ማርቆስ 6፡1-56

1. ኢየሱስ ባደገባት የናዝሬት ከተማ ተቀባይነትን አጣ (ማር. 6፡1-6)

ለብዙ ሰዎች፥ በተለይም እርሱን በቅርብ ለሚያውቁት ከስብእናው አልፎ የኢየሱስን መለኮታዊነት መመልከቱ ከባድ ነበር። በሥጋዊ ሁኔታው ኢየሱስን ከሌሎች ሰዎች የሚለይ ምንም ነገር አልነበረም። በአሁኑ ዘመን የክርስቶስን ሥዕል በብርሃን አሸብርቆ መሥራት የተለመደ ቢሆንም፥ ትክክለኛ መልኩ እንደዚህ ዓይነት አልነበረም። የናዝሬት ሰዎች ለምን ሊቀበሉት አልፈቀዱም? ምክንያቱም ከተአምራቱ ሁሉ ባሻገር፥ መለኮታዊነቱን ሊመለከቱ አልቻሉም ነበር። ኢየሱስ እንደ ሰው ተራ የአናጺነት ተግባር የሚያከናውን ሰው ነበር። ቤተሰቦቹ ድሆችና በማኅበረሰቡ ውስጥ የማይታወቁ ነበሩ። በሥጋዊ ሁኔታው መሢሕ የሚያስመስል ምንም ዓይነት ነገር አልነበረውም። ማርቆስ የኢየሱስን መለኮታዊነትና ሰብአዊነት ሚዛናዊ አድርገን ማነጻጸር እንዳለብን ገልጿል። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም፥ ሰው ነው። ግልጽ ተቃውሞ በነበረበት ናዝሬት ኢየሱስ ተአምራትን የማድረግ ኃይል ቢኖረውም፥ ይህንኑ ከማድረግ ተቆጥቧል።

2. ኢየሱስ 12ቱን ደቀ መዛሙርቱን ላከ (ማር. 6፡6-13)።

አንድ ሰው ከተወሰነ ሥራ በላይ ሊያከናውን አይችልም። ስለሆነም፥ አገልግሎቱ እንዲያድግና ወደ ሁሉም ሰው እንዲደርስ ከተፈለገ፥ ክርስቶስ ሥራውን ለማከናወን ሌሎችን ማሠልጠን ያስፈልገው ነበር። ክርስቶስ ለተወሰነ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ሲያሠለጥን ነበር። እነዚህ ደቀ መዛሙርት ስለ ንስሐ ሲሰብክ፥ አጋንንትን ሲያወጣና ሰዎችን ሲፈውስ ተመልክተዋል። አሁን የተመለከቱትን ተግባራዊ የሚያደርጉበት ጊዜ ደረሰ። ክርስቶስ ብዙ ሰዎች ወንጌል የሚሰሙበትን አጋጣሚ ለማመቻቸትና ደቀ መዛሙርቱን በመፈተን ለአመራር ለማዘጋጀት ሲል፥ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው። ለዚህም ሁለት ምክንያቶች ነበሩ። በመጀመሪያ፥ እርስ በርሳቸው መደጋገፍ ነበረባቸው። አንድ ሰው (ወንጌላዊ) በቀላሉ ብቸኝነትና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ሊሰማው ስለሚችል፥ ሁለት ሆነው ኅብረት ሊያደርጉና ሊበረታቱ ችለው ነበር፡፡ ሁለተኛ፥ በአይሁዶች ልማድ አንድን እውነት ለማጠናከር ቢያንስ የሁለት ሰዎች ምስክርነት ወሳኝ ነበር (ዘዳግ 19:5)። ከዚህ የተነሣ፥ ስለ ክርስቶስ በቂ ምስክሮች ነበሩ። ክርስቶስ ያደረገውን ሁሉ (መስበክ፥ አጋንንትን ማውጣትና መፈወስን) 12ቱ ደቀ መዛሙርት የማከናወን ብቃት ተሰጥቷቸዋል። ማርቆስ ክርስቶስ ይህንን ሥልጣንና ኀይል እንደ ሰጣቸው ያሳያል። በተመሳሳይ መንገድ የእኛም ኃይልና ሥልጣን የሚመነጨው ከራሳችን ሳይሆን ከክርስቶስ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- መሪዎች ብዙውን ጊዜ እንደ ልባቸው የሚረዳቸው ሰው እንደሌለ በመግለጽ ያማርራሉ። ሀ) ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ማሠልጠኑ እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን መሪ አገልግሎቱን ለማስፋትና የቤተ ክርስቲያንን የአመራር ፍላጎቶች ለማሟላት፥ ሊያከናውን ስለሚገባው ተግባር ምን ዓይነት አርአያነትን ይሰጣል? ለ) ይህ ብዙም የማይታየው ለምን ይመስልሃል? ሐ) አንተ የቤተ ክርስቲያን መሪ ከሆንህ፥ እግዚአብሔር አሠልጥነህ በሥራህ ውስጥ የምታሳትፋቸውን አምስት ወጣቶች እንዲሰጥህ በጸሎት ጠይቅ።

3. የመጥምቁ ዮሐንስ አንገት መቀላት (ማር. 6፡14-29)

ማርቆስ የዮሐንስን መሞት የገለጸው አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮችን በመጨመር ነበር። ለምን? ምናልባትም የመጥምቁ ዮሐንስ ሞት በሌሎች ላይ ለሚደርሰው ስደት አርአያነት ያለው ተግባር ሳይሆን አይቀርም። መጥምቁ ዮሐንስ ክፋትን ስለ ተቃወመ ታስሮ ነበር። ሰዎች በኃጢአታቸው ሲቀጥሉ ዝም ብሎ ሊመለከታቸው ይችል የነበረ ቢሆንም፥ ይህን አላደረገም። እኛም በተመሳሳይ መንገድ የሰዎችንና የአገራችንን ኃጢአት ማጋለጥ አለብን። ይህንን በምናደርግበት ጊዜ ግን ስደት ሊገጥመን እንደሚችል ማወቅ አለብን።

4. ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን መገበ (ማር 6፡30-44)።

ማርቆስ ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን እንደ መገበ በገለጸበት ታሪክ ውስጥ፥ ስለ ጠቅላላዎቹ ደቀ መዛሙርት የስብከት ጉዞ ዘግቧል። «ሐዋርያ» የሚለው ቃል በግሪክ ቋንቋ ሌላውን ሰው ወክሎ አንድን ተግባር የማከናወን ሥልጣን የተሰጠውን ሰው ያመለክታል። በአዲስ ኪዳን ውስጥ፥ ይህ ቃል በሁለት የተለያዩ መንገዶች አገልግሏል። በመጀመሪያ፥ ይህ ለ12ቱ ደቀ መዛሙርት የተሰጠ ስያሜ ነው። አዲስ ኪዳን ሁልጊዜም እነዚህ 12 ደቀ መዛሙርት ቤተ ክርስቲያንን ለመምራትና ከእግዚአብሔር የሆነውንና ያልሆነውን ለመበየን ሥልጣን እንደ ተሰጣቸው አድርጎ ያቀርባል። በተጨማሪም፥ አዲስ ኪዳን ጳውሎስም የ12ቱን ያህል ሥልጣን እንዳለው ያስተምራል (ሮሜ 1፡1)። ከጳውሎስና ከ12ቱ ሐዋርያት ሞት በኋላ በቤተ ክርስቲያን እንዲህ ዓይነት ልዩ ስፍራ የነበረው ሰው እንደ ነበር የሚያመለክት መረጃ የለም። ከእነዚህ መሪዎች ሞት በኋላ የዚህ ዓይነቱ ሥልጣን እንዳበቃ የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ጸሐፊዎች ጠቅሰዋል። ስለዚህ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሰዎች ምን ሊያደርጉ እንደሚገባ ለመናገር የሚያስችል ፍጹም ሥልጣን ያላቸው ሐዋርያት ይኖራሉ ብለን መጠበቅ የለብንም። በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በቤተ ክርስቲያን ላይ ሙሉ ሥልጣን ያለን ሐዋርያት ነን የሚሉ ሰዎች ተግባር፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለው አደገኛ ትምህርት ነው።

ሁለተኛ፥ ሌሎችም ሐዋርያት ተብለው ተጠርተዋል። ምንም እንኳ የተለየ ሥልጣን ቢኖራቸውም፥ የ12ቱንና የጳውሎስን የሚያህል ሥልጣን አልነበራቸውም። እነዚህ አገልጋዮች (እና የአዲስ ኪዳን የትንቢት ስጦታ የነበራቸው ሰዎች) ዐበይት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ተደርገው የሚቆጠሩ ሲሆን፥ ምናልባትም እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን የመትከልና በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት የመምራት ስጦታ ከሰጣቸው ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ሳይሆኑ አይቀሩም። በርናባስ (የሐዋ. 14፡14፥ የጌታ ወንድም የሆነው ያዕቆብ (ገላ. 1፡19)፥ አንዲራኒቆንና ዩልያን (ሮሜ 16፡7) ሐዋርያት መሆናቸው ተጠቅሷል።

ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን ከመገበበት ታሪክ፥ ስለ ኢየሱስ አያሌ እውነቶችን እንመለከታለን። በመጀመሪያ፥ ኢየሱስ የሰዎችን ፍላጎት ለማሟላት፥ ነገሮችን የመለወጥና የማብዛት ሥልጣን ያለው የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ሁለተኛ፣ ኢየሱስ መልካም እረኛ መሆኑን እንመለከታለን። በመዝሙር 23፡1 እንደ ተመለከተው፥ ክርስቶስ የበጎቹን ፍላጎት ያሟላል። ይህ ታሪክ የክርስቶስ ተከታዮች ለሥጋዊ ፍላጎቶቻቸው፥ በተለይም ለሚበሉት ምግብ መጨነቅ እንደሌለባቸው ያስተምራል። ክርስቶስ ሁልጊዜም ለተከታዮቹ በመራራት ፍላጎታቸውን ያሟላላቸዋል። በመጨረሻም፥ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት (በተለይም ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች) ያላቸውን ትንሽ ነገር ወስዶ በማብዛት የእግዚአብሔርን መንጋ ፍላጎቶች እንደሚያሟላ የሚያስገነዝብ ነው። እንዲሁም፥ የሰዎችን ፍላጎቶች እንዴት እናሟላለን ብለን ሳንጨነቅ፥ ለእግዚአብሔር ያለንን በልግስና ልንሰጥና እግዚአብሔር እንደሚያባዛው ልንተማመንበት ይገባል። ምክንያቱም ሕዝቡ የእግዚአብሔር ሀብት በመሆናቸው፥ እግዚአብሔር ይራራላቸዋል፤ ስለሆነም፥ መሪዎቹ የሕዝቡን ፍላጎቶች እንዲያሟሉም ይጠቀምባቸዋል።

5. የኢየሱስ በውኃ ላይ መራመድ (ማር. 6፡45-56)

አንዳንድ ጊዜ ፍርሃት ተፈጥሯዊና ጠቃሚ ምላሽ ነው። በመኪና መንገድ ላይ ተጠንቅቀን እየሄድን ሳለ፥ ጥሩምባው ሲነፋና ፍሬኑ በሚያዝበት ወቅት ሰቅጣጭ ድምፅ ሲሰማ፥ በፍርሃት ከመንገዱ ፈቀቅ እንላለን። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ፍርሃት ያለማመን ምልክት ይሆናል። የክርስቶስ ተከታዮች እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ በእምነት ለመመላለስ ከፈለጉ፥ የስደትንና የችግሮችን ፍርሃት ማስወገድ አለባቸው። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ በውኃ ላይ ሲራመድ በማየታቸው፥ (አይሁዶች) መናፍስት ከውኃ ውስጥ ወደ ላይ እንደሚወጡ የሚያስረዳ ባሕል ነበራቸው) እና በነፋሳት ላይ ባሳየው ኀይል በመደነቃቸው፥ «ያለ መጠን እጅግ ተገረሙ ስለ እንጀራው አላስተዋሉምና ነገር ግን ልባቸው ደንዝዞ ነበር።” (ማር. 6፡51-52)። ክርስቶስን በበለጠ ስናውቅ፥ እርሱ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንዳለ ሁልጊዜም ማስታወስ አለብን። እርሱ ከእኛ ጋር ካለ የሚያስፈራን ነገር አይኖርም። ክርስቶስ ፍላጎታችንን ሁሉ ከማሟላቱም በላይ፥ የተፈጥሮንም ኃይል ይቆጣጠራል። ነፋስን መቆጣጠር ከቻለ፥ ማዕበልንም ሊቆጣጠር ይችላል። ማዕበሉን እንደተቆጣጠረ ሁሉ፥ ደቀ መዛሙርቱ የሚጋፈጧቸውን ችግሮችና ስደትም ሊቆጣጠር ይችላል። የሕይወት ማዕበል በሚያጋጥመን ጊዜ የምንፈራ ከሆነ ክርስቶስ ነገሮችን ሁሉ የሚቆጣጠር የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆኑ እምነት የለንም ማለት ነው። እምነት በቃል ወይም በዝማሬ ብቻ የሚገለጽ አይደለምና። ሕይወታችንን በምናምነው እውነት ላይ ተመሥርተን ልንመራ ይገባል። ክርስቶስ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነ ካመንን፥ እርሱ ነገሮችን እንደሚቆጣጠር በማወቅ ወደ ሕይወታችን ለሚመጡ ጉዳዮች ሁሉ በእርሱ ልንተማመን ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በፍርሃት ስለተያዝክበት ጊዜ ግለጽ። ይህ በክርስቶስ ላይ ስላለህ የእምነት ጥልቀት ምን ያሳያል? ለ) ፍርሃት፥ አንድ ክርስቲያን እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ እንዳይኖር የሚያደርገው እንዴት ነው? ሐ) የፍርሃት መድኃኒቱ ምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

4 thoughts on “ማርቆስ 6፡1-56”

 1. ቤእውነት እግዚአብሔር ይህን ትምህርት ያዜጋጁ አተባባርያን ይባርክ ።ምክንያቱም የጌታን ቃል ላማማር ግዜ ላአጡ እንዴ እኔ ሌሜስሉ ሳወች ቤጣም ጣቃም ትምህርት ናው ስለዝህ የጌታ ሀዳራ አሌባቹና ብቻል ብቻል በስልክ ቁጡርንም ውስዳቹ ዴውላቹም ዛሬ የfb bibel ጥናት ጊዜ ናው እንድትሉ የሳማይ ማንግስት ወራሽ እንድንሆን እግዚአብሔር ይርዳን ስሜ እሽቱ ኢያሱ ሌንጫ እባላሀላው ስልክ ቁጡር 0916353305 ዩንቭርስት ተማር ሀዋሳ ኔኝ ።፨፨፨፨፨።

  1. ይህንን የመፅሐፍ ቅዱስ ጥናት በሥልኬ በማገኛቴ በጣም ደሥተኛ ነኝ እግዝአብሔር ዘመናችሁን ይባርክ! የዕኛ የክርስትያኖች ዋናው የመኖራችን ዓላማ የእግዝአብሔርን ቃል በአግባቡ በመረዳት ለሌሎችም ማበማሰረድት በጋራ የእርዝአብሔርን መንግሥት መውረሥ ስሆን ይህንን ተግባር በይፋ ሥለጀመራችሁ ተባረኩ እኔ ለእናንተ የምያሣሥበችሁ ጥናት ቀን በሥልኬ ደውላችሁ እንድታሣውቁ በጌታ ፍቅር እጠይቃለሁ 0924815048:0947494805:0969943311:0905153431 የኔ ሥልኮች ናቸው! GOD BLESS YOU!!

   1. ወንድሜ ብሩክ፣

    በመጀመሪያ ለዝግጅት ክፍላችን ስለጻፍክልን እና አበረታች መልእክትህን ስላደረስከን አመሰግናለሁ፡፡ የወንጌል በድረገጽ ዌብ ሳይት ተከታታይ (follower) በመሆን ለጠየከው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ትችላለህ፡፡ ይህን ለማድረግ፣ የወንጌል በድረ-ገጽ አገልግሎት ዌብ ሣይት (https://ethiopiansite.com/) የፊት ገጽ ግርጌ ላይ በመሄድ፣ በስተቀኝ ባልው ክፍት ሣጥን ውስጥ የኢ-ሜይል አድራሻህን በመጻፍና “ድረ-ገጹን ይከታተሉ” የሚለውን ቁልፍ በመጫን የዌብ ሣይቱ ተከታይ (follower) መሆን ትችላለህ፡፡ ይህን ስታደርግ በዌብ ሣይቱ ላይ አዳዲስ ጽሑፎች ሲጫኑ፣ በኢ-ሜይል አድራሻህ የማንቂያ መልእክት (notification) የምታገኝ ይሆናል፡፡

    የወንጌል በድረ ገጽ አገልግሎት ዌብ ሳይት (https://ethiopiansite.com/) በርካታ መንፈሳዊ ጽሑፎችን የያዘ ሳይት ነው፡፡ በዌብ ሳይቱ የድነት (የደኅንነት) ትምሕርቶች (https://goo.gl/fDtBXd)፣ የደቀ መዝሙር ማሰልጠኛ ማኑዋሎች (https://goo.gl/26UzGK)፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መሳሪያዎች (https://goo.gl/Eou24Y)፣ ለተለያዩ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጡ አጫጭር የጥናት ጽሑፎች (https://goo.gl/UWbZjw)፣ ወዘተ ተካተዋል፡፡ እንግዲህ እንደ ምርጫህ ሊንኮቹን በመጫን ጥናትህን ማካሄድ ትችላለህ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የግል ጥያቄዎች ቢኖርህ በሚከተለው ኢሜይል ልትልክልኝ ትችላለህ፣ በደስታ ለመርዳት ዝግጁ ነኝ (tsegaewnet@gmail.com)፡፡

    የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከአንተና ቤተሰብህ ጋር ይሁን። አሜን።

  2. ወንድሜ እሸቱ፣

   በመጀመሪያ ለዝግጅት ክፍላችን ስለጻፍክልን እና እጅግ አበረታች መልእክትህን ስላደረስከን በጣም አመሰግናለሁ፡፡ የወንጌል በድረገጽ ዌብ ሳይት ተከታታይ (follower) ለመሆን የምትሻ ከሆነ የወንጌል በድረ-ገጽ አገልግሎት ዌብ ሣይት (https://ethiopiansite.com/) የፊት ገጽ ግርጌ ላይ በመሄድ፣ በስተቀኝ ባልው ክፍት ሣጥን ውስጥ የኢ-ሜይል አድራሻህን በመጻፍና “ድረ-ገጹን ይከታተሉ” የሚለውን ቁልፍ በመጫን የዌብ ሣይቱ ተከታይ (follower) መሆን ትችላለህ፡፡ ይህን ስታደርግ በዌብ ሣይቱ ላይ አዳዲስ ጽሑፎች ሲጫኑ፣ በኢ-ሜይል አድራሻህ የማንቂያ መልእክት (notification) የምታገኝ ይሆናል፡፡

   የወንጌል በድረ ገጽ አገልግሎት ዌብ ሳይት (https://ethiopiansite.com/) በርካታ መንፈሳዊ ጽሑፎችን የያዘ ሳይት ነው፡፡ በዌብ ሳይቱ የድነት (የደኅንነት) ትምሕርቶች (https://goo.gl/fDtBXd)፣ የደቀ መዝሙር ማሰልጠኛ ማኑዋሎች (https://goo.gl/26UzGK)፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መሳሪያዎች (https://goo.gl/Eou24Y)፣ ለተለያዩ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጡ አጫጭር የጥናት ጽሑፎች (https://goo.gl/UWbZjw)፣ ወዘተ ተካተዋል፡፡ እንግዲህ እንደ ምርጫህ ሊንኮቹን በመጫን ጥናትህን ማካሄድ ትችላለህ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የግል ጥያቄዎች ቢኖርህ በሚከተለው ኢሜይል ልትልክልኝ ትችላለህ፣ በደስታ ለመርዳት ዝግጁ ነኝ (tsegaewnet@gmail.com)፡፡

   የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከአንተና ቤተሰብህ ጋር ይሁን። አሜን።

Leave a Reply

%d bloggers like this: