የሉቃስ ወንጌል ጸሐፊ

ምንም እንኳ «የሉቃስ ወንጌል» የሚለው ርእስ የመጀመሪያው ቅጂ አካል ባይሆንም፥ መጽሐፉ ከተጻፈ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ርእስ በመሆን ሊያገለግል ችሏል። ይህም የሆነው የሉቃስን ወንጌል ከሌሎች ወንጌላት ለመለየት ሲባል ነው። ይህ ደግሞ ገና ከጥንት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጀምሮ ሉቃስ ይህንን ወንጌል እንደ ጻፈው የሚታመን መሆኑን ያስረዳል። የጳውሎስ የወንጌል አገልግሎት ባልደረባ የነበረው ሉቃስ፥ የዚህ ወንጌል ደራሲ መሆኑን ሁሉም የጥንት የቤተ ክርስቲያን አባቶች በአንድ ድምፅ ይስማሙበታል። ምሑራን ሉቃስ የዚህ ወንጌል ጸሐፊ መሆኑን መጠራጠር የጀመሩት ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ ብቻ ነው። እነዚህ ምሑራን ጥርጣሬያቸውን ያቀረቡት ከሉቃስ ዘመን በኋላ ስለ ተነሡት የቤተ ክርስቲያን ችግሮች የሚዘግቡ አሳቦች በመጽሐፉ ውስጥ እንደሚገኙ በመግለጽ ነበር። ይህም ሆኖ ሉቃስ የዚህ ወንጌል ደራሲ አለመሆኑን የሚያሳይ ጠንካራ መረጃ አልተገኘም።

እንደ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች ሁሉ ስለ ሉቃስም ያለን መረጃ የተወሰነ ነው። ከሦስቱ የጳውሎስ መልእክቶች እንደምንረዳው፣ ሉቃስ በሙያው ሐኪም የነበረ ሲሆን፣ የጳውሎስ የቅርብ ጓደኛና የሥራ ባልደረባ ነበር። ሉቃስ ሌሎች ስደትን ፈርተው ገሸሽ ባሉ ጊዜ ከጳውሎስ ያልተለየ ሰው ነበር። ከዚህ ውጭ ስለ ሉቃስ የምናውቃቸውን ነገሮች የምናገኘው ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ነው።

ምንም እንኳ ሉቃስና የሐዋርያት ሥራ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ሁለት የተለያዩ መጻሕፍት የነበሩ ቢሆኑም፣ ሉቃስና የሐዋርያት ሥራ ቀድሞ ሁለት ዐበይት ክፍሎች ባሉት አንድ መጽሐፍ ውስጥ ተጠቃልለው እንደ ነበር ብዙ ምሑራን ይስማማሉ። ክፍል አንድ ስለ ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት የሚናገር ሲሆን፤ ክፍል ሁለት ደግሞ የክርስቶስ አገልግሎት እንዴት በሮም ግዛት ውስጥ እንደ ተስፋፋ ያስረዳል። የሐዋርያት ሥራን በጥንቃቄ ስናነብ በሁለተኛው የጳውሎስ የወንጌል ጉዞ ወቅት የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ከመቅጽበት የታሪኩ አካል ሆኖ እናገኘዋለን። ታሪኩ «እነርሱ» እያለ ሲናገር ቆይቶ «እኛ» እያለ መተረክ ይጀምራል። ከጢሮአዳ ጀምሮ ሉቃስ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር አብሮ ይሠራ ነበር፡፡ ጳውሎስና ሲላስ ጉዞአቸውን ሲቀጥሉ እርሱ አብሮአቸው አልቀጠለም፤ ፊልጵስዩስ ላይ የቀረ ይመስላል። እግዚአብሔር በጳውሎስ አማካይነት ሉቃስን በጢሮአዳ ወደ ክርስቶስ መርቶት ይሁን ወይም ቀደም ሲል ክርስቲያን ይሁን የምናውቀው ነገር የለም። ከፊልጵስዩስ በኋላ አሁንም ታሪኩ ወደ «እነርሱ» ይቀየራል። ነገር ግን በሦስተኛው የጳውሎስ የወንጌል ጉዞ ፍጻሜ ወቅት፣ ሉቃስ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝ አብሮት ነበር። ጳውሎስ በኢየሩሳሌምና በቂሣሪያ በታሰረባቸው አራት ዓመታት ውስጥ፥ ሉቃስ አብሮት ሳይሰነብት አልቀረም። ወደ ሮምም አብሮት የሄደ ይመስላል። በእነዚያ አራት ዓመታት ሉቃስ የኢየሱስን እናት ማርያምን፣ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያትና ሌሎች ኢየሱስ ሕይወታቸውን የለወጠላቸውንና የፓለስቲና ነዋሪዎችን ለማነጋገር መረጃ ለመሰብሰብ ጥሩ ዕድል አግኝቷል። ጳውሎስ ሮም በእስር ቤት ሆኖ የቆላስይስንና የፊልሞናን መልእክቶች በሚጽፍበት ጊዜ፥ ሉቃስ አብሮት ነበር። ከብዙ ዓመታት በኋላ ጳውሎስ ሊገደል በተቃረበበት ጊዜም ሉቃስ አብሮት ነበር።

ሉቃስ አይሁዳዊ አልነበረም። ይህም አንድን ሙሉ መጽሐፍ የጻፈ ብቸኛ አሕዛብ ያደርገዋል። የት ተወልዶ እንዳደገ አናውቅም። የምዕራብ ቱርክ ሰው ቢሆንም፥ በአንጾኪያ አካባቢ እንዳደገ የሚያስረዳ መረጃ አለ። ሐኪም እንደ መሆኑ፣ ሉቃስ የግሪክን ባህል እንደ ተማረ ምንም አያጠራጥርም። በተጨማሪም ሉቃስ ጥሩ የታሪክ ጸሐፊ ነበር። ምንም እንኳ ኢየሱስን በዓይኑ ባያየውም፣ ሉቃስ እንደ አንድ የታሪክ ጸሐፊ ስላመነበት ስለ ክርስቶስ ጥንቃቄ የተሞላበትን ጥናት አድርጓል። እርሱ ስደትና ሞትን መቀበል ካለበት ጥናቱ በተራ ወሬ ላይ ሳይሆን በእውነተኛ መረጃ ላይ እንዲደገፍ ፈልጎ ነበር። ሉቃስ ይህንኑ መረጃ ለማግኘት የተጠቀመባቸውን መንገዶች ይዘረዝርልናል። አንደኛው፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገሩና በጽሑፍ የሰፈሩ መዛግብትን አገላብጧል። ምናልባትም ከእነዚህ መዛግብት መካከል የማቴዎስና የማርቆስ ወንጌላት ይገኙበት ይሆናል ሁለተኛው፣ የዓይን ምስክሮችንና የተከበሩ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ቃለ መጠይቅ አድርጓል። ለምሳሌ፣ ሉቃስ የኢየሱስ እናት ከሆነችው ከማርያም ጋር በመነጋገሩ ምክንያት፥ ታሪኳን ብቻ ሳይሆን በልቧም ውስጥ ስለነበረው ነገር ጎልቶአል (ሉቃስ 2፡19)። ሁሉንም መረጃ ከሰበሰበና ታሪኮቹን ፈር ካስያዘ በኋላ፣ ሉቃስ ስለ ክርስቶስ በሚጽፈው መጽሐፍ ውስጥ የትኞቹ መካተት እንዳለባቸው ወሰነ። እንደ ሌሎቹ የወንጌላት ጸሐፊዎች ሁሉ ታሪክን ብቻ አልጻፈም። ይልቁንም ስለ ክርስቶስ ለማስተማር ፈልጎ ነበር። ይህንንም ያደረገው ሰዎች ለእምነታቸው ጽኑ መሠረት እንዲኖራቸውና ክርስቶስን መከተል ማለት ምን ማለት እንደሆነ እርሱን እንዲያውቁ ለማድረግ ነበር። ሉቃስ መረጃውን በሚሰበስብበትና በሚጽፍበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ይመራው ነበር፤ ዛሬ በእጃችን ያለው ወንጌል በሰው የተጻፈ ታሪክ ብቻ ሳይሆን፣ መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዳችን እንድናውቅ፣ እንድናምንና ከሕይወታችን ጋር እንድናዛምድ የሚፈልገውን እውነት ሁሉ እንዲጽፍ አድርጎታል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d