የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የተለያዩ ዐበይት ሃይማኖቶችንና ቅዱሳት መጻሕፍቶቻቸውን ዘርዝር። ለ) 2ኛ ጴጥ. 1፡20-21 አንብብ። ጴጥሮስ ስለ ብሉይ ኪዳን ምን ተናገረ? ሐ) 66ቱ መጻሕፍት ብቻ የእግዚአብሔር ቃል ናቸው የሚለውን መቀበል ወሳኝ የሚሆነው ለምንድን ነው?
እያንዳንዱ ሃይማኖት ከአምላኩ እንደ ተቀበለ የሚያምነው ልዩ መጽሐፍ አለው። ሂንዱዎች ቬዳስ፥ ቡድሒስቶች ቲፒታካ፥ ሙስሊሞች ደግሞ አላህ ለመሐመድ ሰጠው የሚሉት ቁርዓን ከእስትንፋሰ-እግዚአብሔር የተገኙ መጻሕፍት አለን ይላሉ። ለምሳሌ፥ የያህዌ ምስክሮች የመጠባበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ያብራራል በማለት ይናገራሉ። ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ለሰው ልጆች አንድ እስትንፋሰ እግዚአብሔር መጽሐፍ ብቻ እንደ ሰጠ ያምናሉ። ይህም መጽሐፍ፥ ብሉይና አዲስ ኪዳን የተሰኙ ክፍሎች ያሉት መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ምንም እንኳ ሌሎች መጻሕፍት አንዳንድ ጠቃሚ መረጃ ዎችን ሊሰጡን ቢችሉም፥ ምንም ስሕተት የሌለባቸው የእግዚአብሔርን ቃል የያዙ 66ቱ መጻሕፍት ብቻ እንደሆኑ እናምናለን።
በኢየሱስ ክርስቶስ ዘመን አብዛኞቹ አይሁዶች 39ኙ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በሰዎች መጻፋቸውንና የእግዚአብሔር ቃል እንደሆኑም ተረድተው ነበር። ምንም እንኳ እግዚአብሔር ቃሉን ለመጻፍ ሰዎችን መሣሪያ አድርጎ ቢጠቀምም፥ በእነዚህ 39 መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘው አሳብ ሁሉ እግዚአብሔር ራሱ በቀጥታ መጥቶ የተናገረው ሥልጣናዊ ቃል እንደሆነ ተረድተው ነበር። ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ከሦስቱም ዐቢይ የብሉይ ኪዳን ምድቦች፥ ማለትም ከሕግ፥ ከነቢያትና ከጽሑፎች እየጠቀሰ በማስተማር የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን አስረድቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳት ጽሑፎች የሰው ሳይሆኑ፥ የእግዚአብሔር ሥራዎች እንደሆኑ ገልጾአል (2ኛ ጢሞ. 3፡16)።
እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳን ዘመን የሠራው፥ በብሉይ ኪዳን በሠራው መንገድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ሥራ ብቻ አይደለም። የእግዚአብሔርም ሥራ ብቻ አይደለም። እግዚአብሔር ሰዎች እንዲጽፉለት የፈለገውን አሳብ ቃል በቃል አልተናገረም። (ይህ ሙስሊሞች መሐመድ ከአላህ ቃል በቃል ተቀብሎ ጽፎአል ብለው ከሚያምኑት የተለየ ነው)። እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ የሰውና የእግዚአብሔር ሥራ ውጤት ነው። የተለያዩ የአዲስ ኪዳን ደራሲያን መልእክቶቻቸውን የጻፉት የራሳቸውን ቃል በመጠቀም ነበር። ለዚህም ነው ምሑራን አንዳንድ መጻሕፍት የተጻፉበት የግሪክ ቋንቋ ከሌሎች የላቀ መሆኑን የሚናገሩት። በጽሑፋቸው ውስጥ የእያንዳንዱ ደራሲ ባሕርይ ይታያል። ጳውሎስ በጸጋ፥ ዮሐንስ በእምነት ወይም ብርሃን ላይ ሲያተኩሩ እንመለከታለን። እያንዳንዱ ደራሲ የተወሰኑ ቃላትን ይደጋግማል። ለምሳሌ፥ ዮሐንስ «ብርሃን» እና «ጨለማ» የሚሉትን ቃላት በተደጋጋሚ ጠቅሷል። ይህም መንፈስ ቅዱስ የደራሲያኑን ማንነት ችላ እንዳላለ ያሳያል። ይህ ባይሆን ኖሮ፥ እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ተመሳሳይ ቃሎችን፥ አገላለጾችንና ሥነ ጽሑፋዊ ዘዴዎችን ያንጸባርቅ ነበር። ይህን በመጻሕፍቱ ውስጥ አናይም። ምናልባት አብዛኞቹ ደራስያን የእግዚአብሔርን ቃል እየጻፉ መሆናቸውን ላያውቁ ይችሉ ይሆናል። እግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት እየተመሩ ቃሉን ከእርሱ ጋር እንዲጽፉ ሲፈቅድ፥ ስለ ጸሐፊዎቹ ምን ልንማር እንደምንችል፥ ያተኮረባቸውን አሳቦች ልንመለከት፥ የወደደችውን ቃላት ልናጤን፥ . . ወዘተ. እንችላለን።
የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የሰው ቃሎች ብቻ አይደሉም። እነዚህ መጻሕፍት በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የተሰጡ የእግዚአብሔር ቃላት እንደሆኑ ተገልጾአል (2ኛ ጴጥ. 1፡20-21)። መንፈስ ቅዱስ የእያንዳንዱ ደራሲ ስብእናና ችሎታ እንዲንጸባረቅ በመፍቀድ የጽሕፈት ሂደቱን ስለ ተቆጣጠረ፥ ሁሉም ነገር ተጽፎ ከተጠናቀቀ በኋላ እግዚአብሔር ሊያስተላልፍ የፈለገው አሳብ ያለምንም ስሕተት በትክክል ሊተላለፍ ችሏል። መንፈስ ቅዱስ የእያንዳንዱን ደራሲ አሳብ፥ ቃልና ዐረፍተ ነገር ስለተቆጣጠረ የመጨረሻ ውጤቱ የእግዚአብሔር እንጂ የሰው ቃል እንዳልሆነ እንገነዘባለን። ምሑራን በመጽሐፍ ቅዱስና በክርስቶስ መካከል ተመሳሳይነት አለ ይላሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ጊዜ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው እንደሆነ ሁሉ፥ መጽሐፍ ቅዱስም በአንድ ጊዜ የእግዚአብሔርና የሰው ሥራ ነው። ይህም መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ሌሎች መጻሕፍት ማጥናት እንደሌለብን ያስገነዝበናል። ይልቁንም እግዚአብሔር በቀጥታ እንደሚናገረን አድርገን ልናጠናው ይገባል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሞቱ በፊት ደቀ መዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስን እንደሚቀበሉ ነግሯቸው ነበር። ከመንፈስ ቅዱስ ዐበይት ሥራዎች አንዱ በአንዳንድ ሰዎች ልብ ውስጥ በመሥራት ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲጽፉ ማድረግ ነበር። ክርስቶስ በዮሐ 16፡12-15 እንደተናገረው፥ «የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፥ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ፡- ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ።» በተጨማሪም ክርስቶስ፥ «አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል፤ እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል» ብሏል (ዮሐ 14፡26)። አንዳንድ ምሑራን፥ «ያሳስባችኋል» የሚለው አራቱን ወንጌላት እንደሚያመለክትና «ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል» የሚለው መልእክቶችን፥ እንዲሁም «የሚመጣውንም» የሚለው ደግሞ የዮሐንስ ራእይን እንደሚያመለክት ይናገራሉ።
በኋላም ሐዋርያው ጴጥሮስ፥ «የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቁጠሩ። እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥ በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ። በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ» (2ኛ ጴጥ. 3፡15-16) ብሏል። ጴጥሮስ፥ ጳውሎስ የጻፋቸው መልእክቶች የብሉይ ኪዳንን ያህል ሥልጣን እንዳላቸው ገልጾአል። ይህም ሐዋርያት ገና በሕይወት ሳሉ እንኳ አንዳንድ መጻሕፍትን ከብሉይ ኪዳን እኩል ማየት እንደ ጀመሩ ያመለክታል። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን 27ቱን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል ናቸው ብላ ለመቀበል 200 ዓመታት ያህል ወስዶባታል።
የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል ካልሆነው ለመለየት፥ ለጥንት ክርስቲያኖች ወሳኝ ተግባር ነበር። በዚያን ጊዜ ሐዋርያት ነን ብለው የተናገሩ ደራሲያን ነበሩ። እነዚህ ሰዎች የጻፉት አሳብ ግን ሐዋርያቱ ከጻፉት ጋር ይጋጭ ነበር። በስደት ወቅት ክርስቲያኖች ለእውነት ለመሞት ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ነበረባቸው። ስለዚህ ለውሸት መሞት አይፈልጉም ነበር። መጻሕፍቱን መገልበጡ ደግሞ ረዥም ጊዜ የሚወሰድ ተግባር ነበር። ስለሆነም በዓለም ሁሉ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የእግዚአብሔር ቃል የሆኑትን መጻሕፍት መሰብሰብ ጀመሩ። በተጨማሪም የተሻሉ ናቸው የሚባሉ የቀዳሚ ጽሑፎችን ቅጂ መፈለግ ጀመሩ።
እነዚህ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶች አንድ ጽሑፍ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑንና አለመሆኑን ለመለየት የተጠቀሙባቸው መመዘኛዎች ምን ምን ነበሩ?
1 ደራሲው ማን ነው? ደራሲው የማይታወቅ ወይም አጠራጣሪ ከሆነ፥ መጽሐፉን እንደ ቅዱስ መጽሐፍ አድርገው አይቀበሉም ነበር። ዋናው መመዘኛቸው ደራሲው ከቀደምት ሐዋርያት አንዱ መሆን አለበት የሚል ነበር። የጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች የመጀመሪያው ምእተ ዓመት ሐዋርያት እውነትን የመደንገግ ሥልጣን እንደተሰጣቸው ተረድተው ነበር። ስለሆነም እነዚህ ሐዋርያት እግዚአብሔር ሥልጣን ያለውን ቃሉን ለመጻፍ የሚጠቀምባቸው መሆኑን ያውቁ ነበር።
ደራሲው ሐዋርያ ካልሆነ፥ እንዲህ ብለው ይጠይቃሉ፥ «መጽሐፉ ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ ይህ ጸሐፊ ከሐዋርያት ጋር የቀረበ ግንኙነት ነበረው?»። ዮሐንስ ማርቆስና ሉቃስ የጳውሎስ የቅርብ ተባባሪዎች ስለነበሩ፥ የጻፉዋቸው መጻሕፍት እንደ እግዚአብሔር ቃል ተቆጥረው ተቀባይነት አግኝተዋል።
2 መጽሐፉ ከብሉይ ኪዳንና ከሐዋርያት አስተምህሮ ጋር ሙሉ ለሙሉ ይስማማል? እግዚአብሔር አይዋሽም፤ ከራሱም ጋር አይቃረንም። ስለሆነም መጽሐፉ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳንና በሐዋርያት አማካይነት ካስተማረው አሳብ ጋር መስማማት አለበት። ካልተስማማ፥ መጽሐፉ የእግዚአብሔር ቃል ሊሆን አይችልም።
3 መልእክቱ የሚጠቅመው ለመላው የክርስቶስ አካል ነው ወይስ ለአንድ ግለሰብ ወይም ቤተ ክርስቲያን? ሐዋርያት የጻፉት ጽሑፍ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ አካል አልሆነም። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የጻፈው አንድ መልእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሌለ እናውቃለን። አንዳንድ መልእክቶች ብዙ መንፈሳዊ እውነት ወይም ለቤተ ክርስቲያን የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ አልነበራቸውም። ስለሆነም የጥንት ቤተ ክርስቲያን አባቶች አልተቀበሏቸውም። እንደ ፊልጵስዩስ ዐይነት ሌሎች መልእክቶች ምንም እንኳ ለአንድ ቤተ ክርስቲያን የተላኩ ቢሆኑም በየትኛውም ዘመንና ስፍራ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች የሚጠቅም ትምህርት ይዘዋል። ስለሆነም የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸው ታውቋል።
የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የአዲስ ኪዳን አካል የሆኑትን መጻሕፍት ለመወሰን ረዥም ጊዜ የወሰደባቸው ለምን ነበር? በአንድ በኩል አብዛኛዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን ለመለየት ብዙ ጊዜ አልወሰደም ነበር። ጳውሎስ ከሞተ ከጥቂት ትውልዶች በኋላ የእርሱ መልእክቶች፥ አራቱ ወንጌላት፥ 1ኛ ዮሐንስ፥ እንዲሁም የዮሐንስ ራእይ የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸው ተረጋግጧል። ሌሎች መጻሕፍት ረዥም ጊዜ የወሰዱት ለምን ነበር?
- የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ከግብፅ እስከ ሮም ድረስ ተስፋፍታ እንደነበር ማስታወስ ይኖርብናል። አንዳንድ መጻሕፍት የተጻፉት በኢየሩሳሌም ሲሆን፥ ሌሎቹ የተጻፉት በሮም ነበር። እነዚህ መጻሕፍት በእጅ ተባዝተው በብዙ መቶ ኪሎ ሜትር ተራርቀው ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት እስኪላኩ ድረስ ጊዜ ወስዶ ነበር። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ደግሞ መጽሐፉን አንብበው እስኪረዱ ድረስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ለመወሰን ጊዜ ይወስድባቸው ነበር። ስለዚህ አንድን መጽሐፍ እንደ እግዚአብሔር ቃል መቀበሉ ከባድ ውሳኔ እንደሆነም ተገንዝበው ነበር።
- የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ስለ አንድ ጉዳይ ተነጋግረው ለመወሰን ይቸገሩ ነበር። አንድ መሪ ከኢየሩሳሌም ወደ ሮም ለመድረስ በወራት ለሚቆጠር ጊዜ ጉዞ ማድረግ ነበረበት። ስለሆነም በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት ቢያገለግሉም፥ መሪዎቹ ተገናኝተው የሚወያዩበትና የሚወስኑበት መድረክ ባለመኖሩ እስከ 350 ዓ.ም. ድረስ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል አካል መሆናቸው በይፋ አልተረጋገጠም ነበር።
- የጥንት ክርስቲያኖች እንደ ዕብራውያን ያሉትን መጻሕፍት ማን እንደጻፋቸው አያውቁም ነበር። ስለሆነም መሪዎቹ የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን ከመቀበላቸው በፊት በጸሎት ይገመግሟቸው ነበር።
- እንደ 2ኛ ዮሐንስ ያሉት መጻሕፍት ቀን ዓለም አቀፋዊ መልእክት ስላልነበራቸው፥ የእግዚአብሔር ቃል አካል ይሁኑ ወይም አይሁኑ የሚለው ሲያከራክር ቆይቷል።
ይህ የምርጫ ሂደት ሙሉ ለሙሉ የሰው ሥራ ነበር? እነዚህ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የእግዚአብሔር ቃል ለሆኑት «ዕውቅና እንዲሰጡ» መግለጻችን ይታወሳል። መጽሐፎቹ ቢመረጡም ባይመረጡም የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸው አይቀርም። ነገር ግን ቃሉን እንዲጽፉ ሰዎችን የቀሰቀሰው መንፈስ ቅዱስ የምርጫውንም ሂደት መርቷል። በመሆኑም መንፈስ ቅዱስ በጥንት ክርስቲያኖች ልብ ውስጥ በመሥራት፥ እነዚህ መጻሕፍት ከሌሎች የተለዩ መሆናቸውን እንዲነዘቡ አስችሏቸዋል። እነዚህ የጥንት ክርስቲያኖች የመጽሐፎቹን ጠቃሚነት እንዲገነዘቡ፥ መንፈስ ቅዱስ እነርሱና የቤተ ክርስቲያን መሪዎቻቸው በ27ቱ መጻሕፍት ላይ የነበረውን የእግዚአብሔርን እጅ እንዲመለከቱ መርቷቸዋል። አዲስ ኪዳንን በምናነብበት ጊዜ እነዚህ መጻሕፍት እውነትን በማቅረቡ በኩል ምን ያህል ከፍተኛ ሚና እንደሚወጡ ልንገነዘብ እንችላለን። ከእነዚህ መጻሕፍት መካከል አንዱ ቢጎድል፥ ስለ እግዚአብሔር አሳብ አንድ ጠቃሚ ነገር ይጎድልብን ነበር።
የይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች 27ቱ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውን ያምናሉ። ታዲያ ብዙ ሰዎች ጊዜ ወስደው የእግዚአብሔርን ቃል የማያጠኑት ለምንድን ነው? ለ) የእግዚአብሔርን ቃል በጥንቃቄ ከማጥናት ይልቅ ቪዲዮ ወይም ሌሎች የማብራሪያ መጻሕፍትን የእምነታችን ምንጮች ስናደርግ መጽሐፍ ቅዱስ የእውነት ዋንኛ ዳኛ ነው የሚለውን በተግባራችን ምን እያደረግን ነው? ሐ) እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር እንድንለካበት እንከን የሌለውና የማይለወጥ ቃል የሰጠን ለምን ይመስልሃል?
በእጃችን ያለው የአዲስ ኪዳን ቅጂ ምን ያህል አስተማማኝ ነው?
የውይይት ጥያቄ፡- ሙስሊሞች ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ለውጠዋል ብለው ይናገራሉ። ሀ) ይህ በእምነታችን ላይ የተሰነዘረ አደገኛ ክስ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ለዚህ ክስ ምን መልስ ትሰጣለህ?
ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ታላላቅ ከተሞች፥ በክርስቲያኖች እጅ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ በስሕተት የተሞላና በክርስቲያኖች የተለወጠ እንደሆነ የሚናገሩ ሙስሊሞች ያሳተሟቸው መጻሕፍት ሞልተዋል። ይህም የብዙ ደካማ ክርስቲያኖችን እምነት አሽመድምዷል። ይሁንና ሙስሊሞች የሚናገሩት እውነት ይሆን? ምንም እንኳ ይህ ከዚህ መጽሐፍ ዐላማ ውጭ ቢሆንም፥ የአዲስ ኪዳንን ትክክለኛነት ቀጥለን እንመለከታለን። ለሙስሊሞች እንዴት መልስ መስጠት እንዳለብህ ለማወቅ የሚከተሉትን መጻሕፍት ማንበቡ ጠቃሚ ነው፡- ላለማደናገር፥ ማወዳደር፥ ማሰላሰል፥ ማጠቃለል፤ እንድረስላቸው የክርስቲያን-ሙስሊም ውይይት፡፡
በጥንት ጊዜ ወረቀት አገልግሎት ላይ ከመዋሉ በፊት መጻሕፍት የሚጻፉት ከሚከተሉት ሦስት ነገሮች በአንዱ ላይ ነበር። አንዳንድ አጫጭር አሳቦች በሸክላ ላይ ይጻፉ ነበር። ምንም እንኳ በቀላሉ የሚሰበር ቢሆንም፥ ይህ መጻፊያ ቶሎ ስለማያረጅ ለብዙ ምእተ ዓመት ለመቆየት ይችላል። ዛሬ በጥንት ዘመን እንደ ተጻፉ የሚነገርላቸው ሸክላዎች ቢኖሩም፥ መጽሐፍ ቅዱስ ግን በሸክላ ላይ አልተጻፈም። ሁለተኛው መጻፊያ የእንስሳት ቆዳ ነበር። ይህም የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስትጠቀም የነበረውን ብራና የሚመስል ነው። ብራና ብዙ የመቆየት ዐቅም ቢኖረውም፥ የመድረቅ፥ የመሰንጠቅ ወይም ቀለሙ የመፍዘዝ ባሕርይ አለው። ሦስተኛው መጻፊያ ከፖፒረስ (እንደ ወረቀት የተዘጋጀ ተክል) የሚሠራ ሲሆን፥ ብዙ ሳይቆይ የሚያረጅ መጻፊያ ነው። በጥንት ጊዜ ማተሚያ ቤቶች ስላልነበሩና ዳግም ማተም ስለማይቻል ያረጁትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ለመገልበጥ ወይም ሌላ ቅጂ ለማባዛት የሠለጠኑ ጸሐፍት ያስፈልጉ ነበር። የጥንት ሥነ ጽሑፍ ምሑራን መጽሐፍ ቅዱስን በተለይም የአዲስ ኪዳን ምንባቦችን በመመርመር፥ የሚከተሉትን ነገሮች አጢነዋል፡፡
- ጸሐፍቱ የእግዚአብሔርን ቅዱስ ቃል የሚጽፉ መሆናቸውን ተገንዝበዋል። ይህም ጽሑፉን በሚገለብጡበት ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል። ጽሑፉን በትክክል መገልበጣቸውን ለማረጋገጥ ደግሞ ሌሎች ጸሐፍት ያመሳክሩት ነበር። ስለሆነም እነዚህ ጸሐፍት እኛ ለጋዜጣ ጽሑፍ ከምናደርገው የበለጠ ጥንቃቄ አድርገዋል።
- የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ የተጻፉት በግሪክ ቋንቋ ነው። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ብንመረምር፥ የሕትመት ስሕተቶችን ልንመለከት እንችላለን። አንዳንድ ጊዜም የትርጉም ስሕተቶች ያጋጥማሉ። አንድ ሰው ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላ ቋንቋ በሚተረጉምበት ጊዜ፥ የምንጭ ቋንቋውን የሚመስል አሳብ ለማቅረብ እንደሚቸገር እንረዳለን። ለዚህም ምክንያቱ ቃላት የተለያየ ትርጉም ስላላቸው ነው። ብዙውን ጊዜ አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የሚወጡት የመጀመሪያውን መጽሐፍ አሳብ ይበልጥ የሚገልጹ ትርጉሞችን ለማዘጋጀት በሚደረግ ጥረት ነው።
- እነዚህ ጸሐፍት መጻሕፍቱን በሚገለብጡበት ጊዜ፥ በቅጂው ሂደት ወቅት አንዳንድ ስሕተቶች ለመከሰት ችለዋል። ከጋዜጣ ላይ አንድ ጽሑፍ ወስደህ በእጅህ አምስት ጊዜ ብትገለብጥ፥ በአንድ ወይም በሁለት ቅጂዎች ላይ ስሕተት ልትሠራ ትችላለህ። ከዚያም ቅጂዎቹን ለአምስት ጓደኞችህ ብትልክና ሌሎች አምስት ሰዎች በእጃቸው ገልብጠው እንዲልኩ ብታደርግ፤ ስሕተቶቹ እየበዙ ይሄዳሉ። ስሕተት ያለባቸውን ቅጂዎች የተቀበሉት ሰዎች ስሕተቶቹን ይገለብጣሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ራሳቸው ተጨማሪ ስሕተቶችን ይሠራሉ። ስለሆነም ቅጂዎችን ለሌሎች በሚያስተላልፉበት ጊዜ የአንተን ብቻ ሳይሆን የራሳቸውንም ስሕተቶች አብረው ያስተላልፋሉ። ይህ በአንድ የጋዜጣ ጽሑፍ ላይ ሊከሰት ከቻለ፥ ለብዙ ዓመታት ሲገለበጡ የኖሩት ብዙ የአዲስ ኪዳን ቅጂዎች ሁኔታ ምን ሊመስል እንደሚቻል መገመት ይቻላል።
- አዲስ ኪዳን ከጥንቱ ሥነ ጽሑፎች ሁሉ በቅጂው ጥራት ተወዳዳሪ አልተገኘለትም። ምሑራን ከ5000 በላይ ሙሉ ወይም ከፊል የአዲስ ኪዳን ምንባቦችን የያዙ ቅጂዎች አሰባስበዋል። ምሑራን እነዚህን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተሰበሰቡትን ጥንታዊ ቅጂዎች በሚያነጻጽሩበት ጊዜ፥ አንዳንድ ልዩነቶች ቢኖሩባቸውም የትኛውም ግድፈት የክርስቲያኖችን አስተምህሮ እንደማያፋልስ ተገንዝበዋል። ከሌሎች መዛግብት ጋር ሲነጻጽር፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙ ልዩነቶች በጣም አነስተኛ ናቸው። (ለምሳሌ፥ በሉቃስ 10፡1 እንዳንድ የአዲስ ኪዳን መዛግብት 70፥ ሌሎች ደግሞ 72 ደቀ መዛሙርት እንደ ተላኩ ይናገራሉ።)
- ከጥፋት ተርፈው ከቆዩት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አንዳንዶቹ በጣም አርጅተዋል። አንዳንዶቹ ጥናታዊ መጻሕፍት የተገለበጡት ደራሲው ከጻፋቸው ከ1000 ዓመት በኋላ ሲሆን፥ አዲስ ኪዳንን በተመለከተ ግን የመጀመሪያው ጽሑፍ ከተጻፈ ከአርባ ዓመት በኋላ የተባዙ ቅጂዎች አሉ። ለምሳሌ፥ ምሑራን በ125 ዓ.ም. የተባዛ የዮሐንስ ወንጌል ቅጂ አግኝተዋል። ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈው በ90 ዓም አካባቢ በመሆኑ፥ ይህ ከ40 ዓመት ያነሰ ጊዜ እንደሆነ ያመለክታል። እንደዚሁም በ60 ዓም. አካባቢ የተባዛ የማቴዎስ ወንጌል ቅጂ ተገኝቷል። ይህም ብዙዎቹ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ከመጀመሪያው ጽሑፍ ጋር እጅግ የሚቀራረቡ ቅጂዎች እንዳሏቸው ያመለክታል።
- ምሑራን አሁን ያሉትን በሺዎች የሚቆጠሩ ልዩ ልዩ ቅጂዎችና ጥንታዊ ትርጉሞችን (ለምሳሌ ላቲን) ካነጻጸሩ በኋላ፥ ጸሐፍት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን በከፍተኛ ጥንቃቄ እንደገለበጡ አረጋግጠዋል። በተጨማሪም የአዲስ ኪዳን ምንባቦችን የሚጠቅሱ ወይም የሚያብራሩ ጥንታዊ የማብራሪያ መጻሕፍትም አሉ። ይህ ሁሉ ምሑራን ዛሬ በእጃችን ያለው የአዲስ ኪዳን ቅጂ ትክክለኛ እንደሆነ እንዲያረጋግጡ ረድቷቸዋል።
ከነዚህ ሁሉ እውነቶች የተነሣ ምሑራን መዛግብቶችን በማነጻጸርና ስሕተቶችን በማረም በእጃችን ያለው የአዲስ ኪዳን ቅጂ ማቴዎስ፥ ጴጥሮስ ወይም ጳውሎስ በመጀመሪያ ከጻፉት ጋር 95 በመቶ ተመሳሳይ እንዲሆን ለማድረግ ችለዋል። አንዳንድ ጥያቄዎችን የሚያስነሡ ጉዳዮች ቢኖሩም፥ የምንባቡን ፍች የማይለውጡ አነስተኛ ዝርዝር ጉዳዮች ብቻ ናቸው። ቁርዓንን ጨምሮ የትኛውም መጽሓፍ የዚህ ዓይነት ትክክለኛነት የለውም። በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ጥቂት የትክክለኛነት ጥያቄ እንዳለ እሙን ቢሆንም፥ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ ለመሆኑ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ ሊገባን አይገባም። የመጀመሪያዎቹ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች በጻፉትና ዛሬ በእጃችን በሚገኘው መጽሐፍ መካከል ይህ ነው የሚባል ሁነኛ ለውጥ የለም። ትርጉሞችም በከፍተኛ ጥንቃቄ የተዘጋጁ በመሆናቸው፥ በመጀመሪያው ጽሑፍና በትርጉሞቹ መካከል የሚገኘው ለውጥ በእምነታችን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ብለን ሳንጠራጠር እንደ እግዚአብሔር ቃል መቀበል እንችላለን።
ለመሆኑ ክርስቲያኖች ዛሬ በእጃችን ያለው መጽሐፍ ምንም ስሕተት የለውም ለማለት እንችላለን? አንችልም። ነገር ግን ሁለት ነገሮችን መናገር ይቻላል። አንደኛው፥ የመጀመሪያው የሐዋርያት ጽሑፍ ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሔር ቃል ነው። የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑም፥ ሐዋርያቱ የተጠቀሙበትም ቃል ሆነ የጻፉት አሳብ አንዳች ስሕተት የለውም። እንደ እግዚአብሔር ሁሉ፥ እነዚህም መጻሕፍት ውሸት የለባቸውም (ያዕ. 1፡17 ዘኁል. 23፡19)። ሁለተኛው፥ በየዘመኑ የተባዙት ቅጂዎች ስሕተት ባይታጣባቸውም፥ እነዚህ ልዩነቶች ግን አንዳች የአስተምህሮ ለውጥ አላስከተሉም። ስለ እግዚአብሔር፥ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ስለ ደኅንነት፥ ስለ መንግሥተ ሰማይ፥ ሲኦል የምናውቀው ሁሉ ምንም ዓይነት ስሕተት የለውም። ስለሆነም ቅጂዎቹ በሚባዙበት ጊዜ ስሕትቶች እንደ ተከሰቱ ብናምንም፥ የትኞቹም ስሕተቶች ስለ ደኅንነትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የምናምነውን እውነት አይለውጡም።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች የሚያጠኑት መጽሐፍ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ሙሉ በሙሉ ማመን አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ትክክል ነው ወይስ አይደለም በማለት መጠራጠር ብንጀምር ምን ይከሰታል?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)