ማርቆስ 8፡1-38

  1. ኢየሱስ አራት ሺህ ሕዝብን መገበ (ማር. 8፡1-21)

ክርስቶስ ምንም ያህል ሥራ ቢበዛበትም ስለ ሰዎች ጥቅም የሚያስብ ሲሆን፤ ጉዳታቸው ልቡን ይሰማውና ይራራላቸው ነበር። በዚያን ጊዜ ለሰዎች መጎዳት የራራው ክርስቶስ፥ ዛሬም የሚያስፈልገንን ሁሉ በሚመለከትበት ጊዜ ይራራልናል።

ክርስቶስ አሁን አራት ሺህ ሕዝብ ለመመገብ ያነሣሣውን የርኅራኄ ምክንያት ቀደም ሲል አምስት ሺህ ሕዝብ በመገበበት ወቅት፥ ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሮ የነበረውን ትምህርት አጠናክሯል። በዚህም ክርስቶስ ፍላጎታቸውን ሁሉ የሚያሟላ አምላክ መሆኑን አሳይቷል።

ፈሪሳውያን እንዲህ ያለ ታላቅ ተአምራት ቢመለከቱም እንኳ፥ በክርስቶስ ለማመን ፈቃደኞች አልነበሩም። የአንድ ግለሰብ ልብ ከደነደነና በክርስቶስ ላለማመን ከወሰነ፥ ምንም ዓይነት ተአምራት ቢመለከት ሊያምን አይችልም። እግዚአብሔር ኀይሉን ለማሳየት በተአምራት ሊጠቀም ቢችልም፥ ሰዎች ሁልጊዜ በተአምራት ላይ ካተኮሩ፥ ይህ ፍላጎታቸው የእምነት እጥረት እንዳለባቸው ያሳያል። ፈሪሳውያን ክርስቶስ መሢሕነቱን ለማረጋገጥ ከዚያ የበለጡ ተአምራት እንዲሠራ ጠይቀውታል። ክርስቶስ ግን ተአምራት የማያምን ትውልድ ምልክቶች መሆናቸውን በመግለጽ፥ ለማመን ለማይፈልጉ ሰዎች ታምራትን እንደማያደርግላቸው ገልጾአል።

ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ራስን የማጽደቅ አመለካከት እንዳይይዙና ለማመን ተጨማሪ ተአምራትን እንዳይሹ አስጠንቅቋቸዋል። ራስን የማጽደቅ አመለካከት እንደ እርሾ መንፈሳዊነታቸውን በማጥፋት ወደ ሌሎችም ይዛመት ነበር።

12ቱ ደቀ መዛሙርት እንደ ብዙዎቻችን ከመንፈሳዊ እውነት ይልቅ በምድራዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮራቸው፥ የክርስቶስን ትምህርት በተሳሳተ መንገድ ተረጎሙ። የሚያስቡት ክርስቶስ ስለ ፈሪሳውያን ባስተማረው ጉዳይ ላይ ሳይሆን፥ ስለ ምግብ ነበር። ይህም ክርስቶስ ፍላጎታቸውን ሊያሟላ እንደሚችል አለማመናቸውን ያሳያል።

  1. ኢየሱስ ዓይነ ስውሩን ፈወሰ (ማር. 8፡22-26)

ይህ ተአምር በሁለት ደረጃዎች የተከናወነ በመሆኑ፥ በክርስቶስ አገልግሎት ውስጥ ለየት ያለ ነበር። ብዙውን ጊዜ የክርስቶስ ተአምራት በአንድ ጊዜ የተሳካ ውጠቶችን የሚያስገኙ ነበሩ። በዚህ ጊዜ ግን ክርስቶስ መጀመሪያ በታወሩት በሰውዬው ዓይኖች ላይ ምራቁን ቀባ። የግለሰቡ ዓይኖች በከፊል ስለ ተፈወሱለት፥ ሰዎች እንደ ዛፍ ሲመላለሱ አየ። ነገር ግን ክርስቶስ እንደገና ሲዳስሰው ዓይነ ስውር የነበረው ግለሰብ አጥርቶ ለማየት ቻለ።

ይህ ምንን ያሳያል? ይህ አንዳንድ ጊዜ ተአምራት በከፊል ብቻ ውጤታማ እንደሚሆኑ ያሳያል? ዛሬ የመፈወስ ኃይል እንዳላቸው የሚያስቡ አንዳንድ ሰዎች እንደዚያ ይላሉ። ነገር ግን በዚህ ግንዛቤና በክርስቶስ ፈውስ መካከል አንዳንድ ዐበይት ልዩነቶች አሉ። ክርስቶስ አንድም ሰው በከፊል ፈውሶ ብቻ አላሰናበተም። የፈውሱን እርግጠኝነት ተጠራጥሮ እንደገና የተሟላ ፈውስ የሰጠው ራሱ ክርስቶስ ነበር። ማንም ሰው ከክርስቶስ ዘንድ ከፊል ፈውስ አግኝቶ የሄደ የለም። ዛሬም እግዚአብሔር አንድን ሰው በተአምራዊ መንገድ ከፈወሰው፥ ከፊል ሳይሆን ሙሉ ፈውስ ነው።

ክርስቶስ ይህንን ባለ ሁለት ደረጃ ፈውስ ያካሄደው አንዳች መንፈሳዊ እውነት ለማስተማር ይሆን? የአንድን ሰው መንፈሳዊ ዓይኖች መክፈት ማለትም፥ መንፈሳዊ እውነትን መረዳት ብዙውን ጊዜ የሂደት አካል ነው። በአንድ ጊዜ መንፈሳዊ እውነቶችን ሙሉ በሙሉ ሊረዳ የሚችል ሰው የለም። ደቀ መዛሙርቱም አልተገነዘቡም ነበር። ለዚህም ነበር ስለ ክርስቶስ አገልግሎት ብዙ ነገሮችን ከትንሣኤው በፊት ለመረዳት ያልቻሉት። ጳውሎስም ሳይቀር ነገሮችን በድንግዝግዝ እንደሚያይ ለማመን ተገድዷል (1ኛ ቆሮ. 13፡12)። ይህን ስላለ ግን ተስፋ እንቆርጣለን ማለት አይደለም። ይህ ትሑት እንድንሆን ያስተምረናል። በተጨማሪም፥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ማደጋችንን እንድንቀጥል ያስተምረናል።

  1. ጴጥሮስ የኢየሱስን መሢሕነት መሰከረ (ማር. 8፡27-30)

የማርቆስ ወንጌል የተመሠረተው በዚህ አጭር ምንባብ ላይ ነው። ማርቆስ ክርስቶስ መሢሑ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በብዙ የተለያዩ መንገዶች አሳይቷል። በመጨረሻም፥ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ግል እምነታቸው የተጠየቁበት ጊዜ ደረሰ። ብዙውን ጊዜ ሌሎች ሰዎች ወይም ወላጆቻችን የሚያምኑትን ሃይማኖት መከተሉ ቀላል ነው። ነገር ግን ጠቅላላው ማንነታችን በእምነታችን ሊለወጥ በሚችልበት መልኩ በግላችን እውነትን ማመን አለብን። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን በጠየቀበት ሰዓት፥ መጀመሪያ ስለ ሌሎች ከጠየቀ በኋላ፥ የራሳቸውን እምነት እንዲገልጹት አድርጓል።

  1. ኢየሱስ ስለ መጭው ሞቱና የደቀ መዝሙርነት መንገድ አስተማረ (ማር. 8፡31-38)።

ጴጥሮስና ደቀ መዛሙርቱ የክርስቶስን መሢሕነት ከተገነዘቡ በኋላ፥ ጠቅላላው የኢየሱስ አገልግሎትና የማርቆስ ወንጌል ትኩረት ተለውጧል። በመጀመሪያ፥ ምን ዓይነት መሢሕ እንደሆነ የነበራቸውን የተሳሳተ ግንዛቤ ማስተካከል ነበረበት። እርሱ መከራ የሚቀበልና የሚሞት እንጂ፥ ወረራ የሚያካሂድና የሚገዛ ንጉሥ አልነበረም። ሁለተኛ፥ ለደቀ መዛሙርቱ እርሱን መከተል መስቀልን እንደሚያስከትል ነግሯቸዋል። ይህም ክርስቶስን በሚከተሉበት ጊዜ በመንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወታቸው እንደሚሞቱ የሚያመለክት ነበር።

ከዚህ ጊዜ አንሥቶ፥ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለሚመጣው ሞቱ ይናገር ጀመር። መጀመሪያ ይህ ደቀ መዛሙርቱን ስላስደነገጣቸው፥ ጴጥሮስ እንዲህ ዓይነት የመሢሕነት እርምጃ አይድረስብህ አለው። ክርስቶስ ሰይጣን በጴጥሮስ ቃላት ተጠቅሞ ከመስቀል ሊመልሰው የመፈለጉን ፈተና ተገነዘበ። ክርስቶስ ይህን ሁኔታ ስለ ደቀ መዝሙርነትም ለማስተማር ተጠቅሞበታል። ክርስቶስ የሚሞትበትን መስቀል ተሸክሞ ወደ ጎልጎታ በመሄድ ለሰው ልጆች ደኅንነትን አስገኝቷል። ደቀ መዛሙርቱም እያንዳንዳቸው የሚሸከሙት መስቀል ነበራቸው። መስቀላችን መንፈሳዊ ነው። ራሳችን በሕይወታችን ላይ ላለን ቁጥጥር፥ ለዓለማዊ ብልጽግና መሞት አለብን። የደቀ መዝሙርነት መንገድ ማለት ሥጋዊ ሕይወታችንን ጨምሮ በዚህ ዓለም ጠቃሚዎች ናቸው የተባሉትን ነገሮች ሁሉ ማጣትን ያካትታል። ከዚያ በኋላ ለሰው ከሁሉም የበለጠ ዋጋ ያለውን የዘላለምን ሕይወት እናገኛለን። ነገር ግን ሕይወታችንን ብንታደግና በዓለም ጠቃሚዎች የሆኑትን ነገሮች ብንከተል፥ የዘላለም ሕይወታችንን እናጣለን። በስደት ጊዜ፥ በክርስቶስ አፍረን እርሱን ከመከተልና ቃሉን ከማስተማር ብንቆጠብ፥ ዘላለማዊ ጉዳት ይደርስብናል። በዘላለሙ መንግሥት፥ ክርስቶስ በአባቱ ፊት አያከብረንም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች ጠቃሚዎች እንደሆኑ የሚያስቧቸውንና፥ ክርስቲያን ከሆኑ በኋላ ለመተው የሚቸገሩባቸውን ነገሮች ዝርዝር። ለ) ክርስቲያኖች በክርስቶስና በቃሉ ማፈራቸውን የሚያሳዩባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ሐ) የመስቀሉን መንገድ መከተል እንዴት እንደ ለወጠህ ግለጽ።

ከዚህ በኋላ፥ ክርስቶስ በሞቱ ላይ ስላተኮረ ታሪኩ ተለውጧል። እርሱም ቀስ በቀስ ወደሚሞትባት የኢየሩሳሌም ከተማ ተጓዘ፡፡ ለደቀ መዛሙርቱም ስለ ሞቱና ትንሣኤው በተደጋጋሚ ይነግራቸው ጀመር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: