ሂደት ውስጥ እያለፈ ያለ ወይም አልፎ የነበረ አንድም የቅሬተ አካል ማስረጃ የላቸው፡፡ እስከ አሁን ድረስ የአሣ ክንፍ ለመሆን በሂደት ላይ ያለ የአሣ ክንፍ፣ የሰውን አእምሮ ለመሆን በሂደት ላይ ያለ አእምሮ፣ እግር ወይም አይን ለመሆን በሂደት ላይ ያለ እግር ወይም አይን ወይም ሌላ ብልት አልተገኘም፡፡

እንግዲህ ምርጫው ሁለት ነው። “አሣ ወደ አምፊቢያንነት ለመለወጥ 50 ሚሊዮን የዝግመት ለውጥ ያስፈልገዋል” የሚለውን በሳይንሳዊ ማስረጃ ላይ ያልተመሰረተን መላምት በእምነት መቀበልና የዳርዊንን ሐይማኖት መቀላቀል አልያም ሳይንስ እንኳን ሳይቀር የሚያረጋግጠውን ሌላኛውን እውነታ መቀበል፡፡

በመላምቱ አራማጆች ጭምር የሚነሳና ምላሽ የማያገኙለትን አንድ ጥያቄ እነሆ፡- “አንድ ፍጡር ከሌላው የአንድ ፍጡር ተመሣሣይ ዝርያ (species) በሂደት የተገኘ የለውጥ ውጤት ነው ካልን፣ ለምንድን ነው አሁን በተጨባጭ በአለማችን ከምናየው ቁርጥ ያለ የፍጥረት ቅርፅ በተቃራኒው በሂደት ላይ ያሉ ፍርፆችን (ከፊል አንዱን ከፊል ሌላውን) የማናየው?” በአንድ ተንቀሳቃሽ ፊልም ላይ እንዳየሁት ከወገብ በታች አሳ ከወገብ በላይ ሰውን ማለት ነው፡፡ ትልቅ ጥያቄ፣ ነገር ግን ምላሽ ያላገኘ፤ ነገር ግን በግድ እንድናምነው የሳይንስ ካባ ለብሶና በባዮሎጂ ክፍለ ጊዜ የሚሰበክልን የቻርላስ ዳርዊን ሐይማኖት። የዚህ ሐይማኖት ጀማሪና አቀጣጣይ መንፈሳዊ አባት ማን እንደሆነ ለማወቅ የግድ ሌላ ምንጭ ማገላበጥ ይኖብሃል – መፅሐፍ ቅዱስን፡፡

አሁን ደግሞ በየጊዜው ተገኙ የሚባሉ የቅሬተ አካል ስብርባሪዎች (fragments) እንዴት በተለያየ ሂደት የሰውን አጠቃላይ አፅም እንዲወክሉ እንደሚደረግ አንድ ምስጢር ላጫውታችሁ፡፡ መቼም የዚህ ሐይማኖት ድራማ አያልቅምና፡፡ ይሄ ጉዞ ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ይመልሰናል፡፡ መቼም ሁላችን ስለ ሉሲ ሳንሰማ አንቀርም፡፡ እንዳውም ኩራት ቢጤ ሳይነካካን የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ምክንያት ቢሉ የሰው ዘር መገኛ አፍረ ላይ እኛም በቅለናል ተብሎ ተሰብኮልናልና፡፡ ስብከቱንም አሜን ያልን ጥቂቶች አንሆንም ብዬ እግምታለሁ፡፡ ከዚህ ቅሬተ አካል ጋር ተያይዘው የሚቀርቡ ዜናዎች፣ የማን አባባል እንደሆነ ባላስታውስም፣ ‘ውሸትን ደጋግመህ ከተናገርከው እንደ እውነት ይቆጥርልሃል’ የሚባለውን ብሂል ያስታውሱኛል።

ዶክተር ሊኬይ፣ በአሁኑ ሰአት አለማችን ያበረከተቻቸው ታላቅ የቅሬተ አካል አንትሮፓሎጂስት ናቸው፡፡ እኚህ ሰው የሉሲን የራስ ቅል አፅም ያገኙ ናቸው፡፡ ይህ ግኝት በአሁኑ ሰአት ታላቅ ግኝት የሚባል መሆኑን እንዳንዘነጋ፡፡ የዚ ቅሬተ አካል አግኚ ያሉትን ቃል ይስሙ፡- “የሉሲ (Australopithecus afarensis) ቅሬተ አካል ጎዶሎና አብዛኛው ክፍሏ “በፓሪስ ፕላስተር አማካኝነት የተሳለ የአይነ ህሊና ስዕል ነው፡፡’’ ዶክተሩ ራሳቸው ይህንን አምነው ተናግረዋል፡- “ከ3.5 – 4 ሚሊዮን አመት የኖረ ቅሬተ አካል ከመሆኑ ውጭ ምን አይነት ፍጥረት እንደነበረ አሳማኝ ማጠቃለያ ላይ መድረስ አይቻልም”፣ ይላሉ ዶክተሩ። ሚዲያውስ ምን አለ? ይህንን ማብራራት አያስፈልገኝም። ሁሌ የምትሰሙት ነውና፡፡ መጀመሪያ የራስ ቅልና ጥቂት የአጥንት ስብርባሪ ይገኛል፤ ከዛ እድሜ ለፓሪስ ፕላስተር፣ ቅሬተ አካሉ የሰው ምስል እንዲመስል በሚያስችል መልኩ የተቀሩ ክፍሎቹ እንዲሟሉ ይደረጋል። ከዛም ልክ እንዳዋለደ ሰው፣ ለቅሬተ አካሉ ፆታና ስም ይሰጠዋል፡፡ በመጨረሻ የዝግመታዊ ለውጥ ሐይማኖት ማረጋገጫ ይባላል፡፡ የሰው ልጅ እንዴት ስህተትን ለመቀበል የተዘጋጀ ልብ እንዳለው ለማወቅ፣ የራስ ቅሉን ያገኘው ዶክተር በአንደበቱ ‘ያገኘሁት ቅሬተ አካል የምን ፍጥረት አፅም እንደሆነ አላውቅም’ እያለ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ግን የቅሬተ አካሉን ፍጥረት ሰው ፆታውን ደግሞ ሴት አድርጎ መቀበሉ በቂ ማረጋገጫ ይመስለኛል፡፡

ሌላ ጊዜ ደግሞ አንድ ቦታ የተገኘ የአንድ ፍጥረት ቅሬተ-አካል ከሌላ በ 10 ማይል ርቀት ላይ ካተገኘ ቅሬተ-አካል ጋር በግድ ተገጣጥሞ አንድ ቅርፅ እንዲያገኝ ይበጅና በዚህ ግኝት ጦጣ እንዴት ሰው እንደሆነች ሊሰብኩህ ይሞክራ፡፡ እስቲ አንድ በጣም የሚያስገርመኝን እና የዝግመታዊ ለውጥ አራማጆቹ በየጊዜው በሚያወጧቸው ፅሁፎች ላይ አበክረው የሚጠቀሟቸውን ሐረጎች ላካፍላችሁ፡- “ምናልባት፣ እንደሚመስለው ከሆነ፣ ሰዎች ገምተዋል፣ እንገምታለን፣ አሁንም ምስጢር እንደሆነ ነው፣ ተብሎ ይታሰባል፣ ሊሆን ይችላል፣ ምናልባት፣ ወዘተ።’’ እነዚህ ሐረጎች ማለቂያ ያላቸው አይመስሉም፡፡

ብዙ ሰዎች ለምን ይህን ሞኛሞኝ አስተሳሰብ ለመቀበል ይቀላቸዋል ብለህ ትጠይቅ ይሆናል፡፡ ምናልባት ደጋግሞ የተነገራቸውን ውሸት እንደ እውነት ለመቀበል አልቆረቆራቸው ይሆናል፤ ምናልባት ሳይንስ መስሏቸው የሃይማኖትን ጎራ ላለመቀላቀልና ዘመናዊ ሆኖ ለመኖር ካላቸው የራስ ክብር የመነጨ ይሆናል (የሚያሳዝነው አሁንማ ያሉት ሃይማኖት ውስጥ መሆኑ ነው እንጂ) ፤ ምናልባት…

የቅሬተ አካል መዝገብ የዝግመታዊ ለውጥ አራማጆች የተመኙትን መረጃ የቀዱበት ሳይሆን ማስረጃ ለማግኘት ተመኝተው አንድም ያላገኙበት መዝገብ ነው፡፡ ይህ መዝገብ አንድ እውነት ብቻ ነው እስከአሁን የሚናገረው። እርሱም ፍጥረት በሂደት ሳይሆን በድንገት በአንድ ወቅት በሙሉ ቅርፃቸው እንደተገኙ፡፡ ይህን አለመቀበል እምነትን መካድ ብቻ ሳይሆን የስሜት ሕዋስንም መካድ ነው። ይህን አለመቀበል መፅሐፍ ቅዱስን አለመቀበል ብቻ ሳይሆን እውነታውን የሚያረጋግጠውን ሳይንስን ጭምር መካድ ነው፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሰዎች አማኞችም አይደሉም፡፡ ሳይንቲስቶችም አይደሉም፡፡ ወደ ሳይንስ ወይም እምነት ለመድረስ በዝግመታዊ ለውጥ ላይ ያሉ “ሳይንሳዊ” ሐይማኖተኞች ናቸው ብንል ቀደም ብለን ያነሳነውን ከፊል አሳ ከፊል ሰው ምስል በሕሊናችን ይከሰት ይሆን?

ይቀጥላል

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading