የማርቆስ ወንጌል ዓላማ

እንደ ዮሐንስ (ዮሐ 20፡31)፥ ማርቆስ ዓላማውን በግልጽ አላሰፈረም። ነገር ግን ማርቆስ ወንጌሉን የጻፈባቸው ሁለት ዐበይት ምክንያቶች አሉ። በመጀመሪያ፥ ማርቆስ ወንጌሉን የጻፈው ለአሕዛብ ስለ ክርስቶስ ለመናገር ነበረ። የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ሲሞቱ፥ ቤተ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ማንነት ግልጽ ታሪክ ይዛ መገኘቷ ወሳኝ ሆነ። ሁለተኛ፥ ማርቆስ ክርስቲያኖች እንደ ክርስቶስ ተከታዮች እንዴት መኖር እንዳለባቸው ሊያስተምራቸው ፈለገ።

የዉይይት ጥያቄ፡- ማር. 1፡1 አንብብ። ሀ) ማርቆስ መጽሐፉ ስለ ምን እንደሚናገር ግለጽ? ይህ ስለ ዓላማው ምን ይነግረናል? ለ) ማርቆስ ኢየሱስን ማን ብሎ ጠራ?

  1. ማርቆስ መጽሐፉን የኢየሱስ ክርስቶስ «ወንጌል» ሲል ይጠራዋል። በግሪክ ቋንቋ ወንጌል ማለት «መልካም የምሥራች» ነው። ስለሆነም፥ ማርቆስ የዓለም መሪዎች የነበሩትን ሮማውያን ጨምሮ ለዓለም ሁሉ መልካም የምሥራች ጽፎ ነበር። በተጨማሪም ማርቆስ ወንጌሉን፥ «መጀመሪያ» ይለዋል። ለዚህም ምክንያቱ የክርስቶስ ታሪክ በተከታዮቹ አገልግሎት መቀጠሉ ነው። ታሪክ ሁሉ የክርስቶስ ሥራ ነው ማለት ይቻላል። ስለሆነም ማርቆስ ስለ ክርስቶስ የሦስት ዓመታት አገልግሎት አጠር ያለ ገለጻ ያደርጋል። እንደ ማቴዎስና ሉቃስ፥ ስለ ክርስቶስ ልደት አልተረከም፡፡ ማርቆስ እጥር ምጥን ባለ ይዘት ስለ ክርስቶስ ማንነትና የተገናኛቸውን ሰዎች ስለለወጠበት ሁኔታ ገልጾአል።
  2. አንዳንድ ምሑራን ማርቆስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሞተበትን ምክንያት ለሮማውያን ለማስረዳት እንደ ሞከረ ያስባሉ። መስቀል ወንጀለኞች እንጂ መልካም ሰዎች የሚሞቱበት አልነበረም። የእግዚአብሔር ልጅ እንዴት በመስቀል ላይ ሊሞት ይችላል? ማርቆስ ግን መስቀሉ የእግዚአብሔር ርግማን ሳይሆን፥ የዕቅዱ አካል እንደነበረ ያሳያል። ክርስቶስ ተአምራትን መፈጸሙ፥ አጋንንትን ማውጣቱ፥ የወደፊት ክስተቶችን መተንበዩና ከሞት መነሣቱ ሁሉ፥ የክርስቶስ ሞት አጋጣሚ፥ ወይም እርባና ቢስ አሳዛኝ ድርጊት ወይም የወንጀለኝነቱ ምልክት እንዳልሆነ ያረጋግጣል።
  3. ማርቆስ ክርስቲያን ላልሆኑት አንባቢያን፥ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነና ሊያምኑበት የሚገባ መሆኑን ለማሳመን ይፈልጋል። ክርስቶስ «የእግዚአብሔር ልጅ» መሆኑን ያውቅ ስለነበር፥ ታሪኮቹ መለኮታዊ ባሕርያቱን ያሳያሉ። ማርቆስ ታሪኩን የጀመረው በክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነት እንደሚያምን በመግለጽ ሲሆን፥ ከመጨረሻ ታሪኮቹ በአንዱ ውስጥ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የተናገረ ሮማዊ ተጠቅሷል (ማር. 15፡39)። ማርቆስ ስለ ክርስቶስ የገለጸውን ታሪክ በምንመለከትበት ጊዜ፥ የክርስቶስን አስተሳሰብ የሚያሳዩ ቀጣይ አሳቦች ተንጸባርቀውበታል።

ሀ. «ጌታ» ለሆነው ክርስቶስ መንገድ ለመጥረግ መጥምቁ ዮሐንስ ያበረከተው ድርሻ (ማር. 1፡3)፡፡

ለ. እግዚአብሔር አብ ክርስቶስን ልጅ ሲል በግልጽ ጠርቶታል (ማር. 1፡11፤ 9፡7)።

ሐ አጋንንት፥ ክርስቶስ «የእግዚአብሔር ቅዱሱ» (የእግዚአብሔር ሌላው ስሙ) እና «የእግዚአብሔር ልጅ» እንደሆነ ያውቃሉ (ማር. 1፡24፣ 3፡11 5፡7)።

መ. ክርስቶስ በአምላክነቱ ኃጢአትን ይቅር ከማለቱም በላይ፥ የሰዎችን ልብ ያውቅ ነበር (ማር. 2፡5፥ 8-10)፡፡

ሠ. ክርስቶስ «የብሩኩ ልጅ» መሆኑን ተቀብሏል (ማር. 14፡62)፡፡

ረ አሕዛብ የሆነው ሮማዊ ወታደር ሳይቀር፥ ክርስቶስ «የእግዚአብሔር ልጅ» መሆኑን ተረድቷል (ማር. 16፡39)።

  1. ማርቆስ ክርስቶስ የሞተው፥ «ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት» መሆኑን አመልክቷል። (ማር. 10፡45)። ከመጽሐፉ ቢያንስ ግማሽ ያህሉ በኢየሱስ ሞት ላይ ያተኩራል።

የውይይት ጥያቄ፡– ማር. 1፡12-13፤ 3፡22-27፤ 8፡34-38፤ 10፡29-30፥ 33–34፣ 13፡9-13 አንብብ። ከክርስቶስ ሕይወትና ትምህርት፥ ስለ ፈተናና ስደት ምን እንማራለን?

  1. ማርቆስ በስደት ውስጥ ለሚያልፉ ክርስቲያኖች (ምናልባትም በኔሮ ዘመን)፥ የማበረታቻ አሳቦችን ይሰጣል። ይህ ክርስቶስን የመከተላቸው አካል እንደሆነ ያስረዳል። እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ በስደት ጊዜ ክርስቶስን መካድ የለበትም ይላል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: