ኢየሱስ በዐሥራ ሁለት ዓመቱ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ ( ሉቃስ 2፡41-52)

አንድም የወንጌል ጸሐፊ ኢየሱስ ከመወለዱ ጀምሮ ሠላሳ ዓመት እስኪሞላው ድረስ ስለ ነበሩት ዓመታት ምንም ነገር አልነገረንም። ስለ ኢየሱስ የልጅነት ጊዜ ብናውቅ እንወድ ነበር። ምን ሠርቶ ነበር? ምን ያደርግ ነበር? አንዳንዶች ይህንን ነገር ባለማወቃቸው ግራ ተጋብተው ኢየሱስ በልጅነቱ ስለፈጸማቸው ተአምራት የፈጠራ ታሪኮችን አዘጋጅተዋል። ይሁንና ኢየሱስ ኃጢአት ካለመሥራቱ በቀር ከሌሎች የናዝሬት ከተማ ልጆች የተለየ ነገር የታየበት አይመስልም። ኢየሱስ እንደ ሌሎች የአይሁድ ልጆች ሁሉ ብሉይ ኪዳንን ሳይማር አይቀርም። የአናጺን ሙያ ተምሮ አባቱን በሥራ ያግዝ ነበር። በቤት ውስጥም ዮሴፍና ማርያም የወለዷቸውን ሌሉች ልጆች በማሳደግ ሊረዳቸው ቆይቶ ይሆናል። ዮሴፍ ኢየሱስ 12 ዓመት ሲሆነው ሳይሞት አልቀረም። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በዮሴፍ እግር ተተክቶ የቤተሰቡ ራስና አስተዳዳሪ ሳይሆን ኣልቀረም። በሰዎች ላይ የሚደርሰው መከራና ሐዘን በእርሱም ላይ ደርሷል፤ የሚበሉትን እንዳጡ፥ የሚወዳቸውን ሰዎች በሞት እንደ ተነጠቁ፣ ደግሞ በድህነት ውስጥ እንደ ነበሩ ሰዎች እርሱም የተለያዩ ችግሮችን ሳይቀምስ አልቀረም።

ይሁንና ሌላ መረጃ ባይኖርም ሉቃስ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን የተለየ ግንኙነት ያውቅ እንደ ነበረ የሚጠቁም አንድ ታሪክ ዘግቧል። በአይሁድ ባህል አንድ ልጅ እንደ ትልቅ ሰው የሚቆጠረው በ13 ዓመቱ ነበር። ከሃይማኖታዊ ማኅበረሰብ ጋር የመሳተፍን መብት የሚቀዳጀው ዕድሜው 13 ዓመት ሲሞላ ነው። አንድ ልጅ 12 ዓመት ሲሞላው ብዙ ትምህርቶችን ይቀበልና 13 ዓመት ሲሆነው እንደ አዋቂ የሚታይበትን ሥርዐት ያከብራል። ዮሴፍና ማርያምም አይሁዶች ሊካፈሉ የሚገባቸው ሦስት በዓላት (ፋሲካ፣ በዓለ ኀምሳና የዳስ በዓል፥ ዘጸአት 23፡14-17፤ ዘዳግ 16፡16) በአንዱ ላይ ለመገኘት ኢየሱስን ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ። ብዙውን ጊዜ የአንድ አካባቢ ሰዎች አብረው ይሄዱ ነበር። በዓሉ ላይ ከተገኙ በኋላ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ፥ ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስ አብረዋቸው ከሚሄዱት ሰዎች መካከል ይኖራል ብለው አስበው ነበር። ማታ ሲሆን ግን አብሯቸው እንዳልተመለሰ ተነዘቡ። ለሦስት ቀናት ከፈለጉት በኋላ በቤተ መቅደስ ውስጥ አገኙት። ምግብ ከየት ያገኝ እንደነበረና የት ያድር እንደ ነበር አልተጠቀሰም። ነገር ግን የሃይማኖት መሪዎችን ጥያቄ በመመለስና ለእነርሱም ጥያቄዎችን በማቅረብ ከዕድሜው በላይ አዋቂ እንደሆነ አስመስክሯል። ወላጆቹ በገሠጹት ጊዜ፣ ኢየሱስ «በአባቴ ቤት ውስጥ ልኖር እንደሚገባኝ አታውቁምን?» ሲል ግልጽ መልስ ሰጥቷቸዋል። ኢየሱስ እግዚአብሔር በተለየ መንገድ ኣባቱ እንደሆነ ያውቅ ነበር። የሕይወት ተልዕኮውም የተለየ መሆኑን ቀድሞውኑ ተረድቷል። ዮሴፍና ማርያም ማንነቱን ስለ ዘነጉ ኢየሱስ እንደገና አስታውሷቸዋል። ማርያም ይህን የኢየሱስን የልጅነት ጊዜ ስታስብ በእግዚአብሔር ሥራ ላትደነቅ አልቀረችም፡፡

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: