የኢየሱስ መጠመቅ (ማቴ. 3፡13-17)

የኢየሱስ ሕይወት ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር አመራር ሥር ነበር። ይፋዊ አገልግሎቱ እስኪደርስ ድረስ በትዕግሥት በናዝሬት ከተማ ውስጥ ሲጠብቅ ቆየ። በዚያን ጊዜ የመጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎት በስፋት ይታወቅ ነበር። አንድ ቀን ኢየሱስ ከናዝሬት ተነሥቶ ዮሐንስ ወደሚያጠምቅበት ዮርዳኖስ ወንዝ (ይሁዳ ውስጥ) መጣ። መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስ መሢሕ እንደሆነ ያውቅ ነበር። ብዙውን ጊዜ ትልቁ ትንሹን ስለሚያጠምቅ፥ መጀመሪያ ዮሐንስ ክርስቶስን ለማጥመቅ አልፈለገም ነበር። አንዳንድ ምሑራን ዮሐንስ ከእርሱ የውኃ ጥምቀት የሚበልጠውን የክርስቶስን የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ፈልጎ ነበር ይላሉ።

ክርስቶስ ግን ጽድቅን ሁሉ ለመፈጸም ዮሐንስ ሊያጠምቀው እንደሚገባ ገለጸ። ምናልባትም ክርስቶስ ይህን ሲል በእግዚአብሔር የታቀደለት እንደሆነና ዮሐንስ ሊያጠምቀው እንደሚገባ መግለጹ ይሆናል። ይህ የታዛዥነትና የጽድቅ መንገድ ነበር። ምሑራን ክርስቶስ ለምን እንደ ተጠመቀ ይከራከራሉ። ክርስቶስ ከኃጢአት የጠራ ስለሆነ (ዮሐ 8፡46፤ ዕብ. 4፡15)፤ የእርሱ ጥምቀት ከኃጢአት ንስሐ መግባትንና የሕይወት ለውጥን የሚያመለክት አልነበረም። ምክንያቱ ግን ሌላ ነው። አዘውትረው ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።

1) ክርስቶስ ከመጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎት ጋር እንዲተባበር ለማድረግ። ክርስቶስ መጥምቁ ዮሐንስ እንዲያጠምቀው በመጠየቁ፥ ከዮሐንስ የንስሐና የጥምቀት መልእክት ጋር መስማማቱን ለሕዝቡ እያሳየ ነበር። እንዲያውም ራሱ ክርስቶስም ተመሳሳይ መልእክት ሰብኳል (ማቴ. 4፡17)።

2) ክርስቶስ አማኞች ሁሉ ሊከተሉት የሚገባውን ምሳሌ እያዘጋጀ ነበር። ጥምቀት ለአማኞች ከሚያስፈልጉ ዐበይት መመዘኛዎች አንዱ ነው። [መጽሐፍ ቅዱስ አማኞች ሁሉ እንዲጠመቁ ያዝዛል(ማቴ. 28፡19-20)።] ስለሆነም፥ ክርስቶስ ለሌሎች አርአያ ለመሆን ሲል ተጠምቋል።

3) ይህ የክርስቶስ ይፋዊ አገልግሎት ጅማሬ ነበር። እስከዚህ ጊዜ ድረስ ክርስቶስ በናዝሬት ይፋዊ ያልሆነ ሕይወት ሲመራ የቆየ ሲሆን፥ ካሁን በኋላ ግን የመሢሕነት አገልግሎቱ አደባባይ ይወጣል።

4) ክርስቶስ ኃጢአት ሠርቶ ባያውቅም፥ ራሱን ከኃጢአተኞች ጋር እያስተባበረ ነበር። ከአገልግሎቱ አንዱ የሆነው የሊቀ ካህንነት ተግባሩ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጥምቀት ለክርስቶስ አስፈላጊ ከነበረና ክርስቲያኖችም እንዲጠመቁ ከታዘዙ፡ ብዙ ክርስቲያኖች ያልተጠመቁት ለምንድን ነው? ለ) ጥምቀት ለክርስቲያኖች ምንድን ነው? (ሮሜ 6፡1-14፤ ቲቶ 3፡5 የሐዋ. 2፡38 አንብቡ።)

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሦስቱ የሥላሴ አካላት አብረው የሠሩበት አንዱ ግልጽ ምሳሌ የክርስቶስ ጥምቀት ነው።

የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ በምድር ላይ በዮሐንስ እጅ የተጠመቀው ነበር።

መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በክርስቶስ ላይ ወረደ። ምንም እንኳ አምላክ እንደ መሆኑ መጠን፥ በራሱ ሥልጣን ሊሠራና ሊያስተምር ቢችልም፥ ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ ለአማኞች ምሳሌ በመሆን ለመንፈስ ቅዱስ ራሱን አስገዝቷል። መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ መውረዱ መሢሕ ሆኖ ለመቀባቱ ምልክት ነበር (ኢሳ. 11፡2)። መንፈስ ቅዱስ የርግብን አምሳል የመረጠው ለምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ርግብ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሆና ተጠቅሳለች። በፍጥረት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ (እንድ ርግብ) ሰፍፎ እንደ ነበር ተገልጾአል (ዘፍጥ. 1፡2)። ለአይሁዶች፥ ርግብ ገርና ሰላማዊ ኣገልግሎትን ታመለክታለች። ምንም እንኳ አይሁዶችና ዮሐንስ ጠላትን እያወደመና የጽድቅን መንግሥት እየመሠረተ በኃይል እንዲገለጥ ቢፈልጉም፥ ክርስቶስ የመጣው በትሕትናና በገርነት መንፈስ ነበር (ማቴ. 11፡29)።

እግዚአብሔር አብም በሥራው ውስጥ ተሳትፎአል። ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ እግዚአብሔር ልዩ ልጁ እንደሆነ በይፋ መስክሯል። (ይህ የእግዚአብሔር ቃል መዝ. 2፡7ን እና ኢሳ 42፡1ን ያንጸባርቃል። እነዚህም ስለ መሢሑ መምጣት የሚናገሩት ትንቢቶች ናቸው።) እግዚአብሔር በክርስቶስ ባሕርይና ተግባራት ሙሉ በሙሉ ደስ ተሰኝቶ ነበር። ክርስቶስ ሁሉም ሊከተሉት የሚገባ ፍጹም ሰው ነበር። ይህ እግዚአብሔር በክርስቶስ ደስ መሰኘቱን በይፋ ከመሰከረባቸው ሦስት አጋጣሚዎች አንዱ ነው (ማቴ. 17፡5 ዮሐ 12፡28)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ማቴ. 3፡16-7 እግዚአብሔር በሦስት አካላት (አብ፥ ወልድና መንፈስ ቅዱስ) እንደሚገለጥ የሚያሳየው እንዴት ነው? ለ) በሥላሴ ውስጥ ሦስት አካላት እንደሌሉና፥ ኣንዱ ኣምላክ ኣንዳንድ ጊዜ ኣብ፥ ሌላ ጊዜ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እየሆነ እንደሚገለጥ የሚያስተምረው «የኢየሱስ ብቻ» (Only Jesus) ተከታይ፣ ከሳተበት ለመመለስ ማቴ. 3፡16-17ን እንዴት ልትጠቀም ትችላለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)

3 thoughts on “የኢየሱስ መጠመቅ (ማቴ. 3፡13-17)”

  1. Keep it up ….Geta iyesus zemenachihun yibark…kenante kininet yetenesa inem metsahaftin manbeb jemerku silezih tebareku

    1. ዳዊት፣ ስለ ማበረታቻህ እግዚአብሔር አብዝቶ ይባርክህ፡፡ በወንጌል በድረገጽ አገልግሎት ስለተጠቀምክ በጣም ደስ ብሎናል፡፡ መጻሕፍትን ይበልጥ እንድትመረምር ስላበረታታህም ደስታችን እጥፍ ድርብ ነው፡፡ ጸጋ ይብዛልህ!

  2. የጌታ ጸጋ ሀይል ይብዛላችሁ..i am so much happy …i praise God for you…may God have number of people who submit all their time , effort ….every thing to achieve the heavenly mission of God (the gospel movement )
    …..

Leave a Reply

%d bloggers like this: