የብሉይና አዲስ ኪዳናት ዐበይት ጭብጦች

አንድ የልቦለድ መጽሐፍ ለማንበብ ትፈልጋለህ እንበል። በዚህን ጊዜ የመጽሐፉን የመጀመሪያ ምዕራፍ ብቻ እንዳነበብህ የታሪኩን አጀማመር ልታውቅ ትችላለህ። ታሪኩ እንዴት እንደ ተጠናቀቀ ግን ልታውቅ አትችልም፡፡ ከእያንዳንዱ ምዕራፍ ኣንዳንድ ገጽ ብታነብ ደግሞ ስለ ታሪኩ አጠቃላይ አሳብ ይኖርሃል። ነገር ግን በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙትን ክንዋኔዎች በትክክል ልትረዳ ኣትችልም። ወይም ደግሞ የመጽሐፉን ሁለተኛ ክፍል ብቻ ብታነብ ደግሞ፥ አንዳንድ ነገሮች ለምን በዚያ መንገድ እንደ ተጻፉ ለማወቅ የተለያዩ ጥያቄዎችን ማንሣት ትጀምራለህ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከላይ በተጠቀሰው መሠረት አንድን የልቦለድ መጽሐፍ ስታነብ፥ በኣእምሮህ ውስጥ የሚመጡ ጥያቄዎችን ዘርዝር። ለ) ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ከላይ በተጠቀሰው መንገድ የሚያነቡት ለምንድን ነው? ሐ) ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ለማወቅ በሚፈልጉበት ጊዜ ሙሉውን ታሪክ ካልተረዱ ምን ዓይነት ችግር ሊከሰት ይችላል ብለህ ታስባለህ?

መጽሐፍ ቅዱስ «የእግዚአብሔር ታሪክ ነው»። ይህ ታሪክ እግዚአብሔር ስለ ራሱ፥ ስለ ሰው ልጆችና በሁለቱ መካከል ስላለው ግንኙነት የተናገረበት እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ታዲያ የእግዚአብሔርን ታሪክ በአግባቡ የሚያነቡ ብዙ ክርስቲያኖች አለመኖራቸው ነው። መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል እንዲነበብ በሚፈልገው መንገድ በማንበብ ፈንታ፥ እነርሱ የሚወዷቸውን ክፍሎች ብቻ ያነብባሉ። ከዚህም የተነሣ ብዙ ክርስቲያኖች እጅግ ጠቃሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ገለል አድርገው ይተዋሉ። ይህም ስለ እግዚአብሔርና ከሰዎችም ጋር ስላለው ግንኙነት ግራ የተጋባ ነገር ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል።

አዲስ ኪዳን፥ እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ስለሚያደርገው ግንኙነት መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠን የመጨረሻው ትምህርት ነው። መደምደሚያ እንደ መሆኑ መጠን፥ እጅግ አስፈላጊ የሆነ የታሪኩ ክፍል ነው። እግዚአብሔር ከልጆቹ ጋር የሚያደረገውን ግንኙነት ለማወቅ ከፈለግን በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙትን 27 መጻሕፍት በሚገባ መረዳት አለብን።

በዚህ ጥናታችን በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙትን ዐበይት ትምህርቶች በሙሉ ለመረዳት እንሞክራለን። በተጨማሪም፥ መንፈስ ቅዱስ ለአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ሊያስተላልፍ የፈለገውን መልእክት እንዲገልጥልን እየተማጠንን እያንዳንዱን መጽሐፍ አጠር አጠር አድርገን እንመለከታለን። የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናት ብቻ ሳይሆን ዛሬ በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ ስላለብን፥ የአዲስ ኪዳንን እውነቶች ወስደን ከሕይወታችን ጋር ለማዛመድ እንጥራለን። እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ልባችን ከእርሱ ጋር እንዲዛመድ ሳናደርግ ዝም ብለን ስለ እግዚአብሔር ማጥናቱ ፋይዳ የለውም። ስለሆነም፥ ቃሉን በምናነብበት ጊዜ ሳሙኤል እንዳለው፥ « ባሪያህ ይሰማልና ተናገር » ልንል ይገባል (1ኛ ሳሙ. 3፡9-10)።

ቀጥለህ የጥያቄዎቹን መልስ በደብተር ላይ ጻፍ። የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ከሌለህ ለጥናትህ ስለሚረዳህ መግዛት ይኖርብሃል። አዲሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉምና የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ካሉህ ለጥናትህ ተጠቀምባቸው።

የእያንዳንዱን ዕለት ትምህርት በኣንድ ቀን ለማጠናቀቅ ሞክር። አንዳንዱ ትምህርት ከሌሎቹ ስለሚረዝም፥ ከሳምንታዊ ስብሰባው በፊት ጥናትህን ለማጠናቀቅ በቂ ጊዜ መመደብ ይኖርብሃል። በትምህርቶቹ ውስጥ ኣያሌ የማጣቀሻ ምንባቦች አሉ። «አንብብ» የሚል የተጻፈሳቸውን ጥቅሶች የግድ ማንበብ ይኖርብሃል። እንደዚህ የሚል ማሳሰቢያ የሌለባቸውን ግን ጊዜ ካለህ ብቻ ልታነባቸው ትችላለህ።

የመግቢያ ትምህርቶቹ ስለ አዲስ ኪዳን አንዳንድ ጠቃሚ አሳቦችን ያስጨብጡሃል። ምንም እንኳ እነዚህ አሳቦች አዲስና አስቸጋሪ ቢሆኑብህም፥ ለመረዳት ግን የተቻለህን ጥረት አድርግ። ከዚህ ጥናት ዓላማዎች አንዱ ተማሪው አዲስ ኪዳንን ሙሉ በሙሉ እንዲያነብ መርዳት ነው። ስለሆነም፥ ተማሪው እንዲያነብ የተጠየቀውን ክፍል በሙሉ ማንበብ አለበት። ከእያንዳንዱ ጥናቶች ጋር ተያይዘው የቀረቡት ጥያቄዎች ምን ያህል ግንዛቤህን ለመመዘን የቀረቡ በመሆናቸው ጊዜ ሰጥተህ ስራቸው፡፡

(ማስታወሻ ፡- በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የቀረቡት ታሪኮች ሁሉ መንፈሳዊ እውነቶችን ለማብራራት የተዘጋጁ እንጂ፥ እውነተኛ ገጠመኞች አይደሉም።)

የብሉይና ኣዲስ ኪዳናት ዐበይት ጭብጦች

መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ውስጥ ከሚገኙ መጻሕፍት ሁሉ እጅግ ልዩ መጽሐፍ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ጽፎ ለመጨረስ 500 ዓመታት ፈጅቷል። ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ኦሪት ዘዳግም ያሉት የመጀመሪያዎቹ መጻሕፍት የተጻፉት በ1400 ዓ.ዓ ኣካባቢ ነበር። የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዮሐንስ ራእይ የተጻፈው በ100 ዓ.ም አካባቢ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ የ66 ልዩ ልዩ መጻሕፍት ስብስብ ሲሆን፥ የደራስያኑም ቁጥር ቢያንስ 45 ይሆናል። ከእነዚህ መጻሕፍት መካከል አንዳንዶቹ የታሪክ መጻሕፍት ሲሆኑ፥ ሌሎቹ ደግሞ ግጥሞችን ያካተቱ ናቸው። ለግለሰቦችና ለአብያተ ክርስቲያናት የተጻፉ ደብዳቤዎችም ይገኙባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በረጅም ጊዜ ውስጥና በብዙ ደራስያን አማካይነት የተጻፈ በመሆኑ ብዙ የሚጋጩ አሳቦችና ስሕተቶች ይኖሩታል ብለን ልናስብ እንችላለን፡

ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ በምናጠናበት ጊዜ በውስጡ የሚገኙ መጻሕፍት ሁሉ የሚያስደንቅ የአሳብ ስምምነት እንዳላቸው እንገነዘባለን። ምንም እንኳ እግዚኣብሔር በሰዎች ተጠቅሞ መጽሐፍ ቅዱስን ቢጽፍም፥ ዋንኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ግልጽ ነው። (2ኛ ጴጥ. 1፡20-21 አንብብ።) በ1500 ዓመታት ውስጥ በተጻፉት 66 መጻሕፍት መካከል ያለውን ስምምነት ሊያብራራ የሚችለው ይህ ቃል ብቻ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ በጥሩ ሁኔታ እንደተሠራ የጋቢ ጥለት፥ በውስጡ ከዳር እስከ ዳር እየተጠላለፉ የእግዚአብሔርን ታሪክ የሚያስተሳስሩ ጭብጦች አሉት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በአግባቡ ለመረዳት እነዚህን ጭብጦች ማወቅ አለብን።

የውይይት ጥያቄ፡– ስለ ብሉይና ስለ ኣዲስ ኪዳን ባለህ ዕውቀት መሠረት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ጭብጦች ምን ምን እንደሆኑ ግለጽ።

1 እግዚአብሔር ሁሉን ነገር የሚቆጣጠር ልዑል የሆነ ፈጣሪ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚጀመረው፥ «በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ» በማለት ነው (ዘፍጥ. 1፡1)። የመጽሐፍ ቅዱስ ዐቢይ ጭብጥ፥ የእግዚአብሔር ባሕርይና የዓላማው መገለጥ ነው። እግዚአብሔር የአጽናፈ ዓለሙ (ዩኒቨርስ) ማዕከል፥ ሁሉንም ነገር ወደ ሉዓላዊ ዕቅዱ የሚመራ፥ ሁሉን አዋቂና ሁሉን ቻይ አምላክ ነው። ምንም እንኳ በአጽናፈ ዓለሙ አማካይነት ስለ እግዚአብሔር አንዳንድ ነገሮችን መማር/ማወቅ ብንችልም፥ እግዚኣብሔር ማን እንደሆነ ትክክለኛውን ማረጋገጫ የምናገኝው ከዘፍጥረት እስከ ራእይ በሚገኙት ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ነው። እግዚአብሔር ልጁን ወደዚህ ምድር በላከው ጊዜ ራሱን እንደገለጠ፥ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ሰዎች ክርስቶስን በሚመለከቱበት ጊዜ እግዚአብሔር አብን በማየት፥ የእግዚአብሔርን ባሕርይ ይበልጥ ፍጹም በሆነ መንገድ ይረዱታል (ዮሐ 14፡8-11፤ ዕብ. 1፡1-3)። ይህም ሆኖ፥ ብዙዎች ነገሩ አልገባቸውም ነበር።

አንዳንድ ጊዜ ሰይጣን እግዚአብሔር እኛን ማገልገል ይገባዋል ብለን እንድናስብ ያደርገናል። ሰው ከምንም ነገር በላይ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ስለሚገባ፥ እግዚአብሔር ፍላጎታችንን ማሟላት አለበት ብለን እናስባለን። መጽሐፍ ቅዱስ ግን እግዚአብሔር የእውነት ሁሉ ማዕከል እንደሆነና ሰዎች እግዚአብሔርን ማገልገል እንደሚገባቸው በግልጽ ያስተምረናል። እርሱ ፈጣሪ፥ እኛ ደግሞ ፍጥረቱ ነን። ጳውሎስ እንዳለው፥ እኛ የተፈጠርነው እርሱን ለማክበር ነው (1ኛ ቆሮ. 10፡31፤ ኤፌ. 1፡11-12፤ 3፡20-2)። መጽሐፍ ቅዱስ አሁን ያለውን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር እንደ ፈጠረና እርሱ ብቻ ያልተፈጠረ አምላክ እንደሆነ ያስረዳል። በዘፍጥረት 1-2 ላይ ስለ መጀመሪያው ፍጥረት እናነባለን። ዘፍጥረት 3 ስለ ሰው ልጅ ዓመፅ ቢገልጽም፥ እግዚአብሔር ግን የፈጠረውን ዓለም ለመቆጣጠር አልተሳነውም። ነገሮችን ከፍና ዝቅ እያደረገ ታሪክን በመቆጣጠር ላይ ይገኛል (ኢሳ. 5፡26፤ 40፡15-17)። እግዚአብሔር የነገሥታትን ልብ ያንቀሳቅሳል (ምሳሌ 21፡1)። እርሱ የታሪክን ፍጻሜ ወስኖአል። እግዚአብሔር በእርሱ ላይ የሚያምፁትን ሁሉ እንዴት እንደሚያንበረክካቸው ከራእይ መጽሐፍ እንመለከታለን። ይህንን ዓለም ከፍጻሜ ካደረሰ በኋላ፥ ፈቃዱ ብቻ የሚከናወንበትን ዓለም ፈጥሯል። እግዚአብሔር የሁሉም ተቆጣጣሪና የነገሮችንም ፍጻሜ የወሰነ አምላክ በመሆኑ፥ ወደፊት የሚከሰተውን ነገር ልንለውጥ አንችልም። ነገር ግን የዘላለማዊ መንግሥቱ አካል እንሆን ዘንድ ፈቃዳችንን ከፈቃዱ ጋር እንድናስማማ ያሳስበናል። አሁን የምናደርገው ውሳኔ የዘላለም ዕጣ ፈንታችንን ይወስነዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ምንም ያህል ክፉ ቢመስልም እንኳ፥ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ነገሮችን እንደሚቆጣጠር ማስታወስ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

2 እግዚአብሔር ከሰው ጋር ያለው ግንኙነትና የዓለም በኃጢአት መበከል፡- የትም ብንሄድ ዓለም በኃጢአት ተበክላ እናገኛታለን። በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚገድሉ እንደ ኤድስ ያሉ በሽታዎች አሉ። እንደ ድርቅና ጎርፍ የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎችም የእግዚአብሔርን ፍጥረት ሰላም በመንሳት ላይ ናቸው። በአገሮች፥ በሕዝቦችና በጎሳዎች መካከል መከፋፈልና ጦርነት በመቀስቀሱ ምክንያት በሺህ የሚቆጠሩ ወገኖች ሕይወት እየተቀጠፈ ነው። እነዚህ ሁሉ ከየት መጡ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሁለተኛው የኃጢአት ጭብጥም ይነግረናል። በዘፍጥረት 3 ላይ እንደተናገረው፥ እነዚህ ሁሉ ችግሮች የተከሰቱት በአዳምና በሔዋን ኃጢአት ምክንያት ነው። ጳውሎስ በሮሜ 5፡12-13 ላይ እንደተናገረው፥ ከአንዱ ሰው ከኣዳም የተነሣ ኃጢአትና ሞት በሰዎች ሁሉ ላይ ደረሰ። ይህ በአዳምና በሔዋን የተጀመረው የዓመፀኛነት መንፈስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተንጸባርቋል። የአዳምና ሔዋን ልጆችም የኃጢአትን መንገድ ተከተሉ፤ ከዚያም ቃየን አቤልን ገደለ። ከጥፋት ውኃ በፊት ዓለም ሁሉ በዓመፅ ስለ ተበላሸች የጥፋት ውኃ ጠርጎ ወሰዳቸው። የተመረጡት የእስራኤል ሕዝብ እንኳ ሐሰተኞች ጣዖታትን እየተከተሉ በእግዚአብሔር ላይ ማመፃቸውን ቀጠሉ። ይህ የዓመፅ መንፈስ ወደ አዲስ ኪዳንም ዘልቋል። ጳውሎስ ራሱ ለማድረግ የሚፈልጋቸውን መልካም ነገሮች ለማድረግ ባለመቻሉ ኃጢአት እንደሠራ ተናግሯል (ሮሜ 7፡7-25)። ስለሆነም ሰዎች ሁሉ በቅዱስ እግዚአብሔር ላይ የሚያምፁ ኃጢአተኞች እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ያብራራል። ስለዚህ ሁላችንም ዘላለማዊ ሞት የሚገባን ሰዎች ነን። እያንዳንዳችን በአሳባችን፥ በአመለካከታችንና በተግባራችን ስለምናምፅ፥ ይህ የተባለው ሁኔታ በሕይወታችን ውስጥ መኖሩን እንገነዘባለን። የእግዚአብሔር ልጆች ብንሆንም እንኳ ኃጢአት የሕይወታችን ክፍል ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረታት ቤተ ክርስቲያን ለእርሱ ያላት ፍቅር ሲቀዘቅዝ ከኃጢአተኛነት ጋር ትታገላለች። በራእይ 2-3፤ ቤተ ክርስቲያናት ከኃጢአት መንገዳቸው ካልተመለሱ ክርስቶስ እንደሚፈርድባቸው በመግለጽ አስጠንቅቋቸዋል። በራእይ 20-22 ላይ እግዚአብሔር ስለ ታሪኩ ፍጻሜ ተናግሯል። በዚህ ክፍል ኃጢአት፥ ሞት፥ ሰይጣንና በእግዚአብሔር ላይ ያመፁ ሁሉ እንደሚጠፉ ተገልጾአል።

ኃጢአትን በተመለከተ፥ የእግዚአብሔር ባሕርይ ሁለት ተቃራኒ ምላሾች አሉት። አንደኛው፥ እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ከኃጢአት የተለየ ቅዱስ አምላክ ስለመሆኑ ነው። ይህም ቅዱስና ጻድቅ በመሆኑ ዓመፀኞችን እንዲቀጣ ያደርገዋል። ሁለተኛው፥ እግዚአብሔር በፍቅር፥ በምሕረትና በጸጋ የተሞላ አምላክ ነው። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር ሰዎች ከዓመፃቸው ተመልሰው ይቅርታ የሚያገኙበትን መንገድ ያዘጋጃል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ በዓለም ውስጥ የኃጢኣትን ውጤቶች ስለምትመለከትበት ሁኔታ ግለጽ። ለ) ይህ የኃጢአትና ዓመፅ ዝንባሌ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታየው እንዴት ነው? ሐ) እግዚአብሔር አንድ ቀን በአዳምና በሔዋን ኃጢአት ምክንያት የመጡትን ክፉ ነገሮች ሁሉ እንደሚያስወግድ ማወቅህ እንዴት ያበረታታሃል?

3 በኃጢኣት በተሞላ ዓለም ውስጥ እግዚአብሔር አሁንም ሰዎችን ለራሱ መምረጡን ቀጥሎበታል። አንድ አስደናቂ እውነት፥ እግዚኣብሔር ሁልጊዜ በእርሱና በሕዝቡ መካከል የነበረውን ግንኙነት ለማደስ መፈለጉ ነው። እግዚአብሔር የፍቅር፥ የምሕረትና የጸጋ አምላክ ነው። በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ አዳምና ሔዋን ኃጢኣት ሠርተው በሚሸሹበት ጊዜ እግዚአብሔር ሲፈልጋቸው እንመለከታለን (ዘፍጥ. 3፡8-9)። ከአብርሃም እስከ አዲስ ኪዳን ዘመን ድረስ፥ እግዚኣብሔር እስራኤላውያን የእርሱ ሕዝቡ እንዲሆኑለት ሲመርጣቸው እንመለከታለን። ሕዝቡ ሁሉ ከራሱ ጋር ግንኙነት እንዲኖረው ስለሚፈልግ፥ እስራኤላውያን የኣሕዛብ ብርሃን እንዲሆኑ ፈልጎ ነበር (ኢሳ. 42፡6)። የሚያሳዝነው ግን እስራኤላውያንም እንደ አዳምና ሔዋን በማመፃቸው፥ በእነርሱ አማካይነት ኣሕዛብን ወደ እውነተኛው አምላክ ለማምጣት የነበረው ዓላማ ሳይፈጸም ቀረ። በአዲስ ኪዳን መጀመሪያ ላይ፥ እግዚአብሔር ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ዓለም እንደ ላከው እናነባለን። ክርስቶስ የጠፉትን ሊፈልግና ሊያድን ወደ ዓለም እንደ መጣ ገልጾአል (ሉቃስ 19፡10)። የክርስቶስ ሞት ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች የሚሆኑበትን በር ወለል አድርጎ ከፍቷል። ክርስቶስ ወደ ሰማይ የተመለሰው «ቤተ ክርስቲያን» በሚል ስያሜ የሚጠሩትን አዲስ ሕዝብ ከፈጠረ በኋላ ነበር። በክርስቶስ ያመኑ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል ሆነዋል። ከዚያም የእግዚአብሔር ተወካዮች በመሆን ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ ይመሰክራሉ (2ኛ ቆሮ. 5፡18-19)። የሚያሳዝነው ታዲያ ቤተ ክርስቲያንም በኃጢአት ስለ ተተበተበች ወንጌሉን ወደ ጠፉት ለመውለድ ሲሳናት ማየት ነው። ከዚህ ድካም ባሻገር፥ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያኑን መገንባቱን ቀጥሏል። በዓለም ዙሪያ ብዙ ሰዎች በክርስቶስ አማካይነት እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ እየመጡ ናቸው። በመጨረሻው ዘመን ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔር በፈለገው መንገድ እርሱን በእውነትና በመንፈስ እንደሚያመልኩት የዮሐንስ ራእይ ይነግረናል። አንድ ቀን እግዚአብሔር ኃጢአትንና ፍሬዎቹን ሁሉ በማስወገድ፥ ሰዎች በእርሱ ላይ የማያምፁበትን ዘመን ያመጣል (ራእይ 7፡9፥ 21፡4)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ቤተ ክርስቲያን ብዙውን ጊዜ ክርስቶስ በማቴዎስ 28፡19-20 የሰጠውን ተልእኮ ለመፈጸም ያልቻለችው ለምንድን ነው? ለ) የክርስቶስን ትእዛዝ ለመፈጸም የአንተ ቤተ ክርስቲያን ምን እያደረገች ነው? ሐ) እንተስ ይህንን ትእዛዝ ተግባራዊ ለማድረግ ምን እያደረግህ ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

5 thoughts on “የብሉይና አዲስ ኪዳናት ዐበይት ጭብጦች”

  1. Mulugete Sileshi Zaro

    ትምህርቱን ለመማርና ለመቀጠል ፈሌግያለው ነገር ግን መልሱን ሰጭን አይቀበልም ምን ላድርግ

    1. ወንድሜ ሙሉጌታ፣

      ለተፈጠረው ችግር ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ ተጨማሪ መረጃ ብትሰጠን ችግሩን ለመፍታት እንሞክራለን፡፡ የትኛውን ጥናት እያደረክ ሳለ ነው መልሱን ለመጫን የተቸገርከው? (መልስህን፣ ለምሣሌ የንጉሡ የኢየሱስ ልደት (ማቴ. 1፡18-2፡23) ብለህ ልትልክልን ትችላለህ፡፡

      የጌታ ኢየሱስ ጸጋ ይብዛልህ!
      አዳነው ዲሮ
      tsegaewnet@gmail.com

  2. እጅግ በጣም አስፈላጊ እና ጠቃሚ ሥራ ነው። እግዚአብሔር አገልግሎታችሁንና ዘመናችሁን ይባርክ።

Leave a Reply to tsegaewnetCancel reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading