የብልኁ መጋቢ ምሳሌ (ሉቃስ 16፡1-15)

ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ከተረዷቸው የኢየሱስ ምሳሌዎች አንዱ ይህ ነው። ይህንን ምሳሌ በትክክል ለመገንዘብ፣ የምሳሌን ዓላማ ማስታወስ አለብን። ምሳሌ የሚቀርበው አንድን ዐቢይ እውነት ለማብራራት ነው። ዝርዝር ነጥቦች ሁሉ ከእኛ ሕይወት ጋር ላይዛመዱ ወይም ላይተረጎሙ ይችላሉ። በዚህ ምሳሌ ላይ እንደምንመለከተው ኢየሱስ አታላዩ አስተዳዳሪ ትክክል ሠርቷልና በምሳሌነት ልንከተለው ይገባል እያለ አይደለም። ወይም ደግሞ አስተዳዳሪው እግዚአብሔር አብ ነው እያለ አይደለም። ምሳሌው ያተኮረው በአስተዳዳሪው ሥራ ላይ ነው። የነበረበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ያለፈበት መንገድ አስተዋይነቱን ያመለክታል። ኢየሱስ ለማብራራት የፈለገው አስተዳዳሪው ስለ ወደፊቱ ማሰቡ አስተዋይነቱን እንደሚያመለክት ነው። ሰውዬው አለቃው የሰጠውን ሥልጣን በመጠቀም የወደፊት ቤቱን በመሥራት ላይ ነበር።

በጥንት ጊዜ ሀብታም ነጋዴዎች ባሪያዎቻቸው ወይም ሌሉች ተቀጣሪዎች ሥራቸውን እንዲቆጣጠሩ ይቀጥሯቸው ነበር። (ለምሳሌ፣ ጶጢፋራ ዮሴፍን እንደቀጠረው። ዘፍጥረት 39፡4)። ኢየሱስ የተናገረው የጌታውን ገንዘብ ሲያባክን ስለ ተደረሰበት እንዲህ ዐይነት አስተዳዳሪ ነው። ሥራውን እንደሚያጣ ስለ ተገነዘበ፣ ለወደፊት ሕይወቱ ዕቅዶችን አወጣ። በተባረረ ጊዜ ይረዱት ዘንድ ሰዎችን ለማግባባት ፈለገ። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን ይህ ሰው ያደረገው ነገር ትክክል ነው ወይስ አይደለም? በሚለው አሳብ ላይ የተለያዩ አሳቦችን ይሰጣሉ። ጌታውን እያጭበረበረ ነበር? አንዳንዶች የአስተዳዳሪነት ሥልጣኑን ተጠቅሞ የሰዎችን ዕዳ እንደ ቀነሰ ይናገራሉ። አይሁዶች ለሌሎች አይሁዶች በሚያበድሩበት ጊዜ ወለድ አያስከፍሉም ነበር (ዘጸ. 22፡25፤ ዘሌዋ. 25፡36-37)። ስለሆነም አይሁዶች ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር ቢኖር ወለዱን ለመደበቅ ተበዳሪው መክፈል ያለባቸውን ዕቃዎች ብዛት መጨመር ነበር። ለምሳሌ፣ አንድ ሰው 100 ኩንታል ጤፍ ቢበደር፣ የ50 ኩንታል ጤፍ ዕዳ እንዳለበት አድርገው ያስፈርሙታል ማለት ነው። በዚህ ዐይነት የሚመዘገበው ሰውዬው የሚከፍለው መጠን ብቻ በመሆኑ፣ የወለዱ መኖር አይታወቅም ነበር። ስለሆነም አስተዳዳሪው ቀደም ሲል በአራጣ መልክ ስላበደራቸው አሁን ያንን እያነሣላቸው ነው የሚሉ ምሑራን አሉ። ሥራ አስኪያጁ መጀመሪያ የተበደሩትን ገንዘብ ብቻ በማስከፈል ተገቢውን ተግባር እንዳከናወነ ያስረዳሉ። በተጨማሪም የሰዎችን ፍቅር በማትረፍ ከሥራ በሚወጣበት ጊዜ እንዲረዱት ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ ነበር። ባለቤቱ አስተዳዳሪውን በአስተዋይነቱ አመስግኖታል።

ከዚህ እንግዳ ምሳሌ ኢየሱስ ስለ ገንዘብ በርካታ ቁልፍ እውነቶችን ለማስተማር ፈልጓል።

ሀ. ሁላችንም አንድ ቀን በፈራጁ አምላክ ፊት እንቆማለን። ሁላችንም በኃጢአት ስለተበላሸን በራሳችን ለእርሱ የተገባን ሰዎች እንዳልሆንን መገንዘብ አለብን። ይልቁንም የፍርድ ቀን እንደሚመጣ በማሰብ ሁላችንም ለዚያ መዘጋጀት አለብን። በመጀመሪያ፥ ስለ ኃጢአት ዕዳችን በኢየሱስ ማመን አለብን። ቀጥሎም፥ ለወደፊቱ ያለንን ገንዘብ በሚጠቅም ነገር ላይ በማዋል ልንዘጋጅ እንችላለን። ለዘላለም የሚኖሩት የእግዚአብሔር መንግሥትና የእግዚአብሔር ሕዝብ ብቻ ናቸው። ስለሆነም ባሉን ነገሮች ጊዜያዊ ፍላጎቶቻችንን ሳይሆን ዘላለማዊ ነገሮችን ማከናወን አለብን።

ለ. ገንዘብ በራሱ ክፉ አይደለም። ይልቁንም ዘላለማዊ በረከቶችን ለሚያመጣ ነገር መሣሪያ ሊሆን ይችላል። አስተዳዳሪው ከሥራ በሚወጣበት ጊዜ ለመዘጋጀት አራጣዎችን እንደ ቀነሰ ሁሉ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብም የዓለምን ሃብት ዘላለማዊ በረከት በሚያስገኝ መንገድ መጠቀም አለባቸው። ገንዘብን ለራስ ጥቅም ከማዋል ይልቅ የእግዚአብሔር ልጆች ዘለቄታዊና መንፈሳዊ ውጤት በሚያስገኙ ነገሮች ላይ ልናውል ይገባል። (ለምሳሌ፣ መጽሐፍ ቅዱስ መግዛት፣ ወንጌላውያንን መደገፍ)። ብዙ ምሑራን ኢየሱስ ለማለት የፈለገው ክርስቲያኖች ድሆችን መርዳት እንዳለባቸው ነው ይላሉ። ስለሆነም ወደ መንግሥተ ሰማይ ስንደርስ ድሆች ተሰብስበው ያመሰግኑናል። ያን ጊዜ እግዚአብሔርም ዋጋችንን ይሰጠናል።

ሐ. የገንዘብ አጠቃቀማችን ለእግዚአብሔር ታማኞች መሆን አለመሆናችንን ያመለክታል። እግዚአብሔር ትንሽ ገንዘብ ሰጥቶን በማይረቡ ነገሮች ላይ ካዋልነው፣ እግዚአብሔር ተጨማሪ ገንዘብ እንዲሰጠን ዝግጁ አይደለንም ማለት ነው። ይኸው ተመሳሳይ መርሕ ለአመራርም ይሠራል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ የሚመረቁ ብዙ ወጣቶች ወዲያውኑ በሥልጣን ዙፋን ላይ ጉብ ማለት አለብን ብለው ያስባሉ። ነገር ግን የእግዚአብሔር አሠራር ሁልጊዜ ከትንሹ ወደ ትልቁ ነው። በዝቅተኛ የአመራርና አገልግሎት ስፍራ ታማኝነትን እስካላሳየን ድረስ፣ እግዚአብሔር ታላቅ ኃላፊነት አይሰጠንም። ብዙ ጊዜ በአገልግሎት ያልተሞከሩ ሰዎች ታማኝነታቸውን ስላላሳዩ፤ ብዙ ሥልጣን መስጠቱ አደገኛ ነው። የገንዘብ አጠቃቀም፣ አገልግሎት፣ ስጦታዎቻችን፣ ከሌሎች ጋር ያሉን ግንኙነቶችና የሕይወት ቅድስናን በመሳሰሉት ነገሮች ታማኝነታችን ከተረጋገጠ፣ እግዚአብሔር የኃላፊነት አደራውን እየጨመረብን ይሄዳል። ስለሆነም ታላላቅ የአመራር ሥልጣኖችን ከመፈለግ ይልቅ ባለንበት ስፍራ ታማኝነትን ልናሳድግ ይገባል። ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ ያነሣናል።

መ. ምንም እንኳ ገንዘብ ለዘላለማዊ ነገሮች መሣሪያ ሊሆን ቢችልም፣ በቀላሉ ሕይወታችንን ሊቆጣጠር ስለሚችል አደገኛ ነው። ስለሆነም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ገንዘብ (የትኛውም ቁሳዊ ሀብት) በጌትነት እንዳይሠለጥንባቸው ያስጠነቅቃል። ለዚህም ምክንያቱ ሕይወታችን በአንድ ጊዜ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ ሊገዛ አይችልም። ሊኖረን የሚችለው አንድ ጌታ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ለኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከኢየሱስ ሌላ ሊሆን አይችልም።

ኢየሱስ ገንዘብን በመቃወም የተናገረው አሳብ ፈሪሳያውን እንዲቀልዱበት አደረጋቸው። እንደ ብዙ ክርስቲያኖች ሁሉ፣ ገንዘብ ለእነርሱ በጣም አስፈላጊ ነገር ነበር። ኢየሱስ ግን በገንዘብ ቁጥጥር ሥር የዋለ ሕይወት ራስ ወዳድነትና ትዕቢት የነገሠበት በመሆኑ፣ በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ እንደሆነ ገልጾአል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሕይወትህን መርምር። ገንዘብ ሕይወትህን እንዲቆጣጠር የፈቀድህበት መንገድ ይኖር ይሆን? ለ) ገንዘብ ለአንዳንድ ክርስቲያኖች አምላክ ሲሆን የተመለከትህባቸውን ሁኔታዎች ግለጽ። ሐ) ገንዘብ በማስተዋል ለዘላለማዊ በረከት ልንጠቀም የምንችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር። መ) ላለፉት ሦስት ወራት የገንዘብ አያያዝህ ምን ይመስል እንደነበር አስብ። ገንዘብ ወዳድ ሆነህ ለግል ጉዳዮች የዋለው ምን ያህል ነበር? ለዘላለማዊ ነገሮች የተሰጠውስ? ገንዘብ አምላካችን ሳይሆን ለዘላለማዊ በረከት በሚውልበት መንገድ እንዴት ልንይዘው እንደምንችል ግለጽ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: