ከምናውቀው በላይ አናምንም፤ ከምናምነው በላይ አንኖርም!!!

በአሜሪካ ያሉ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ክርስቲያኖች ስለ ሚቆረቆሩለትና የሕይወታቸው መመሪያና መሰረት አድርገው ስለሚቀበሉት መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው እውቀት አስደንጋጭ እየሆነ መምጣቱን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወጡ ያሉ የክርስቲያን የምርምር መረጃዎች ያመለክታሉ። ተመራማሪዎቹ ጆርጅ ጋለፕ እና ጂም ካስልሊ ችግሩን በአጠቃላይ እንዲህ ብለው አቅርበዋል:- “አሜሪካውያን መጽሐፍ ቅዱስን እጅግ የሚያከብሩ ቢሆንም በጥቅሉ ግን አያነቡትም ማለት ይቻላል፤ እናም ይህ ሁኔታ አገሪቱን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መሃይምነት ጎዳና እየመራት ይገኛል፤” ብለዋል። ሁኔታው ብዙዎች ከሚያስቡት በላይ አስከፊ እንደሆነም በምርምራቸው ያገኙትን ስታስቲካዊ መራጃ በማቅረብ ለማስረዳት ሞክረዋል።

ለአብነት ይላሉ ተመራማሪዎቹ፣ ከጎልማሳዎቹ አሜሪካውያን ክርስቲያኖች መካከል አራቱንም ወንጌሎች በስም መጥራት የሚችሉቱ ቁጥራቸው ከ50 በመቶ ጥቂት ከፍ የሚሉት ብቻ ናቸው። ብዙ ክርስቲያኖች ከሁለት ወይም ከሶስት በላይ የሚሆኑትን የኢየሱስ ክርስቶስን ደቀ መዛሙርት ስም መጥራት አይችሉም። ባርና የሚሰኘው የምርምር ቡድን መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ፣ 60 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያን ከአስርቱ ትዕዛዛት መካከል አምስቱን እንኳ መጥራት አይችሉም።

82 በመቶዎቹ አሜሪካውያን፣ “እግዚአብሔር እራሳቸውን የሚረዱትን ይረዳል”፣ የሚለው የተለመደ አባባል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንደሆነ ያምናሉ። ዳግም ልደት እንዳላቸው የሚናገሩ 81 በመቶ የሚሆኑ ክርስቲያኖች ሳይቀሩ ይህንኑ አባባል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንደሆነ ያምናሉ። አብዛኛዎቹ በእድሜ የገፉ ክርስትያኖች የሕይወት ዋነኛ አላማ፣ ቤተሰባቸውን መንከባከብ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል ብለው ያስባሉ። አንድ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተመራቂዎች የምርምር ጥናት እንዳመለከተው ደግሞ፣ ከ 50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ክርስቲያኖች፣ ሰዶምና ጎሞራ ባልና ሚስት እንደሆኑ ያስባሉ። በተጨማሪም፣ ከአንድ ጥናት ላይ የተሰበሰበ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ቀላል ቁጥር የሌላቸው አማኞች በማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ 7 ድረስ ያለውና በጌታችን ኢየሱስ የተሰበከው የተራራው ስበከት፣ የታዋቂው አሜሪካዊ ወንጌላዊ ቢሊ ግራሃም ስብከት እንድሆነ ያስባሉ።

ይህን አስፈሪ ስታትስቲካዊ መረጃ በሚከተሉት ጥቂት አረፍተ ነገሮች ላጠቃልን የመፍትሄውን ሃሳብ እንድጠቁም ይፈቀድልኝ። የምናውቀውን እናምናለን፤ የምናምነውን ደግሞ እንኖራለን። ካላነበበን አናውቅም፤ የማናውቀውን ደግሞ አናምንም፤ ካላመንን ደግሞ ልንኖረው አንችልም። ከምናውቀው በላይ አናምንም፤ ከምናምነው በላይ አንኖርም። ይህ ትውልድ፣ በአሜሪካውያኑ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን የንባብ ባህል ገና ዛሬም ዳዴ በሚልባት የአገራችን ክርስቲያኖች ላይ ጭምር የሚያንጃብበውን ይህን ግልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት መሃይምነት አደጋ በማንበብ ጸንቶ ሊታገለው ይገባል እላለሁ።

በዚህ ትግል ውስጥ የማያሳፍር የክርስቶስ ወታደር ለመሆን የሚሹ ከሆነ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ጤናማ በሆነ የውድድር መንፈስ በመታገዝ የምናጠናበትን የ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ክለብ እንዲቀላቀሉ በነጻ ተጋብዘዋል!!! የ https://ethiopiansite.com/ ድረ-ገጽ (website) ተከታታይ (follower) በመሆን በርካታ የድነት፣ የደቀ መዝሙር ትምሕርቶችና ክርስትናን አስመልክቶ በተደጋጋሚ ለሚነሱ ጥያቄዎች ከዝግጅት ክፍሉ የተሰጡትን ጠቃሚ ትምሕርቶች ያገኛሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጥያቄዎቹን በቀጥታ ለማግኘት ደግሞ፣ በድረ-ገጹ የፊት ገጽ (home page) ላይ በመሄድ “የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትዎን ይመዝኑ” ያሚለውን ሜኑ (menu) ይጫኑ። በድረ-ገጽ ስር የተዘጋጁት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎቹ ሁሉ ግብረ-መልስ (feedback) ያላቸው ናቸው። ጥያቄዎቹን ሰርተው እንደላኩ (submmit)፣ ጥያቄዎቹ የተዘጋጁበት ፕሮግራም ምላሽዎን ተመልክቶ ወዲያውኑ ውጤትዎን እና ግብረ መልስዎን ይነግርዎታል። ጥያቄዎቹን ደጋግመው መስራት የተፈቀደ ብቻ ሳይሆን ይበረታታልም። በጥያቄዎቹ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሚሹ ከሆነ ደግሞ፣ የዝግጅት ክፍሉን በኢ-ሜይል (tsegaewnet@gmail.com) መጠየቅ ይችላሉ።

“የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤…” ቆላስይስ 3:16

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading