ክርስቶስ የፈጸማቸውን የተለያዩ ተአምራት ማቴዎስ 8:1-9:38

የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 8-9 ኣንብብ። ሀ) ክርስቶስ የፈጸማቸውን የተለያዩ ተአምራት ዘርዝርና እያንዳንዳቸው ስለ ክርስቶስ ምን እንደሚያስተምሩ ግለጽ። ለ) ከእነዚህ ምዕራፎች ስለ ደቀ መዝሙርነት ምን እንማራለን? ሐ የክርስቶስ ፈውስ ዛሬ ብዙ ኣገልጋዮች ከሚያካሂዱት ፈውስ ጋር በምን እንደሚመሳሰልና እንደሚለያይ ግለጽ።

ማቴዎስ የክርስቶስን የሕይወት ታሪክ የጻፈው፥ እውነተኛ መሢሕ መሆኑን ለአይሁዶች ለማሳመንና ለክርስቲያኖች ደግሞ የክርስቶስ ተከታይ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለማመልከት መሆኑን ተመልክተናል። ማቴዎስ ክርስቶስ ስለፈጸማቸው ኣሥር ተአምራት የገለጸበት ሁኔታም እነዚህኑ ጭብጦች ያሳየናል። ማቴዎስን ከሌሎች ሁለት የወንጌል መመሳሰል ጋር በምናነጻጽርበት ጊዜ፥ 1) ማቴዎስ እነዚህን ታሪኮች በጊዜ ቅደም ተከተል እንደማይተርክ እንመለከታለን። ከእነዚህ ተአምራት ውስጥ አንዳንዶቹ ከተራራው ስብከት በፊት የተፈጸሙ ሲሆኑ፥ የተቀሩት ግን ከዚያ በኋላ የተፈጸሙ ሳይሆኑ አይቀሩም። ማቴዎስ ግን ክርስቶስ የፈጸማቸውን የተአምራት ዓይነቶች ለማብራራት ተጠቅሞባቸዋል። 2) ማቴዎስ በክርስቶስ ትምህርት ላይ በማተኮሩ ምክንያት፥ ስለ እነዚህ ተአምራት ከማርቆስና ሉቃስ ያነሰ ማብራሪያ ይሰጣል።

 1. የለምጻሙ ሰው መፈወስ ተአምር (ማቴ. 8፡1-4)

በአይሁዶች አመለካከት እንደ ለምጽ ያለ አስከፊ በሽታ አልነበረም አይሁዶች በአያሌ ምክንያቶች ለምጽን ይጠሉ ነበር። በመጀመሪያ፥ በሽታወ ሊፈወስ የማይችልና የግለሰቡን መልክ የሚያበላሽ ነው ብለው ስለሚገምቱ ነበር። ሁለተኛ፥ በአይሁድ እምነት ለምጻም ሰው ርኩስ በመሆኑ፥ ከቤተሰቡና ከኅብረተሰቡ ተለይቶ ሌሎች የማይፈለጉ ሰዎች ከሚኖሩበት ወጣ ያለ ኣካባቢ ለመኖር ይገደድ ስለነበረ ነው።

ለምጻሙ ሰው ክርስቶስ እንዲፈውሰው በጠየቀው ጊዜ፥ ክርስቶስ አንድ ቃል በመናገርና በመዳሰስ ፈወሰው። ክርስቶስ ለምጻሙን በመንካቱ በሽታውን አለመፍራቱንና ለበሽተኛው ርኅራኄ እንዳለው አሳይቷል። የክርስቶስ ዳሰሳ ከማርከስ ይልቅ በሽተኛውን ከለምጹ አነጻው። ክርስቶስ ግለሰቡ እንደገና ከማኅበረሰቡ ለመቀላቀል የብሉይ ኪዳንን መስፈርቶች እንዲያሟላ በማዘዙ፥ ለሕጉ የነበረውን አክብሮት አሳይቷል (ዘሌዋ. 13-14)።

ከዚያም ለምጻሙ ስለ ተአምሩ ለማንም እንዳይናገር አስጠነቀቀው። ለምን? ለዚህ በምክንያትነት የሚጠቀሱ አያሌ አሳቦች አሉ። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ በተአምር አድራጊነት ለመታወቅ ኣልፈለገም ነበር። ስለሆነም የተአምራት ሠሪነቱ ዜና እንዲሰራጭ አልፈቀደም። ሁለተኛ፥ ክርስቶስ አገልግሎቱ ሚዛናዊነትን እንዲያጣ አልፈለገም። ፍላጎቱ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ዘላቂ ፍሬና ለውጥ ሊያስከትል በሚችለው የማስተማር አገልግሎቱ ላይ ለማተኮር ነበር። በፈውስ አገልግሎቱ ላይ ማተኮር፥ የሰዎችን አሳብ ይበልጥ በመሳብ፥ አስፈላጊ ከሆነው ጉዳይ ለማስተማሪያ የሚፈልገውን ጊዜ ይሻማበት ነበር። ሦስተኛ፥ ሕዝቡ ለመንፈሳዊ ለውጦች ትኩረትን ሳይሰጥ ሥጋዊ ፍላጎታቸውን የሚያሟላ ዓይነት መሢሕ አድርገው እንዲረዱት አልፈለገም ነበር።

ማቴዎስ ይህን የመጀመሪያ ተአምር የጠቀለው፥ ለአያሌ ምክንያቶች ነበር። በመጀመሪያ፥ አይሁዶች በመሢሑ የአገዛዝ ዘመን ለምጽ እንደማይኖር ያምኑ ነበር። ስለሆነም ክርስቶስ እንደ መሢሕ ለምጽን የማስወገድ ኃይል እንዳለው ለማሳየት ፈለገ። ሁለተኛው፥ ማቴዎስም ኢየሱስ በየትኛውም ዓይነት በሽታ ላይ ኃይል እንዳለው አሳየ። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ለምጽን መፈወስ ከቻለ የትኛውንም ዓይነት በሽታ ሊፈውስ ይችላል ማለት ነው። የክርስቶስ ተከታዮች የሆንን ሁላችን ክርስቶስ ከበሽታ ሊፈውስ እንደሚችል ማመን አለብን። ነገር ግን ክርስቶስ በሽታዎችን ሁሉ የመፈወስ ኃይል ቢኖረውም፥ የሚሠራው እንደ ፈቃዱ ስለሆነ፥ የተገዥነት መንፈስ ሊኖረን ይገባል።

ዛሬ ብዙ ሰዎች የፈውስ አገልግሎት ይዘው ወደ ተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ይሄዳሉ። የፈውስ አገልጋይ ሁሉ ከእግዚአብሔር እንዳልሆነ ግልጽ ነው (2ኛ ተሰ. 2፡9 ራእይ 3፡13-14፤ 19፡20 አንብብ።) አንድ የፈውስ አገልጋይ እግዚአብሔርን መወከል አለመወከሉን እንዴት እናውቃለን? ባለፈው ሳምንት እንደተመለክተነው፥ ቀዳሚው መንገድ የግለሰቡን ባሕርይ መፈተን ነው። ግለሰቡ በማቴዎስ 5፡3-12 ላይ የተጠቀሱት ባሕርያት አሉት? ከዛሬው ታሪክ የምንመለከታቸው ሌሎች ፍንጮች አሉ። ግለሰቡ የክርስቶስን የፈውስ አገልግሎት ምሳሌ ይከተላል? የክርስቶስን የፈውስ አገልግሎት በምንመለከትበት ጊዜ፥ ሰዎች ሁሉ ብድግ ብለው በመቆም ፈውሳቸውን እንዲቀበሉ እንዳላዘዘና «አጠቃላይ» ፈውስ እንዳልሰጠ እንመለከታለን። ከሕዝቡ መካከል ሳይሆን፥ ከሚፈውሰው ግለሰብ ጋር በግል ይገናኝ ነበር። በተጨማሪም፥ ሰዎች እንደ ተአምራት ሠሪ እንዲረዱትና ወደ እርሱ እንዲሳቡ የማድረግ ፍላጎት አልነበረውም። ስለዚህ ሕዝቡ ስለ ተአምራቱ እንዳያወሩ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ነበር። ክርስቶስ ሰዎች ከእርሱ ጋር ግንኙነት እንዲመሠርቱና እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንዲኖሩ ማስተማር ከፈውስ እንደሚበልጥ ያውቅ ነበር። በዚህም እንዲሁም የክርስቶስ ፈውስ ቅጽበታዊና የተሟላ እንደሆነ እንመለከታለን። ከፊል ፈውስ (ለምሳሌ፥ የሽባው ወደ ማነከስ ደረጃ መሻሻል) ወይም በሽታው ዳግም ያገረሸበት ሁኔታ አልነበረም።

የውይይት ጥያቄ፡ ዛሬ የምንመለከታቸው አብዛኞቹ የፈውስ አገልግሎቶች ከነዚህ መመዘኛዎች አንጽር እንዴት ይታያሉ?

 1. የመቶ አለቃው ባሪያ ፈውስ (ማቴ. 8፡5-18)

ምንም እንኳ ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈው ለአይሁዶች ቢሆንም፥ ክርስቶስ ለአሕዛብም ትኩረትን እንደሰጠ አመልክቷል። ስለሆነም፥ ማቴዎስ የመቶ አለቃውን ባሪያ የፈውስ ታሪክ አካትቷል። የመቶ አለቃው የ100 ሰዎች ወታደሮች ሹም የሮም ጦር መኮንን ነበር። ይህ የመቶ አለቃ ዋነኛ የንግድ መተላለፊያ በሆነችው በቅፍርናሆም ይኖር ነበር። ምንም እንኳ የሮም ወታደሮች በአይሁዶች የተጠሉ ቢሆኑም፥ ይህ የመቶ አለቃ በጣም የተከበረ መሁኑን (ሉቃስ 7፡1-5) ይናገራል። ይህን ሰው ራሳቸው አይሁዶች ነበሩ ወደ ክርስቶስ አምጥተው እንዲፈውሰው የለመኑት።

ማቴዎስ የዚህን መቶ አለቃ አስደናቂ እምነትና ስለ ክርስቶስ ኃይል የነበረውን ግንዛቤ ገልጾአል። ሰውዬው አሕዛብ ቢሆንም፥ እምነቱና ለክርስቶስ የሰጠው እውቅና ከአብዛኞቹ አይሁዶች የላቀ ነበር። አይሁዶች እንረክሳለን ብለው ስለሚፈሩ፥ ወደ አሕዛብ ቤት አይሄዱም ነበር። ነገር ግን ክርስቶስ ለዚህ ዓይነት ግርጃ ስለማይገዛ ወደ ግለሰቡ ቤት ለመሄድ ፈለገ። የመቶ አለቃው ግን ከለከለው። ይህን ያደረገው ክርስቶስ እንዳይረክስ ስለፈለገ ነበር ወይስ፥ ኃጢአተኛ በመሆኑ ክርስቶስን በቤቱ የማስተናገድ ብቃት እንዳልነበረው በመገንዘብ? መልሱን አናውቅም። ከግለሰቡ ምላሽ የምንረዳው ነገር ቢኖር፥ በክርስቶስ ኃይል ላይ ሙሉ እምነት እንደ ነበረው ነው።

የመቶ አለቃው የክርስቶስን ኃይል ከራሱ ሥልጣን ጋር አነጻጸረ። ሮማውያን ሁሉም ሥልጣን ከንጉሡ እንደሚመነጭ ያምኑ ነበር። ያ ሥልጣን በተዋረድ እስከ ተራው ወታደር ይደርሳል። በየትኛውም የተዋረዱ ደረጃ ላይ አልታዘዝም ማለት ንጉሡን ካለመታዘዝ እኩል ይቆጠር ነበር። ተግባራቱም የሚፈጸሙት በቃል ትእዛዝ ነበር። እንደ መቶ አለቃ፥ ሥራውን ራሱ የማከናወን ግዴታ አልነበረበትም። ሥልጣን ማለት ሌሎችን እያዘዙ ማሠራት ማለት ነበር። የመቶ አለቃው ይህንኑ ግንዛቤውን ከክርስቶስ ጋር አዛምዷል። ሁሉም አጠቃላይ ሥልጣን ከእግዚአብሔር እንደሚመነጭና እንደ እግዚአብሔር ወኪል የክርስቶስ ቃላት የእግዚአብሔርን ሥልጣን እንደሚያንጸባርቁ ተገነዘበ። የመቶ አለቃው ክርስቶስ ታላቅ ኃይል እንዳለውና ራሱ ወደ ቤቱ መምጣት እንደማያስፈልገው አመነ። የአፉ ቃል ብቻ ፈውስን ያመጣል ብሎ አሰበ። የክርስቶስ ንግግር እግዚአብሔርን ስለሚወክል፥ የአፉ ቃል እንደሚፈውስ አመነ። የዚህን ግለሰብ እምነት ታላቅነት የምንገነዘበው ስለ ክርስቶስ ኃይልና ከእግዚአብሔር ጋር ስላለው ግንኙነት ከማወቁ ላይ ብቻ ሳይሆን፥ ክርስቶስ ከበሽተኛው አጠገብ ርቆ ቢገኝም እንኳ ሊፈውስ እንደሚችል በማመኑ ነው። እስከዚህ ጊዜ ድረስ፥ ክርስቶስ ይህንን አላደረገም ነበር።

ክርስቶስ በመቶ አለቃው እምነትና ግንዛቤ ተደነቀ። ኢየሱስ ለአይሁዶችና ለደቀ መዛሙርት ብዙ አሕዛብ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንደሚጨመሩ በመግለጽ አስጠነቀቀ። ሥጋዊ ዝርያቸው የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካል ያደርገናል ብለው የሚያስቡ ብዙ አይሁዶች ደግሞ ከመንግሥቱ ውጭ ቀርተው የዘላለምን ፍርድ ይቀበላሉ።

 1. ኢየሱስ የጴጥሮስን ኣማትና ሌሎች ሰዎችን ፈወሰ (ማቴ. 8፡14-17)

ማቴዎስ የክርስቶስን የፈውስ አገልግሎት ማብራራቱን ቀጥሏል። የጴጥሮስ አማትና ሌሎችም የከተማይቱ ነዋሪዎች ተፈወሱ። በተጨማሪም፥ ክርስቶስ አጋንንትን ከሰዎች ኣስወጣ። ነገር ግን ማቴዎስ በዚህ ታሪክ ውስጥ አጽንኦት የሰጠው ለተአምሩ ሳይሆን፥ ለብሉይ ኪዳን ትንቢት ፍጻሜ ነበር። ክርስቶስ በሁሉም ዓይነት በሽታዎች ላይ ኃይል እንዳለው በማሳየቱ፥ በኢሳይያስ 53፡4 እንደተተነበየው፥ መሢሑ የእግዚአብሔር ባሪያ መሆኑን አረጋግጧል።

እነዚህ ሦስት ተአምራት ሁሉ፥ ማቴዎስ በዓለም የማይጠቅሙ ተደርገው የሚታሰቡትን ሰዎች መምረጡ አስገራሚ ነው። የመጀመሪያው ከበሽታው የተነሣ ከኅብረተሰቡ የተገለለ ለምጻም ሲሆን፥ ሁለተኛው በብዙ ምክንያት የተናቀ አሕዛብ ነበር። ሦስተኛዋ በጾታዋ ምክንያት ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣት ሴት ነበረች። ምናልባትም ማቴዎስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለም ለናቃቸው ሰዎች የሚያስብ መሆኑን ለማሳየት የፈለገ ይመስላል። ማንም ለእርሱ አላስፈላጊ አይደለም፤ እርሱ ሰዎችን በእኩል ደረጃ ያያል።

 1. ክርስቶስ ደቀ መዝሙርነት ስለሚያስከፍለው ዋጋ አብራራ (ማቴ. 8፡18-22)

ማቴዎስ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን ስለፈለገ አንድ ሰው በመግለጽ፥ የተአምራት ትረካውን ገትቷል። በዚህም ማቴዎስ ዋንኛው ጉዳይ ደቀ መዝሙርነት እንጂ ተአምር እንዳልሆነ አሳይቷል። ክርስቶስን መከተል ማለት ምን ማለት ነው? በመጀመሪያ፥ አንድ የሕግ መምህር ክርስቶስን ለመከተል ሲጠይቅ፥ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ሥጋዊ ምኞት የሌላቸው መሆኑን በመግለጽ አስጠነቀቀው። የሰው ልጅ የሚያርፍበት ስፍራ አልነበረውም። ስለዚህ ክርስቶስ የሚሄድበት የመስቀሉ መንገድ ብዙውን ጊዜ የመከራ መንገድ ስለነበረ፥ ማንም ሰው ለሥጋዊ ጥቅም ክርስቶስን መከተል አይችልም ነበር። መለኮታዊው ንጉሥ ምንም ነገር እስከማይኖረው ድረስ ራሱን ዝቅ ካደረገ። ደቀ መዛሙርቱም አርአያነቱን ለመከተል መሞከር ነበረባቸው። ክርስቶስ ግለሰቡ የደቀ መዝሙርነትን ዋጋ ለመክፈል መፍቀዱን እየፈተነ ነበር።

የዉይይት ጥያቄ፡- ዳን. 7፡13-14 አንብብ። ሀ) ዳንኤል ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የተመለከተውን ግለጽ። ለ) እግዚአብሔር የአገዛዝ ሥልጣን የሰጠው ለማን ነበር? ሐ) ማቴ. 9፡6፤ 12፡8፤ 3፡416፡27፤ 17፡12፤ 19፡28፤ 240፤ 26፡64 አንብብ፡ እነዚህ ምንባቦች ስለ ሰው ልጅ ምንን ያስተምራሉ?

እዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስቶስ ራሱን የሚጠራበትንና በምዕስለ ወንጌላት ውስጥ በብዛት ተደጋግሞ የተጠቀሰውን ስም እናገኛለን። ሌሎች ብዙውን ጊዜ በዚህ ስም አይጠሩትም። በወንጌላት ውስጥ ይህ ስም ያገለገለው ለክርስቶስ ብቻ ነበር። ይህ ስም ከየት መጣ? ሁለት አማራጭ ምንጮች አሉ። በመጀመሪያ፥ ይህ ሰብአዊ ሰውን ለማለት የተጠቀመበት እንደሆነ የሚናገሩ ወገኖች አሉ። ምክንያቱም ቃሉ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ብዙውን ጊዜ በዚህ ትርጉም አገልግሏል። በመዝሙር 8፡4 ላይ «የሰው ልጅ» የሚለው ቃል የሰው ልጆችን ሁሉ የሚያመለክት ሲሆን፥ ለሕዝቅኤል ከተሰጡት ስሞች አንዱ ነው (ሕዝ. 2፡1-8)።

አብዛኞቹ ምሑራን የዚህ አገላለጽ ምንጭ ዳንኤል 7፡13-14 እንደሆነ ያምናሉ። ዳንኤል በራእዩ «የሰውን ልጅ» የሚመስል መለኮታዊ አካል ወደ እግዚአብሔር አብ ዘንድ ሄዶ የንግሥናን ሥልጣን፥ ክብርና ኃይል እንደ ተቀበለ ተመልክቷል። ይህም ለክርስቶስ መለኮታዊ መሢሕነት ግልጽ የሆነ የማዕረግ ማስረጃ ነበር።

ኢየሱስ ይህንን ስም ለራሱ የመረጠው ለምንድን ነው? ምናልባትም ይህ አይሁዶች ለመሢሕነት በብዛት ያልተጠቀሙበት ስለሆነ፥ የተሳሳተ ግንዛቤን ያስወግዳል በሚል እምነት ይሆናል። ክርስቶስ ይህን ስም ተጠቅሞ ምን ዓይነት መሢሕ እንደሆነ ለማሳወቅ ይችል ነበር። «የዳዊት ልጅ» ወይም «መሢሕ» የሚሉ ሌሎች ስሞች፥ ሰዎች በእስራኤል ላይ ስለሚነግሥ ፖለቲካዊ መሪ እንዲያስቡ ያደርጉ ነበር። ክርስቶስ የመጣው ግን በዚህ መንገድ አልነበረም። እርሱ የመጣው መከራን እንደሚቀበል የእግዚአብሔር ባሪያ ሆኖ ነበር (ኢሳ. 53)። አንድ ቀን በአጽናፈ ዓለሙ ላይ መለኮታዊ ገዥ ሆኖ ይመጣል። ክርስቶስ በዚህ ስም ላይ ያስተማረውን ብናስተውል፥ የሰው ልጅ መከራ እንደሚቀበልና እንደሚሞት መግለጹን እንረዳለን። ይህም አብዛኞቹ አይሁዶች ያልተገነዘቡት የመሢሑ አገልግሎት ነበር። ነገር ግን ክርስቶስ ወደፊት የሰው ልጅ በክብር፥ በደመና ለመግዛት ከመላእክቱ ጋር ወደ ምድር እንደሚመለስም ተናግሯል። ይህ ከዳንኤል ራእይ ጋር የበለጠ ተመሳሳይነት አለው። ስለሆነም ይህ ክርስቶስ ሰው በመሆኑ ላይ ሳያተኩር፥ ይበልጥ አምላክነቱንና በምድር መንግሥታት ሁሉ ላይ የሚነግሥ መሆኑን ያስረዳል።

ሁለተኛው ምሳሌ አባቱን ለመቅበር ጊዜ ስለፈለገው ግለሰብ የሚናገር ነው። ብዙ ምሑራን ይህ ሰው ክርስቶስን ለመከተል ባለመፈለጉ ያቀረበው ተራ ማመኻኛ እንደሆነ ያስባሉ። እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ፥ በእስራኤል አገር ሰው ከሞተ በአንድ ወይም ሁለት ቀናት ውስጥ ይቀበር ስለነበር፥ አባቱ እንደ ሞተ ካወቀ ቀድሞውኑ ሊቀብር ይችል ነበር። ስለሆነም፥ ብዙ ምሑራን አባቱ ገና እንዳልሞተ ያስባሉ። አዛውንት አባት ስላለው፥ ሰውዬው እስኪሞት ድረስ ለመጠበቅ ፈልጎ ነበር። ምናልባትም ግለሰቡ ለቤተሰቡ ባለው ፍቅር ሳቢያ በአባቱ እርጅና አመኻኝቶ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሚሆንበትን ጊዜ እያራዘመ ይሆናል። ምናልባትም አባቱ ልጁ እንዳይለየው ወይም ክርስቶስን እንዳይከተል ይፈልግ ይሆናል። ስለሆነም፥ የአባቱን ቁጣ ፈርቶ እስኪሞት ለመጠበቅ ፈልጎ ይሆናል። ክርስቶስን እንዳይከተል ምን እንደ ከለከለው በትክክል ባናውቅም፥ ክርስቶስ ግን ሰውዬው እውነትን የመናገር ጉድለት እንዳለበት የተጎነዘበ ይመስላል። ሰውዬው ክርስቶስን ለመከተል ቢፈልግም፥ ቤተሰቡን ለመተው አልወደደም። ስለሆነም ክርስቶስ የእርሱ ደቀ መዝሙር መሆንና እርሱን መውደድ፥ ቤተሰብን ከመውደድና ከቤተሰብ ግዴታዎች እንደሚበልጥ ገለጸለት። የአንድ ሰው የቤተሰብ ግንኙነቶች ክርስቶስን ከመከተል ከከለከለው፥ ቤተሰቡን መካድ አለበት። (ሉቃስ 9፡59-60 አንብብ።) ኢየሱስ የዚህን ግለሰብ ለደቀ መዝሙርነት ራሱን የመስጠት ደረጃ እየፈተነ ነበር። ክርስቶስ ወደ አባቱ የሚሄድበት ጊዜ ቅርብ ስለነበረ ሰውዬው፥ እርሱን የሚከተልበት ረጅም ጊዜ አልነበረውም። ስለሆነም፥ መንፈሳዊ «ሙታን» እና ክርስቶስን ለመከተል የማይፈልጉ ሰዎች «በሥጋቸው» የሞቱትን መቅበር እንዳለባቸው ገልጾለታል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተሰብ አባላትንና ቤተሰባዊ ግዴታዎችን ከመከተል፥ ክርስቶስን ማስቀደም የሚቀልባቸውን መንገዶች በምሳሌ አስረዳ። ለ) አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሚዛናዊነትን አጥተው ጠቅላላ ጊዜያቸውን ለቤተ ክርስቲያን በመስጠት ለቤተሰቦቻቸው ጊዜ ሊያጡ የሚችሉት እንዴት ነው? ሐ) ሙሉ በሙሉ ተሰጥተን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ላለመሆን ብዙውን ጊዜ ማመኻኛዎችን የምናቀርበው እንዴት ነው?

 1. ክርስቶስ ማዕበሉን ጸጥ አደረገ (ማቴ. 8፡23-2)

ማቴዎስ ክርስቶስ በበሽታ ላይ የነበረውን ኃይል ያሳየ ሲሆን፥ እንደ መሢሕ በተፈጥሮ ላይ ያለውንም ኃይል ለማሳየት ፈልጓል። ስለሆነም በአንዲት ትእዛዝ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱንና ታንኳይቱን ሊያወድም የደረሰውን ማዕበል ጸጥ ያሰኘበትን አጋጣሚ ተረከ። ደቀ መዛሙርቱ በታንኳይቱ ውስጥ አብሯቸው እያለ መፍራታቸው ያለማመናቸው ምልክት ነበር። ጊዜው ከመድረሱ በፊት ማንኛውም ማዕበል በኢየሱስ ላይ አደጋ ሊያስከትል አይችልም ነበር። ደቀ መዛሙርት ሁሉ በሰው ሕይወት እንደ ረሀብ፥ በሽታ፥ ሞት፥ የምድር መንቀጥቀጥ፥ ጎርፍና የመሳሰሉ ማዕበሎች እንዳሉ መገንዘብ አለባቸው። ክርስቶስ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ከእኛ ጋር ያለ አማኑኤል እንደሆነ ማስታወስ አለብን። የትኛውም ማዕበል ጌታችንን አያናውጠውም። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በፍርሃት መሸነፋቸው ያለማመናቸው ምልክት ነበር። እኛም እንዲህ ባለ ሁኔታ ብንሸበር አንድም ክርስቶስ ከእኛ ጋር መሆኑን፥ አልያም እርሱ የሕይወት ማዕበሎችን ሁሉ እንደሚቆጣጠር ዘንግተናል ማለት ነው።

 1. ክርስቶስ በአጋንንት የተያዘ ግለሰብ ፈወሰ (ማቴ. 8፡28-34)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች የሚፈሯቸውን እንደ ክፉ ዓይን፥ ክፉ መናፍስት፥ ጠንቋዮች ያሉ ነገሮችን ዘርዝርና የሚፈሩበትን ምክንያት ግለጽ። ለ) በዚህ ክፍል ከመናፍስት ዓለም ጋር ስላለን ግንኙነት ምን እንማራለን?

አብዛኞቹ ሰዎች የመናፍስት ዓለምን ይፈራሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች፥ ሰዎች ለሞቱ አያትና ቅድማያቶቻቸው መናፍስት፥ በጥንቃቄ መሥዋዕት እያቀረቡ የመንፈሶቻቸውን ቁጣ ለማርገብ ይጥራሉ። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ፥ ክርስቲያኖችም ጭምር ክፉ ዓይን፥ ክፉ መናፍስትን ወይም ጠንቋዮችን ይፈራሉ። በአንድ አካባቢ፥ ቃልቻው የአምልኮ ሥርዓቱን ለመጀመር ከበሮውን ሲመታ፥ በአካባቢው የነበሩ ክርስቲያኖች በፍርሃት ተዋጡ። ወደ ውጭ ሮጠውም በመውጣት፥ «በኢየሱስ ስም» እያሉ ይጮኹ ጀመር። ይህ አይነቱ ባሕሪይ ለክርስቲያኖች ተቀባይነት የማይኖረው በምን ምክንያት ነው?

የክርስቶስ ተከታዮች ከመናፍስት ዓለምና ምትሐት ጋር ባለው ግንኙነት የክርስቶስን ማንነት ማወቁ አስፈላጊያችን ነው። እንደ መሢሕ መንፈሳዊ መንግሥቱን ለመጀመር፥ ክርስቶስ የሰይጣንን መንግሥት ማሸነፍ ነበረበት። ኢየሱስ በሰይጣን ላይ ሥልጣን እንዳለው ለማሳየት፥ ማቴዎስ ክርስቶስ ወዲያው ሁለት ሰዎችን ከአጋንንት ቁጥጥር ሥር ነፃ እንዳወጣቸው አመልክቷል።

ማቴዎስ ስለ ጦርነቱ ሊገልጽ፥ በኣጋንንት የተያዙትን ሁለት ሰዎች ኃይል አብራራ። ማንም ሰው ሊቆጣጠራቸው አይችልም ነበር። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ከክርስቶስ ጋር ሲገናኙ፥ አጋንንቱ የክርስቶስን ማንነትና በእነርሱ ላይ ሥልጣን እንደነበረው ተገነዘቡ። መለኮታዊና ሙሉ የእግዚአብሔር ሥልጣን ያለው «የእግዚአብሔር ልጅ» መሆኑን አወቁ። አጋንንቱ የኋላ ኋላ ክርስቶስ እንደሚያሸንፋቸው ያውቁ ነበር፡ ፍርድ እንደሚሰጣቸውና በሲዖል እንደሚሠቃዩም ያውቁ ነበር። ይህም አጋንንት ብዙ ነገሮችን እንደማያውቁና የእግዚአብሔር ጊዜ ከእነርሱ እንደ ተሰወረ ያሳያል። በምድር ላይ የክርስቶስ ሚና ምን እንደሆነና መጀመሪያ በመስቀል ላይ ኃይላቸውን እንዴት እንደሚያወድም አያውቁም ነበር (ቆላ. 2፡13-15)። ነገር ግን አጋንንቱ ወዲያው ለክርስቶስ ታዘዙ። በቀላል ትእዛዝ ከክርስቶስ ወደ እሪያዎች እንዲገቡ አደረ። እሪያዎቹም ወዲያውኑ ባሕር ውስጥ ገብተው ሰጠሙ። የሚገርመው፥ መሢሑ በመካከላቸው ቢሆንም፥ የአካባቢው ሕዝብ ለንብረታቸው ሳስተው ክርስቶስ እንዲሄድላቸው ጠየቁት።

የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የመናፍስትን ዓለም ማወቅ አለባቸው። ነገር ግን የመናፍስትን ዓለምም ሆነ እንደ ቃልቾች ለክፉ መናፍስት የሚሠሩትን ሰዎች መፍራት የለባቸውም። ደቀ መዛሙርቱ ሁልጊዜ ሊያስታውሱት የሚገባው መርሕ በዓለም ካለው ይልቅ በእኛ ያለው ይበልጣል» (1ኛ ዮሐ. 4፡4) የሚለውን ነው። አማኑኤል የሆነው ክርስቶስ፥ ከእኛ ጋር እንዳለና የመናፍስትን ዓለም እንዳሸነፈ ማስታወስ አለብን (ዮሐ 16፡33)። እንደዚህ ዓይነት የማይታዩ ነገሮችን መፍራት ያለማመን ተግባር ብቻ ሳይሆን፥ ሰይጣን እንዲቆጣጠረን የሚያደርግም ነው።

 1. ክርስቶስ ሽባውን ሰው ፈወሰ (ማቴ. 9፡1-8)

ይህ ታሪክ ሁለት እውነቶችን ያስተምራል። ሽባና ሙሉ በሙሉ ምስኪን በሆነ ሰው ላይ የተገለጸውን የክርስቶስን ኃይል ከማመልከቱም በላይ፥ ክርስቶስ ኃጢአትን የማስተሰረይ ሥልጣን ያለው አምላክ መሆኑን ያሳያል። ክርስቶስ ግለሰቡን ከመፈወሱ በፊት ኃጢአቱን ይቅር አለ። ይህም ከእግዚአብሔር በቀር ማንም ሰው ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንደሌለው የሚያውቁትን የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች አስደነገጠ። ኢየሱስም ኃጢኣትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው ለማረጋገጥ ሰውዬውን ፈወሰው።

ክርስቲያኖች ለበሽተኞች በምናገለግልበት ጊዜ፥ መጠንቀቅ አለብን። በሽታዎችና ክፉ ነገሮች ሁሉ በሰውዬው ኃጢአት ምክንያት እንደሚከሰት በማሰብ፥ በሽተኛው ኃጢአቱን እንዲናዘዝ እንጫነዋለን። ክርስቶስ በሰው ሕይወት ውስጥ የነበረውን ሁሉ ስለሚያውቅ ይህንን ሊያደርግ ይችል ነበር። ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉም በሽታ በኃጢአት ምክንያት እንደማይመጣ ያውቅ ነበር (ዮሓ 9፡1-5)። በሚፈውስበት ጊዜ የኃጢአትን ይቅርታ የሰጠው በአንድ አጋጣሚ ብቻ ነው። እንግዲህ ሰዎች በሚታመሙበት ጊዜ ምን ማድረግ አለብን? ያዕቆብ በ5፡14-16 ላይ ከሁሉም የበለጠ ምሳሌ ይሰጠናል። የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የታመመውን ግለሰብ መጎብኘት አለባቸው። ሽማግሌዎቹ ግለሰቡ ሕይወቱን የሚመረምርበትን ዕድል ሊሰጡትና በዓመፀኝነት የሚመላለስ ከሆነ የእግዚአብሔርን ይቅርታ እንዲጠይቅ ማድረግ አለባቸው። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ሽማግሌዎች ሰውዬው በዐመፃ መመላለስ አለመመላለሱን ሊያውቁ ይችላሉ። ሰውዩውን በዘይት መቀባት አለባቸው። ይህ ምናልባትም መድኃኒት መውለድን (በጥንቱ ዘመን ዋንኛው መድኃኒት ዘይት ነበር) ሊያመለክት ቢችልም፥ እግዚአብሔር ግለሰቡን መቀባቱን የሚያሳይ ይሆናል። ሽማግሌዎቹ ታማሚውን በእግዚአብሔር እጆች ውስጥ አኑረው እንዲፈውሰው በመጠየቅ፥ ሊጸልዩለት ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ ይህን ምሳሌ ከመከተል ይልቅ፥ የፈውስ ስጦታ ያለውን እገልጋይ የሚፈልጉት ለምንድን ነው?

 1. ክርስቶስ ማቴዎስን ለደቀ መዝሙርነት ጠራው (ማቴ.9፡1-13)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በከተማችሁ ውስጥ እጅግ የጎደፈ ስም ያላቸውን አንዳንድ ሰዎች ስም ዘርዝር። እነዚህ ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው? ሰዎች የጠሏቸው ለምንድን ነው? ለ) ብዙ ክርስቲያኖች ከእነዚህ ሰዎች ጋር ዝምድና በመመሥረት ስለ ክርስቶስ ለመመስከር የማይፈልጉት ለምንድን ነው? ሐ) ክርስቲያኖች ክርስቶስ ለማድረግ ስለሞከረው ነገር የዘነጉት ምንድን ነው?

ማቴዎስ ከክርስቶስ ጋር ፊት ለፊት የተገናኘበትን ጊዜ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ሳያስታውሰው አልቀረም። ማቴዎስ ታሪኩን በአጭሩ ጽፎታል። ማቴዎስ በአይሁዶች እጅግ ከተጠሉት ቀረጥ ሰብሳቢዎች መካከል አንዱ ነበር። ሰዎች እንደ ስግብግብና አገሩን የካደ ሰው አድርገው ይገምቱት ነበር። ተራ አይሁዳዊ እንኳን ከእርሱ ጋር አይዛመድም ነበር። አይሁዶች እንደ እርሱ ያለውን ሰው ከመሳደብ፥ ከመበደል፥ ከመጸየፍና ከመትፋት የተለየ ተግባር አይፈጽሙበትም ነበር። ክርስቶስ በፍቅርናሆም አካባቢ በሚሠራበት ጊዜ ማቴዎስ ስለ ክርስቶስ ሳይሰማ አልቀረም። ክርስቶስ ተኣምራት ሲሠራ ሊመለከት ቢችልም፥ እንደ እርሱ ላለ ሰው የሚጨነቅ አልመሰለውም። ስለሆነም፥ ክርስቶስ ገንዘብ ወደሚሰበሰብበት ስፍራ መጥቶ ደቀ መዝሙሩ እንዲሆን ሊጠይቀው፥ ተደነቀ። ከዚያም ሁሉንም ትቶ ተከተለው። በዚያን ምሽት ግብዣ አድርጎ ቀረጥ ሰብሳቢ ባልደረቦቹ ሁሉ ከክርስቶስ ጋር እንዲገናኙ አደረገ ይህ ፈሪሳውያንን በማስቆጣቱ፥ «ክርስቶስ በትክክል ከእግዚአብሔር ዘንድ ቢመጣ ኖሮ፥ ማቴዎስ ክፉ ሰው እንደሆነ አውቆ ከእርሱ ጋር ኅብረት አያደርግም ነበር ብለው አጉረመረሙ።

ማቴዎስ በዚህ የግል ታሪክ ሁለት እውነቶችን ለማስተላለፍ ፈልጓል። ኣንደኛ፥ የደቀ መዝሙርነትን ዋጋ ለማሳየት ፈልጓል። እንደ ጴጥሮስና እንድርያስ ሁሉ፥ ለማቴዎስ ክርስቶስን መከተል ማለት ጠቅላላ የሕይወት ለውጥ የሚጠይቅ እርምጃ ነበር። ሥራውንና ሀብቱን እንዲተው ቢያስገድደውም እንኳ፥ ሙሉ ሕይወቱን ሰጥቶ ጌታውን መከተል ነበረበት። ሁለተኛ፥ ክርስቲያኖች በራሳቸው ጽድቅ ተመክተው የተከበሩ ሰዎች ብቻ ወንጌሉን ሰምተው የቤተ ክርስቲያን አባል እንዲሆኑ ከማድረግ እንዲቆጠቡ ያስጠነቅቃል። እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ወንጌሉን ሙሉ በሙሉ በተሳሳተ መንገድ መተርጎም ይሆናል። የሃይማኖት መሪዎችን፥ የተከበሩ አሁዶችንና የክፉ ኃጢአተኞችን ጨምሮ፥ ሁሉም በኃጢአት በሽታ ታምመዋል። ለሁሉም የክርስቶስ ፈውስ ያስፈልጋቸዋል። ኢየሱስ ራሳቸውን የሚያጸድቁትንና መንፈሳዊ ሕይወታቸው መልካም እንደሆነ የሚያስቡትን አይፈውስም። ነገር ግን ኃጢአተኛነቱን የተነዘበውን የክፋውን ኃጢአተኛ ሳይቀር ይፈውሳል። ክርስቶስ ከሰማይ ወደ ምድር የመጣው ለኃጢአት በሽተኞች ነበር። ክርስቲያኖች ማኅበረሰቡ ለናቃቸው ሴተኛ አዳሪዎች፥ የጎዳና ተዳዳሪዎች ፉጋዎች ወንጌሉን ለማካፈል በማይፈልጉበት ጊዜ፥ የፈሪሳውያንን መንፈስ ማሳየታቸው ነው። ይህ እግዚአብሔር የተቀበለን እኛ ከእነዚህ ወገኖች ተሽለን በመገኘታችን ነው ከሚል አመለካከት የመነጨ ነው። ነገር ግን ለሁሉም የክርስቶስ መድኃኒትነት እንደሚያስፈልግ በትሕትና መገንዘቡ መልካም ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች እንደ ፈሪሳውያን ራሳቸውን ጻድቅ አድርገው በመኮፈስ የሚከተሏቸውን መንገዶች አብራራ። ለ) የቤተ ክርስቲያንህ ምእመናን ክፉዎች ወይም ማኅበረሰቡ ያስወገዳቸው አድርገው የሚያስቧቸውን ጨምሮ፥ ሰዎችን ሁሉ እንዲቀበሉ ለማስተማር የምትችለው እንዴት ነው?

 1. ኢየሱስ እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ለምን እንደማይጾሙ ገለጸ (ማቴ. 9፡14-17)

ፈሪሳውያንና የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት፥ የክርስቶስን ሕይወት በጥንቃቄ ሲመረምሩ ነበር። በዚህ ጊዜ ልክ እንደ እነርሱ ሰኞና ሐሙስ ቀን እንደማይጾም ተገነዘቡ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ መንፈሳዊ እንዳልሆነ ማሰባቸው አልቀረም። ምክንያቱን ሲጠይቁት ክርስቶስ ሁለት ምክንያቶችን ሰጣቸው።

ሀ. በሠርግ ጊዜ፥ የሙሽራው ወዳጆች ከመጾምና ከማዘን ይልቅ ከሙሽሮቹ ጋር ይደሰታሉ አላቸው። መሢሑና ሙሽራው ክርስቶስ በዚህ ጊዜ በመካከላቸው ነበር። እርሱ ስላለ፥ አሁን መደሰት ያስፈልጋቸዋል። ክርስቶስ ከእነርስ ጋር በማይሆንበት ጊዜ ግን ይጾማሉ።

ለ. በመሢሑ መምጣት ፍጹም አዲስ ሥርዓት ያለበት ምዕራፍ ተከፍቷል። ኢየሱስና ትምህርቶቹ አዲስ ወይንና አዲስ ልብስ ነበሩ። የእርሱ መንግሥት አዲስ ወይን፥ በብሉይ ኪዳንና ፈሪሳዊ የአምልኮ ሥርዓት ውስጥ ሲጨመሩ (አሮጌው የወይን አቁማዳ፥ አሮጌ ልብስ)፥ አሮጌውም አዲሱም ይበላሻሉ። ይህም አዲሱን ወይን በማይለጠጥ አሮጌ የወይን አቁማዳ ውስጥ እንደ መጨመር ይሆናል። ይህ አሮጌውን የወይን አቁማዳ መቅደድ ብቻ ሳይሆን፥ አዲሱንም ወይን እንዲነፍስበት ያደርገዋል። ወይም ደግሞ አሮጌን ልብስ በኣዲስ ጨርቅ መጣፍ ይሆናል። ልብሱ በሚታጠብበት ጊዜ፥ አዲሱም አሮጌውም ጨርቅ ይበላሻል። በዚህም ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር ለሚደረገው ግንኙነት አዲስ ግንዛቤ የሚያስፈልግበትን ኣዲስ ምዕራፍ እየከፈተ ነበር (አዲስ የወይን አቁማዳ፥ አዲስ ልብስ)።

ማቴዎስ አይሁዶች፥ በተለይም የአይሁድ ክርስቲያኖች ኢየሱስ የብሉይ ኪዳን አምልኮ ወይም ፈሪሳዊ የሃይማኖት ግንዛቤ ቅጥያ እንደሆነ አድርገው እንዳይነዘቡ እያስጠነቀቃቸው ነበር። ክርስቶስ የመጣው የነበረውን ለመጠገን ሳይሆን፥ አዲስ መንፈስ በማምጣት ሙሉ በሙሉ ለመለወጥ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች፥ ክርስቶስ ወደ ሕይወታችን መጥቶ ጥቂት ለውጦችን ብቻ እንደሚያደርግ ያስባሉ። ክርስቶስ ግን ወደ ሕይወታችን በሚመጣበት ጊዜ መላውን ሕይወታችንን ስለሚለውጥ፥ ለእርሱ የተዘጋጀ አዲስ የወይን አቁማዳ መኖር እንዳለበት ገልጾአል። ይህም አስተሳሰባችንን፥ ባሕርያችንን፥ የእሴት ግንዛቤያችንና ተግባራችንን ይለውጠዋል።

 1. የክርስቶስ ኃይል በሞትና በሁሉም ዓይነት በሽታዎች ላይ (ማቴ. 9፡18-34)

ማቴዎስ እንደገና ወደ ክርስቶስ ተአምራት ተመልሶ፥ የመሢሕነቱን ማረጋገጫዎች ያቀርባል። ክርስቶስ በበሽታ ላይ ብቻ ሳይሆን፥ በሞትም ላይ ኃይል አለው። ክርስቶስ የሞተች ልጅ ከማስነሣቱም በላይ፥ ለ12 ዓመታት ደም የፈሰሳትን ሴት ፈውሷታል። ማቴዎስ ለ12 ዓመታት ደም የፈሰሳትን ሴት ታሪክ የጠቀሰው ለሁለት ምክንያቶች ነበር። በመጀመሪያ፥ ታሪኳን የእምነትን ኃይል ለመግለጽ ተጠቅሞበታል። ችግሮች ገጥመውን ክርስቶስ ጥልቅ ፍላጎታችንን እንደማያሟላ በምናምንበት ጊዜ ይህንኑ ያደርገዋል። ሁለተኛ፥ ሙሉ ለሙሉ ምስኪን ለሆኑት ሰዎች ክርስቶስ እንደሚራራላቸው ያሳያል። ደም የሚፈስሳት ሴት እንደ ርኩስ ትቆጠር ስለ ነበር፤ የነካችው ነገር ሁሉ ርኩስ ነበር። ይህም በቤቱ ውስጥ ባሉት ሁሉ ላይ የመጨነቅ ስሜት ያስከትል ነበር። በዚህች ምስኪን ሴት ላይ የተከሰተው ዓይነት ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ፥ ባሏና ቤተሰቦቿ በአንዲት ትንሽ ክፍል ይወስናት ወይም ባሏ ይፈታት ነበር።

ማቴዎስ ኢየሱስ ሁለት ዓይነ ስውሮችን እንዳገኘም ይነግረናል። እነዚህ ሰዎች ሥጋዊ ዓይነ ስውርነት ቢያጠቃቸውም፥ ክርስቶስ «የዳዊት ልጅ» መሆኑን ማወቃቸው ከፈሪሳውያን በላይ ጠቢባን እንደ ነበሩ ያሳያል። ይህም ለመሢሑ የተሰጠ ሌላው ስም ነበር። እምነታቸው ሥጋዊ ዓይኖች ካሏቸው ሰዎች የበለጠ በመሆኑ፥ ክርስቶስ ዓይኖቻቸውን ከፍቷል። በተጨማሪም፥ ክርስቶስ አንድ ግለሰብ እንዳይናገር ዲዳ ያደረገውን መንፈስ አስወጥቷል። ማቴዎስ፥ ይህ ሁሉ የመሢሑን በመካከላቸው መገኘት እንደሚያረጋግጥ በመግለጽ እንዲቀበሉት ተፈታተኗቸው።

ለዚህ ሁሉ፥ ሥጋዊ ዓይኖች ያሏቸውና መንፈሳዊ ነገሮችን ሊመለከቱ የማይችሉ የሃይማኖት መሪዎች የሰጡት ምላሽ ምን ነበር? ዓይኖቻቸው የተመለከቱትን ልባቸው ለማመን አልፈቀደም፥ ሊሰጡ የፈቀዱት ማብራሪያ ቢኖር ክርስቶስ በሰይጣን ኃይል እንደሚሠራ መግለጽ ነበር። የእግዚአብሔርን ኃይል ለመቀበል ስላልፈለጉ፥ የክርስቶስን ሥራ በሌላ ኃይል አሳበቡ። ይኸው ክርስቶስ በሰይጣን ኃይል እንደሚሠራ የመግለጺ ሁኔታ ክርስቶስ የዚህን አስተሳሰብ አባይነት ለማሳየት እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ ቀጥሏል (ማቴ. 12፡22-29)።

 1. ክርስቶስ ለሕዝቡ ችግር አዘነ (ማቴ. 9፡35-57)

ክርስቶስ በአንድ አካባቢ ከማገልገል ይልቅ፥ ከአንዱ መንደር ወደ ሌላው እየተዘዋወረ የምሥራቹን ቃል ያበስር እንደነበር ማቴዎስ ገልጾአል። ክርስቶስ በሄደበት ስፍራ ሁሉ የተጎዱትን ሰዎች ይረዳና ይፈውስ ነበር። ክርስቶስ ከስፍራ ስፍራ በሚጓዝበት ጊዜ፥ 1) የሰዎቹ ችግር ምን ያህል እንደ በዛ ተመልክቷል። እንደ አይሁዶች፥ ከእግዚአብሔር ጋር ውስጣዊ ሰላምን የሚያመጣ ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባ ነበር። ጉድለቶቻቸውን ለማሟላት ሊረዷቸው የሚገባቸው የሃይማኖት መሪዎች ነበሯቸው። ነገር ግን እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተቅበዝብዘው ነበር። ክርስቶስ የሕዝቡን ፍላጎት በሙሉ ሊያሟላ እንደማይችል ተገንዝቧል። 2) ክርስቶስ ከነበረው ከፍተኛ ችግር አንጻር፥ ሠራተኞቹ ምን ያህል ጥቂቶች እንደሆኑም አጢኗል። ለዚህ ችግር መልሱ ምን ነበር? የመንፈሳዊ ሠራተኞች መብዛት ነው። ስለሆነም ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ብዙ መንፈሳዊ መሪዎችን ከእግዚአብሔር ዘንድ እንዲጠይቁ ነግሯቸዋል።

የክርስቶስ ውጥረት ዛሬም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚጋፈጡት ነው። የሕዝቡ ችግሮችና የአገልግሎት በሮች በጣም ብዙ ናቸው። ስለ ክርስቶስ ሰምተው ሊድኑ የሚገባቸው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ነገር ግን የገንዘብ ውስንነት ከመኖሩ የተነሣ፥ የሠለጠኑ ወይም ወንጌሉን ለማካፈል የቆረጡ አገልጋዮች ጥቂቶች ናቸው። መልሱ ምንድን ነው? ስለዚህ መልስ ብዙውን ጊዜ እናጉረመርማለን። ወይም የሥልጠና ትምህርት ቤቶችን መክፈት እንዳለብን እናስባለን። የዛሬውና በክርስቶስ ዘመን የነበረው ችግር የሠራተኞች እጥረት ብቻ አልነበረም። ፈሪሳውያንና ሌሎችም የሃይማኖት መሪዎች ነበሩ። በቀዳሚነት ችግሩ ለሕዝቡ ፍላጎቶች የክርስቶስ ዐይነት የርኅራኄ ልብ ያላቸው መሪዎች አለመኖራቸው ነበር። በዋናነት ልናደርግ የምንችለው ነገር ቢኖር፥ በሥራው ላይ አብረውን የሚሰማሩ ተጨማሪ ሠራተኞችን እንዲልክልን መጸለይ ነው። ይህም ማለት ግን ራሳችንም ሆነ ሌሎች በአገልግሎት የሚሳተፉበትን ሁኔታ ማመቻቸትን ይጨምራል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) መከሩ ከቤተ ክርስቲያንህ ሠራተኞች በላይ ሊበዛ የሚችለው እንዴት ነው? ለ) አንተና የቤተ ክርስቲያንህ ሽማግሌዎች እግዚአብሔር መንፈሳዊ ልብ ያላቸውን ተጨማሪ ሠራተኞች እንዲያስነሣ የምትጸልዩት እንዴት ነው? ሐ) ከቤተ ክርስቲያንህ መንፈሳዊ አመለካከትና መንፈሳዊ ስጦታ ያየህባቸውን የአምስት ወጣቶች ስም ዘርዝር። ለእነዚህ ወጣቶች በመጸለይ ጀምርና እንዴት ወደ በሳል እገልግሎት እንዲያድጉ ልታሠለጥናቸው እንደምትችል፥ እግዚአብሔርን ጠይቅ። መ) ቤተ ክርስቲያንህ እግዚአብሔር የጠራቸውን፥ ለአገልግሎት ያዘጋጃቸውንና የሥራ በር የከፈተላቸውን ሰዎች ለማግኘት ምን እያደረገች ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d