ፀሎት – ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር

ፀሎት አፅናፈ አለሙን (the universe) ከፈጠረና ከሚቆጣጠር፣ እንዲህ ታላቅ ሆኖ ሳለ ደግሞ ዝርዝርና ትናንሽ በሆኑ የሕይወታችን ክፍሎች ውስጥ ሳይቀር ድርሻ እንዲኖረው ከሚሻ የፍቅር አምላክ ጋር የምናደርገው ጥልቅ ውይይት እንደሆነ ማወቅ አለብን፡፡

እግዚአብሔርን መቅረብም ሆነ ማነጋገር የምችለው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ በኩል መሆኑን ዘወትር በማስታወስ፣ ወደ እርሱ ስቀርብ በታላቅ አክብሮት ሊሆን ይገባል፡፡ የትኛውም መልካም ስራዬ እግዚአብሔር ፊት እንደማያቀርበኝ መረዳት ይኖርብኛል፡፡ የሁሉ ፈጣሪ ወደ ሆነው አምላክ በፀሎት መቅረብን እንደ ታላቅ እድል መቁጠር ይኖርብኛል፡፡

በየትኛውም ውይይት ላይ እንደ ተለመደው፣ መስማት የውይይት ትልቁ ክፍል ነው፡፡ እግዚአብሔር በልቤ ሲናገር ወይም አንድ አዲስ ነገር ሲገልጥልኝ በማሰላሰልና በማድመጥ ጊዜውን መጠቀም ይኖርብኛል፡፡ ዘወትር ከእርሱ አንዳች ነገር እንደ ምንጠብቅ ሆነን (with expectation) እንድንኖር ይወዳል፡፡

እግዚአብሔር ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚፈልጋቸውን ነገሮች (priorities) በመፈለግና ሲገልጥልንም በመቀበል መኖር፣ ለእግዚአብሔር ያለንን ክብርና የሚገባውን ትክክለኛ ስፍራ መስጠታችንን የምናረጋግጥበት አንዱ መንገድ ነው፡፡ ትራፊውን ጊዜያችንን፣ ትራፊውን ጉልበታችንን እና ትራፊ የሆነውን ነገራችንን ከመስጠት ልምምድ ወጥተን ምርጥ የምንለውን ነገራችንን ለእርሱ የማቅረብ ልምምድ ውስጥ በመግባት ለእርሱ ያለንን ጥልቅ ፍቅር እንድናሳየው ይጠብቅብናል፡፡

ሀ. ከእግዚአብሔር ጋር ያለኝ የውይይት (የፀሎት) ጊዜ መጠን- በሚኖረኝ የልብ ዝግጅት፣ ቅድሚያ ስለ ምሰጣቸው ነገሮች ባለኝ እውነተኛ ግምገማ (assessment of my priorities) እና ስለ እርሱ ባለኝ እውቀት መጠን እየጨመረ ይሄዳል፡፡

መዝ. 5፡3 (አ.መ.ት.) እግዚአብሔር ሆይ፤ በማለዳ ድምጼን ትሰማለህ፤ በማለዳ ልመናዬን በፊትህ አቀርባለሁ፤ ፈቃድህንም በጥሞና እጠባበቃለሁ፡፡

በተጨማሪ ተከታዮቹን ጥቅሶች ይመልከቱ፡-
መዝ. 37፡7 (አ.መ.ት.) በእግዚአብሔር ፊት ጸጥ በል፤ በትዕግሥትም ተጠባበቀው፤

መዝ. 119፡147 (አ.መ.ት.) ትረዳኝ ዘንድ ጎሕ ሳይቀድ ተነሥቼ እጮኻለሁ፤

ምሳሌ 3፡5-6 በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል።

ኢሳ. 50፡4 (አ.መ.ት.)…በየማለዳው ያነቃኛል፤ በመማር ላይ እንዳለ ተማሪ ለመስማት ጆሮዬን ያነቃዋል።

ለ. ፀሎት፣ እግዚአብሔርን ማድነቅና ማመስገን ያካትታል፡፡
መዝ. 145፡2-3 በየቀኑ ሁሉ እባርክሀለሁ፣ ስምህንም ለዘላለም ዓለምም አመሰግናለሁ፡፡ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፣ እጅግም የተመሰገነ ነው፣ ለታላቅነቱም ፍፃሜ የለውም፡፡

በተጨማሪ ተከታዮቹን ጥቅሶች ይመልከቱ፡-
መዝ. 146፡1-2
ዳን. 6፡10
ኤፌ. 5፡19-20
ፊሊ. 4፡6-7
ቆላ. 4፡2-4
1ተሰ. 5፡16-17

ሐ. ፀሎት መናዘዝ፣ መታረቅን እና ሌሎችን ይቅር ማለትን ያካትታል፡፡
መዝ. 32፡5 ኃጢአቴን ላንተ አስታወቀሁ፣ በደሌንም አልሸፈንሁም፣ ለእግዚአብሔር መተላለፌን እነግራለሁ አልሁ፣ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውክልኝ፡፡

በተጨማሪ ተከታዮቹን ጥቅሶች ይመልከቱ፡-
መዝሙር 66፡18
ምሳሌ 28፡13
ማቴ. 5፡23-24
ማር. 11፡25
ሮሜ. 12፡18
1ዮሐ. 1፡9-10

መ. ፀሎት ልመናዎችን/ምህላ፣ ስለ ግል ፍላጎቶቻችን ጥያቄዎች ማቅረብንም ያካትታል፡፡
ያዕ. 1፡5 ከእናንተ ማንም ጥበብ ቢጎድለው ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን ለእርሱም ይሰጠዋል፡፡

በተጨማሪ ተከታዮቹን ጥቅሶች ይመልከቱ፡-
ማቴ. 6፡5-8
ማቴ. 6፡25-34

ፀሎት – በ ‹‹ስውር ስፍራ›› የሚደረግ ጦርነት ነው 

አንተ ግን ስትጸልይ፣ ወደ እልፍኝህ ግባ፣ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፣ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሀል፡፡ – ማቴዎስ 6፡6

ወደ እልፍኛችን ከገባንና በራችንን ከዘጋን በኋላ ልናደርግ የሚቸግረን ትልቁ ነገር ቢኖር መፀለይ ነው፡፡ አእምሮአችንን ለፀሎታችን ልንጠቀምበት በምንችለው ሁኔታ ማዘጋጀት አስቸጋሪው ሥራችን ይሆናል፡፡ የመጀመሪያ ውጊያችን የሚሆነው ሀሳባችንን ማሰባሰብና ለፀሎት ራሳችንን መግዛት ነው፡፡ በግል የፀሎት ጊዜ ያለው ታላቁ ጦርነት ሀሳባችንን ማሰባሰብና ለፀሎት ያልተዘጋጀውን አዕምሮአችንን ለዚሁ መንፈሳዊ ስራ እንዲነሳሳ ማድረግ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ፣ በእግዚአብሔር ፊት በተመስጦ መሆን መማርና አዕምሮአችንን ማሰልጠን ይጠበቅብናል፡፡

ለፀሎት የተለየ ስፍራ ቢኖረን ይመረጣል፡፡ ያም ሆኖ ግን ወደዚህ ስፍራችን ስንገባ ሀሳባችን መባከኑ እንግዳ ነገር አይሆንም፣ ‹‹ይህ ነገር ዛሬ መሰራት አለበት››፤ ‹‹ያኛውን ደግሞ ነገ መጨረስ ይኖርብኛል፡፡›› የሚሉ ሀሳቦች በአዕምሮአችን መመላለስ ይጀምራሉ፡፡ በፀሎት ወቅት የተረጋጋ የአዕምሮ ሁኔታን ለመፍጠር፣ የአዕምሮአችንን ደጆች ለሚያንኳኩ ስሜቶቻችን ሆን ብለን ደጃችንን በመዝጋት፣ እርሱን ብቻ ማሰብ ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር በስውር አለ፡፡ ከ ‹‹ስውር ስፍራውም›› ይመለከተናል፡፡ እርሱ የሚመለከተን፣ ሰዎች እኛን ወይም ራሳችን ራሳችንን እንደ ምንመለከተው አይደለም፡፡ እግዚአብሔር እኛን በሚያየን በዚህ ‹‹ስውር ስፍራ›› መኖር መለማመድ ስንጀምር እግዚአብሔርን መጠራጠር አይሆንልንም፡፡ ከማንም እና ከምንም ነገር በላይ ስለ እርሱ እርግጠኞች እንሆናለን፡፡ ወደዚህ ‹‹ስውር ስፍራ›› ስትገባ በእለት ተዕለት ሕይወትህ እግዚአብሔር በእርግጥ ትክክል እንደሆነ ታረጋግጣለህ፡፡ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ከእግዚአብሔር ጋር የማውጋት ልማድ ይኑርህ፡፡ የማለዳው ጎህ ሲቀድ የሕይወትህን ደጆች ወለል አድርገህ ከፍተህ እግዚአብሔርን በፀሎት አስቀድም፡፡ ይህ ድርጊትህ በእርሱ ላይ ያለህን መደገፍ ያሳያልና፡፡ (My utmost for His Highest በ አስዋልድ ቻምበር የተጻፈ)

የምክር ሃሳብ፡- ወደ ፀሎት በገባህ ጊዜ የሚደርስብህን የትኩረት መበታተን ችግር ለመቀነስ፣ ወደ አይምሮህ እየመጡ የሚያስቸግሩህ እና ኋላ ላይ ልትሰራቸው የሚገቡህን ነገሮች የምታሰፍርበት ማስታወሻ ደብተር አዘጋጅ፡፡

ረ. ፀሎት ምልጃንና ስለሌሎች ሰዎች ፍላጎቶች መፀለይን ያካትታል፡፡
2ቆሮ. 1፡8-11 በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን፣ ወንድሞች ሆይ፣ ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና፤ ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤ አዎን፣ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፣ እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር። እርሱም ይህን ከሚያህል ሞት አዳነን፣ ያድነንማል፤ እናንተም ደግሞ ስለ እኛ እየጸለያችሁ አብራችሁ ስትረዱን፣ በብዙ ሰዎች በኩል ስለ ተሰጠን ስለ ጸጋ ስጦታ ብዙዎች ስለ እኛ ያመሰግኑ ዘንድ፣ ወደ ፊት ደግሞ እንዲያድን በእርሱ ተስፋ አድርገናል።

በተጨማሪ ተከታዮቹን ጥቅሶች ይመልከቱ፡-
ኤፌ. 6፡18-20
ቆላ. 4፡12

ሠ. ፀሎት ምንም እንኳን የማይቋረጥና በማንኛውም ሰአት ልናደርገው የምንችለው ነገር ቢሆንም ለእርሱ የተወሰነ ሰዓት ሊኖረን ይገባል፡፡
መዝ. 55፡17 በማታና በጠዋት በቀትርም እናገራለሁ፣ እጮኸማለሁ፣ ቃሌንም ይሰማኛል፡፡

በተጨማሪ ተከታዮቹን ጥቅሶች ይመልከቱ፡-
መዝ. 119፡62
መዝ. 119፡164
ዳን. 6፡10
ሮሜ. 12፡12
1ተሰ. 5፡17

በ 1ተሰ. 5፡17 ላይ የተሰጠ አስተያየት
‹‹የማያቋርጥ ፀሎት፣ በሚቻል ወቅት ሁሉ የሚደረግ፣ ቀጣይነት ያለው ፀሎት ማለት እንጂ አንድም ጊዜ የማይቆም ማለት አይደለም፡፡ ጳውሎስ ይህንን ጉዳይ ያነሳው ያለ ማቋረጥ ሃሳብን ለእግዚአብሔር ማስገዛት ፈታኝ በሆነበት የዕለት ተዕለት ሕይወታችን፣ በተቻለ መጠን ያለማቋረጥ ከእግዚአብሔር ሕብረት ስር የመሆንን አስፈላጊነት ለመግለፅ ነው፡፡››

ለእግዚአብሔር ማሳሰብ
እግዚአብሔር የማያውቀውን ነገር ልንነግረው አንችልም፡፡ ስንፀልይ የምንናደርገው ነገር ቢኖር እርሱ አስቀድሞ የሚያውቀውን ነገር በአንደበታችን ወይም በራሳችን ቃል ለእርሱ መልሶ መናገር ነው፡፡

ይህ ጉዳይ እንድንፀልይ የሚያበረታታን እንጂ ፀሎትን አላስፈላጊ የሚያደርገው አይደለም፡፡ ስለ እኛ እና ስላለንበት ሁኔታ በሚገባ ከሚያውቅ ሰው ጋር ያው የሚያውቀውን ጉዳይ ስናወራ እረፍት ይሰማናል፡፡ የእግዚአብሔር ምላሽ በሰጠነው መረጃ ላይ ሳይሆን እርሱ ስለእኛ ሁኔታ በሚያውቀው ፍፁም እውቀት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ተደላድለን እንድንኖር ያደርገናል፡፡ በእኛ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ ስለሚችሉ ያለፉ፣ የአሁኑ እና የወደፊቱ ሁኔታዎቻችንን ጠንቅቆ ያውቃልና፡፡

ኢየሱስ በማቴ. 6፡8 ላይ እንዳለው አባታችን ሁሉን ያውቃል፡፡ እርሱ ሃሳቦቻችንንና ፍላጎቶቻችንን ያውቃል፡፡ መንገዶቻችንን ጠንቅቆ ይረዳቸዋል (መዝ. 139፡3)፡፡ የልባችንን ጭንቀትና ስቃይ ያውቃል፤ የማያቋርጥ ተስፋ መቁረጥ የሚያደርስብንን የስሜት ጉዳትም ይገነዘባል፤ በውስጣችን ያሉ ሁለቱ ተቃራኒ ተፈጥሮዎች በነፍሳችን ላይ የሚያደርጉት ጦርነትም ከእርሱ የተሸሸገ አይደለም፡፡

እንዲህ ከሆነ፣ ካሉብን ችግሮችና ተቃውሞዎች እንዴት እና በየትኛው ሰዓት መውጣት እንዳለብን ለማወቅ እግዚአብሔር ላይ የመታመን አስፈላጊነት አይታያችሁም? ሕይወታችን ሊታነፅ የሚችልበትን የተሻለ መንገድ እኛ ለእግዚአብሔር ልንጠቁም የምንችል ይመስላችኋል? በፍፁም፤ እግዚአብሔርን ምንም ነገር ልናስተምረው አንችልም፡፡ እርሱ ብቻውን እኛን ወደ ክብር የሚያደርሰውን ጎዳና ያውቃል፡፡ ካሉት መንገዶች ሁሉ፣ ለማንነታችን እና በእኛ ውስጥ እርሱ ላስቀመጠው ነገር የሚስማማውን ልዩ መንገድ መርጦልናል፡፡ Our Daily Bread (መስከረም 19, 2004 እ.ኤ.አ.)

እግዚአብሔርን እውቀት ልናስገበየው አንችልም፡፡ ልናፈቅረውና ልንደላደልበት ግን እንችላለን፡፡ እርሱ ከኛ የሚጠይቀው ይህንን አንድ ነገር ነው፡፡

እግዚአብሔር ከመነሻው የመጨረሻውን ያውቃል፤ ስለዚህ በመካከል በሚፈጠሩ ነገሮች ላይ ሁሉ በእርሱ ልንታመን እንችላለን፡፡

ማጠቃለያ

በእግዚአብሔር ላይ ያለኝን መታመን በጨመርኩ መጠን እርሱ ለእኔ ባለው ፍቅር እርግጠኛ እየሆንኩ እሄዳለሁ፡፡ አንዳንዴ ነገሮች ከዚህ አስተሳሰብ ተቃራኒ ቢመስሉም፣ እግዚአብሔር ለእኔ ያለው ሃሳብ በጎና የሚጠቅመኝ ነው፡፡ ከዚህ ሃሳብ በተቃራኒው መሆን ከራሱ ባሕሪ ጋር መጋጨት ይሆናልና፡፡

ተከታዮቹን ጥቅሶች ይመልከቱ፡-
መዝ. 34፡15
መዝ. 37፡4-5
መዝ. 86፡5
መዝ. 145፡18-19
ኤር. 10፡23
1ዮሐ. 5፡14-15

እኔ ግን ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ፥ ቀኝ እጄንም ያዝኸኝ። እኔ ግን ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ፥ ቀኝ እጄንም ያዝኸኝ። በሰማይ ያለኝ ምንድር ነው? በምድርስ ውስጥ ከአንተ ዘንድ ምን እሻለሁ? የልቤ አምላክ ሆይ፥ ልቤና ሥጋዬ አለቀ እግዚአብሔር ግን ለዘላለም እድል ፈንታዬ ነው። (መዝሙር 73፡23-26)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading