ማቴዎስ 19፡1-30

  1. ኢየሱስ ስለ ጋብቻና ፍቺ አብራራ (ማቴ. 19፡1-12)

አብዛኞቹ ሰዎች ግልጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትእዛዝ በማይኖርበት ጊዜ፥ በደንቦችና ሕግጋት ለመተዳደር ይፈልጋሉ፡፡ ግልጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትእዛዝ በማይኖርበት ጊዜ፥ «ይህን ላደርግ እችላለሁ?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ይፈልጋሉ፡፡ ሌሎች ከሕይወታቸው ጋር ስለማያዛምዷቸው ሥነ መለኮታዊ እውነቶች ይከራከራሉ፡፡ በኢየሱስ ጊዜ፥ የሃይማኖት መሪዎች ከተከራከሩባቸው ጉዳዮች አንዱ የፍች ጥያቄ ነበር፡፡ በወቅቱ ሁለት ቡድኖች የነበሩ ሲሆን፥ አንደኛው ወገን ፍች በዝሙት ምክንያት ብቻ ሊካሄድ እንደሚችል ያስተምር ነበር። ሁለተኛው ወገን አንድ ሰው ባሻው ምክንያት ሚስቱን ሊፈታ እንደሚችል ይገልጽ ነበር። ሚስቱ ወጥ ካሳረረች ወይም ከእርስዋ የተሻለች ቆንጆ ልጃገረድ ካገኘ ሊፈታት ይችል ነበር።

ኢየሱስ ሕይወትን የሚመለከተው በተለየ ዓይን ነው። ፍሬ በሌላቸው ሥነ መለኮታዊ ክርክሮች ላይ ጊዜውን ለማሳለፍም ሆነ ሰዎች የሚያደርጓቸውን ተግባራት ዝርዝር ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ከተግባራት በስተ ጀርባ ባሉት መርሆዎች ላይ ያተኩር ነበር። ስለሆነም የትኛውም ፈሪሳዊ ከፈልገው በላይ አጥልቆ በመመልከት የጋብቻን ዓላማ መርምሯል። ኢየሱስ ያለዝሙት ምክንያት መፋታት እንደማይቻል የሚያስተምረውን ቡድን አሳብ ቢቀበልም፥ በእግዚአብሔር ፍጹማዊ አሳብ ላይ ትኩረት አድርጓል። እግዚኣብሔር ጋብቻን የፈጠረው ሁለት ሰዎች በሥጋ፣ በአሳብ፥ በልብና በዓላማ አንድ ይሆኑ ዘንድ ነው። ጋብቻን ከዚህ አሳንሶ የሚመለከት ማንም ሰው ከእግዚአብሔር ፍላጎቶችና ፈቃድ ውጭ ይኖራል።

የውይይት ጥያቄ- ሀ) ሦስት አማኞች መልካም ጋብቻ ምን ዓይነት እንደሆነ እንዲገልጹ ጠይቃቸው። በባልና በሚስት መካከል ሊኖር የሚገባው ምን ዓይነት እንኙነት ነው? ለ) በባልና በሚስት መካከል ሊኖር የሚገባው ምርጥ የዕለት ተዕለት እንኙነት ምን ዓይነት ይመስልሃል?

  1. ኢየሱስ ልጆችን ያከብራል (ማቴ. 19፡13-15)

ልጆች ለኢየሱስ አስፈላጊዎች ናቸው? ይህ ታሪክ ኢየሱስ ልጆች በጣም አስፈላጊዎች ናቸው ብሎ እንደሚያስብ በግልጽ ያሳያል። እርሱ ፍቅሩን ለልጆች ለማሳየት ጊዜ አጥቶ አያውቅም። እኛስ? ለዚህ ክፍል ተጨማሪ ማብራሪያ በማቴ. 18፡1-9 ላይ የተሰጠውን አስተያየት አንብብ።)

  1. ኢየሱስን ለመከተል የፈለገ ሀብታም ወጣት ሹም (ማቴ. 19፡16-30)

በክርስትና ሕይወት ከሚያጋጥሙን ዐበይት አደጋዎች አንዱ ከክርስቶስ በላይ ሌላ ነገርን መውደድ ነው። ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ፥ በመዝሙር በማገልገል፥ በመጸለይና በመስበክ ጥሩ ግብረገባዊ ሕይወት ብንመራም፥ የገንዘብ፥ የሰው ወይም የትምህርት የመሳሰለ ሌላ ፍቅር ከልባችን ውስጥ ተሰውር ሊቀመጥ ይችላል። ነገር ግን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን ከፈለግን፥ ከሁሉም በላይ እርሱን ልንወድ ይገባል። ከእርሱ ጋር ያለን ግንኙነት ከየትኛውም ነገር በላይ አስፈላጊ ነው።

ማቴዎስ ይህን እውነት ለማብራራት ምሳሌ ሰጥቷል። ኣንድ ቀን አንድ ሀብታም ወጣት ወደ ኢየሱስ መጣ፡፡ ይህ ወጣት የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት ይችል ዘንድ ኢየሱስ እንድ ትእዛዝ ወይም ቀለል ያለ ነገር እንዲሰጠው ጠየቀ፡፡ ኢየሱስ ሰውዬው ግብረገባዊ ሕይወት እንደሚመራ ያውቅ ነበር። ዐሥርቱን ትእዛዛት በሙሉ እንደ ጠበቀ ሲናገር፥ ኢየሱስ አልጠረጠረውም። ይህ ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ቢመጣ ኖሮ፥ በደስታ ተቀብለን የኳየር ዘማሪ ወይም የሽማግሌዎች ቦርድ አባል እናደርገው ነበር። ግለሰቡ ጥሩ ሰው፣ ቀናተኛና ሀብታም ነበር። ኢየሱስ ግን ከጥሩ ውጫዊ ማንነቱ አጥልቆ ወደ ልቡ ተመለከተ። ለሰውዬው የግል ጣዖት የሆነበት ሌላ ፍቅር ነበረው። ያም የገንዘብ ፍቅር ነበር። ስለሆነም፥ ኢየሱስ ከጣዖቱ እንዲላቀቅ ጠየቀው። “ገንዘብህን ተወውና ደቀ መዝሙሬ ልትሆን ትችላለህ” አለው። ሰውዬው ግን ገንዘቡን በጣም ይወድ ስለነበር፡ አዝኖ ኢየሱስን ትቶ ተመልሶ ሄደ።

ኢየሱስ በሰው ልብ ውስጥ አንድ ተቀዳሚ ፍቅር ብቻ ሊኖር እንደሚገባ አስተምሯል፡፡ ይህም ለእግዚአብሔር የሚኖረን ፍቅር ነው። አንድ ነገር በጣም አስፈላጊ ቢሆንብንና ኢየሱስ ያንን «ተው» በሚለን ሰዓት ፈቃደኞች ባንሆን፥ ነገሩ ጣዖት ይሆንብናል ማለት ነው። ለብዙ ሰዎች እግዚአብሔርን ከሁሉም በላይ እንዳይወዱት የሚቀናቀናቸው ገንዘብ ነው። ለሌሎች ትምህርት ነው። ለምሳሌ፥ ለአብርሃም ልጁ ይስሐቅ ጣዖት ሊሆንበት ይችል ነበር። ለዚህም ነው እግዚአብሔር ይስሐቅን እንዲሠዋለት የጠየቀው። አብርሃም እግዚአብሔርን ከሁሉም በላይ እንደሚወድ በማሳየቱ የጣዖት አደጋ ይሆንበት የነበረ የልጁ ይስሐቅ ፈተና ተወገደለት፡፡)

ወጣቱ ባለጸጋ ከዘላለማዊው ሕይወት ይልቅ ጊዜያዊው ሀብት ስለ በለጠበት ኢየሱስን ላለመከተል መረጠ። በአንጻሩ ጴጥሮስና ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን ለመከተል ሲሉ ዋስትናቸውንና ምድራዊ ሀብታቸውን ሁሉ ወደ ጎን ትተዋል። እንግዲህ ምን ያገኙ ይሆን? ጊዜያዊና ዘላለማዊ ሽልማቶችን ያገኛሉ? ኢየሱስ በዘላለማዊ መንግሥቱ ውስጥ ሥልጣን እንደሚኖራቸው ገልጾላቸዋል። አንዳንድ ምሑራን የደቀ መዛሙርቱ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ መንገሥ፣ በሺህ ዓመቱ ዘመን፥ ደቀ መዛሙርቱ ከክርስቶስ ጋር እንደሚነግሡ ያሳያል ይላሉ። ምናልባትም ይህ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ሥልጣን እንደሚኖራቸው የሚያመለክት ይሆናል፡፡ የዘላለም ሕይወትም ይኖራቸዋል። ሁለተኛ፥ በምድር ላይ ሥጋዊ ቤተሰቦቻቸውን ሊያጡ ቢችሉም፥ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ መንፈሳዊ ቤተሰቦች ይኖሯቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ፍቅራችንን በመካፈል ክርስቲያኖች በሙሉ ልባችን ኢየሱስን እንዳንወድና እንዳንከተል ሊያደርጉ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? ለ) አንዳንድ ጊዜ በልብህ ኢየሱስ እንዳይነግሥ ጣዖት አድርገህ የምታስቀምጣቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ሐ) ልብህን መርምርና ለኢየሱስ ብለህ የምታስወግደው ነገር ካለ ተመልከት፡፡ አሁኑኑ ይህንኑ አድርግ፡፡

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: