የአራቱ ወንጌላት መግቢያ

ወንጌላት እንዴት ተጻፉ?

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በአማርኛ «ወንጌል» ማለት ምን ማለት ነው? ለ) «የምሥራች» ማለት ምን ማለት ነው? የምሥራች ከሚባሉ ነገሮች አንዳንዶችን ዘርዝር። ሐ) የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የመጀመሪያዎቹን አራት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት «ወንጌላት» ብለው የሰየሙት ለምንድን ነው? (ማር. 1፡1 አንብብ።) መ) ወንጌል ማለት ምን ማለት እንደሆነ በራስህ አገላለጽ ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።

የመጀመሪያው የአዲስ ኪዳን ክፍል ስለ ክርስቶስ ሕይወት የሚናገሩ አራት መጻሕፍት የሚገኙበት ነው። የጥንት ክርስቲያኖች እነዚህን መጻሕፍት ወንጌል በማለት ጠርተዋቸዋል። «ወንጌል» ማለት «የምሥራች» ማለት ነው። ወንጌል ከሚለው የግእዝ ቃል ይልቅ «የምሥራች» ወይም ብስራት የሚለው የተሻለ ይሆናል።

የጥንት ክርስቲያኖች እነዚህን የመጀመሪያ አራት መጻሕፍት ወንጌል ብለው የጠሩበት ምክንያት፥ እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ አንድ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሰው ልጆች ኃጢአት መሥዋዕት እንዲሆንና የሰዎችንም የሞት ፍርድ ዕዳ እንዲከፍል የላከው መሆኑን የሚናገሩ መልካም ዜናዎች በመሆናቸው ነው (2ኛ ቆሮ. 5፡21)። የእግዚአብሔር ልጅ በሰዎች መካከል በመኖር የእግዚአብሔርን ባሕርይና ሕዝቡ እንዲኖሩ የሚፈልገውን ሕይወት አሳይቷቸዋል (ዮሐ. 1፡14)። ክርስቶስ ሞትን ካሽነፈና በእኛም ምትክ ያቀረበውን መሥዋዕት እግዚአብሔር እንደተቀበለው ካረጋገጠ በኋላ፥ ከሞት በመነሣት ወደ ሰማይ አርጓል። በክርስቶስና በማዳኑ የሚያምኑ ሰዎች ለእርሱ እየተገዙ መኖር አለባቸው። የኃጢአት ይቅርታ ካገኘን በኋላ፥ እንደ ልጆቹ በእግዚአብሔር መንፈሳዊ ቤተሰብ ውስጥ ተቀባይነትን እናገኛለን (ዮሐ. 1፡12)። በተጨማሪም እኛ የዓለም ምስክሮች ነን (ማቴ. 28፡19-20)።

የውይይት ጥያቄ፡- በእነዚህ አራት ወንጌላት ውስጥ የሚገኙ እውነቶች መልካም ዜናዎች ከሆኑ፥ ብዙ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ለሌሎች ለመናገር የማይፈልጉት ለምን ይመስልሃል?

በእግዚአብሔር ዕቅድ ኢየሱስ ምንም መጽሐፍ አልጻፈም። ሙስሊሞች አላህ ቁርዓን ለመሐመድ ቃል በቃል እያጻፈ ሰጥቶታል ይላሉ። ክርስቶስ ቃሉን ለደቀ መዛሙርቱ ቃል በቃል እየተናገረ አላጻፋቸውም። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በክርስቶስ ተከታዮች ልብ ውስጥ በመሥራት እግዚአብሔር ሰዎች እንዲያውቁ የሚፈልገውን አሳብ እንዲጽፉ አድርጓቸዋል። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ስለ ክርስቶስ ሕይወትና ትምህርት የሚያስረዳውን ታሪክ የጻፉት ክርስቶስ ካረገ ከ30 ዓመት በኋላ ነው።

አራቱ ወንጌላት የተጻፉት በአራት የተለያዩ ደራሲያን ነው። ከ12ቱ ደቀ መዛሙርት መካከል የነበሩት ማቴዎስና ዮሐንስ የክርስቶስን ሕይወት ከመመልከታቸውም በላይ፥ ትምህርቱን ተከታትለዋል። የተቀሩት ሁለቱ የወንጌላት ጸሐፊዎች ግን የክርስቶስ ሕይወትና ትምህርት ምስክሮች አልነበሩም። ማርቆስና ሉቃስ የክርስቶስን ሕይወት ታሪክ ለመጻፍ የቻሉት ከደቀ መዛሙርቱና ከሌሎች ሰዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ነበር።

ምሑራን ወንጌላት በሂደት መጻፋቸውን ያምናሉ።

1. ወንጌል የሚጀምረው በኢየሱስ ነው። የተመሠረተውም ከሰማይ ወደ ምድር መጥቶ በኖረው በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትና ትምህርት ላይ ነው። ወንጌል የፈጠራ ታሪኮችና ተረቶች ወይም አፈ ታሪኮች ጥርቅም ላይሆን፥ እውነት ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ዮሐንስ የተደረገውን ሁሉ በዓይኖቹ እንደተመለከተ የገለጸው። ክርስቶስ በታሪክ ምዕራፍ ውስጥ የታየ እውነተኛ ሰው ነበር (1ኛ ዮሐ 1፡1-2)። ሐዋርያት ለሌሎች የተናገሯቸውን ነገሮች በዓይኖቻቸው ተመልክተዋል (የሐዋ. 10፡37-39)።

2. ከክርስቶስ ሞት በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ ያደረገውንና ያስተማረውን ለሌሎች መናገር ጀመሩ። እነዚህ ክርስቲያኖች ታሪኮቹን ለወዳጆቻቸው በመናገራቸው፥ ስለ ክርስቶስ ሕይወትና ትምህርት የሚያስረዱ እውነቶች ከቤተ ክርስቲያን ወደ ቤተ ክርስቲያን መተላለፍ ጀመሩ። ሐዋርያት ብሉይ ኪዳንን በሚያጠኑበት ጊዜ፥ በክርስቶስ ሕይወት ብዙ ትንቢቶች እንደ ተፈጸሙ ተገነዘቡ። ስለሆነም እነዚህን የትንቢት ፍጻሜዎች በጽሑፍ እኖሩ። ክርስቶስ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን እንደ ፈጸመ የሚያመለክቱ 80 ያህል ጥቅሶች በአዲስ ኪዳን ውስጥ ይገኛሉ። ሐዋርያት ለመጭው ትውልድ ያስተላለፉት ስለ ክርስቶስ የሚናገሩትን እውነቶች ብቻ ሳይሆን፥ የክርስቶስን ሕይወት ትርጓሜዎች ጭምር ነበር። ሐዋርያት የክርስቶስን ማንነት ይበልጥ በተረዱ ቁጥር፥ ስለ ክርስቶስ ማንነት ትምህርታዊ ገለጻዎችን መስጠት ጀመሩ። አንዳንድ ምሑራን እነዚህ . የክርስቶስ ታሪኮች በቃል የተጠኑ ታሪኮችና በጥንቃቄ ለሌሎች የተላለፉ እንደሆኑ ያስባሉ።

3. በቃል የሚተላለፍ መልእክት ፍጥነት ቢኖረውም፥ ስሕተት ግን ሊኖረው ይችላል። እነዚህ ስሕተቶች አንዳንድ ጠቃሚ እውነቶችን ሊያስቀሩ ወይም ታሪኩን ከመጠን በላይ ሊያጋንኑ ይችላሉ። ስለሆነም ሰዎች እነዚህን ታሪኮች በጽሑፍ ማስፈር ጀመሩ። ሉቃስ በመጽሐፉ መጀመሪያ ላይ እንደገለጸው፥ መጽሐፉን ለመጻፍ የተለያዩ ምንጮችን መርምሯል (ሉቃስ 1፡1-2 አንብብ)። ነገር ግን የተጻፉት ታሪኮች ቅዱሳት መጻሕፍት አልነበሩም። እነዚህ ታሪኮች በስሕተት የተሞሉ ባይሆኑም፥ መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት ታሪክ ምንጭ እንዲሆኑ አላደረገም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እያንዳንዱ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ማንነት፥ ስለ ሠራቸው ሥራዎችና በእርሱ ማመን ማለት ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ ማወቁ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) በኢትዮጵያ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት አዳዲስ ክርስቲያኖች እነዚህን ነገሮች እንዲያውቁ ጥረት የሚያደርጉ ይመስልሃል? ሐ) እያንዳንዱ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ማንነትና ለምን በእርሱ ማመን እንደሚያስፈልግ ግልጽ መረዳት እንዲኖረው ለማድረግ ቤተ ክርስቲያንን የሚረዳ ምን አሳብ አለህ?

4. መንፈስ ቅዱስ በአራት ሰዎች ሕይወት ውስጥ በመሥራት አራቱን ወንጌላት እንዲጽፉ መርቷቸዋል። ስለ ክርስቶስ ሕይወትና ታሪክ ሥልጣናዊ ጽሑፍ ማዘጋጀት ያስፈለገው ለምን ነበር?

ሀ. ወንጌል በሮም ግዛቶች ሁሉ ሲስፋፋ ስለ ክርስቶስ የሚናገሩ ታሪኮች ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው ሰው ሲተላለፉ መለወጣቸው አልቀረም። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በክርስቶስ ስላመኑ፥ ሐዋርያት ሁሉንም ክርስቲያኖች ለመጎብኘትና ስለ ክርስቶስ ለማስተማር አይችሉም ነበር። ስለሆነም ስለ ክርስቶስ ሕይወት፥ ስላስተማራቸው ነገሮችና ስለ ማንነቱ እውነተኛ ታሪክ ማግኘት አስፈላጊ ሆነ። ይህ በተለይ ክርስቶስን ላላዩትና ስለ ክርስቶስ ግልጽ ግንዛቤ ለማግኘት ለሚፈልጉ ሁለተኛ ትውልድ ክርስቲያኖች የበለጠ አስፈላጊ ነው።

ለ. ብዙዎቹ የዓይን ምስክሮችና ሐዋርያት በሞት እየተለዩ ነው። ሌሎች ደግሞ ከስደት የተነሣ ተበታትነው ነበር። ስለሆነም እነዚህ የዓይን ምስክሮች ከመሞታቸው በፊት በዓይን ምስክሮች የተረጋገጠ ትክክለኛ ታሪክ መጻፍ አስፈላጊ ነበር። ታሪኮቹ የተጻፉት ስለ ክርስቶስ በሰሙት ሰዎች ብቻ ቢሆን ኖሮ፥ ትክክለኛነታቸው አጠራጣሪ ይሆን ነበር። ከክርስቶስ ጋር የነበሩ፥ የተፈወሱ፥ በውኃ ላይ ሲራመድና ሙታንን ሲያስነሣ የተመለከቱ ሰዎች ታሪኩን መናገራቸው አስፈላጊ ነበር።

ሐ. ምናልባትም ትክክለኛ ያልሆኑ ታሪኮችም ሳይጻፉ አልቀረም። ስለሆነም ሐዋርያት ተአማኒነት ያላቸውን የክርስቶስ ሕይወት ታሪኮች መጻፍ አስፈለጋቸው።

መ. አዳዲስ ክርስቲያኖችን ለማስተማር። አንድ ሰው በክርስቶስ ማመኑ ስለ ክርስቶስ ከመመስከር አይገታውም። ይህ የሂደቱ ጅማሬ ብቻ ነው። አዳዲስ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ምን ማመንና እንዴት መኖር እንዳለባቸው መማር አለባቸው። ስለሆነም ወንጌላቱ ከተጻፉበት ዓበይት ምክንያት ውስጥ አንዱ አዳዲስ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስና እርሱን ስለ መከተል ግንዛቤ እንዲያገኙ ለመርዳት ነበር።

ብዙ ሰዎች አራቱ ወንጌላት ስለ አንድ ሰው የሕይወት ታሪክ የሚናገሩ ናቸው ብለው ያስባሉ። ከዚህም የተነሣ ከዝነኛ ሰው ታሪካዊ ዘገባ ጋር ያነጻጽሩታል። ነገር ግን አራቱ ወንጌላት በታሪክ ጸሐፊዎች ከተጻፉ ግለ ታሪኮች ጋር የሚመሳሰሉባቸውና የሚለያዩባቸው መንገዶች እንዳሉ መገንዘብ ጠቃሚ ነው። ወንጌላትን በምናጠናበት ጊዜ የሚከተሉትን ነገሮች እናገኛለን።

ሀ. አራቱ ወንጌላት ክርስቶስ ስላደረጋቸው ነገሮች እውነተኛውን መረጃ ያቀርባሉ። ይህም ከግለሰብ የሕይወት ታሪክ ጋር ያመሳስላቸዋል።

ለ. አራቱ ወንጌላት የክርስቶስን ከፊል ታሪክ ብቻ ይናገራሉ። ከአራቱ ወንጌላት ክርስቶስ ያደረገውንና የተናገረውን ሙሉ በሙሉ በዝርዝር ለማቅረብ የሞከረ የለም። እያንዳንዱ የወንጌል ጸሐፊ የመረጠው የተወሰኑትን ታሪኮች ብቻ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ የኢየሱስ ታሪክ በሙሉ ቢጻፍ ኖሮ፥ በቂ ቀለም ማግኘት እንደማይችል ገልጾአል (ዮሐ. 20፡30-31፤ 21፡25)።

ሐ. አራቱ ወንጌላት የማስተማሪያ መሣሪያዎች ናቸው። እያንዳንዱ የወንጌል ጸሐፊ፥ የተወሰኑ ታሪኮችንና ኢየሱስ ያስተማራቸውን የተወሰኑ ትምህርቶች መርጦ ለክርስቲያኖችና ክርስቲያን ላልሆኑ ሰዎች ለመግለጽ ሞክሮአል። ጸሐፊዎቹ ክርስቲያን ላልሆኑ ሁሉ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅና ብቸኛው የደኅንነት መንገድ እንደሆነ ለማሳመን ጥረዋል። ለምሳሌ፥ ሐዋርያው ዮሐንስ ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ ወደ ዓለም ከመምጣቱ በፊት ማን እንደነበረ አብራርቷል (ዮሐ 1፡1-14)። በተጨማሪም ጸሐፊዎቹ የሚያድን እምነት ምን እንደሆነና ይህም ሙሉ ታማኝነትን እንዴት እንደሚጠይቅ ለማሳየት ሞክረዋል። የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ክርስቶስ አዳኛቸው በመሆኑ፥ በሁኔታዎች ሁሉ በእርሱ መታመን ያስፈልጋቸው ነበር። ዐይነ ስውራንን ያበራው፥ ሙታንን ያስነሣውና ማዕበሉን ጸጥ ያደረገው እርሱ በሚያጋጥማቸው ሁኔታ ውስጥ ሁሉ ከእነርሱ ጋር ነበር።

ወንጌላትን ስናነብና ስናጠና ልናነሣቸው የሚገቡ ሁለት ጥያቄዎች አሉ።

  1. «ስለ ክርስቶስ፥ ስለ ማንነቱና እንድናደርጋቸው ስለሚፈልጋቸው ነገሮች ምን መማር እንችላለን?» ከአንድ ሰው ጋር ያለን ግንኙነት ይበልጥ የሚጠነክረው፥ ስለ ግለሰቡ፥ ስለ ባሕርዩ፥ ዋጋ ስለሚሰጣቸው ነገሮችና ማንነቱን ስለቀረጹት ነገሮች በማወቅ ነው። ከክርስቶስ ጋር ያለንም ግንኙነት የሚጠነክረው እርሱን የበለጠ በማወቅ ነው። ክርስቶስን በበለጠ ለማወቅ ከሚረዱን ነገሮች አንዱ በአራቱ ወንጌላት ውስጥ ስለ እርሱ የተገለጹትን እውነቶች በጥንቃቄ ማጥናት ነው።
  2. «ደራሲው የኢየሱስ ተከታይ ለመሆን ሊያስተምረን የፈለገው አሳብ ምንድን ነው?» ክርስቶስ እርሱን መከተል ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለሦስት ዓመት ያህል ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯል። አራቱ ወንጌላትም ይህንኑ አሳብ ዘግበውልናል። የክርስቶስ ተከታዮች ባሕርይ ምን መሆን አለበት? ኢየሱስን መከተል ደቀ መዛሙርቱን ምን ዋጋ ያስከፍላቸዋል? የክርስቶስ ተከታዮች ለሌሎች ሊያስተላልፉ የሚገባው መልእክት ምንድን ነው? ክርስቶስን ለመከተል የሚፈልጉ ሰዎች ዋና ኃላፊነት ምንድን ነው? አራቱ ወንጌላት ለእነዚህ ጥያቄዎች በሙሉ መልስ ይሰጣሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህን ሁለት ጥያቄዎች በተደጋጋሚ መጠየቅ ያለብን ለምንድን ነው? ለ) በቅርቡ ከክርስቶስ ጋር ያለህ ግንኙነትና ዕውቀት እንዴት እያደገ እንደ መጣ ግለጽ። ሐ) ፊልጵስዩስ 3፡10 አንብብና ይህን ጥቅስ በሕይወትህ ተግባራዊ ለማድረግ የምትችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ድካም ከሚታይባቸው ምክንያቶች አንዱ፥ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ አለማወቃቸው ሳይሆን አይቀርም። ደኅንነት ለማግኘት በክርስቶስ ማመን በቂ እንደሆነ እናውቃለን። ነገር ግን ብዙዎቻችን ክርስቶስን መከተል ማለት ምን ማለት እንደሆነ አልተማርንም። ይህም ብዙ ክርስቲያኖች እንደ ዓለማውያን እንዲመላለሱ አድርጓቸዋል። ችግሮች በሚገጥሙን ጊዜ ማጉረምረም ወይም ከክርስቶስ መንገድ መውጣት እንጀምራለን። ብዙዎቻችን ለዓለማውያን ምን እንደምናካፍል አናውቅም። ምናልባትም አብያተ ክርስቲያናት፥ የጥንት ክርስቲያኖች አዳዲስ ክርስቲያኖችን ለማሠልጠን የተጠቀሙባቸውን መሣሪያዎች ማለትም አራቱን ወንጌላት መጠቀም ይኖርባቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አዳዲስ ክርስቲያኖች አንዱን ወይም ሁሉንም ወንጌላት እንዲያጠኑ በማድረግ ለማስተማር ዐቅድ፡፡ የትኛውን ወንጌል ትመርጣለህ? ለምን? ሥልጠናውን እንዴት ታደራጀዋለህ? ለ) ብዙ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ማንነትና እርሱን መከተል ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም። በግንዛቤያቸው እንዲያድጉ ለማገዝ አራቱን ወንጌላት እንዴት ልትጠቀም ትችላለህ?

አራት ወንጌላት የሆኑት ለምንድን ነው?

የውይይት ጥያቄ፡- እንድ አውቶቡስና የጭነት መኪና በማቋረጫ መንገድ ላይ ተጋጩ እንበል። ይህን አደጋ አራት ሰዎች ተመለከቱት። ከእነዚህ አራት ሰዎች ውስጥ አንዲት ሴት፥ አንድ ፖሊስ፥ አንድ ጠበቃና አንድ መካኒክ ነበሩ። በችሎቱ ፊት ዳኛው ስለተከሰተው አደጋ እንዲያብራሩ ጠየቋቸው። ሀ) አራቱ ሰዎች የተከሰተውን ጉዳይ በዝርዝር ለማስረዳት ይችላሉ? ለ) እነዚህ አራት ምስክሮች ከአንድ ምስክር የሚሻሉት እንዴት ነው?

መንፈስ ቅዱስ ስለ ክርስቶስ ሕይወት ይጽፉ ዘንድ አራት ሰዎችን ለምን እንደ ተጠቀመ በእርግጠኝነት አናውቅም። ይሁንና ከላይ የቀረበው ማብራሪያ አንድ ፍንጭ የሚሰጠን ይመስላል። ሴት ከወንድ በላይ ነገሮችን የማጤን ጥበብ አላት። ፖሊሱ ደግሞ ከጠበቃውና ከሜካኒኩ በተለየ መንገድ ሪፖርቱን ሊያቀርብ ይችላል። እያንዳንዱ አስተያየት ደግሞ ዳኛው የተፈጸመውን ክስተት ከተለያየ አቅጣጫ እንዲገነዘብ ይረዳዋል። ሴቲቱ ምናልባትም በአደጋው ምክንያት ስለተከሰተው ሥቃይና ሕመም ልትናገር ትችላለች። ፖሊሱ ደግሞ ስለ መኪናው ሕጋዊ ምዝገባና ስለ ሾፌሩ ትክክለኛነት ወይም ጥፋተኛነት ሊያስረዳ ይችላል። ጠበቃው ደግሞ ሕጋዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር፥ ለተከሰተው አደጋ ማን ካሳ ሊከፍል እንደሚገባ ሊገልጽ ይቻላል። ሜካኒኩ ደግሞ ሾፌሩ ፍሬን ስለ መጠቀሙ፥ ወዘተ… በማስረዳት ሜካኒካዊ ጉዳዮችን ያብራራል። ይህ ሁሉ አስተያየት ዳኛው ትክክለኛ ውሳኔ ለመስጠት እንዲችል ይረዱታል።

ልክ እንዲሁ እግዚአብሔር ስለ ልጁ ከተለያዩ እይታዎች አንጻር እንዲመሰክሩ አራት ሰዎችን ተጠቅሟል። ከእያንዳንዱ የወንጌል ጸሐፊ ስለ ክርስቶስ የተለያየ እይታ እናገኛለን። ማቴዎስ አይሁዳዊ ቀራጭ (ግብር ሰብሳቢ) ነበር። እርሱም፥ ለአይሁዶች የዳዊት ልጅ ስለሆነው ስለ ክርስቶስ ጻፈላቸው። ሮም ይኖር የነበረው ማርቆስ፥ «ኢየሱስ ማን እንደሆነ ሥራ ለሚበዛባቸው ሮማውያን» አስረድቷል። የታሪክ ምሑርና ሐኪም የነበረው ሉቃስ ለሰዎች ስሜትና ፍላጎት ትኩረት ሰጥቷል። በተጨማሪም ሉቃስ ክርስቶስ አሕዛብንና ድውያንን፥ መከራ የደረሰባቸውን፥ ድሆችንና ሴቶችን እንዴት እንደረዳ አብራርቷል። ዮሐንስ፥ «ክርስቶስ ማን ነው?» የሚለውን ጥያቄ መልሷል። ከክርስቶስ ሕይወት ወሳኝ ትምህርቶችን እያወጣ አብራርቷል። ይህም እያንዳንዱ የወንጌል ጸሐፊ አንዱን ክርስቶስና ሕይወቱን ከተለያየ አንጻር በመመልከት ሙሉ ገለጻ እንደ ሰጡን ያሳያል። በመሆኑም አራቱ ወንጌላት ከአንድ ወንጌል ይልቅ ስለ ክርስቶስ ግልጽ ምስል እንዲኖረን አድርገዋል።

ብዙ ምሑራን እያንዳንዱ ወንጌል ለተወሰኑ ሕዝቦች የተጻፉ ናቸው የሚል ግምት አላቸው። ማቴዎስ ለአይሁዶች፥ ማርቆስ ለሮሜ ሰዎች፥ ሉቃስ ለግሪኮች፥ ዮሐንስ ለመላው ዓለም እንደ ጻፉ ያስባሉ። በተጨማሪም ምሑራን እያንዳንዱ ደራሲ በክርስቶስ ማንነት ላይ የተለይ ትኩረት እንዳደረገ ያስረዳሉ። ማቴዎስ፥ ክርስቶስ የአይሁድ ንጉሥ እንደሆነ፥ ማርቆስ የእግዚአብሔር አገልጋይ እንደሆነ፥ ሉቃስ ፍጹም የሰው ልጅ እንደሆነ፥ እንዲሁም ዮሐንስ ክርስቶስ ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ያስረዳል ይላሉ።

ሌላው አራቱ ወንጌላት የተጻፉበት ምክንያት ከብሉይ ኪዳን የመጣ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ። በብሉይ ኪዳን ዘመን አንድ ሰው በጥርጣሬ ወይም በአንድ ሰው ምስክርነት ብቻ ሊፈረድበት ወይም ሊገደል አይችልም ነበር። እንዲፈረድበት ቢያንስ ሁለት ወይም ሦስት ምስክሮች ያስፈልጋሉ (ዘዳግ 19፡15)። ስለሆነም እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱ ልጅና ብቸኛው የደኅንነት መንገድ መሆኑን ለመመስከር ከሦስት አልፎ አራት ምስክሮችን ሰጥቷል። የእነዚህ አራት ምስክሮች ቃል ሰዎችን ሊያሳምናቸው ይገባል።

ምስክረ ወንጌላት

የውይይት ጥያቄ፡– እነዚህን ምንባቦች አነጻጽር፡ ማቴ. 9፡2-8፤ ማር. 2፡3-12፤ ሉቃስ 5፡18-26፤ ማቴ. 10፡22፤ ማር. 13፡13 ሉቃስ 21፡17 ምንባቦቹ የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?

ምሑራን ሁለት በባሕርያቸው የሚለያዩ ወንጌላት እንዳሉ አስተውለዋል። ማቴዎስ፥ ማርቆስና ሉቃስ አንደኛው ዐይነት ወንጌል ናቸው። እነዚህ ወንጌላት አስተምህሮአዊ ትንታኔ የላቸውም። ይሁንና ክርስቶስ ያደረገውንና ያስተማረውን አገልግሎት በሰጠበት ታሪካዊ መንገድ ያቀርባሉ። ሦስቱም ክርስቶስ ተአምራትን እንዳደረገና በምሳሌዎች እንዳስተማረ ያስረዳሉ። በእነዚህ ሦስት ወንጌላት ውስጥ ጎልቶ የሚታየው የክርስቶስ አምላክነት ሳይሆን ሰብዓዊነት ነው። ምሑራን እነዚህን ሦስት ወንጌላት «ምስክረ ወንጌላት» በማለት ይጠሯቸዋል። ምስክረ ወንጌላት የተባሉት በቅርጽና በገለጻ ስለ ክርስቶስ ያቀረቡት አሳብ አንድ ዓይነት በመሆኑ ነው።

ነገር ግን የመጨረሻው የዮሐንስ ወንጌል በጣም የተለየ ነው። ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ ካደረጋቸው ተአምራት ሰባቱን ብቻ ጽፎአል። ሐዋርያው ዮሐንስ ያተኮረው በክርስቶስ ረዣዥም ስብከቶች ላይ ነው። ምሳሌዎችን ከመጠቀም ይልቅ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነትን እንዴት በግልጽ እንደ ተናገረ አሳይቷል። በኢየሱስ ሰብአዊነት ላይ ከማተኮር ይልቅ፥ ክርስቶስ አምላክ እንደሆነ በግልጽ ዘግቧል።

የማቴዎስ፥ የማርቆስና የሉቃስ አጻጻፍ በአንዳንድ ስፍራዎች ላይ እጅግ መመሳሰል፥ ለምሑራኑ ችግሮችን አስከትሏል። የሁለት ተማሪዎች የጽሑፍ ፈተና ቃል በቃል ወይም በአሳብ ደረጃ ተመሳሳይነት ካለው አንዱ የሌላውን እንደ ኮረጀ ያህል ማለት ነው። ሁለት የተለያዩ ሰዎች አንድ ዓይነት ቃላትና የአሳብ አወራረድ ተከትለው ሊጽፉ አይችሉም። ነገር ግን በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወንጌላት ላይ የተካሄደው ጥንቃቄ የተሞላበት ጥናት አንዳንድ ጊዜ ቃላቱ፣ ብዙ ጊዜ ደግሞ አሳቦቹ ተመሳሳይ መሆናቸውን አረጋግጧል። ምሑራን የማርቆስ ወንጌል 93 በመቶ በማቴዎስና በሉቃስ፥ የማቴዎስ ወንጌል 58 በመቶ በማርቆስና በሉቃስ፥ እንዲሁም የሉቃስ ወንጌል 41 በመቶ በማቴዎስና በማርቆስ ውስጥ እንደሚገኝ ገምተዋል፤ በአንጻሩም በሌሎቹ ሦስት ወንጌላት ውስጥ የሚገኘው የዮሐንስ ወንጌል 8 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው።

ስለሆነም ምሑራኑ የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ ወንጌላት እንዴት እንደ ተጻፉ በሚያቀርቧቸው ጥናቶች ይለያያሉ። አብዛኞቹ የተከተሉት የጥናት አሳብ ማርቆስ መጀመሪያ እንደ ተጻፈ ነው። ማቴዎስም ማርቆስ ከጻፈው ውስጥ ብዙውን በመውሰድ ለራሱ ዓላማ በሚመች መንገድ ጽፎአል። ማቴዎስ ከማርቆስ በተጨማሪ ሌሎች ምንጮችን ተጠቅሟል። ሉቃስም የማቴዎስንና የማርቆስን ወንጌል ሳይጠቀም አይቀርም። አንዳንድ ምሑራን ማቴዎስና ሉቃስ የተጠቀሙበት ሌላም ምንጭ እንዳለ ያምናሉ።

ሌሎች ደግሞ አንዱ ወንጌል ከሌላው በቀጥታ እንዳልቀዳና ይልቁንም የሦስቱ ወንጌላት ጸሐፊዎች ተመሳሳይ ትውፊቶችን እንደ ተጠቀሙ ያስረዳሉ። እነዚህ ምሑራን በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ የሚናገሩ ታሪኮች ባጭር ባጭሩ ተጽፈው ይገኙ ነበር ይላሉ። እነዚህ አጫጭር ታሪኮች በቃል እየተጠኑ ለአዳዲስ ክርስቲያኖች በጥንቃቄ ይተላለፉ ነበር። በመሆኑም ሦስቱ የወንጌላት ጸሐፊዎች እነዚህን በቃል የተጠኑ ታሪኮች ተጠቅመዋል ይላሉ።

በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ሌሎችም ብዙ ግምታዊ አሳቦች አሉ። ለምሳሌ፥ ሦስቱም ወንጌላት አሁን አንድ በጠፉ ጥንታዊ ወንጌል ተጠቅመዋል የሚሉም አሉ። የወንጌላት ጸሐፊዎች ተጽፈው የተቀመጡትን አጫጭር ታሪኮች እንደ ተጠቀሙ የሚናገሩ ምሑራንም ሞልተዋል። አንዳንዶች የማቴዎስ ወንጌል የመጀመሪያው ወንጌል ስለሆነ ሌሎቹ ሁለት ጸሐፊዎች እርሱን እንደ ዐቢይ ምንጭ እንደ ተጠቀሙ ያስባሉ። ስለሆነም ምሑራን እነዚህ ሦስት ወንጌላት ለምን በጣም ሊመሳሰሉ እንደ ቻሉ ሁሉንም የሚያስማማ መልስ ሊሰጡ አልቻሉም። የምናውቀው ነገር ቢኖር መንፈስ ቅዱስ በጽሕፈት ሂደቱ ውስጥ አመራር ሰጪ እንደ ነበረ ነው። መንፈስ ቅዱስ ለሰው ሁሉ እንዲተላለፍ የሚፈልጋቸውን አሳቦች ጸሐፊዎቹ እንዲዘግቡ መርቷቸዋል። በተጨማሪም ታሪኮቹ ክርስቶስ በትክክል ያደረገውንና ያስተማረውን እንዲያንጸባርቁ አድርጓል።

የውይይት ጥያቄ፡- ወንጌላትን የመጻፉ ሂደት የመንፈስ ቅዱስና የሰዎች የጋራ ጥረት ውጤት ነው። ይህ መንፈስ ቅዱስ የሚሠራበት የተለመደ መንገድ መሆኑን ግለጽ። መንፈስ ቅዱስ አንተን፥ ትምህርትህንና ችሎታዎችህን፥ ስለ ተጠቀመበት መንገድ አንዳንድ ማብራሪያዎችን ስጥ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d