የዮሐንስ ወንጌል መግቢያ

ከአሥር ዓመት በፊት ብርቱካን ክርስቶስን ለመከተል ወስና ነበር። ነገር ግን ሁልጊዜ ልቧ በጥርጣሬ ይፈተናል። ኃጢአት ስትሠራ ወይም ለክርስቶስ ያላት ፍቅር ሲቀንስ፤ «እውነት እኔ ክርስቲያን ነኝ? ከበፊቱ ተለውጫለሁ? አሁንም ቢሆን ሳልፈልግ ኃጢአት መሥራቴ አልቀረም። ምናልባትም ኢየሱስን ለመከተል ያደረግሁት ውሳኔ ብቁ ስላልሆነ እንደገና ይህንኑ ማድረግ ያስፈልገኝ ይሆናል» እያለች ትጨነቃለች። ምንም እንኳ ክርስቲያኖች አንዳንድ ጊዜ ስለ እምነታቸው ጥያቄዎችን ሊያነሡ ቢችሉም፣ ባለማቋረጥ በጥርጣሬ የተሞላ ሕይወት ደካማ በመሆኑ፥ ሰይጣን በቀላሉ ሊያሸንፋቸው ይችላል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙውን ጊዜ እንደ ብርቱካን ስለ ደኅንነታቸው እውነተኝነት ሲጠራጠሩ ያየሃቸውን ሰዎች ሁኔታ ግለጽ። ለ) ብዙውን ጊዜ ስለ መዳናቸው የሚጠራጠሩት ለምንድን ነው?

ሐዋርያው ዮሐንስ ክርስቲያኖች ስለ እምነታቸው በግልጽ የመረዳታቸው ጉዳይ አሳስቦት ነበር። ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈው፥ ሰዎች ክርስቶስ ማን እንደሆነ በትክክል ተገንዝበው የጸና እምነትና ልበ ሙሉነት እንዲኖራቸውና እግዚአብሔር የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጣቸው እንዲያውቁ ለመርዳት ነው። (ዮሐ 20፡31 አንብብ።) በኋላም በትክክል መዳናቸውን ያውቁ ዘንድ የ1ኛ ዮሐንስን መልእክት ጽፎላቸዋል (1ኛ ዮሐ 5፡13፣ 2፡3-6፣ 3፡14-20)። ሰይጣን ከሳሽ በመሆኑ ያመነውን ነገር እንድንጠራጠር ይፈልጋል ራእይ 12፡10-12። በእውነተኛው በእግዚአብሔር ላይ በጣልነው እምነት ሳይሆን በእምነታችን ላይ እንድንደገፍ ይሻል። በዚህም ዐይነት፥ ፍሬያማ ክርስቲያኖች እንዳንሆን ያውከናል። እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ በማመናችን ልጆቹ እንደሆንን አውቀን በልበ ሙሉነት እንድንመላለስ ይፈልጋል። ልጆቹ እንደ መሆናችን መጠን፣ የኃጢአትን ይቅርታ እንዳገኘን፣ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን እንደሚኖርና የዘላለምን ሕይወት እንዳገኘን እርግጠኞች ነን።

የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወንጌላት ኢየሱስ ስላደረጋቸውና ስላስተማራቸው ቁም ነገርች (ምሳሌዎቹን ጨምሮ) ተመሳሳይ ነገሮችን ይናገራሉ። «የእግዚአብሔር መንግሥት» (መንግሥተ ሰማይ) እና «የሰው ልጅ» የመሳሰሉ ሐረጎች በብዛት ይገኙባቸዋል። የማርቆስ ወንጌል በማቴዎስና ሉቃስ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንደሚገኝ ቀደም ብለን ተመልክተናል። የማቴዎስ አብዛኞቹ ታሪኮች ደግሞ በማርቆስና በሉቃስ ውስጥ ይገኛሉ። ሉቃስም የሁለቱን ወንጌላት ግማሽ ያህል ታሪኮች አካትቷል። ምንም እንኳ እነዚህ ሦስቱም ጸሐፊዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የራሳቸውን ዓላማ ይዘው ቢጽፉም፣ ስለ ኢየሱስ የሚያቀርቧቸው አሳቦች በአብዛኛው ተመሳሳይነት አላቸው።

የዮሐንስ ወንጌል ግን ከሌሎች ሦስቱ በጣም የተለየ ነው። እንዲያውም 90 በመቶ የሚሆነው የዮሐንስ ወንጌል ከሦስቱ ወንጌላት የተለየ ነው። የዮሐንስ ወንጌል ስለ ኢየሱስ ያቀረባቸው ታሪኮች ጥቂት ሲሆኑ፣ ብዙ ነገረ መለኮታዊ ውይይቶች አሉት። በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ታሪኮች የሉም። እዚህ ብዙዎቹ የኢየሱስ ትምህርቶች ከተመሳሳይ ወንጌላት የተለዩ ናቸው። ሦስቱ ተመሳሳይ ወንጌላት ያቀረቧቸው ምሳሌዎች ስለ ኢየሱስ ማንነትና በመስቀል ላይ ስላከናወናቸው ተግባራት ነገረ መለኮታዊ አንድምታዎችን እንድንገምት የሚያደርጉን ሲሆኑ፣ ዮሐንስ ቀን ኢየሱስ መለኮታዊ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነና በእርሱ በማመን የዘላለም ሕይወት እንደሚገኝ በቀጥታ ይገልጽልናል። ዮሐንስ በቃላት አጠቃቀሙ ሳይቀር ለየት ብሎ በመቅረብ፣ እንደ ብርሃን፣ ጨለማ፣ እምነት፣ ኩነኔ፣ ምልክት ከመሳሰሉት ጋር ያስተዋውቀናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ስለ ዮሐንስ ወንጌል ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንብብ። ስለ ደራሲውና ስለ ጻፈው ወንጌል የምታውቀውን ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading