ማቴዎስ 16፡1-28

  1. ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ኢየሱስን ፈተኑት (ማቴ. 16፡1-12)

ኢየሱስ በሽተኞችን በመፈወስ፥ አጋንንትን በማውጣት፣ እንዲሁም ሙታንን በማስነሣት ተኣምራዊ ኣገልግሎት አካሂዷል። ይህም ሆኖ፥ የሃይማኖት መሪዎቹ ክርስቶስ መሢሕ አይደለም ብለው ደምድመው ነበር። ሰዎች አስቀድመው ስለ አንድ ነገር በልባቸው ከወሰኑና አዲስ እውነት ለመቀበል አእምሯቸውን ከዘጉ፥ ታላላቅ ተአምራት ቢሠሩ እንኳ ምንም ነገር ወደ እምነት አያመጣቸውም። ምንም እንኳ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ለዓመታት ጠላቶች የነበሩ ቢሆኑም፥ የጋራ ጠላታቸው የነበረውን ኢየሱስን ለማሸነፍ አብረው ይሠሩ ነበር። ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እርሱ መጥተው መሢሕነቱን ለማረጋገጥ “ከሰማይ ምልክትን” እንዲያሳያቸው ጠየቁት። የሃይማኖት መሪዎቹ ከኢየሱስ ተአምራት በቂ ማረጋገጫ ስላገኙ፥ የማመን ፍላጎት ቢኖራቸው ኖሮ፥ ይህንኑ ያደረጉ ነበር። እነርሱ ግን የማመን ፍላጎት አልነበራቸውም። ኢየሱስም ለመታየት ብሎ ተአምራት አልሠራም። ስለሆነም፥ ኢየሱስ «ከዮናስ ምልክት» ማለትም ከሞቱ፥ ከመቀበሩና ከመነሣቱ ተአምር በቀር ሌላ ነገር ሊያሳያቸው እንደማይፈልግ በድጋሚ ኣስገነዘባቸው።

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎችን ገሠጻቸው። ተራ ሰዎች የኣየሩንና የጸሐዩን ሁኔታ ተመልክተው የዝናብን መምጣት ወይም አለመምጣት ሊተነብዩ ይችላሉ። የሃይማኖት መሪዎቹ ግን የኢየሱስን መሢሕነት የሚያመለክቱ እነዚያ ሁሉ ማረጋገጫዎች እያሉ፥ የብሉይ ኪዳንን ትንቢቶች ሊረዱ ኣልቻሉም ነበር።

ብዙዎቻችን እንደ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን የመሆን ዝንባሌ ማሳየታችን ኢየሱስን አሳስቦታል፡ በውጫዊ ሕግጋት ላይ እያተኮሩ የእግዚአብሔር እጅ ታላላቅ ነገሮችን ሲሠራ ለማየት ባለመፈለጋቸው፥ ኢየሱስ ግብዝታቸውንና መንፈሳዊ ትዕቢታቸውን «የፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን እርሾ» ሲል ጠርቷል። ስለሆነም ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ከእነዚህ አመለካከቶች ሙሉ በሙሉ እንዲጠበቁ አስጠንቅቋል። እንዲህ ዓይነቱ እርሾ በሰው ሕይወት ውስጥ ካደገ በኋላ ያጠፋዋልና፡፡

የውይይት ጥያቄ:- ሀ) ከላይ የተገለጹት ዝንባሌዎች ብዙውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታዩት እንዴት ነው? ለ) የዚህ አይነት እርሾ በልብህ ውስጥ እንዳይኖር ምን እያደረግህ ነው?

ኢየሱስ ስለ እርሾ ሊናገር፥ ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ላይዙ በመምጣታቸው ጌታ የሚገስጻቸው መሰላቸው መንፈሳዊ እውነትን ለመረዳት አለመቻላቸው ኢየሱስን አሳዘነው እርሱ ከእነርሱ ጋር እያለ እንዴት ለሥጋዊ ምግብ ይጨነቃሉ? በትንሽ ምግብ አምስት ሺህ፥ በኋላም አራት ሺህ ሰዎችን ሲመግብ እይተዋል። ኢየሱስ ፍላጎቶቻቸውን ስለሚያሟላ፣ ደቀ መዛሙርቱ ለመሠረታዊ ነገሮች መጨነቅ አልነበረውም።

  1. ጴጥሮስ የክርስቶስን መሢሕነት መሰከረ (ማቴ 16፡13-20)

የማቴዎስ መጽሐፍ ማዕከል ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ የለጠው ምስክርነት ነው። ማቴዎስ የኢየሱስን ተአምራትና ትምህርቶች በማቅረብ እርሱ አይሁዶች ሊያምኑበት የሚገባ መሢሕ መሆኑን መስክሯል አሁን ምርጫው የራሳቸው ነበር፡፡ ያ ሁሉ ማረጋገጫ እያለ በኢየሱስ ላለማመን እንደ ወሰኑት ፈሪሳውያን ሊሆኑ ይሻሉ? ወይስ የሃይማኖት ምሁር ባይሆንም እንኳ ኢየሱስ መለኮታዊ መሢሕና “የሕያው እግዚአብሔር ልጅ” እንደሆነ በግል ሊመለከት እንደቻለው እንዲ ጴጥሮስ ሊሆኑ ይሻሉ?

ይህ የጴጥሮስ ምስክርነት የመጽሐፉ ማእከላዊ ነጥብ ነው። ከዚያ በኋላ፥ ማቴዎስ በመጪው የኢየሱስ ሞት ላይ ያተኩራል። ኢየሱስ ራሱ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ ሞቱና ትንሣኤው አስተምሯል።

ኢየሱስ “ቤተ ክርስቲያን” የሚለውን ቃል ሁለት ጊዜ ብቻ ጠቅሷል። ይህ ቤተ ክርስቲያን የተባለ የአማኞች የአንድነት አካል መጀመሩን የሚያሳይ ቀዳሚ ቃል ነው (ማቴ 18፡17 አንብብ።) በግሪክ ቋንቋ፥ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል “ተጠርተው የወጡ የክርስቶስ ተከታዮች ስብስብ” የሚል ፍች ይሰጣል፡ በኣዲስ ኪዳን ይህ ቃል የሚያመለክተው፥ የቤተ ክርስቲያንን ሕንጻ ሳይሆን፥ የክርስቲያኖችን ቡድኖች ነው። እነዚህም በአንድ ቤት ውስጥ የሚሰባሰቡትን ወይም ከኣንድ የቤት ቤተ ክርስቲያን የሚበልጡ ወገኖች የሚካተቱበትን የአንዲት ከተማ ወይም በየትኛውም ስፍራ የሚገኙትን ክርስቲያኖች ሁሉ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ይህ በኢትዮጵያ ቃሉ በቀዳሚነት ክርስቲያኖች የሚሰባሰቡበትን ሕንጻ ከሚያመለክትበት ሁኔታ የተለየ ነው፡፡

በዚህ ክፍል ምሑራን የሚከራከሩባቸው ሁለት ዐበይት ጥያቄዎች አሉ። በመጀመሪያ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን የሚሠራበት ዓለት ምንድን ነው? ሁለተኛ ለጴጥሮስ የተሰጠው ሥልጣን ምንን ያመለክታል?

1 የቤተ ክርስቲያን መሠረት የሆነው ዓለት ምንድን ነው? ለዚህ ጥያቄ የሚቀርቡ አራት ዐበይት ትርጉሞች አሉ።

ሀ. አንዳንዶች ዓለቱ ጴጥሮስ እንደሆነ ያምናሉ። ክርስቶስ ስሙን “ዓለት” የሚል ፍቺ ወደሚሰጠው ጴጥሮስ የለወጠው ለዚሁ ነው ይላል። የሮም ካቶሊኮች ይህ ቃል ጴጥሮስና ከእርሱ በኋላ የሚሾሙት ሊቀ ጳጳሳት መንፈሳዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ለእግዚአብሔር፥ የክርስቶስን ያህል ሥልጣን እንዳላቸው የሚያሳይ መሆኑን ያምናሉ። ሊቀ ጳጳሱና ካህናቱ የአማኙን መዳን ወይም አለመዳን የመወሰን መብት እንዳላቸው ያምናሉ። ይህ አተረጓጎምና ለሊቀ ጳጳሱ የተሰጠው ሥልጣን ሊሆን የማይችል ነው፡፡ ክርስቶስ ለጴጥሮስ ይህን ሥልጣን ቢሰጠው እንኳ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የጴጥሮስ ሥልጣን ወደ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደሚተላለፍ የሚያመለክት አሳብ የለም። እግዚአብሔር ጴጥሮስ የመጀመሪያውን ስብከት በበዓለ ኀምላ እንዲያቀርብ በማድረጉ፥ በአይሁዶች መካክል ቤተ ክርስቲያን ተወልዳለች (የሐዋ. 2:38-41)። እግዚአብሔር ሰማርያውያን እውነተኛ አማኞች መሆናቸውን እንዲመሰክርና መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ተጠቅሞበታል (የሐዋ. 8፡14-17)። እንዲሁም፥ ጴጥሮስ ለቆርኔሌዎስ በመመስከር አሕዛብን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዲያመጣ ተጠቅሞበታል (የሐዋ. 10፡27-48)።

ለ. ሌሎች ደግሞ ጴጥሮስ የሌሎች ሐዋርያት እንደራሴ እንደሆነ ያስባሉ። በኤፌ. 2፡20 ጳውሎስ ሁሉም ሐዋርያት የቤተ ክርስቲያን መሠረት እንደሆኑ ገልጾአል። እነዚህ ሐዋርያት ወንጌልን የመስበክ ብቻ ሳይሆን፥ በዓለም ሁሉ የማሰራጨት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር። በተጨማሪም፥ ለቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ፥ እውነተኛው ዶክትሪን የትኛው እንደሆነ፥ ክርስቶስ ማን እንደ ነበረ የመመስከር ሥልጣን ነበራቸው። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ፥ ሐዋርያት የቀድሞይቱን ቤተ ክርስቲያን ሊመሩና አስተምህሮቷን መልክ ሲያስይዙ እንመለከታለን።

ሐ. ዓለቱ ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ በዚህ ስፍራ ለዓለት ሁለት ቃላት ተጠቅሟል። ስምዖን የሚለውን ስም ወደ ጴጥሮስ በለወጠበት ጊዜ የተጠቀመው ቃል «ትንሽ ዓለት» የሚል ፍች ይሰጣል። ስለሆነም፥ ክርስቶስ ስምዖን ጴጥርስ (ትንሽ ዓለት) ሲሆን፥ በዚህ “ትልቅ ዓለት” ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ ብሏል። ትልቁ ዓለት ማን ነው? ሰዎች የሚሰናከሉበትና የእግዚአብሔር አዲስ ዕቅድ የማዕዘን ራስ የሆነው የተተወው ዓለት ማን ነው? እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ግልጽ ነው (ማቴ. 21፡42-44 አንብብ።) የቤተ ክርስቲያን መሠረት የሆነው ክርስቶስ ነው። (1ኛ ቆሮ. 3፡11 አንብብ።) ከሞተ፥ ከተቀበረና ሞትን አሸንፎ ከተነሣ በኋላ፥ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን ለመመሥረት መንፈስ ቅዱስን ላከ። የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ መሆኑ መጠን፥ ክርስቶስ ገዥ ነው።

መ. ዓለቱ ጴጥሮስ የሰጠው ምስክርነት ነው። አንድ ሰው ለመዳንና የቤተ ክርስቲያን አካል ለመሆን ማንን ማመን አለበት? ማመን ያለበት ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ የሆነ መሢሕ መሆኑን ነው። ይህ መሠረታዊ የአስተምህሮ ሐቅ አንድ ሰው ደኅንነትን ለማግኘትና የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል ለመሆን ሊያሟላው የሚገባው መሠረታዊ እውነት ነው።

2 ክርስቶስ ለጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማይን ቁልፎች እንደ ሰጠ ሲናገር ምን ማለቱ ነው? በማቴዎስ 18፡18፣ ለሁሉም ደቀ መዛሙርት ተመሳሳይ ሥልጣን ተሰጥቷል። አሁንም ምሑራን በዚህ ጉዳይ ላይ በመስራከር የተለያዩ ኣተረጓጎሞችን ይሰጣሉ።

ሀ. የሮም ካቶሊክ ክርስቲያኖች ይህን ጥቅስ የሚጠቀሙት የሊቀ ጳጳሱን ሥልጣን ለማረጋገጥ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ክርስቶስ ለጴጥሮስ ታላቅ ሥልጣን እንደ ሰጠው ያምናሉ፡ ካቶሊኮች ጴጥሮስ በምእመናን ላይ መንፈሳዊ ሥልጣን (ቁልፍ) እንዳለውና በእርሱ ውሳኔ የዘላለምን ሕይወት ሊያገኙ ወይም ወደ ሲኦል ሊወርዱ እንደሚችሉ ያስባሉ፡፡ ከዚህ በመነሣት፥ በአሁኑ ዘመን የሚያገለግለው ሊቀ ጳጳስ የጴጥሮስ ቀጥተኛ ተተኪ እንደሆነና ይህንኑ ተመላላይ ሥልጣን እንደ ተቀበለ ያስተምራሉ። ነገር ግን እነዚህ ምንባቦች ለጴጥሮስ ይህን ያህል ያልተገደበ ሥልጣን መስጠታቸው አጠራጣሪ ከመሆኑም በላይ፣ አዲስ ኪዳን ውስጥ ይህ ሥልጣን ወደ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደሚተላለፍ የሚያመለክት አሳብ አለመጠቀሱ ሊጤን ይገባል። ስለሆነም ይህ ትክክለኛ አተረጓጎም እንዳልሆነ እንረዳለን።

ለ. ሌሎች ክርስቲያኖች እነዚህ ምንባቦች ለጴጥሮስ ከፍተኛ ሥልጣን እንደተሰጠው የሚያመለክቱ መሆናቸውን ይሰማሉ። ይህ ግን ጴጥሮስ «አንተን ወደ መንግሥተ ሰማይ አስገባሃለሁ እላስገባህም?» የሚልበት ኃጢአትን ይቅር የማለትና ያለማላት ሥልጣን እንልሆነ ያስረዳሉ። ይህ ግን በእግዚአብሔር የተስፋ ቃሉችና በግለሰቡ እምነት ላይ ተመሥርቶ ጴጥሮስ የእግዚአብሔር መንግሥት አካል መሆኑን የሚያውጅበት ሥልጣን ነው። በግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ለጴጥሮስ የተሰጠው ሥልጣን «የመንግሥተ ሰማይን ቁልፎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር ላይ ያሰርከው ሁሉ ቀደም ሲል በሰማይ የታሰረ ነው በምድር የፈታከው ሁሉ ቀደም ሲል በሰማይ የተፈታ ነው።” ተብሎ ሊነበብ ይችላል፡፡ እነዚህ ምሑራን ጴጥሮስ በክርስቶስ ያመኑት እንደዳኑና ያላመኑት ግን ጥሩ አይሁዶች ቢሆኑም እንኳ እንዳልዳኑ የመወሰን ፍጹማዊ ሥልጣን እንዳለው ያስረዳሉ፡፡ ሁልጊዜም የማሰሩን ተግባር የሚያከናውነው የሰውን መዳን ወይም እለምዳን በዋንኛነት የሚወሰነው እግዚአብሔር እንደሆነ ያምናሉ።

ሐ. ቁልፎቹ የተለያዩ የሕዝብ ቡድኖችን በእኩልነት ወደ ቤተ ክርስቲያን ማምጣትን ሊያመለክት ይችላል። ስለሆነም፥ በሐዋርያት ሥራ 2 ጴጥሮስ በክርስቶስ ላመኑት አይሁዶች ወደ እግዚአብሔር የሚገቡበትን በር ከፍቷል። በሐዋርያት ሥራ 8 ደሞ የሰማርያውያን እምነት እውነት መሆኑን በመመስከርና በክርስቶስ መንግሥት (በቤተ ክርስቲያን) ከአይሁዶች እኩል መሆናቸውን በመግለጽ በር ከፍቶላቸዋል። በሐዋርያት ሥራ 10 ላይ አሕዛብን በእኩል ደረጃ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አስገብቷቸዋል።

ከሁሉም የሚሻለው ግንዛቤ፣ እነዚህ ቁልፎች ቀደም ሲል ክርስቶስ ባስተማረው እውነት ላይ በመመሥረት ጴጥሮስና ሌሎች ሐዋርያት ወደ እግዚአብሔር መድረስ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን መሆኑን በግልጽ የማወጅ ሥልጣን እንደተሰጣቸው የሚያስረዳው አመለካከት ይመስላል። ሰዎች ይህን ቃል ሰምተው ካመኑ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት አካል መሆናቸውን፥ ካላመኑ ቀን፥ የእግዚአብሔር መንግሥት አካል አለመሆናቸውን የማሳወቅ መለኮታዊ ሥልጣን ነበራቸው። ይህ ሥልጣን ከብሉይ ኪዳን ከሊቀ ካህናቱ ወይም ከሃይማኖት መሪዎች የመነጨ ላይሆን፥ ለአነስተኛ የደቀ መዛሙርት ቡድን የተሰጠ ነው፡፡

እኛስ እንደ ክርስቲያኖች ዛሪ ተመሳሳይ ሥልጣን አለን? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጠውን እውነት የምንገልጽ እስከሆነ ድረስ፥ ለዚህ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ልንሰጥ እንችላለን። ለዓለም ብቸኛው የመዳን መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ የመናገር ሥልጣን አለን፡፡ ለማመን ለሚሹትም፥ «ከልባችሁ ካመናችሁ፥ ትድናላችሁ” ልንል እንችላለን። እንዲሁም በመስቀል ላይ ሊያድናቸው በሞተው የእግዚአብሔር ልጅ ለማመን ለማይፈልጉት፥ ምንም ያህል መልካም ወይም ጻድቃን ቢሆኑም፥ የእግዚአብሔር መንግሥት አካል አለመሆናቸውን በሥልጣን ልንናገር እንችላለን። ሥልጣናችን የሚገደበው በችሎታችን ወይም በእምነታችን ሳይሆን፥ እግዚአብሔር በቃሉ ውስጥ በሚናገረው እውነት ነው። አንድን ሰው ወደ ሲኦል ወይም ወደ መንግሥተ ሰማይ የመላክ ችሎታ የለንም። እንዲሁም፣ የሐዋርያትን ያህል እውነትን የመበየን ሥልጣን የለንም።

ኢየሱስ የገሃነም ደጆች ቤተ ክርስቲያንን እንደማይቋቋሟት ገልጾአል። የኣማኞች አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ልትጠፋ የማትችል ነች፡፡ ከስፍራ ስፍራና ከአገር አገር ትስፋፋለች። ሰይጣን ምንም ያህል ቢዋጋት፥ አያሸንፋትም። ይህ ግን የአንድ አጥቢያ ክርስቲያኖች ምን ቢያምኑ ወይም ቢያደርጉ ከጥቃት ነጻ ናቸው ማለት ነው? አይደለም። የአንድ አጥቢያ አማኞች ወይም የቤተ ክርስቲያን ክፍሎች 1) በክርስቶስ ባያምኑና ንጹሕ እምነት ባይኖራቸው፥ ወይም 2) በክርስቶስና በትእዛዛቱ ላይ በይፋ ቢያምፁ፣ ከታሪክ እስኪጠፉ ድረስ ሊቀጡ ይችላሉ። በራእይ 2፡5 ኢየሱስ የመጀመሪያ ፍቅራቸውን ላጡት ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያን) መቅረዛቸውን እንደሚወስድባቸው በመግለጽ አስጠንቅቋቸዋል። ይህም ከእንግዲህ እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን ሊሆኑ እንደማይችሉ የሚያሳይ ነው። በታሪክ ሁሉ ለእምነታቸው ታማኞች ሆነው ባለመገኘታቸው ምክንያት፥ የጠፉ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትና ክፍሎች (ቤተ እምነቶች) አሉ። ነገር ግን ሁለንተናዊቷ (ዩኒቨርሳሏ) ቤተ ክርስቲያን አትጠፋም፡፡ ድፍረታችን የሚመነጨው ለቃሉ ከመታዘዝ፥ ከንጽሕናና በፍቅር ከመመላለሳችን ነው። በዚህን ጊዜ ማንም ምንም ሊያሸንፈን አይችልም። የእግዚአብሔር መንግሥት የሆነችው ቤተ ክርስቲያንም ሙሉ በሙሉ እንደማትጠፋ እናውቃለን፡፡

የውይይት ጥያቄ ሀ) ከእነዚህ ምንባቦች፥ ስለ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሥልጣን ምን ልንማር እንችላለን? ለ) ስለ ክርስቶስ መንግሥት ኃይል ምን እንማራለን? ሐ) የዚያ መንግሥት አካል ለመሆን ከፈለግን ልንጠነቀቅ የሚገባን ከምንድን ነው? ሕይወትህንና ቤተ ክርስቲያንህን መርምር። ቤተ ክርስቲያን ወደ ሐሰት ትምህርት ልትገባ፥ ንጽሕናዋን ልታጎድፍ ወይም ፍቅርን ልታጣ የምትችለው እንዴት ነው? መ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይህንን ለመከላከል የሚያደርጉት ሚና ምንድን ነው? በቤተ ክርስቲያንህ፥ መሪዎች ይህንን እያደረጉ ናቸው? እንዴት?

  1. ኢየሱስ ስለ ሞቱና ስለ ደቀ መዝሙርነት ኣስተማረ (ማቴ 16፡21-28)

ጴጥሮስ ኣስደናቂ የእምነት ምስክርነት እንደ ሰጠ ሁሉ፥ ኢየሱስ ስለ መጭው ሞቱ ደቀ መዛሙርቱን ያስጠነቅቅ ጀመር። ይህ ሙሉ በሙሉ ደቀ ዛሙርቱ ስለ መሢሑ መንግሥት ከተገነዘቡት ሁሉ የተለየ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ይገሥጽ ጀመር፡ ኢየሱስ ቀን ሰይጣን በጴጥሮስ ንግግር እየተጠቀመ መሆኑን በማስተዋል፥ ሰይጣንን ገሠጸው። ጴጥሮስም ስፍራውን በመዘንጋቱ ተሳስቶ ነበር፡፡ ክርስቶስ የሕያው እግዚኣብሔር ልጅ (መሢሕ) ከሆነ፥ ወደፊት የሚሆነውን የመተንበይ መብት ይኖረዋል። የእግዚአብሔርን አሠራር በምንጠይቅበት ጊዜ ሁሉ ከእርሱ ጋር ያለንን የፍጡርና ፈጣሪ፥ የባሪያና ጌታ ግንኙነት፥ እንዲሁም ክርስቶስ የእግዚአብሔር መንግሥት ገዥ መሆኑን ዘንግተናል ማለት ነው።

ኢየሱስ አሁንም ይህንን ጊዜ በመጠቀም ደቀ መዛሙርቱን አስተምሯል። ደቀ መዛሙርቱ የኢየሱስ ተከታዮች በመሆናቸው ብዙ በረከቶች ያሉት ታላቅ የምድራዊ መንግሥት አካል እንደሚሆኑ ያስቡ ነበር። ይሁን እንጂ በዚህም ጊዜ ሳይቀር፥ ከራስ ወዳድነት አሳቦች አልጸዱም ነበር። ኢየሱስ ስለሚጠብቀው መስቀል ከተናገረ በኋላ፥ እነርሱም የየራሳቸው መስቀሎች እንዳሉባቸው ነገራቸው፡፡ መስቀል የሞት ስፍራ ስለሆነ፣ ኢየሱስ እርሱን የሚከተል ሰው ሁሉ ለመሞት እንደሚገደድ እያመለከተ ነበር። እያንዳንዱ ደቀ መዝሙር ለግል ፍላጎቶቹ ሊሞትና የኃይልና የክብር ጥማቱን ሊጥል ይገባ ነበር። ራስ ወዳድነታችን ወይም በራሳችን መንገድ የመጓዝ ፍላጎታችን ሊሞትና ለጌታችን ልንገዛ ይገባል። የእግዚአብሔር መንግሥት ምሥጢር፥ ከጊዜያዊና ቁሳዊ ምድራዊ ሕይወታችን ይልቅ በራስ ወዳድነት የመጠቀም ፍላጎታችንን መተው ነው፡፡ የዘላለምን ሕይወት የምናገኘው በዚህ ጊዜያዊ ሕይወት ላይ ያለንን ቁጥጥር በመተው ነው። ነገር ግን ጊዜያዊውን ሕይወት ለመቆጣጠር የሚፈልግ ሰው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ያጣል።

የውይይት ጥያቄ:- ሀ) የተሰቀልኽው ወይም የሞትኽው እንዴት ነው? (ገላ 2፡20 አንብብ።) ለ) ብዙ ክርስቲያኖች ይህን እንዲያደርጉ ያልተነገራቸው ለምንድን ነው? ክርስቶስ ለእያንዳንዱ አዲስ ክርስቲያን ስለ መስቀሉ ምን ለማስተማር የሚፈልግ ይመስልሃል? ሐ) በቤተ ክርስቲያንህ እውነተኛ ደቀ መዝሙርነትንና የመስቀሉን ዋጋ እንዴት እንደምታስተምር ምሳሌዎችን በመስጠት ኣስረዳ።

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የመከራ ጊዜ እየመጣ መሆኑን ነገራቸው። ክርስቶስ በቅርቡ የሚሞት ቢሆንም፥ ከመላእክት ጋር በታላቅ ክብር ይመለሳል። በዚያን ጊዜ እያንዳንዱ ሰው ለራስ ወዳድነት ስለ መሞቱ ወይም ለራሱ ስለ መኖሩ ይገመገማል። ከዚያም ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ በቅርቡ የክብሩን ፍንጭ እንደሚመለከቱ ተናግሯል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d