መከራና የእግዚአብሔር ሉአላዊነት

ወንጌልን የተቀበልኩበት ጊዜ ዛሬም ድረስ ትዝ ይለኛል፡፡ በነዚያ ጣፋች ጊዚያት ስለክርስትና አስበው የነበረውንም የልጅነት ሃሳብ አልዘነጋውም፡፡ ያኔ ክርስትና ለኔ በምድር ላይ የገነት ኑሮን መኖር አይነት ነበር፡፡ በተቀበልኩት አዲስ ሕይወት ውስጥ እንኳን መከራና ስቃይ እንደሚገጥመኝ ላስብ ቀርቶ፣ የምጠብቀው ታክሲ ውስጥ ሌላ ሰው ቀድሞኝ ሲገባ “ለምን ሆነ?” ብዬ የምገረምበት ወቅት ነበር፡፡ ለምን ስለክርስትና እንደዚያ ላስብ እንደቻልኩ በውል አላስታውሰውም፡፡ ምናልባት የራሴ የቁም ሕልም አልያም ከቅርብ ጓደኞቼ የሰማሁት ምኞት ይሆናል፡፡ ክርስትና እና ምቾት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች እንደሆኑ ያሰብኩበት ያ ዘመን ብዙ ሳይዘገይ  ከዚህ እውቀቴ ጋር የሚላተሙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሆችና የግል ተሞክሮዎች ገጠሙት፡፡ በወቅቱ፣ “እግዚአብሔር በእንደነዚህ አይነቶቹ ስቃይና መከራዎች ውስጥ እንዳልፍ የሚፈቅድ ልብ የለውም፡፡ እርሱ ርህሩህ እና የፍቅር አምላክ ነው፡፡ መከራዎቼን ያመጣቸው ሰይጣን ወይም የእምነት ጉድለቴ ነው” እል እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ባለጠጋውና ባለጤናው እምነት የታጠቀ የእምነት አርበኛ፣ ምስኪኑና የአልጋ ቁራኛው ደግሞ የእምነት ደሃ እንደሆኑ በሚሰበክበት በዚያ ጊዜ ውስጥ አንድ ነገር መምረጥ ነበረብኝ – የግል አስተያየቴን ወይም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርህን፡፡ ሁለተኛውን መርጬ የተማርሁትን እነሆ፡፡

እግዚአብሔር እኛን ይዞን የሚጓዝበት መንገድ ብዙውን ጊዜ እኛ ለራሳችን ካየነው ጥሩ መንገድ አንጻር በተቃራኒው ሊመስል ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንዴ እየተጓዝንበት ያለንበት የእግዚአብሔር መንገድ ትክክለኛ ያልሆነ ይመስለናል፡፡ ለዚህ ነው ብዙዎቻችን፣ በትክክለኛው መንገድ ላይ ብሆን ኖሮ፣ የእግዚአብሔር መልካምነት፣ ሁል ጊዜ ከችግር ነፃ በሆነ የሕይወት ጎዳና ይመራኝ ነበር ብለን የምናስበው፡፡

ይህ ሃሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሃሳብ የወጣና ሊሰራ የማይችል ሕልም ነው፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር ምድራዊ ምቾት በሌለበት ጎዳና ሊመራን ይችላል፡፡ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፣ ‹‹… ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም››፡፡ፊል. 1፡29፡፡ ስንጓዝበት ከነበረው የመከራ ጉዟችን ስንወጣ እያንዳንዱን ሁኔታ እግዚአብሔር ለዘለቄታዊ ጥቅማችን ሲል የፈቀደው እንደነበረ ይገባናል፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ የሆነው ኤፍ ቢ ሜየር እንዲህ አለ፣ ‹‹ካለፍንበት መንገድ የተሻለ ተስማሚ ወይም ደህና መንገድ የለም፤›› ‹‹አንድን መንገድ ልንመረጠው የምንችለው እግዚብሔር እንደሚያየው፣ እኛም ማየት ስንችል ብቻ ነው፡፡›› ዴቪድ ሮፐር ይህን አስመልክቶ ሲናገር ደግሞ እንዲህ ይላል፣ «እግዚአብሔር መከራዎቻችንን የፈቀደበት ምክንያት አውቀነው ቢሆን ኖሮ የትኛውም መከራ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንድንገባ ባላደረገን ነበር፡፡››

ኢየሱስ እርሱን ለመከተል ካልቆረጥኩ በቀር ደቀ መዝሙሩ ልሆን እንደማልችል በግልፅ ነግሮኛል፡፡ (ማቴ. 10፡38፣ ማቴ. 16፡24፣ ሉቃስ 14፡27፣ ዮሐ. 12፡26 ይመልከቱ)፡፡ እርሱን መከተል ስጀምር፣ በእኔ አይን የማያስደስቱና አልፎ አልፎም በእኔ ችሎታ ላልፋቸው የማልችላቸው ጉዳዮች እንዲገጥሙኝ ይፈቅዳል፡፡ በዚህ ወቅት፣ ማንኛውም ሁኔታ (የማይረቡ የሚመስሉ ሁኔታዎችን ጨምሮ)፣ መልካምም ይሁን መጥፎ፣ ሁሉም በእግዚአብሔር የመፍቀድ ስልጣን ስር መሆናቸውን ማስገንዘብ እጅግ ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ እግዚአብሔር በዘላለም ዕቅዱ ውስጥ ያለውን የእርሱን ፈቃድ በእኔ በመፈፀም፣ ቅዱስና ጠቃሚ ዕቃ አድርጎ ለማበጀት ማንኛውንም ሁኔታ ይጠቀማል፡፡

እግዚአብሔር በሁኔታዎች ላይ ሉአላዊ ስልጣን እንዳለው የማይገነዘብ ክርስቲያን ለሁኔታዎች የሚሰጠው ምላሽ በማጉረምረም፣ በማሳበብ፣ ስለ ችግሮቹ ከመጠን በላይ በማሰብ፣ ራሱን እድለ ቢስ አድርጎ በመቁጠር፣ በቁጣና በመራርነት የተሞላ ነው፡፡ በተቃራኒው፣ ከእርሱ ጋር ስተባበር፣ እርሱ ለእኔ ያቀደውን ነገር እውቅና ስሰጥ፣ ትክክለኛ ምላሽ ስሰጥ እና ሊያስተምረኝ የፈለገውን ትምህርት ስረዳ እግዚአብሔርን ያስደስተዋል፡፡

  1. እግዚአብሔር በአፅናፈ አለሙ ሁሉ እና በእርሱም ውስጥ በሚሆነው ነገር ላይ ሁሉ ፍፁም ቁጥጥር አለውን? የእግዚአብሔርን ሉአላዊነት በተወሰነ መልክ የሚፈታተን ሰው ወይም ኃይል ይኖር ይሆንን? እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ትክክል የሆነውን ያደርጋልን? እግዚአብሔር ስህተት ይሰራ ይሆንን? እግዚአብሔር መጥፎ ሥራ ይሰራ ይሆን? እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ሊታመን ይችላልን?

ከላይ ለተገለጹት ጥይቄዎች መልስ ለማግኘት የሚከተሉትን ጥቅሶች እንዲያጠኑ እጋብዛለሁ፡-

ዘዳ. 32፡4፣ ምሳሌ 18፡30፣  ምሳሌ 21፡30፣ ኢዮብ 34፡12-16፣ ኢሳ. 46፡11፣ ዳን. 4፡32

  1. እግዚአብሔር በእኔ ሕይወት ዙሪያ ባሉ አጠቃላይ ሁኔታዎች እና በእኔ ሕይወት ዝርዝር ጉዳይ ላይ ፍፁም ቁጥጥር አለውን? (መዝሙር 139 በማንበብ ያሰላስሉ)

በተጨማሪ የሚከተሉትን ጥቅሶችንም ያጥኑ፡-

ሐዋ. 17፡25፣ ኢዮብ 34፡14-15፣ ኤር. 1፡5፣ ኤር. 10፡23፣ ምሳሌ 16፡9፣ ምሳሌ 19፡21፣ ኤር. 29፡11፣ ማቴ. 6፡25-27፣ 34፣ ሮሜ. 8፡28፣ 1ቆሮ. 10፡13  

  1. መከራና ስቃይ፣ የክርስትና ‹‹መደበኛ›› ሕይወት አካሎች እንደሆኑ እግዚአብሔር በቃሉ ነግሮኛል፡፡ መከራና ስቃይ እግዚአብሔር በእኔ ያለመደሰቱ ምልክት ተደርገው መወሰድ የለባቸውም፡፡ ልክ እንደዚሁ በረከቶች ሁሉ ለእርሱ ታማኝ የመሆን ውጤቶች እንደሆኑ ማሰብ የለብኝም፡፡ እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ ነው፡፡ ልጆቹ የማያስደስቱት እንኳን ቢሆኑ እንክብካቤ ያደረግላቸዋል፡፡

ሀ. ከዚህ በታች ጥቅሶች ውስጥ በዓለም አስተያየት በድህነት የተሰቃዩ፣ በእግዚአብሔር አይን ግን ባለፀጋ ስለነበሩ ሰዎች እናነባለን፡፡ እነዚህ ሰዎች በድኅነቱ ተቀጥተው አልነበረም፤ እግዚአብሔር ለዘላለም ባለፀጋ ያደርጋቸው ዘንድ ለጊዜው ደኅይተው ነበር እንጂ፡፡

እነዚህን ጥቅሶች አጥኗቸው፡-

ሉቃስ 16፡19-31፣ ማር. 12፡41-44  

ለ. ሐዋሪያው ጳውሎስ መከራን እንደ እንግዳ ነገር አልቆጠረም፡፡ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት በርካታ ጥቅሶች ውስጥ፣ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማዕከል በማድረግ ፈጣሪውን ለማስደሰት በተጓዘው ጉዞ ወቅት ያጋጠሙትን ነገሮች እንመለከታለን፡፡

የሚከተሉትን ጥቅሶች ያጥኑ፡-

ሐዋ. 9፡15-16፣ 2ቆሮ. 6፡4-10፣ 2ቆሮ. 11፡23-27፣ ፊል. 3፡7-11፣ ፊል. 4፡11-13፣ ሐዋ. 16፡22-40

ሐ. ሌሎቹ ሐዋሪያትም ቢሆኑ መከራንና ስቃይን እንግዳ እንደሆኑ ነገሮች አልቆጠሯቸውም፡፡

የሚከተሉትን ጥቅሶች ያጥኑ፡-

ሐዋ. 5፡40-41፣ 1ቆሮ. 4፡9-13፣ ራዕ. 1፡9  

መ. እኔም፣ መከራና ስቃይ ሲገጥመኝ እንደ እንግዳ ነገር ላስበው አይገባኝም፡፡

የሚከተሉትን ጥቅሶች ያጥኑ፡-

ዮሐ. 15፡18-21፣ ዮሐ. 16፡33፣ ሐዋ. 14፡22፣ ፊል. 1፡29፣ 1ተሰ. 3፡2-4፣ 2ጢሞ. 1፡8፣ 2ጢሞ. 3፡12፣ 1ጴጥ. 2፡20-21 (በተጨማሪ 1ጴጥሮስ 3፡13-17 ይመልከቱ)፣ 1ጴጥ. 4፡12-16፣ 1ጴጥ. 5፡10፣ ሮሜ. 8፡35-39  

  1. እግዚአብሔር፣ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት አንድ ወይም ከዛ በላይ ምክንያቶች፣ መከራ ወደ እኛ እንዲመጣ ይፈቅዳል፡፡
  • ባሕሪዬን ሊሰራ
  • ባለመታዘዝ ወይም በቸልተኛነቴ ምክንያት
  • ሊያስተምረኝ
  • የሌሎች ሰዎች ፍላጎቶችን እንድረዳ
  • ሕይወቴ ለሌሎች ሰዎች የበረከት ምክንያት እንዲሆን

ሀ. እግዚአብሔር ባህሪዬን ለመስራት፣ ሕይወቴን የሚጠቅምና ቅዱስ ዕቃ ሊያደርግ መከራና ስቃይን ይጠቀማል፡፡ በምድር ላይ በቀረኝ የሕይወት ዘመን የትኛው ሁኔታ በተሻለ መንገድ ሕይወቴን በመልካም ተፅዕኖ ውስጥ ሊከት እንደሚችል እና እኔን ለመባረክ የትኛው የበለጠ ጠቃሚ እንደሆነ እርሱ ብቻውን በትክክል ያውቃል፡፡

የሚከተሉትን ጥቅሶች ያጥኑ፡-

ሮሜ. 5፡3-4፣ ያዕ. 1፡2-4፣ ዕብ. 5፡8-9፣ 1ጴጥ. 4፡12-16   

ለ. አንዳንድ መከራዎች በራሴ አለመታዘዝ እና ቸልተኝነት ሊመጡ ይችላሉ፡፡ በዚህም ሁኔታ ውስጥ አንኳ ብገኝ፣ እግዚአብሔር ታማኝና አፍቃሪ አምላክ በመሆኑ ሁኔታውን ለእኔ የመማሪያ መንገድ ያደርገዋል፡፡ ለአብነት ለአመጋገቤ ቸልተኛ ብሆን በውጤቱ አከላዊ ምቾት በማጣት ልሰቃይ እችላለሁ፡፡

የሚከተሉትን ጥቅሶች ያጥኑ፡-

1ቆሮ. 11፡27-34፣ ዕብ. 12፡6-11   

ሐ. አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር የእርሱን ታማኝነትኃይል እና በቂነት ሊያስተምረኝ እግረ መንገዱንም የእኔን ደካማነት ሊጠቁመኝ መከራና ስቃይ ወደ ሕይወቴ እንዲመጡ ይፈቅዳል፡፡

የሚከተሉትን ጥቅሶች ያጥኑ፡-

2ቆሮ. 1፡8-9፣ 2ቆሮ. 12፡7-10  

መ. እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ለሌሎች ሰዎች ችግር በትክክለኛ ስሜት ትክክለኛ ምላሽ መስጠትን እንድማር እኔን በመከራና ስቃይ እንዳልፍ ያደርጋል፡፡

የሚከተሉትን ጥቅሶች ያጥኑ፡-

2ቆሮ. 1፡3-5፣ ዕብ. 2፡10, 17-18፣ 1ጴጥ. 5፡9-10  

ሠ. አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር በእኔ ሕይወት የበለጠ ደምቆ ለማብራት ሲሻ በመከራና ስቃይ እንዳልፍ ይፈቅዳል፡፡ (ብርኃን፣ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ይበልጥ ያበራል፣ ይበልጥ ጠቀሜታ ይኖረዋልም፡፡)

የሚከተሉትን ጥቅሶች ያጥኑ፡-

ማቴ. 5፡14-16፣ ዮሐ. 9፡1-3፣ ሐዋ. 16፡22-34  

  1. የእግዚአብሔርን ፈቃድ መከተል፣ አንዳንድ ጊዜ ውድ የምላቸውን የራሴን ነገሮች እንድተው ይጠይቀኛል፡፡ እግዚአብሔር ይህን የሚያደርገው እነዚህን ነገሮቼን ለእኔና ለሌሎች ዘላለማዊ ጠቀሜታ በሚሰጥ በተሻለ ነገር ለመተካት ነው፡፡ (ለምሳሌ፡- ምቾት፣ ኃብት፣ ጤንነት፣ ወዘተ)

የሚከተሉትን ጥቅሶች ያጥኑ፡-

ማቴ. 5፡11-12፣ ሉቃስ 21፡1-4፣ ሐዋ. 4፡32-35፣ ሮሜ. 8፡17-18፣ ዕብ. 11፡17-19፣ ዕብ. 11፡24-27፣ 1ጴጥ. 1፡6-7  

  1. እግዚአብሔር ላዘጋጀው ሁኔታዎች የማሳየው ምላሽ፣ እርሱ ለእኔ ያዘጋጀውን እቅድ የመቀበሌና ራሴን በእርሱ ቁጥጥር ስር የማዋሌ አመላካች ነው፡፡

ሀ. ዝንባሌዬ እና ምላሼ ምን መምሰል እንዳለበት ኢየሱስ አሳይቶኛል፡፡

የሚከተሉትን ጥቅሶች ያጥኑ፡-

ማቴ. 26፡51-53፣ ዮሐ. 19፡9-11፣ ዕብ. 5፡8፣ ዕብ. 12፡1-2፣ 1ጴጥ. 2፡19-23

ለ. ሐዋሪያው ጳውሎስ ራሱን በእግዚአብሔር የፍቅር ጥበቃ ውስጥ ለመተው መረጠ፡፡

የሚከተሉትን ጥቅሶች ያጥኑ፡-

ሐዋ. 20፡22-24፣ 2ቆሮ. 12፡7-10፣ ፊል. 3፡10-11፣ ፊል. 4፡12  

ሐ. ኢዮብ ራሱን በእግዚአብሔር ሉአላዊ ጥበቃ ውስጥ አሳልፎ መስጠትን ተምሯል፡፡ በአንድ ቀን እግዚአብሔር፣ ሰይጣን የኢዮብ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ልጆቹን ጨምሮ፣ እንዲወስድ ፈቀደለት (ኢዮብ 1፡4-19)፡፡ በመቀጠልም ሰይጣን የኢዮብን ሰውነት እንዲያሰቃይ፣ እግዚአብሔር ፈቀደለት (ኢዮብ 2፡1-8)፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ ግን የኢዮብ ምላሽ እግዚአብሔርን አስደሰተ፡፡

የሚከተሉትን ጥቅሶች ያጥኑ፡-

ኢዮብ 1፡1-3፣ ኢዮብ 1፡20-22፣ ኢዮብ 2፡7-10

መ. እግዚአብሔር በሕይወቱ እንዲመጣ ለፈቀደው መከራ የዮሴፍ ምላሽ ምን እንደ ነበረ እንመልከት፡- ይቀኑበት የነበሩ ወንድሞቹ ዮሴፍን ጠሉት፤ ለነጋዴዎችም አሳልፈው ሸጡት፤ ገዢዎቹም ወደ ግብፅ ወሰዱት (ዘፍ. 37፡2-36)፡፡ ከዛም አስገድዶ በመድፈር ሙከራ በሐሰት ተከሰሰ፤ ያለምንም በደል በእስር ሰነበተ (ዘፍ. 39፡1-40፡23 እና መዝ. 105፡17-19)፡፡

ዮሴፍ ለወንድሞቹ የእግዚአብሔርን ታማኝነትና ሉአላዊነት መሰከረ፡፡

የሚከተሉትን ጥቅሶች ያጥኑ፡-

ዘፍ. 41፡52፣ 45፡5፣ 45፡8፣ 50፡19-20   

ማጠቃለያ፡ እግዚአብሔር፣ ልታምነው የሚገባ አምላክ ነው፡፡ ሁል ጊዜ ለእኔ እጅግ የሚጠቅም ነገር እንደሚያደርግ ላምነው እችላለሁ፡፡ በሰማይ በእርሱ ፊት ቆሜ፣ በምድር ላይ በእኔ ሕይወት ያደርግ የነበረውን ሥራ በማይበት የመጨረሻ ቀን፣ በእርሱ ላይ አሳርፌው በነረው እምነት አላፍርም፡፡ መከራዎች ካለሁበት ሁኔታ እንዳፈገፍግ እያደርጉኝም፡፡ በሚወደን አምላክ ፈቃድ ወደ ሕይወታችን የሚመጡ መከራዎችን፣ በእምነት ሆነን መቀበል ያስፈልጋል፡«…እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራን የሚቀበሉ፣ መልካምን እያደረጉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ አደራ ይስጡ፡፡›› (1ጴጥ. 4፡19)

የሚከተሉትን ጥቅሶች ያጥኑ፡-

መዝ. 33፡18-21፣ መዝ. 34፡4-8፣ ሮሜ. 8፡31-32፣ 1ዮሐ. 5፡18-19፣ 1ተሰ. 5፡16-18

1 thought on “መከራና የእግዚአብሔር ሉአላዊነት”

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading