ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈው ለማን ነው?

በመጀመሪያዎቹ 100 ዓመታት፥ የማቴዎስ ወንጌል በጣም ተወዳጅ ነበር። የዐይን ምስክር በነበረ ሐዋርያ የተጻፈ በመሆኑ እጅግ ክብር ያለው ወንጌል እንደሆነ ይታሰብ ነበር። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ብዙውን ጊዜ ስለ ክርስቶስና ስላስተማረውም አሳብ በሚያብራሩበት ጊዜ ከማቴዎስ ወንጌል ይጠቅሱ ነበር።

የማቴዎስ ወንጌል በኣዲስ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙ መጻሕፍት ሁሉ የላቀ የአይሁዳዊነት ባሕርይ አለው። ማቴዎስ ኣይሁዳዊ እንደ መሆኑ፥ ዋነኛ አንባቢዎቹ ኣድርጎ የመረጠውም አይሁዶችን ሳይሆን አይቀርም። ክርስቶስም አይሁዳዊ መሆኑን በማመልከት አንዳንድ ምሑራን፥ የማቴዎስ ወንጌል ክርስቶስ ስለኖረበትና ስላስተማረበት ሁኔታ ከሁሉም የበለጠ ሚዛናዊ አመለካከት እንደሚያቀርብ ይናገራሉ። ማቴዎስ ክርስቶስ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ፍጻሜ የሆነ ንጉሥና መሢሕ መሆኑን ለማያምኑ ኣይሁዶች ወንጌሉን ለማካፈል ፈልጓል። ስለሆነም ማቴዎስ ከየትኛውም የአዲስ ኪዳን ጸሐፊ የበለጠ ከብሉይ ኪዳን ጠቅሷል። በተጨማሪም ማቴዎስ አይሁዳዊ አገላለጾችን ተጠቅሟል። ለምሳሌ፥ እንደ አሕዛብ ሁሉ «የእግዚአብሔር መንግሥት» ሳይል «የሰማይ መንግሥት» ብሏል። ለኣይሁዳውያን ክርስቲያኖችም ክርስቶስን መከተል ማለት ምን ማለት እንደሆነ ጽፎአል። ነገር ግን ማቴዎስ ከሚያስተምራቸው ትምህርቶች አንዱ ቤተ ክርስቲያን የሰዎች ሁሉ እንጂ የአይሁዶች ብቻ እንዳልሆነች ነው። ስለሆነም ምንም እንኳ ማቴዎስ የጻፈው ለአይሁዶች ቢሆንም፥ የክርስቶስን ታሪክ አይሁዳውያን ላልሆኑ ለአሕዛብ ክርስቲያኖች አብራርቷል። ለምሳሌ፥ ክርስቶስን ለማምለክ ስለመጡት የመጀመሪያዎቹ አሕዛብ ጠቢባን የገለጸው ማቴዎስ ነው (ማቴ. 2)። ክርስቶስ ወንጌሉ ለዓለም ሁሉ እንዲዳረስ የሰጠውን ትእዛዝ የዘገበው ማቴዎስ ነው (ማቴ. 28፡19-20)።

ማቴዎስ ወንጌሉን በምን ቋንቋ እንደ ጻፈ ምሑራን ይከራከራሉ። ከጥንት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች አንዱ ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈው፥ የአዲስ ኪዳን አይሁዶች ቋንቋ በነበረው የአረማይስጥ ቋንቋ እንደሆነና ከዚያ በኋላ ወደ ግሪክ ቋንቋ እንደ ተተረጎመ ገልጾኣል። ነገር ግን አብዛኞቹ ምሑራን በሮም ግዛት የነበሩት ሰዎች ሁሉ ያነቡት ዘንድ ማቴዎስ ወንጌሉን በግሪክ ቋንቋ እንደ ጻፈ ያምናሉ።

ማቴዎስ ወንጌሉን በሚጽፍበት ጊዜ አይሁዶች የሮምን አገዛዝ ገርስሰው ለመጣልና እንደገና ነፃ መንግሥት ለመመሥረት ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር። በብሉይ ኪዳን ትንቢት የተነገረላቸው መሲሖች እንደሆኑ የሚናገሩ ብዙ የአማፅያን መሪዎችም ተነሥተው ነበር። በጥቂት ዓመታት ውስጥ ይህ የአማፅያኑ ተቃውሞና የሮማውያን ጥላቻ በሮም መንግሥት ላይ ግልጽ ትግል እንዲያካሂዱ አደረጋቸው። ብዙም ሳይቆይ ሮማውያን የአይሁዶችን ተቃውሞ በመምታት በ70 ዓም. ቤተ መቅደሱንና የከተማይቱን ቅጥሮች አፈራረሱ።

በዚህ ጊዜ በአይሁድ ክርስቲያኖችም መካከል ከፍተኛ ውጥረት ነበር። በመጀመሪያ፥ በሮም ላይ ስለተካሄደው አመፅ ምን ዐይነት ምላሽ መስጠት እንደሚገባቸው መወሰን ነበረባቸው። ዝም ብሎ መቀመጡ ከሮማውያን ጋር እንደ ወገኑ ተቆጥሮ በሌሎች ኣይሁዶች እንዲጠፉ ያደርጋቸው ነበር። ሁለተኛው፥ በክርስቶስ ወንድሞቻቸውና እኅቶቻቸው ከሆኑት አሕዛብ ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ መወሰን ነበረባቸው። አይሁዶች የሚጠሉት ሮማውያንን ብቻ ሳይሆን አሕዛብን በሙሉ ነበር። ስለዚህ የአይሁድ እማኞች ከእነርሱ ጎሣ የሆኑትን አይሁዶችን መደገፍ፥ ወይም ለእግዚአብሔር ቤተሰብ የነበራቸው ታማኝነት አብዛኞቹ አይሁዶች ከሚያደርጉት ነገር ለመለየት መወሰን ተገድደው ነበር። በአሕዛብ ላይ ጀርባቸውን ሳያዞሩ እንዴት ታማኝ አይሁዳዊነታቸውን እንደሚያሳዩ ለማወቅ ተቸግረው ነበር። ስለሆነም አንዳንዶቹ የብሉይ ኪዳንን ትምህርት የሚከተሉ ታማኝ አይሁዶች መሆናቸውን ለማረጋገጥ የአሕዛብ ክርስቲያኖች እንዲገረዙ ጠየቁ። ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈው በዚህ የፈተና ወቅት ነበር። ከዓላማዎቹ አንዱ ፖለቲካዊ መሢሖች ሐሰተኞች መሆናቸውን ማሳየት ነበር። የብሉይ ኪዳንን ትንቢቶች ያሟላው እውነተኛ መሢሕ ክርስቶስ ብቻ ነበር። ማቴዎስ የአይሁድ ክርስቲያኖች በፖለቲካዊ ውጥረት ሳቢያ እምነታቸውን እንዳይጥሉ አስጠንቅቋቸዋል። እስከ መጨረሻው ድረስ እምነታቸውን መጠበቅ ያስፈልጋቸው ነበር (ማቴ. 10፡22)። እግዚአብሔር ለአሕዛብ የወጠነው ዕቅድ እነርሱን እንዲጠሉ ወይም አይሁዳዊ እንዲሆኑ ማስገደድን አይጨምርም ነበር። አይሁዶች በክርቶስ መሢሕነት ካላመኑ፥ የእውነተኛው የእግዚአብሔር ሕዝብ አካል ሊሆኑ አይችሉም።

1ኛ የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ አንዳንድ ክርስቲያኖች በአንድ በኩል ለቤተሰባቸው ወይም ለጎሳቸው፥ በሌላ በኩል ለክርስቶስ ታማኝ የመሆኑን አስቸጋሪ ምርጫ ለማድረግ የሚገደዱት እንዴት ነው? ለ) ኣንዳንዶች ለጎሳቸውና ለቤተሰባቸው፥ ወይም መንፈሳዊ ቤተሰቦቻቸው ለሆኑት ሌሎች ክርስቲያኖች ለመታመን የሚገደዱባቸውን ሁኔታዎች ኣብራራ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading