ኢየሱስ ለደቀ መዝሙርነት ምን እንደሚያስፈልግ የሰጠው ትምህርት (ሉቃስ 6፡17-49)

ከጊዜ ወደ ጊዜ የኢየሱስ ዝና እየጨመረ በመምጣቱ፥ ሰዎች የኢየሱስን ትምህርትና ተአምር ለመከታተል ከይሁዳ (80 ኪሎ ሜትር)፣ ከጢሮስና ከሲዶና (ከ60-80 ኪሎ ማትር) ይጎርፉ ነበር። አንድ ቀን ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እርሱን ስለ መከተል አስተማረ። ይህ የኢየሱስ ስብከት በማቴዎስ ምዕራፍ 5 ውስጥ የተጠቀሰው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ሁለቱም ስብከቶች በብፅዕና አሳቦች ጀምረው፥ በቤት ሠሪዎች ታሪክ የሚጠቃለሉ መሆናቸው ነው። ነገር ግን በሉቃስ ወንጌል ውስጥ የሚገኘው ስብከት በማቴዎስ ውስጥ ከሚገኘው አጭር ነው። በማቴዎስ 5-7 ላይ ከቀረቡት ትምህርቶች አንዳንዶቹ በሉቃስ ወንጌል ውስጥ በሌላ ስፍራ ይገኛሉ።

ሀ. በነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ የሚደገፉና በመከራም ጊዜ ኢየሱስን የሚከተሉ ብፁዓን ናቸው (ሉቃስ 6፡17-26)። እንደ ማቴዎስ ሁሉ፤ ሉቃስም ኢየሱስ ያስተማረውን አሳብ ጠቅለል አድርጎ በማቅረብ ይህንን አጭር ስብከት አመልክቷል። አንደኛው፥ ደቀ መዛሙርቱ የመንፈሳዊ መንግሥቱ አባላት እንደ መሆናቸው መጠን፥ እንዴት መመላለስ እንደሚጠበቅባቸው ገልጿል። ሁለተኛው፣ ኢየሱስ ለዚህ ዓለም ውድ የሆነውን ነገር ለእግዚአብሔር መንግሥት ውድ ከሆነው ነገር ጋር አነጻጽሯል። ሦስተኛው ኢየሱስ ለግል ጥቅም የሚከተሉትን ሰዎች በእውነተኛ ሕይወት ለዋጭ እምነት ከሚከተሉት ጋር አነጻጽሯል። አራተኛው፣ ኢየሱስ ሰዎች በመጭው መንግሥት እንዴት እንደሚመላለሱ አሳይቷል።

በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ በዋነኛነት ያስተማረው፥ በሥጋዊ ነገር ደሀ ስለሆኑ ሰዎች ሳይሆን፥ መንፈሳዊ ድሆችን ማለትም በመንፈስ ድሆች እንዲሁም «ጽድቅን ስለሚራቡና ስለሚጠሙ» ነው። ኢየሱስ ያስተማረውን መረዳት ያለብን በዚህ መንገድ ነው። መንፈሳዊ ብቃቶች የደቀ መዛሙርቱ መገለጫዎች ናቸው። በዚህ ስፍራ ግን ኢየሱስም ሆነ ሉቃስ በድሆች ላይ ሲያተኩሩ እንመለከታለን። እዚህ ላይ ግን ሉቃስ ሀብታሞች አይድኑም፥ በአንጻሩም ድሆች ደሀ በመሆናቸው ብቻ ይድናሉ የሚል ነገር አልተናገረም። እርሱ የተናገረው ስለ ውስጣዊ አመለካከታቸው ነው። ድሆች በእምነት ወደ እግዚአብሔር የመመልከትና በእርሱም ላይ የመታመን ዝንባሌ ያሳያሉ። ትሑታንና በእግዚአብሔር ላይ የሚደገፉ ናቸው። ስለሆነም ድሆች መንፈሳዊ ሽልማታቸውን የሚቀበሉት በሰማይ ነው። እዚህ ላይ ሉቃስ የሚናገረው በሥጋዊ ነገር ደሀ ስለ ሆኑ ሰዎች ሳይሆን፥ ኢየሱስን ስለሚከተሉ ድሆች እንደሆነ ግልጽ ነው። በሉቃስ 6፡22 በሰው ልጅ ማለትም በክርስቶስ ምክንያት ሰዎች እንደሚጠሏቸው ተመልክቷል።

በአንጻሩም ሀብታሞች በራሳቸው የሚተማመኑና ራስ ወዳዶች ወደ መሆን ያዘነብላሉ። ገንዘብንና ገንዘብ የሚያመጣውን ምቾት ይወዳሉ። ሀብታሞች ከኢየሱስ ጋር ከመተባበር ይልቅ ከሌሎች ሰዎች ጋር መደሰትን ይመርጣሉ። ስለሆነም ብቸኛው መጽናናታቸው በዚህ ምድር የሚያገኙት ነገር ይሆናል። ሀብታሞች በእግዚአብሔር ፊት ለፍርድ በሚቆሙበት ጊዜ ሀብታቸው ተወስዶባቸው በሐዘን ያለቅሳሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቶስን ለመከተል በወሰኑትና ባልወሰኑት ሰዎች መካከል እነዚህን ሁለት ዝንባሌዎች እንዴት እንደ ተመለከትህ ግለጽ። ለ) ይህ ወንጌልን ማን እንደሚቀበል ለወንጌላውያን የሚሰጣቸው ግንዛቤ ምንድን ነው?

ለ. ጠላቶቻቸውን የሚወዱና መልካም የሚያደርጉላቸው ብፁዓን ናቸው (ሉቃስ 8፡27-36)። ዓለም ሰዎችን በሦስት ቡድን ትከፍላቸዋለች። እነዚህም፤ 1) የምንወዳቸው ቤተሰባችን፤ ዘመዶቻችንና ጎላችን፤ 2) የምንታገሣቸው፡ የሥራ ባልደረቦቻችን ወይም ስለ እነርሱ ብዙም ዕውቀት የሌለን የሩቅ ጎሳዎች፣ 3) የምንጠላቸው፡ የጎዱን ሰዎች ወይም እንደ ጨቆኑን የምናስባቸው ጎሳዎች ናቸው። ከዚህ የተነሣ ዓለም ሁልጊዜ በውጊያ ላይ ነች። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ለሰዎች አንድ ዐይነት አመለካከት ያውም ፍቅር ብቻ እንዲኖራቸው አስተምሯል። የተፈጥሮ ነገር ሆኖ ቤተሰቦቻችንንና ወዳጆቻችንን ስለምንወድ ኢየሱስ እነዚህን አልጠቀሰም። ጠላቶቹንና የሚጨቁኑትን ሰዎች ለመውደድ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ሙሉ በሙሉ የተለወጠ ሕይወት ሊኖረው ይገባል። የኢየሱስ ተከታይ ከመቋቋምና ከመበቀል ይልቅ፥ የሰዎችን ቁጣና ተቃውሞ መቀበል ይኖርበታል። ለምንታገሣቸው ሰዎች ራሳችንን የምንወደውንና የምንከባከበውን ያህል፥ እነርሱንም መውደድና መንከባከብ ይገባል። ኢየሱስ ክርስቲያኖችን ከውስጥ እንደ ለወጣቸው አንዱ መረጃ ፥ ጠላቶቻቸውን መውደዳቸው ነው። በዚህ ጊዜ የኢየሱስ ተከታዮች እንደ እነርሱ ዐይነት ኃጢአተኞችን የወደደውን የእግዚአብሔርን ፍቅር ይላበሳሉ።

ሐ. የሌሎችን ሰዎች ውስጣዊ ዓላማዎች ሳይጠራጠሩ በልግስና የሚሰጡ ብፁዓን ናቸው (ሉቃስ 6፡37-42)። ጳውሎስ ፍቅር ሁልጊዜ እንደሚያምንና ሁልጊዜ ተስፋ እንደሚያደርግ ገልጾአል (1ኛ ቆሮ. 13፡7)። አብዛኛውን ጊዜ በሰዎች መካከል ችግሮች የሚከሰቱት ሌላው ሰው የተናገረውን አሳብ በትክክል ካለመረዳት ነው። ስለሆነም ኢየሱስ ተከታዮቹ ፍቅራቸውን ለሌሎች በሚያሳዩበት ጊዜ፥ የሰዎቹን ጥፋት ለማግኘት መጣር እንደሌለባቸው ገልጾአል። በችግር ላይ ላሉት በልግስና ልንሰጣቸው ይገባል። የሌላውን ሰው ኃጢአት ችላ ማለት ባይኖርባቸውም፣ ክርስቲያኖች ሁልጊዜ በትሕትና መመላለስ ይኖርባቸዋል። እነርሱም እንደ ሌሎቹ ኃጢአተኞች ናቸውና። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲህ ዐይነት ልብ ካላቸው መንፈሳዊ ዐይነ ስውር ሳይሆኑ እንደ መሪያቸው አስተዋዮች ይሆናሉ።

መ. በሥራቸው ተለይተው የሚታወቁ ብፁዓን ናቸው (ሉቃስ 6፡43-45)። የኢየሱስ ተከታይ መሆናችንን የሚያሳየው፥ ሰዎች የሚናገሩት ብቻ አይደለም። በሌሎች ሰዎች ፊት የምናደርገው አምልኮ፣ ጸሎት፣ ዝማሬ፣ ዕልልታና ሽብሸባ ብቻ አይደለም እምነታችንን የሚመሰክረው እንደ ኢየሱስ መኖር አለመኖራችንን የሚያረጋግጠው የሕይወት ፍሬያችን ነው። ይህም አንድ ሰው የኢየሱስ ተከታይ መሆን አለመሆኑን ያመለክታል። የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ከልብ የተለወጠ ሕይወት ይኖራል። ሐሰተኛ የክርስቶስ ተከታይ ዓለማዊ ባሕርይን በማሳየት የሕይወቱን አለመለወጥ ይገልጣል።

ሠ. ለኢየሱስ በመታዘዝ የሚመላለሱ ብፁዓን ናቸው (ሉቃስ 6፡46-49)። በስደትና በመከራ ጊዜ የእምነት ቤታችን ጸንቶ እንደሚቆም በምን እናውቃለን? እምነታችንን አጽንቶ የሚያቆመው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መዘመራችን ነው ወይስ የተነቃቃ አምልኳችን? ወይስ ረጅም ጸሎት መጸለያችን? ወይስ ሕይወታችንን ለመለወጥ የምንገባቸው አያሌ የተስፋ ቃሎች ይሆኑ? ኢየሱስ ብዙ ሰዎች ኢየሱስን፣ «ጌታ ሆይ» ብለው እየጠሩ የእምነት ቤታቸው ግን ሊፈርስ እንደሚችል ገልጾአል። የእምነት ቤታችን ጸንቶ እንዲቆም ከፈለግን፣ ጠላቶቻችንን በመውደድ፣ በመንፈሳዊ እውነቶች ላይ በማተኮር፣ ኢየሱስን በታዛዥነት መከተል ይኖርብናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ዛሬ ስለ ደቀ መዝሙርነት ብዙ እንሰማለን። ነገር ግን የኢየሱስ ተክታዮች መሆናችንን እንዴት እንደምንገልጽ የሚያሳዩ ስብከቶች ሲሰበኩ እንሰማም። ከኢየሱስ ትምህርት አንጻር፣ የኢየሱስ ተከታይ ስለ መሆን አዳዲስ ክርስቲያኖች ሊያውቁት የሚገባው ምንድን ነው?

Leave a Reply

%d bloggers like this: