ቡታ ሙስሊም የነበረች አሁን ግን በኢየሱስ ያመነች ወጣት ልጃገረድ ናት። አባቷ በዚህ ተቆጥቶ እምነቷን እንድትክድ ይገርፋት ጀመር። እርሷ ግን ለመካድ ፈቃደኛ አልሆነችም። ከዚያም አባቷ ክርስቲያኖች በሌሉበት ሩቅ ስፍራ ለአንድ ሙስሊም ሊድራት ወሰነ። እዚያ ከሄደች እምነቷን እንደምትተው እርግጠኛ ሆነ። ከሰርጉ በኋላ የቡታ አማች ልጁ ክርስቲያን ሴት እንዳገባ ሲያውቅ እጅግ ተናድዶ ይደበድባት ጀመር። ለአንድ ሳምንት ያህል በየቀኑ በኃይል መደብደቡን ቀጠለ። የእርሷ ምላሽ ግን፣ «ሊመቱኝ ይችላሉ። ሊገድሉኝም ይችላሉ። ኢየሱስን ግን ሊነኩት አይችሉም። እርሱ በልቤ ውስጥ አለ» የሚል ነበር። በመጨረሻም አማቷ በቆራጥነቷ ተደንቆ ቤተሰቡን ሁሉ በመሰብሰብ፣ «እንደዚህ በእምነቱ የጸና ሰው አጋጥሞኝ አያውቅም። እርሷ የምትለውን መስማት ይኖርብናል» ሲል ተናገረ። በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከዚህች ልጅ ምስክርነት የተነሣ ከቤተሰቡ አባላት ብዙዎች በኢየሱስ አመኑ።
የውይይት ጥያቄ፡- ሉቃስ 12፡4-7 አንብብ። ሀ) ቡታ በዚህ ክፍል ውስጥ የተጠቀሰውን የኢየሱስን ትእዛዝ ተግባራዊ ያደረገችው እንዴት ነው? ለ) እግዚአብሔርን ከሌሎች ሰዎች በላይ መፍራት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ሐ) ሰዎችን ፈርተን እንዳንመሰክር ወይም የሚገባንን ነገር እንዳናደርግ የሚያብራራ አንድ ምሳሌ ለጥ።
የምንናገረው ከምንሠራው ወይም ከምናስበው ካልተስማማ ግብዞች ነን ማለት ነው። ይህ ስውር ኃጢአት ስለሆነ፣ ለክርስቲያኖች እጅግ አደገኛ ከሆኑት ኃጢአቶች አንዱ ነው። ሁላችንም በሰዎች ፊት የበለጠ መንፈሳውያን መስለን ለመቅረብ በሞከርንበት ጊዜ ሁሉ ኃጢአትን አድርገናል። የምንናገረውን እንደማናደርግ ወይም ከእግዚአብሔር እንደ ራቅን ልባችን እያወቀ ሰዎች በተሰበሰቡበት ስፍራ ድምፃችንን አሳምረን እንጸልያለን። ፈሪሳውያን የዚህ ኃጢአት ሰለባዎች ነበሩ። መንፈሳውያን መስለው ለመታየት ቢፈልጉም፥ ልባቸው ከእግዚአብሔር የራቀ ነበር። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ከዚህ ኃጢአት ራሳቸውን እንዲጠብቁ ነግሯቸዋል። በምድርም ሆነ በሰማይ በልባቸው ውስጥ የተደበቁ ነገሮች ገሃድ እንደሚወጡ አስጠንቅቋቸዋል። ኃጢአታችን የተደበቀ ነው ብለን ልናስብ እንችላለን፣ ይሁንና አንድ ቀን ይፋ ወጥቶ ሊያሳፍረን ይችላል።
ነገር ግን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሊጠነቀቁበት የሚገባ ሌላም ችግር አለ። ይህም የስደት ጉዳይ ነው። ብዙውን ጊዜ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ ስንጋብዝ ስደት እንደሚጠብቃቸው አንነግራቸውም። ወይም ደግሞ፣ «አይዞህ፣ ኢየሱስ ከአንተ ጋር ይሆናል» እንላለን። ኢየሱስ የተከተለው ግን በጣም የተለየ አሠራር ነበር። ኢየሱስ እርሱን በመከተል ስለሚገኙት በረከቶችና ምቹ ሁኔታዎች ከመግለጽ ይልቅ የሚደርስባቸውን ችግሮች አብራርቶላቸዋል። እንደዚሁም እርሱን ለመከተል በሚፈልጉ ብዙ ሰዎች ፊት ደቀ መዛሙርቱ ስደት እንደሚጠብቃቸው ተናግሯል። ነገር ግን ስደትን ፈርተው ወደ ኋላ መመላስ አልነበረባቸውም። ሰውንና በስደት የሚመጣውን ሞት ፈርቶ ወደ ኋላ መመለሱ የባሰ አደጋ፣ ማለትም የዘላለምን ፍርድ ያስከትላል። ከዚህ ይልቅ እግዚአብሔርን በመፍራት እየተመላለሱ የዘላለምን ሕይወት ማግኘቱ ምንኛ የተሻለ ነው። በስደት ጊዜ እንኳ እግዚአብሔር የቅርብ አምላካችን እንደሆነና ሁሉንም ነገር እንደሚቆጣጠር ማስታወስ አለብን። ያለእርሱ ፈቃድ የራሳችን ፀጉር እንኳ አይነቀልም። በዳኞች ፊት ምን እንናገር ይሆን? እያሉ ከመጨነቅ ይልቅ መንፈስ ቅዱስ ተገቢውን ቃል እንደሚሰጠን መተማመን አለብን። ስለ ኢየሱስ መመስከር ትልቅ ዕድል ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን እግዚአብሔር እኛን ከመከራ ለማውጣት በመንፈስ ቅዱስ የተመሩ ቃሎችን ይሰጠናል።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)