የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ወንጌልን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ እንዲስፋፋ የሚያደርገው ምንድን ነው? ለ) ወንጌል በኢትዮጵያ ውስጥ በፍጥነት እንዳይስፋፋ የሚያደርገው ምንድን ነው? ሐ) ኢትዮጵያውያን ወንጌልን ወደ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዳይወስዱ የሚከለክላቸው ምንድን ነው?
እግዚኣብሔር የሮም አገዛዝ እስኪመጣ ድረስ፥ ልጁን ወደዚህ ምድር ለመላክ ጊዜ ሲጠብቅ እንደ ነበር ቀደም ብለን ተመልክተናል። እግዚአብሔር ልጁን በፋርስ ወይም በግሪክ ዘመን መላክ ይችል ነበር፤ ዓለም ግን ዝግጁ አልነበረችም። በመጨረሻውም በሮማውያን ዘመን የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ ለሆነው መሢሕ መምጣት ነገሮች ተስተካክለው ነበር። በሮም የአገዛዝ ዘመን ቤተ ክርስቲያን በሁለት ትውልድ ዘመን ውስጥ፥ ከሕንድ እስከ ሰሜን አፍሪካና ከዚያም እስከ ታላቋ ብሪታኒያ ድረስ ለመስፋፋት ችላለች። ለመሆኑ እግዚአብሔር ይህንን ጊዜ ሲጠብቅ የነበረው ለምንድን ነው?
1. ፖለቲካዊ መረጋጋት፡- በደርግ ጨቋኝ አገዛዝ ወቅት ወንጌልን ማሰራጨት ከባድ እንደነበረ ሁሉ፥ በአንዲት አገር ውስጥም ሆነ በአገሮች መካከል ፖለቲካዊ መረጋጋት ከሌለ ወንጌልን ለማስፋፋት አስቸጋሪ ነው። በመካከለኛው ምሥራቅና በምዕራቡ ዓለም ታሪክ፥ የሮምን ኣገዛዝ ያህል የተረጋጋና ለረዥም ጊዜ የቆየ መንግሥት የለም። ክርስትና በተስፋፋባቸው አገሮች ሁሉ የሮም መንግሥት ከ1000 ዓመት በላይ ኃያል ሆኖ ሲገዛ ቆይቷል። ከሕንድ ጀምሮ እስከ እስፓኝ፥ ከዚያም እስከ ታላቋ ብሪታኒያና ሰሜን ኣፍሪካ ድረስ፥ አንድ መንግሥት ብቻ ነበር። ይህም እንደ ጳውሎስ ያሉ አገልጋዮች የቪዛ፥ ፓስፖርት፥ ወይም ሌሎች የመንግሥት ደንቦች ሳያግዷቸው በቀላሉ እንዲንቀሳቀሱ ረድቷቸዋል። ምንም እንኳ በሮም መንግሥት ውስጥ ተተኪው ንጉሥ ማን ይሆን? በሚለው ጥያቄ ላይ ብርቱ ፍጭት ቢኖርም፥ በጥቅሉ ሲታይ ግን፥ በሮም ግዛት ሁሉ አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ ነበር።
2. ባህላዊ ተመሳሳይነት፤ ከ300 ዓመት በላይ የግሪክ ባህል በኦውሮፓና በመካከለኛው ምሥራቅ ተስፋፍቶ ቆይቷል። ግሪኮች ጎይልን ሳይጠቀሙ ሰዎች የግሪክን ቋንቋ እንዲናገሩ፥ በከተሞች ውስጥ እንዲኖሩ አበረታተዋቸዋል። ሮማውያን ሥልጣን ሲይዙ የራሳቸውን ባህልና ቋንቋ በሕዝቡ ላይ ከመጫን ይልቅ፥ የግሪክን ባህልና ቋንቋ መቀጠሉ እንደሚቀል ተገነዘቡ። በአሁኑ ጊዜ የምዕራቡ ዓለም ባህላዊ እሴቶች በትምህርትና በመገናኛ ብዙኀን አማካይነት ሰዎችን አንድ እያደረጉ ከመሆኑ በስተቀር፥ በታሪክ ውስጥ የባህል ተመሳሳይነት ጎልቶ የታየበት እንደዚህ ያለ ዘመን አልነበረም። ብዙ ባህላዊ ልዩነቶች (ለምሳሌ፡- አማራና አፋር፥ ወላይታና ገለብ) በሚታዩበት ጊዜ ወንጌልን ማሰራጨት አስቸጋሪ ስለሆነ፥ ይህ የባህል ተመሳሳይነት ወንጌል በቀላሉ በሮም ግዛት ውስጥ እንዲሰራጭ የበኩሉን እገዛ አድርጓል።
3. ቋንቋ፡- ለወንጌል መስፋፋት ከፍተኛ መሰናክል ከሚሆኑ ነገሮች አንዱ የቋንቋ ልዩነት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ወንጌላውያን ከእንዱ ስፍራ ወደ ሌላው በሚሄዱበት ጊዜ፥ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በቋንቋ ለመግባባት ይቸገራሉ። በኣስተርጓሚ ለመጠቀም ቢፈልጉ እንኳ አንዳንዴ የእሳብ መዛባትን የሚያስከትል ይሆንባቸዋል። ወይም ረዥም ጊዜ ወስደው ቋንቋውን ይማራሉ። ነገር ግን በክርስቶስና በደቀ መዛሙርቱ ዘመን፥ በሮም ግዛት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሁሉ አንድ ቋንቋ ይናገሩ ነበር። ስለሆነም ሐዋርያትና ወንጌላውያኑ በሚሄዱበት ስፍራ ሁሉ ከሰዎች ጋር በግሪክ ቋንቋ ይግባቡ ነበር።
4. የአዲስ ኪዳን ጽሑፎች፡- ሳይንቲስቶች እንደሚናገሩት ሰዎች ከሚሰሙት ነገር ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነውን በፍጥነት ይዘነጋሉ። ብዙውን ጊዜ በቃል ከኣንዱ ሰው ወደ ሌላው ሰው የሚተላለፉ መልእክቶች፥ ስሕተት የማይጠፋባቸው ለዚህ ነው። እግዚአብሔርም ይህንን በመገንዘብ፥ ሰዎች የማይለወጥና ዘላለማዊ ቃል ይዘው የሚቆዩበትን መንገድ አዘጋጀ። ሐዋርያት በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ የቅዱሳት መጻሕፍት አስፈላጊነት እየጨመረ ሄደ። ነገር ግን በምን ቋንቋ ቅዱሳት መጻሕፍትን ይጻፉ? የሮም የሥራ ቋንቋ የነበረውንና ምሁራን የሚጠቀሙበትን ላቲን ይምረጡ? የጳለስቲና ነዋሪዎች ቋንቋ የነበረውን ሐዋርያቱ አፋቸውን የፈቱበትን የአረማይስጥ ቋንቋ ይምረጡ? ይህን ሊያደርጉ አይችሉም። ዋናው ነገር የቋንቋው ክብር አይደለም። እግዚአብሔር የሮም መንግሥት ዓለምን በግሪክ ቋንቋ አማካይነት አንድ እንዲያደርግ በመርዳት፥ አዲስ ኪዳን በግሪክ ቋንቋ የሚጻፍበትን ሁኔታ አመቻቸ። ይህም በሮም ግዛት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በመተርጎም ጊዜ ሳያባክኑ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያነቡ አስችሏቸዋል።
5. ትምህርት፡- ቤተ ክርስቲያን እንድትጠነክር ከተፈለገ ምእመናን በየእሑዱ የሚቀርበውን ስብከት መስማት ብቻ ሳይሆን፥ ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብ አለባቸው። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚነጋገርበት እጅግ አስፈላጊው መንገድ ቃሉ ነው። ነገር ግን ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ለማንበብ ይችሉ ዘንድ ከመሃይምነት መላቀቅ አለባቸው። በታሪክ ውስጥ እንደታየው ማንበብ የሚችሉት ሀብታሞች ብቻ ነበሩ። ተራው ሰው ማንበብ አይችልም ነበር። በአዲስ ኪዳን ዘመን ግን ግሪኮች ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ይሰጡ ስለነበር፥ ብዙ ሰዎች ማንበብ ይችሉ ነበር። ከዝቅተኛ መደብ የመጡ ቢሆኑም እንኳ፥ አብዛኞቹ የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ምእመናን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ይችሉ ነበር። ቤተ ክርስቲያን ማንበብ በሚችሉ ጥቂት ሰዎች ላይ ብቻ መደገፍ አላስፈለጋትም። ቤተ ክርስቲያን አምልኮዋን የምታካሂደው በግለሰብ ቤቶች በመሆኑ፥ ለእያንዳንዲ ቤተ ክርስቲያን ማንበብ የሚችሉ ሰዎች ይመደቡ ነበር። ይህም የክርስቶስን ትምህርቶች ይበልጥ እንዲረዱ አድርጓቸዋል።
6. ጉዞ፡- የፋርስ፥ የግሪክና የሮም መንግሥታት ዐቢይ ከተሞችን የሚያገናኙ መንገዶችን በመሥራት ረገድ እኩል አስተዋጽኦ አድርገዋል። በሮማውያን አገዛዝ ዘመን ሰዎች በመንገዶችና በመርከብ በመጠቀም ወደ ፈለጉበት አገር መሄድ ይችሉ ነበር። ይህ እንደ ጳውሎስ ላሉ ሰዎችና ወንጌልን በየስፍራው ለሚሰብኩ ልዑካን በጣም ጠቃሚ ነበር።
7. ከተሞች፡- ግሪኮች፥ ከተሞች የትምህርትና የሥልጣኔ ምንጭ ናቸው ብለው ያምኑ ነበር። መላው ሕዝባቸው እንደ አዲስ አበባ ባሉ የከተማ ግዛቶች የሚተዳደር ሲሆን፥ የራሱ አስተዳደራዊ አውራጃ ሆኖ ያገለግል ነበር። ሮማውያንም ክልላዊ ሥልጣን በመስጠት የነዚህን ከተሞች ዕድገት አግዘዋል። ምሑራን በአዲስ ኪዳን ዘመን አብዛኛው ሕዝብ በከተሞች ውስጥ ይኖር እንደነበር ያምናሉ። ይህም ወንጌላውያን በታላላቅ ከተሞች ውስጥ ወንጌልን ለመስበክ ዕድል በማግኘታቸው፥ ለወንጌል መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ሰዎች በትምህርት ቤቶች ወይም በገበያ ቦታዎች እየተገናኙ ስለሚነጋገሩ፥ ወደ ከተሞች የመጣ አዲስ ዜና በቀላሉ እንደሚሰራጭ ግልጽ ነው። የገጠር ሰዎችም ወደ ከተማ ለገበያ በሚወጡበት ጊዜ ዜናውን ይዘው ይመለሳሉ። ቤተ ክርስቲያን በመጀመሪያው ምእተ ዓመት በከፍተኛ ፍጥነት እንድታድግ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ይሄ ነበር። –
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ሰባት ነገሮች የወንጌልን ስርጭት እንዴት እንደሚያግዙ አብራራ። ለ) የዛሬውን ዓለም ከክርስቶስ ዘመን ጋር በማነጻጸር ልዩነቱንና ተመሳሳይነቱን እስረዳ። ሐ) ዛሬ ወንጌል ለማሰራጨት ከዚያን ዘመን ይልቅ ይቀላል ወይስ ይከብዳል? አሳብህን አብራራ።
ከእግዚአብሔር ሉዓላዊ ዕቅድና ለሕዝቦች ካለው ፈቃድ የተነሣ፥ ክርስትና በሮም አገዛዝ ተወልዶ በፍጥነት አደገ። በመጀመሪያው ምእተ ዓመትና፥ በ70 ዓ.ም. ኢየሩሳሌምም ከፈረሰች በኋላ የሮም መንግሥት ለአይሁድ ሃይማኖት ትልቅ ግምት ሰጥቶ ነበር። የአይሁድ ሃይማኖት ሕጋዊ በመሆኑ፥ በተከታዮቹ ላይ ስደት አይደርስም ነበር። ከዚህም በተጨማሪ፥ ሮማውያን በሌሎች ሕዝቦች ላይ የሚጭኗቸውን የኣሕዛብ ሃይማኖታዊ ትምህርት በአይሁዶች ላይ ተግባራዊ እንዲሆኑ አይፈቅዱም ነበር። ክርስትናም የይሁዲነት አካል ተደርጎ በመወሰዱ፥ ከሮማውያን ይፋዊ ስደት ለመትረፍ በቅቷል።
በበዓለ ኀምሳ ዕለት ቤተ ክርስቲያን በኢየሩሳሌም ከተማ ተጀመረች (የሐዋ. 2)። በመጀመሪያዎቹ 20 ወይም ከዚያ በላይ ዓመታት፥ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አባላት ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል፥ አይሁዶች ነበሩ። የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ክርስትና ከተለመደው የአይሁዳውያን እምነት የተለየ መሆኑን ተረድተው ነበር። ስለዚህ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የጥንት ክርስቲያኖችን እንቅስቃሴ ለማገድና እነርሱንም ለማሳደድ ይጥሩ ነበር። በመጀመሪያዎቹ 40 የከርስትና ዓመታት ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ዋነኛ አሳዳጆች አይሁዶች ነበሩ። ነገር ግን ብዙ አይሁዶች ክርስትናን እንደ አዲስ ሃይማኖት ስላላዩት አንዳንዶች ነገሩን ለመቀበል ፍላጎት ሲያድርባቸው፥ ሌሎች ደግሞ ነገሩን ታግሠው በአክብሮት ይመለከቱት ነበር።
እንደ ሮማውያን ያሉ የውጭ ሰዎች በክርስትናና በይሁዲነት መካከል የጎላ ልዩነት ስላልታያቸው፥ ክርስቲያኖችን ለማሳደድ አልሞከሩም። ሮማውያን ክርስትና ከይሁዲነት የተለየ መሆኑን ተረድተው ማሳደድ የጀመሩት፥ ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተች ከሠላሳ ዓመት በኋላ ነበር። በመጀመሪያው ምእተ ዓመት መጨረሻ አካባቢ፥ ሮማውያን በክርስትና ላይ መደበኛ ስደት በመቀስቀለ ክርስትና ሕገ ወጥ ሃይማኖት መሆኑን አወጁ።
በመጀመሪያ በክርስቲያኖችና በሮም ባለሥልጣናት መካከል የነበረው ግንኙነት የጠበቀ አልነበረም። ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ አውግስጦስ ቄሣር (30 ዓ.ዓ. -14 ዓ.ም.) አገረ ገዥ ነበር (ሉቃስ 2፡1)። ክርስቶስ አገልግሎቱን በጳለስቲና ሲጀምር ደግሞ፥ ጢባርዮስ ቄሣር (14-37 ዓ.ም.) አገር ገዥ ሆኖ ይሠራ ነበር (ሉቃስ 3፡1)። በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ዘመን ይገዛ የነበረውና የንጉሦችን አምልኮ የጀመረው ጋይዮስ ካሊጉላ ነበር (37-41 ዓ.ም.)። ካሊጉላ በቤተ መቅደሱ ውስጥ እርሱ የሚመለክበት መሠዊያ እንዲታነጽ ሲያደርግ፥ ክርስቲያኖች ማዘናቸው አልቀረም ነበር። በንጉሥ ቀላውዴዎስ ዘመን (41-54 ዓ.ም) በሮም በሚኖሩ ክርስቲያን ባልሆኑ አይሁዶችና ክርስቲያን በሆኑ አይሁዶች መካከል ብጥብጥ የተከሰተ ይመስላል። ይህም ቀላውዴዎስን ስላስቆጣው፥ አይሁዶችን ከሮም አባረራቸው። አቂላና ጵርስቅላ ወደ ቆሮንቶስ የሄዱት በዚህ ጊዜ ነበር (የሐዋ. 18፡2)።
ክርስቲያኖች ከአይሁዶች ይበልጥ እየተለዩ ሲመጡ፥ ብርቱ ስደት ይደርስባቸው ጀመር። በኔሮ ዘመን (54-68 ዓ.ም) ነገሮች ይበልጥ እየከፉ መጡ። ኔሮ በሮም ትልቅ ቤተ መንግሥት ለማሠራት ይፈልጋል የሚል ወሬ ተሰማ። ስለዚህ በተወሰነው የከተማይቱ ክፍል ላይ እሳት ለቀቀበት። እሳቱ ከቁጥጥር ውጭ በመውጣቱ ከሮም ከተማ ብዙው ክፍል ወደመ። ሕዝቡ በቁጣ ይነሣብኛል ብሎ የፈራው ኔሮ፥ አደጋውን ብዙም ከማይታወቁ ክርስቲያኖች ጋር አያያዘው። ብዙ ክርስቲያኖች ታድነው እንዲገደሉ አደረገ። ይህ ስደት በግዛቱ ሁሉ የተከሰተ ሳይሆን፥ በሮም ከተማ ብቻ የተደረገ ነበር።
በተከታዮቹ ሠላሳ ዓመታት ውስጥ ስለ ክርስቲያኖች አኗኗር ሁኔታ የምናውቀው ምንም ነገር የለም። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መሪዎች ካደረሱት ስደት በቀር የሚነግረን ሌላ መረጃ የለም። ይህ ግን ዶሚቲያን (81-96 ዓ.ም.) የንጉሥ ነገሥትነቱን ሥልጣን ሲረከብ ተለውጧል። ዶሚቲያን የሮምን ሃይማኖት ለማስፋፋት ዕቅድ ስለ ነበረው፥ እያረጁ የሄዱትን ቤተ መቅደሶች ማደስ ጀመረ። ከዚያም ሕጋዊ ባልሆኑ ሃይማኖቶች ላይ ጫና አሳደረ። በሮም ንጉሥና በክርስቲያኖች መካከል ችግር የተነሣው ሰዎች እርሱን እንደ አምላክ ቆጥረው መሥዋዕት እንዲያቀርቡለት ባዘዘ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። ይህ እስከዚህ ጊዜ ድረስ ሰዎች በፈቃደኛነት የሚያከናውኑት የነበረ ተግባር ነበር። ክርስቲያኖች ይህን አናደርግም በማለታቸው ምክንያት፥ የተቀሰቀሰው ስደት ምን ያህል እንደተስፋፋ ኣናውቅም። የምናውቀው ነገር ቢኖር በዚህ ጊዜ ሐዋርያው ዮሐንስ በስደት ወደ ፍጥሞ ደሴት እንደተላከ ብቻ ነው (ራእይ 1፡9)። ነገሥታትን ማምለክ የተለመደ በሆነባት በትንሿ እስያ ስደቱ ሳያይል አልቀረም። ብዙ ምሑራን ዮሐንስ በራእዩ ውስጥ ክርስቲያኖችን ስለ መጭው ስደት እያስጠነቀቃቸው እንደነበረ ያምናሉ።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)