የመሢሑ የኢየሱስ መወለድ (ሉቃስ 2፡1-40)

የውይይት ጥያቄ፡- ምርጫው ቢሰጥህ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ በምን ዐይነት ቤት ውስጥ እንዲወለድ ታደርግ ነበር? የትኛውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃ ትመርጥለት ነበር?

የኢየሱስን ሕይወት ከዓለም ታሪክ አያይዞ ያቀረበው ሉቃስ ብቻ ነው። ከሮም ታላላቅ ነገሥታት አንዱ የሆነው አውግስጦስ ቄሣር በሥልጣን ላይ የቆየው ከ31 ዓ.ዓ. እስከ 14 ዓ.ም. ነበር። ቄሬኔዎስ ከ6–4 ዓ.ዓ (ሉቃስ የጠቀሰው ዘመን) ድረስ ሁለት ጊዜ የሶርያ ገዥ ሆኖ ያገለገለ ሰው ነበር። ሄሮድስ የሞተው በ4 ዓ.ዓ ሲሆን፣ ኢየሱስ የተወለደው ከ6–4 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር። እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ታሪክን ይመራል። ምንም እንኳ ዮሴፍና ማርያም በናዝሬት ከተማ ውስጥ ነዋሪ ቢሆኑም፣ እግዚአብሔር፥ መሢሑ በቤተልሔም ከተማ እንደሚወለድ በትንቢት ተናግሮ ነበር (ሚክያስ 5፡2)። እግዚአብሔር አውግስጦስ ቄሣርን በመቀስቀስ አይሁዶች ተገቢውን ቀረጥ እየከፈሉ መሆናቸውን እንዲያረጋግጥ አደረገው። ስለሆነም በጳለስቲና አገር የሚገኙ አይሁዶች ሁሉ ወደ ታሪካዊት ከተማቸው በመሄድ ለቀረጡ ክፍያ እንዲመዘገቡ አዘዘ። ይህ የሆነው ማርያም ኢየሱስን ልትወልድ በደረሰች ጊዜ ነበር።

ማርያምና ዮሴፍ ከሦስት ቀን ጉዞ በኋላ ቤተልሔም ደረሱ። ሰዎች ሁሉ ለዚሁ የቀረጥ ክፍያ ተሰብስበው ስለ ነበር፣ በከተማይቱ ውስጥ የሚገኙ የመኝታ ቤቶች ሁሉ ተይዘው ነበር። ስለሆነም የዓለም ፈጣሪ በከብቶች በረት ውስጥ ተወለደ።

የውይይት ጥያቄ፡- ስለ ኢየሱስ ትሕትና ከዚህ ምን እንማራለን?

ማቴዎስ ሰብዓ ሰገል ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ መሆኑን ተረድተው ለእርሱ እንደ ሰገዱ ሲገልጽ፥ ሉቃስ የነገረን ደግሞ ስለ ድሆችና ከምንም የማይቆጠሩ እረኞች ለኢየሱስ ክብር እንደ ሰጡት ነው። አንዳንድ ምሑራን እነዚህ ሰዎች በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚታረዱ በጎችን የሚጠብቁ እረኞች እንደሆኑ ይገምታሉ። እንደዚህ ከሆነ እግዚአብሔር ለመሥዋዕት የሚሆኑ በጎችን የሚጠብቁ ሰዎች ታላቁን የመሥዋዕት በግ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲያውቁ አድርጓል ማለት ነው።

መልአኩ፥ ለእረኞቹ በቤተልሔም «ክርስቶስ ጌታ የሆነ አዳኝ» እንደሚያገኙ ነግሯቸዋል ማለት ነው። እንደ ማንኛውም ሕጻን መድኃኒታችን በጨርቅ ተጠቅልሎ ተኝቶ ነበር። እንዲህ ዐይነቱን ታላቅ አዳኝ በሀብታም ሰው ቤት ወይም በቤተ መንግሥት ውስጥ ሳይሆን፣ በከብቶች በረት ውስጥ ማግኘታቸው፥ እረኞቹን ሳያስገርማቸው አልቀረም። መሢሑ የተዋረደ ትንሽ ልጅና ጌታ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? መሢሑን የመሰለ ታላቅ አዳኝ በከብቶች በረት ውስጥ የሚወለደው እንዴት ነው? የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና ሰው መሆኑ ነው። አምላክ ሰው የመሆኑ ምሥጢር፥ ራሱን አዋርዶ እጅግ ድሀ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ለመወለድ መፍቀዱ ነው። እግዚአብሔር አንዲት የጎዳና ተዳዳሪ ወንድ ልጅ እንደ ወለደችና ይህም ልጅ ታላቅ ሰው እንደሆነ ቢነግረን፣ ይህ የማይሆን ነገር ነው ብለን እናስባለን። እነዚያ ድሀ እረኞችም እንደዚህ ዐይነት አመለካከት ሳይኖራቸው አይቀርም። መሢሑ ከእነርሱም በላይ ድሀ ነበር!

ሉቃስ የዘገበው ሦስተኛው መዝሙር የብዙ መላእክት መዝሙር ነው። እነዚህ መላእክት ስለ ኢየሱስ ታላቅነት ወይም ስለ ኃይሉና ስለ መጭው መንግሥት ከመዘመር ይልቅ፣ በእግዚአብሔር ፍቅር ላይ ትኩረት አድርገዋል። ሉቃስ ከመዝሙራቸው ውስጥ ሦስት ነገሮችን ለይቷል፦

አንደኛው፥ የእግዚአብሔር በረከት ሁሉን አቀፍ ነው። መላእክት ለአይሁዶች ብቻ ሳይሆን ለሰዎች ሁሉ ሰላም እንዲሆን ዘምረዋል።

ሁለተኛው፣ መላእክቱ የመሢሑ መምጣት በሚያስከትለው ውጤት ላይ ትኩረት ሰጥተዋል። በዚህ ጊዜ ሰላም ይኖራል። ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ በዓለም ላይ ሰላም ኖሮ (ሰፍኖ) አያውቅም። መሢሑ ሲመጣ ግን በሰዎችና በእግዚአብሔር መካከል ሰላም ይወርዳል። መሢሑ መንግሥቱን በሚመሠርትበት ጊዜ በሰዎች ሁሉ መካከል ሰላም ይሰፍናል።

ሦስተኛው፣ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የተለየ ልብ አለው። ሞገሱ ወይም ጸጋው በእነርሱ ላይ አርፎአልና። ኃጢአትን ያልሠሩ ከእግዚአብሔርም ተለይተው የማያውቁ መላእክት፥ የእግዚአብሔርን ፍቅር፣ ጸጋና ምሕረት ለመረዳት ሳይቸገሩ አይቀሩም። እግዚአብሔር ከቶ ለማይገባቸው ሰዎች የሚሰጠውን ምሕረት፣ ጸጋን ፍቅር አልቀመሱም። ነገር ግን እግዚአብሔር ለዓመፀኞች ሰዎች ካለው ታላቅ ፍቅሩ የተነሣ ልጁን ለሰዎች ሁሉ እንዲሞት ላከው። ይህ እግዚአብሔር ለመላእክት ያላደረገው ነገር ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከዚህ መዝሙር እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን አስደናቂ ፍቅር የምንመለከተው እንዴት ነው? ለ) እስቲ እግዚአብሔርን ለአንተ ስላለው ፍቅር አሁን አመስግነው። ሐ) እግዚአብሔር እኛን ከመውደዱ የተነሣ፥ ልጁን ለእኛ ሲል ወደ ምድር ከላከው፣ ይህ በሕይወታችን ላይ ምን ዐይነት ለውጥን ሊያስከትል ይገባል?

ኢየሱስን ለማምለክ የታደሉት እነዚህ ምስኪን እረኞች ነበሩ። ከዚያም በሄዱበት ስፍራ ሁሉ ስለሆነው ነገር በመተረክ ስለ መሢሑ ለመመስከር የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ለመሆን በቁ። በዚህ ስፍራ ሉቃስ የኢየሱስ እናት ማርያም በሰጠችው ምላሽ ላይ ትኩረት ሰጥቷል። ድርጊቱ ካለፈ ከ70 ዓመት በኋላ፣ ማርያም ይህንን ሁሉ እንዳልተረዳችና ስለ ጉዳዩም እያሰበች በልቧ ትጠብቀው እንደ ነበር ለሉቃስ እንደ ገለጸችለት ምንም ጥያቄ የለውም።

እያንዳንዱ አይሁዳዊ ልጅ ሲወለድ፣ ወላጆቹ የሚፈጽሙት የተለያየ ሥርዐት ነበር። በዚህ መሠረት የኢየሱስ ቤተሰቦችም ይህንኑ አድርገዋል፡፡ አንደኛው፥ በስምንተኛው ቀን ሕጻኑ ተገርዞ «ኢየሱስ» የሚል ስም ተሰጠው። ሁለተኛው፣ የተወለደው የበኩር ልጅ ከሆነ ከአንድ ወር በኋላ ይቤዥ ዘንድ ለእግዚአብሔር እልፎ ይሰጣል (ዘጸ. 13፡12-18)። ሦስተኛው፣ ከ40 ቀናት በኋላ እናቱ ማርያም 40 ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዛ ወደ ቤተልሔም በመሄድ ለመንጻት ሥርዐት የሚሆን መሥዋዕት አቀረበች። እንደ ደንቡ ከሆነ፣ የሚፈለገው መሥዋዕት አንድ በግና ሁለት ርግቦች ናቸው። ዮሴፍና ማርያም ሁለት ርግቦች ብቻ ማቅረባቸው ድሆች መሆናቸውን ያመለክታል (ዘሌዋ. 12፡2-8 አንብብ።) ዮሴፍና ማርያም የሙሴ ሕግ የሚጠይቀውን እነዚህን ሁሉ ሥርዐቶች ፈጽመዋል።

ኢየሱስ ከተወለደ በ40ኛው ቀን የመንጻትን መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ቤተ መቅደስ በሄዱበት ወቅት ስምዖን የተባለ አዛውንት ኢየሱስ መሢሑ መሆኑን ተገነዘበ። ይህ ሰው የእስራኤልን መጽናናት ሳያይ እንደማይሞት እግዚአብሔር ገልጦለት ነበር። ይህም የእግዚአብሔርን መጽናናት ለሕዝቡ የሚያመጣው መሢሕ እንደ መጣ የሚያመለክት ነበር። አሁንም የ40 ቀኑ ሕጻን መሢሕን እንዲያስተውል በስምዖን ልብ ውስጥ የሠራው መንፈስ ቅዱስ ነበር። ኢየሱስ መሢሕ መሆኑን የሚያመለክት ምንም ዐይነት ውጫዊ ምልክት አልነበረም። ዛሬ በኢየሱስ ሥዕሎች ላይ እንደምንመለከተው ዐይነት ፀዳል እንኳ በሕጻኑ በኢየሱስ ራስ ላይ አልነበረም። መንፈስ ቅዱስ እነዚህን ምስኪን ወላጆችና ኢየሱስን ለስምዖን ስላሳያቸው ብቻ ነበር መሢሕ መሆኑን የተገነዘበው። ስምዖን በመዝሙሩ ኢየሱስ «ለሰዎች ሁሉ» የእግዚአብሔር መድኃኒት መሆኑን ገልጾአል። ስምዖን ኢየሱስ ለአይሁዶች ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሁሉ የተበረከተ ስጦታ እንደሆነ ተገንዝቦአል። ለእስራኤል ብቻ ሳይሆን ለአሕዛብ ጭምር የእግዚአብሔርን ብርሃን ያመጣ ነበር። ነገር ግን ስምዖን ለማርያም አንድ ሌላ መልእክት ነበረው። ይህ ሰው ታላቁ መሲሕ ብቻ ሳይሆን ሞት የሚጠብቀው መሲሕ እንደሆነ ለመገንዘብ ችሎ ነበር። ስለሆነም በአንድ በኩል ኢየሱስ በእስራኤል መካከል ታላቅ መከፋፈልን እንደሚያመጣ፥ ብዙዎችም በጠላትነት እንደሚነሡበት ለማርያም ገለጸላት። በሌላ በኩል ደግሞ የበኩር ልጇ በመስቀል ላይ ሲሞት ስታይ የማርያም ነፍስ በሐዘን ይወጋል።

ሐና ከእነርሱ ጋር በተገናኘች ጊዜ አንድ ያልተለመደ ነገር ተከሰተ። እርስዋም በጸሎትና እግዚአብሔርን በማገልገል ብዙ ጊዜዋን የምታሳልፍ ነቢይት ነበረች። ለረዥም ጊዜ መበለት ሆና ትኖር ነበር። (ምናልባትም ሉቃስ 84 ዓመት መበለት ሆና ትኖር ነበር ያለው የ84 ዓመት አረጋዊት መሆኗን ለመግለጽ ፈልጎ ይሆናል።) ይህች ሴት ከቤተ መቅደሱ ክፍሎች በአንደኛው ውስጥ ትኖር ነበር። እርሷም ደግሞ ኢየሱስ መሢሕ እንደሆነና ለአይሁዶች መዳንን እንደሚያመጣ ተረድታለች።

የውይይት ጥያቄ፡- ምስኪን እረኞች፣ አንድ ሽማግሌና አንዲት አሮጊት ብቻ ኢየሱስን ለይተው ያወቁት ለምን ይመስልሃል? ንጉሡ ወይም የሃይማኖት መሪዎች ሊለዩት ያልቻሉት ለምንድን ነው? ከዚህ ስለ እግዚአብሔር ምን እንማራለን?

ሉቃስ ዮሴፍና ማርያም ወደ ገሊላ ከተመለሱ በኋላ ኢየሱስ እንዳደገ ይነግረናል (ሉቃስ 2፡40፣ 52)። በአካሉ አድጎ ጠነከረ። በአዕምሮው አድጎ ጠቢብ ሆነ፥ በመንፈስም አደገ፥ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ። ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ታላላቅ ምሥጢራት አንዱ ነው። ሉቃስ ኢየሱስ እንደ ማንኛውም ልጅ ማደጉን ገልጾአል። ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ አምላክ ሆኖ ሳለ፥ እንዴት በሰሴት ማሕፀን ውስጥ ተፀንሶ ከትንሽ ሕዋስ ጀምሮ እያደገ እንደ ሄደ ማብራራት አልተቻለም። በታሪክ ሁሉ የሥነ መለኮት ምሑራን ኢየሱስ እንደ አንድ ሰው እንዴት ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ ሊሆን እንደሚችል ለማብራራት ሞክረዋል። ይህ ከሰው ልጅ ዕውቀት በላይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ኢየሱስ ከዘላለም ዘመን በፊት አምላክ ነው። እንዲሁም ኢየሱስ ትንሽ ሕጻን ሆኖ የተወለደ ሰው ነው። ይህንን ለመግለጽ ከመሞከር ወይም በዚህ እውነት ላይ ከመሟገት ይልቅ እግዚአብሔር የሠራውን ተአምር እንድናሰላስል ይፈልጋል። ታላቁ ምሥጢር እግዚአብሔር እኛን እጅግ ስለ ወደደን፥ ልጁ ከሰማይ ክብሩ ወርዶ ከድሆች እንደ አንዱ እንዲሆንና ለሰዎች ሁሉ ኃጢአት እንዲሞት ማድረጉ ነው። እጅግ መጨነቅ ያለብን ምሥጢሩን ለማወቅ ሳይሆን ለማምለክ ነው። የእግዚአብሔር ፍቅር ምንኛ ታላቅ ነው!

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading