ከዘላለም ሞት ፍርድ ለመዳን ምን ማድረግ አለብኝ?

ሞትን የማይፈራ ማን ይሆን? ሞት በሰው ልጆች ሕይወት ፊት የተደቀነ ትልቅ ጠላት ነው። ሰው ብዙ ነገር ሊያሸንፍ ይችል ይሆናል። ሞትን ማሸነፍ ግን የማይታሰብ ትግል ነው። ብርቱዎች፣ ጀግኖች፣ መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ሳይንቲስቶች ሁሉ የዚህ የሞት ሰይፍ ሰለባ ናቸው። ሞት ትንሽ ትልቅ ሳይል፣ ጥቁር ነጭ ሳይለይ፣ የተማረ መሃይም ሳያስቀር ሁሉን እያጨደ፣ ሁሉን እየከመረ፣ በሁሉ ላይ ነግሶ ዘመን ጠግቧል።

ብዙዎች የሚያውቁት ሞት፣ ነፍስ ከስጋ ተለይታ የምትሄድበትን የመጀመሪያ ሞት ነው። ሞት ይህ ብቻ ቢሆን ሃላፊነት የጎደላቸው፣ ኢሞራላውያን፣ እንዳሰኛቸው የፈቀዱትን እና የወደዱትን ሁሉ እያደረጉ የኖሩ ምግባረ ብልሹዎች፣ እግዚአብሔር የለም ብለው በድፍረት የተናገሩ መናፍቃን ሁሉ ከህሊና ክስ ነጽተው በሰላም ወጥተው ባደሩ ነበር። የክርስቲያኖችም የትንሳኤ ስብከት ከንቱ ድካም ነበር። ሆኖም እውነታው አይደለም። ከሞት በኋላ ሌላ ሞት አለ። ከመጀመሪያው ሞት በኋላ ሁለተኛው ሞት አለ። ከአካላዊው ሞት በኋላ መንፈሳዊው ሞት አለ።

ከሁሉ በላይ የሚያሰጋው ሞት ይህ ሞት ነው። ምክንያቱም ይህ ሞት እንደ አካላዊው ሞት ጊዚያዊ አይደለም። ይህ ሞት ዘላለማዊ ነው። ይህ ሞት ከመኖር ወደ አለመኖር መቀየር ማለትም ጨርሶ መጥፋት ሳይሆን ከእግዚአብሔር ተለይቶ አሳቱ በማይጠፋበት  የስቃይ ስፍራ መኖር ማለት ነው፣ ‘‘እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል’’ (ማቴዎስ 1340-42)

መንፈሳዊ የሆነውን ይህን ሞት መጽሐፍ ቅዱስ ሁለተኛው ሞት እያለ ይጠራዋል፣ ‘‘ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው’’ (ዮሐንስ ራዕይ 2014) ‘‘ዳሩ ግን የሚፈሩና የማያምኑ የርኵሳንም የነፍሰ ገዳዮችም የሴሰኛዎችም የአስማተኛዎችም ጣዖትንም የሚያመልኩ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው’’ (የዮሐንስ ራዕይ 218)

ለመሆኑ ከዚህ ሁለተኛ ሞት እንዴት ማምለጥ እንችላለን? ከሲኦል እሳት፣ ከዚህ የስቃይ ስፍራ የሚድኑት እነማን ናቸው? ምን ባደርግ ነው ከዘላለም ሞት የምድነው?

ከአዳም ውድቀት ጀምሮ በሰው ላይ ተነጣጥራ ያለችው የእግዚአብሔር ቁጣ መብረጃዋ አንድ ነገር ብቻ ነው። የእግዚአብሔር ቁጣ የእግዚአብሔርን ፍትህ ያሳያል። የእግዚአብሔር ፍትህ ደግሞ የእኛን ሞት ይጠይቃል (ሮሜ 6፡23)። የእግዚአብሔር ፍትህ የሃጢአተኛውን ሞት ይሻል (ዕብራውያን 9፡22)። ሁላችን ሃጢአትን ስላደረግን ለዚህ ሞት (የእግዚአብሔር ቁጣ ውጤት) ተዘጋጅቶልናል (ሮሜ 6፡23)። ሃጢአትን ያላደረገ በዚህ ምድር ላይ ስለሌለ (መክብብ 7፡20፤ 1ዮሐንስ 1፡8፤ ሮሜ 3፡10-18) ከዚህ ፍርድ ስር ያልሆነ ሰው በምድር ላይ የለም።

ሆኖም ግን፣ ከዚህ ፍርድ ስር መሆናችን ያሳዘነው እግዚአብሔር የራሱን ፍትሃዊ ፍርድ ራሱ ሊቀበልልን ወሰነ። በዚህም ምክንያት ሁላችን ከምንሞት አንድ ልጁ በእኛ ፈንታ እንዲሞት ፈቀደ (የሐንስ 11፡50-52)።  ይህ ቅዱስ ልጁ፣ ኢየሱስ ይባላል። ኢየሱስ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ነው (ዮሐንስ 1፡29)። እግዚአብሔር በእኛ ላይ ሊያፈሰው የነበረውን ቁጣ በልጁ በኢያሱስ ላይ አፈሰሰው። ኢየሱስ በእኛ ሞት ፈንታ ሞተልን። በዚህ ምትክ ሞት ምክንያት በኢየሱስ ሞት እና ትንሳኤ የሚያምኑ ሁሉ ከእግዚአብሔር ቁጣ እንዲተርፉ ሆነ። እግዚአብሔር፣ በኢየሱስ ሞትና እና ትንሳኤ ያመኑትን ሁሉ፥ ከሞት ፍርድ ያድናቸዋል (1ተሰሎንቄ 4፡14)። ‘‘በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም’’ (ዮሐንስ  3፥36)።

በልጁ ሞት እና ትንሳኤ ማመን ማለት፣ የእርሱ ሞት እግዚአብሔር በእኔ ላይ የነበረውን ቁጣ እንዲያነሳና ከእኔ ጋር ሰላም እንዲያርግ (ሮሜ 5፡1) አድርጎታል ብሎ ማመን ነው። በልጁ የሚያምን ከእንግዲህ የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ የለበትም (ዮሐንስ  3፥36)። የእግዚአብሔር ጠላት (ሮሜ 5፡10) ሳይሆን ወዳጅ ሆኗል። የኢየሱስ የሚያምን ሰው የኢየሱስ ሞት ለእግዚአብሔር ቁጣ በቂ ምላሽ እንደሰጠ ያምናል። ተጨማሪ የማምለጫ ስልቶችንም አይቀየስም። የእግዚአብሔር የድነት መንገድ  (ዮሐንስ 14፡6) በቂ እና ፍጹም እንደሆነ ያምናልና።

ከእግዚአብሔር ቁጣ ለመትረፍ የሚበጁ ሌሎች አማራጮች ሁሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደሉም። በራስዎ ‘‘መልካም’’ ምግባር ወይም ስራ እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተው ከእግዚአብሔር ቁጣ ለመትረፍ እንደሚችሉ ያስቡ ይሆን? ‘‘የተቀደሱ’’ ቦታዎች ላይ በመሄድ ከእግዚአብሔር ፍርድ የሚያመልጡ ይመስሎታል? ሃይማኖታዊ ክብረ በአላትን አዘውትረው በመጠበቅ ከቁጣው የሚሸሸጉ ይመስሎታል? የፓስተር ወይም የጳጳስ ልጅ ወይም ዘመድ በመሆንዎ የእግዚአብሔርን ፍረድ ሊያጣምምሙ የሚችሉ ይመስሎታል? ቁጣውን ለማፍሰስ በገዛ ፃድቅ ልጁ ላይ እንኳ ያልራራ (ሮሜ 8፡34)፣ ለእርሶ ጽድቅ ያውም ደግሞ የመርገም ጨርቅ ለሆነ ጽድቅዎ የሚራራ ይመስሎታል (ሮሜ 10፡2-3)? ገዳም በመግባትዎ፣ ለድሆች በመመጽወትዎ፣ ሳያጓድሉ በመጾምዎ እና በመፀለዮ፣ አዘውትረው ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድዎ ምክንያት እግዚአብሔርን ከቁጣው የሚመልሱት ይመስሎታል? እንዲህ የሚያስቡ ከሆነ እንግዲያው ክርስቶስ በከንቱ ሞተ (ገላቲያ 2፡21)። እነዚህ መልካም ነገሮች ሁሉ ከዚህ ከእግዚአብሔር ቁጣ በክርስቶስ ሞት አማካኝነት ያመለጠ አማኝ ሁሉ ሊያፈራቸው የሚጠበቁ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ (ገላትያ 5፡20) ናቸው። እናም የሚናቁ አይደሉም። ነገር ግን፣ ከእግዚአብሔር ፍርድ የማምለጫ አቋራጮች አይደሉም። ከእግዚአብሔር ቁጣ እና ፍርድ ማምለጥ የሚቻልበት ሌላ አማራጭ ቢኖር ኖሮ እግዚአብሔር ፃድቅ እና አንድያ ልጁን ለሃጢአተኞች ሞት ተላልፎ እንዲሰጥ የሚፈቅድ የመስሎታል?ቅዱስ ጳውሎስ የሰው ልጅ እንዴት ከእግዚአብሔር ቁጣ ሊድን እንደሚችል የተናገረውን ተናግረን እናጠናቅ፣ ‘‘ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን (ሮሜ 5፡9)’’።

መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወትዎ ጌታ በማድረግ ቀሪው ዘመንዎን ለመኖር ወስነው ከሆነ፣ ይህንን ሊንክ በመጫን ስምዎንና የኢ-ሜይል አድናሻዎን ይላኩልንና፣ ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገትዎ የሚቻለንን ሁሉ እገዛ እናደርግሎታለን።

 

1 thought on “ከዘላለም ሞት ፍርድ ለመዳን ምን ማድረግ አለብኝ?”

  1. Pingback: እውን ገሃነም አለ? – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply

%d bloggers like this: