ማቴዎስ 17፡1-27

  1. ኢየሱስ ክብሩን ለጥቂት ደቀ መዛሙርት ገለጠ (ማቴ. 17፡1-13)

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ ከመሞታቸው በፊት የሰው ልጅ በክብሩ ሲመጣ እንደሚያዩት ተናግሮ ነበር፡፡ ይህ የሆነው መቼ ነው? ሁሉም ደቀ መዛሙርቱ ከክርስቶስ ምጽአት በፊት ስለ ሞቱ፥ ይህ ሌላ ነገር የሚያመለክት መሆን አለበት። ምንም እንኳ አንዳንድ ምሑራን ይህ የክርስቶስን ትንሣኤ ወይም የቤተ ክርስቲያንን ጅማሬ እንደሚያመለክት ቢያምኑም፣ ክርስቶስ ለማለት የፈለገው ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ የመንግሥቱን ክብር በተራራ ላይ እንደሚመለክቱ ይምስላል ይላሉ። በተራራው ላይ መለኮታዊ ክብሩን አንጸባርቋል። ተመሳሳይ ወንጌላት ሁሉ ክርስቶስ ይህን ከተናገረ በኋላ፥ በተራራው ላይ እንደ ተለወጠ የሚያመለክተውን ታሪክ ጽፈዋል። ይህም ጸሐፊዎቹ ሁሉ ይህን የተስፋ ቃል ፍጻማ እንደ ተመለከቱ የሚያሳይ ይመስላል።

ኢየሱስ ከሙሴና ኤልያስ ጋር ለምን ተገናኘ? ለዚህ ምክንያቱ ሙሴና ኤልያስ የብሉይ ኪዳን ልዑካን መሆናቸው ነው። ሙሴ ሕግንና ከዘፍጥረት እስከ ዘዳግም ያሉትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ይወክላል። በሲና ተራራ የብሉዩን ቃል ኪዳን እግዚአብሔር የሰጠው ለእርሱ ነበር። ኤልያስ ነቢያትን፥ የተቀሩትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትና የሁሉንም ነገሮች በሚያድስ አካል ይመሰላል (ሚል. 4፡5-6)። ስለሆነም፥ ክርስቶስ ብሉይ ኪዳን በሙሉ ማለትም ሕግና ነቢያት እንዴት በእርሱ እንደ ተፈጸመ አሳይቷል። ሁሉም ወደ ክርስቶስ ቢያመለክቱም ለእርሱ የሚገዙ ናቸው። የክርስቶስ ሞት በብሉይ ኪዳን እንደ ተተነበየ ሁሉ፥ እነ ሙሴ የተሰባሰቡት መፈጸም በሚኖርበት ሞቱ ላይ ለመነጋገር ነበር፡፡

በዚህ አጋጣሚ ክርስቶስ እጅግ ለሚቀርቡት ሦስት ደቀ መዛሙርቱ ስለ መለኮታዊ ባሕርዩና ስለ መጭው ሞቱ ኣስተምሮአል። ይህ ሁሉ በብሉይ ኪዳን ትንቢቶች የተነገረ ነበር። በዚህ ክፍል ውስጥ የክርስቶስ ሞት ሦስት ጊዜ ተጠቅሷል። ይህ እግዚአብሔር አብ ለሁሉም በሚሰማ ድምፅ ክርስቶስ እርሱ የሚወደው ልጁ እንደሆነ ለሁለተኛ ጊዜ የተናገረበት ወቅት ነበር፡፡

  1. ኢየሱስ አጋንንት የነበሩበትን ልጅ ፈወሰ (ማቴ. 17፡14-23)

የክርስትና ሕይወት የተራራና ሸለቆ ገጠመኞችን እንደሚያካትት መግለጽ ይቻላል። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ሕይወታችንን ሁሉ በተራራ ላይ እንድናሳልፍ የሚፈልግ ይመስለናል። ሁልጊዜ እየዘመርን፥ እየጸለይንና እያመለክን እንቆያለን። ከዚህ የበለጠ ምን አለ? ነገር ግን ምንም እንኳ እግዚአብሔር ለልጆቹ አንዳንድ ጊዜ የተራራ ላይ ሕይወት እንዲመሩ ቢያደርጋቸውም፥ እምነታቸው የሚጠናከረውና የሚታየው በሸልቆ ውስጥ ነው። እግዚአብሔርን የምናገለግለው በሸለቆ ስለሆነ፥ እግዚአብሔር ወደ ሸለቆ እንድንመለስ ይፈልጋል።

ኢየሱስ፥ ጴጥሮስ፥ ያዕቆብና ዮሐንስ ከተራራው በወረዱ ጊዜ፥ ወዲያው የሕይወት እውነተኛ ገጽታ ታያቸው። የሕይወት ክብደት፥ መንፈሳዊ ውጊያና የእምነት አስፈላጊነት ጠበቃቸው። የተቀሩት ዘጠኝ ደቀ መዛሙርት ከልጁ አጋንንትን ለማስወጣት ሞክረው ነበር፡፡ ቀደም ሲል አጋንንትን ለማስወጣት የቻሉ ሲሆን፥ አሁን ን አልተሳካላቸውም ነበር። ክርስቶስ አጋንንቱን ካወጣ በኋላ፥ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ስለ መንፈሳዊ ውጊያ አስተማረ። በዚህ ክፍል ሦስት ዐበይት ትምህርቶች ቀርበዋል። በመጀመሪያ፥ ደቀ መዛሙርት አሁን ከሰይጣን ጋር ለነበራቸው ውጊያ በቀደሙት ድሎች መተማመን አላስፈለጋቸውም። በፊት ማሸነፋችን ለአሁኑ ድል ዋስትና አይሰጠንም። ሁለተኛ፣ ኃይሉ የሚወጣው ከእኛ ሳይሆን ከእግዚአብሔር እንደሆነ ማስታወስ አለብን። ለዚህ ነው ሁሉም መንፈሳዊ ጦርነቶች እግዚአብሔር ላይ ሙሉ በሙሉ ጥገኞች መሆናችንን የሚያሳይ ጸሎት ማካተት ያለባቸው። ሦስተኛ፣ ሁሉ መንፈሳዊ ጦርነቶች ተመሳሳይ አይደሉም። አንዳንዶችን በቀላሉ ማሸነፍ ሲቻል ሌሎች ደሞ ረዥምና አስቸጋሪ ውጊያን ይጠይቃሉ። ጦርነቱ የሚካሄደው በአጋንንት ላይ ብቻ ሳይሆን፥ ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ላይ ለመደገፍ ጭምር ነው፡፡ መጾምና በጋራ መጸለይ ልባችንን ከእግዚአብሔር ጋር እንድናስተባብር ይረዳናል። ሙሉ በሙሉ በእርሱ ላይ በምንደፍበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ልናስብ ከምንችለው በበለጠ መንገድ ይሠራል።

አሁንም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ መጭው ሞቱ ነገራቸው። የኢየሱስ አሳብ ሙሉ በሙሉ ባይገባቸውም ኀዘን አጠላባቸው።

  1. ኢየሱስ የቤተ መቅደስን ቀረጥ ከፈለ (ማቴ. 17፡24-27)

ኢየሱስ ለቤተ መቅደስ ቀረጥ እንደከፈለ የሚያስረዳውን ይህንኑ ታሪክ የጠቀሰው፥ ቀራጩ ማቴዎስ ብቻ ነው። ይህ ከ20 ዓመት በላይ የሆናቸው የአይሁድ ዜጎች ሁሉ የሚጠየቁት ቀረጥ ነበር፡፡ ኢየሱስ፥ ጴጥሮስ አሁን የእግዚአብሔር መንግሥት አካል በመሆኑ ከሌሎች፥ የማያምኑ አይሁዶች እንደሚለይ ገለጸለት። ንጉሥ ወይም የንጉሥ ልጅ ከሌሎች ቀረጥ የመሰብሰብ እንጂ፣ የመክፈል ተግባር እንደማይፈጽሙ ሁሉ፥ የሰማዩ መንግሥት ገዥ የሆነው ክርስቶስ፥ የሰማዩ ንጉሥ ልጆች የሆኑት ጴጥሮስና ሌሎች ደቀ መዛሙርት የቤተ መቅደስ ቀረጥ መክፈል አልነበረባቸውም ነበር። ይህ የማያምኑ አይሁዶች ተግባር መሆን ነበረበት፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ሌላም ነጥብ አስተምሯል። ክርስቲያኖች ስለሚገደዱ ላይሆን ለወንጌሉ አላስፈላጊ ጥላቻ ላለማጣት የሚያደርጓቸው ነገሮች አሉ። ስለሆነም፣ በእግዚአብሔር ተአምር የተገኘውን ገንዘብ ኢየሱስና ጴጥሮስ ለሮማ መንግሥት ቀረጥ ከፍለውታል፡፡

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖችን ስለሚያጋጥማቸው መንፈሳዊ ውጊያ፥ አንዳንድ ምሳሌዎችን ልጥ። በቀደምት ድሎች ወይም በራሳችን ብርታት ላይ በምንደገፍበት ጊዜ፥ በአብዛኛው ልንሸነፍ የምችንለው እንዴት ነው? ከክርስቶስ ጋር ያለንን ተገቢ የጥገኝነት ንኙነት በጸሎትና በጾም አማካኝነት የምናሳየው እንዴት ነው? ለ) ክርስቲያን ማድረግ ሳይኖርበት ሌሎችን ላለማስቀየም የሚፈጽማቸውን ተግባራት ምሳሌዎች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: