ኢየሱስ አዲስ ልደት ምን እንደሆነ ለኒቆዲሞስ ገለጸለት (ዮሐ. 3፡1-21)

በወንጌላት ውስጥ ፈሪሳውያን በቡድን ሆነው ኢየሱስንና አገልግሎቱን እንደ ተቃወሙ በሰፊው ተጠቅሷል። ኢየሱስ የመጣው እነርሱ ከጠበቁት በተለየ መንገድ ስለነበረ፥ የሃይማኖት መሪዎቹ መሲሕ መሆኑን ሊቀበሉ አልቻሉም፡፡ ደግሞም ኢየሱስ ሃይማኖታዊ ሕጎቻቸውን ባለመከተሉ፥ መንፈሳዊነቱንም ሊገነዘቡ ተስኖአቸው ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ ከሃይማኖታዊነታቸው ባሻገር፥ ወደ ልባቸው ዘልቆ በመመልከት፥ በግብዝነታቸው ገስጾአቸዋል። ይህ በኢየሱስና በፈሪሳውያን መካከል የነበረው ግንኙነት ፍጥጫና ውጥረት የበዛበት ነበር።

ይህም ሆኖ፥ ከፈሪሳውያኑ አንዱ ጥልቅ መንፈሳዊ ራብ ነበረው። ኢየሱስ የፋሲካን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ሳለ፥ ኒቆዲሞስ የሚባል ፈሪሳዊ መንፈሳዊ ጥያቄዎችን ይዞ ወደ እርሱ ቀረበ። ኒቆዲሞስ በጨለማ የመጣው ምናልባት ኢየሱስን ለብቻው የሚያገኝበት ሰዓት በዚያን ጊዜ ብቻ በመሆኑ ነበር። ወይም ደግሞ ሌሎች ከኢየሱስ ጋር ለመነጋገር መሄዱን እንዳያውቁበት አስቦ ይሆናል።

ኢየሱስ ከኒቆዲሞስ ጋር ባደረገው ንግግር፥ መንፈሳዊነት ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ አስረድቶታል። ኒቆዲሞስ ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ግንኙነት የተመሠረተው፡-

  1. አይሁድ ሆኖ በመወለድ
  2. የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን በመጠበቅና
  3. የአይሁዶችን ሃይማኖታዊ ትእዛዛት በመከተል እንደሆነ ያስብ ነበር።

ኢየሱስ ግን ኒቆዲሞስ የወንጌልን ዋና ሃሳብ እንዲገነዘብ ለማድረግ እጅግ እንግዳ አገላለጾችን ተጠቅሟል። አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ለማድረግ እነዚህ ሦስት ነገሮች ከቶ እንደማያስችሉት ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ ገለጸለት። ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ለማድረግ የሚፈልግ ሰው፥ የግድ «ዳግም መወለድ» እንዳለበት አብራራለት። የግሪኩ ቃል «ከላይ መወለድ» የሚል ፍች አለው። ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ለማድረግ ወይም ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘትና ለመግለጽ በአዲስ ኪዳን ገብተው የምናገኛቸው ቁልፍ ቃሎች የተነገሩት፥ በኢየሱስ ነው። እስቲ የሚከተሉትን እውነቶች በጥሞና ተመልከት።

ሀ. ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት ወይም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት፥ አንድ ሰው ከውኃና ከመንፈስ መወለድ አለበት። ውኃው ምንድን ነው? ለዚህ ጥያቄ ሁለት ምላሾች ተሰጥተዋል። አንደኛው፥ በውኃ ስለ መጠመቅ የሚናገር ሊሆን ይችላል። ከመጥምቁ ዮሐንስ፥ ከኢየሱስና ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ፥ በኢየሱስ ያመነ ሰው ወዲያውኑ በውኃ እንዲጠመቅ ይደረጋል። ይህም የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች አብዛኛውን ጊዜ እምነትንና ጥምቀትን እንደ አንድ ተግባር አድርገው ይመለከቱ እንደ ነበር ያሳያል። ስለዚህ ውኃው አንድ ሰው ድነትን (ደኅንነትን) ባገኘ ጊዜ የሚፈጽመውን ንስሐ፥ እምነትና ጥምቀት የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ሁለተኛው፥ ቃሉ ይበልጥ የሚያመለክተው ሥጋዊ ልደትን ሊሆን ይችላል። አንድ ሕፃን በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ሳለ በውኃ ተከብቦ ይኖራል። ሕፃኑ በሚወለድበት ጊዜ በመጀመሪያ ውኃው ከዚያም ሕፃኑ ይወለዳል። ስለሆነም፥ ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ያመጣው አንድ ሰው መጀመሪያ በሥጋ እንደሚወለድና ከዚያም ከመንፈስ ቅዱስ ዳግም እንደሚወለድ ለመግለጽ ነው።

ከመንፈስ መወለድ ምንድን ነው? ይህ በኢየሱስ ክርስቶስ ባመንን ጊዜ በልባችን ውስጥ የሚፈጸም መንፈሳዊ ልደት ነው። ጳውሎስ በክርስቶስ ከማመናችን በፊት ሙታን እንደነበርን ገልጾአል። (ኤፌ 2፡1-5 አንብብ።) ስለሆነም በሥጋዊ ልደት አማካይነት፥ የምድራዊው ቤተሰብ አባል በመሆን የምድር ሕይወታችንን እንደምንጀምር ሁሉ፥ በመንፈሳዊ ልደት ወደ እግዚአብሔር ቤተሰብ በመቀላቀል መንፈሳዊ ሕይወታችንን እንጀምራለን። ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ልደት አስፈላጊዎች ናቸው።

ለ. መንፈሳዊ ልደት በዓይን አይታይም። የሚታየው የተለወጠው ሕይወታችን ብቻ ነው። ከእግዚአብሔር በቀር መንፈሳዊ ልደት የሚፈጸምበትን ቀን የሚያውቅ ማንም የለም። ኢየሱስ ይህንን እውነታ ያነጻጸረው በዓይን ከማይታይ ነፋስ ጋር ነው። ይሁንና ነፋስ ፊታችንን ሲገርፍ ወይም የዛፍ ቅጠሎችን ሲያወዛውዝ ህልውናውን እንደምናስተውል ሁሉ፥ የመንፈሳዊ ልደትንም መኖር የምናውቀው የአንድን ሰው ሕይወት ሲለውጥ ነው። ጳውሎስ ይህንን አዲስ ልደት «አዲስ ፍጥረት» ይለዋል (1ኛ ቆሮ. 5፡17)።

ሐ. ኢየሱስ የመንፈሳዊ ልደት ማዕከል ነው። ምክንያቱም እርሱ የመጣው ከሰማይ ነው። በብሉይ ኪዳን እንደተሰቀለው የነሐስ እባብ (ዘኁ. 21፡4-9 አንብብ) እርሱም ይሰቀላል ይላል። ያንን የተሰቀለ የነሐስ እባብ የተመለከቱ ሰዎች እንደተፈወሱ ሁሉ፥ ኢየሱስም በመስቀል ላይ ይሰቀላል፤ ለሰዎችም ሁሉ ፈውስ ይሆናል።

መ. ድነት (ደኅንነት) በራሱ የሚሆን ነገር ሳይሆን የሰዎችን ስሜትና አቀባበል የሚሻ ነው። ለመዳን የሚፈልጉ ሰዎች በኢየሱስ ማመን አለባቸው። ማመን ያለባቸው ምንድን ነው? ኢየሱስ ኃጢአታቸውን በመስቀል ላይ እንደ ተሸከመ ማመን አለባቸው። ምክንያቱም በእነርሱ ምትክ ሞቷል። ስለዚህ ከእነርሱ የሚጠበቀው በምትካቸው የሞተውን ኢየሱስ ማመን ብቻ ነው። ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት የተለየ የመዳኛ ሥራ መሥራት አይጠበቅባቸውም። ይህን ጊዜ ሰው ክርስቲያን ሆኖ ይወለዳል የሚለው የተሳሳተ አመለካከታቸው ይወገዳል። የድነት (የደኅንነት) ተስፋቸው ሁሉ የሚያርፈው ኢየሱስ በመስቀል ላይ የፈጸመላቸውን ሥራ በማመን ብቻ ይሆናል።

ሠ. የድነት (የደኅንነት) ወይም በኢየሱስ አነጋገር የዘላለም ሕይወት ምንጩ እግዚአብሔር ነው። እንዲወለድና እንዲሞት ኢየሱስን ወደዚህ ዓለም የላከው እግዚአብሔር አብ ነው። የላከውም ፍርድንና መንፈሳዊ ኩነኔ እንዲያመጣ አይደለም። ይልቁንም ኢየሱስን ወደ ዓለም የላከው፥ ለሰዎች ካለው ፍቅሩ የተነሣ ነው። ልጆቹ እንድንሆንና እንድንድን ስለወደደ ይህን አደረገ፡፡ በኋላ እንደምንመለከተው፥ የሚያምኑትን ሁሉ መርጦ ለኢየሱስ የሚሰጠው አብ ነው (ዮሐ 6፡35-40፤ 15፡16)።

ረ. የአንድ ሰው ውሳኔ ዘላለማዊ ውጤት አለው። ሰዎች የእግዚአብሔርን ስጦታ ከናቁ በዘላለም ኩነኔ ሥር ለመኖር መርጠዋል ማለት ነው። «ቀድሞውንም ተኮንነዋል» ማለት ነው። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች በመንፈስ ሙታን ናቸው። ከእግዚአብሔርም በረከት ስለራቁም፥ አንድ ቀን ቅጣታቸው ፍጻሜ አግኝቶ ለዘላለም በሲኦል ይጣላሉ። ነገር ግን ሰዎች በኢየሱስ ብቻ ካመኑ፥ የዘላለም ሕይወት አላቸው። ይህም ሕይወት ልዩ ሕይወት ነው፤ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት የምናደርግበትና የእግዚአብሔርን ቤተሰብ ፍቅር የምንካፈልበት ሕይወት ነው። ይህንን ሕይወት ይበልጥ ሙሉ በሆነ በረከት የምንወርሰው በመንግሥተ ሰማይ ነው። ከሞት በኋላ ማንም ሰው ሁኔታን መለወጥ አይችልም።

ሰ. በጥቅሉ ሲታይ ብዙ ሰዎች የዓለም ብርሃን የሆነውን ክርስቶስን አይቀበሉም። ለምን? ምክንያቱም ለእግዚአብሔር ለመገዛትና እርሱንም ለመታዘዝ ስለማይፈልጉ ነው። የእግዚአብሔርን «የብርሃን» መንገድ ጠልተው በኃጢአት ሕይወት ደስ ይሰኛሉ። አንድ ሰው ድነትን (ደኅንነትን) የሚያገኘው ጀርባውን ለኃጢአት ጽልመት ሰጥቶና ከዐመፅ ተለይቶ ወደ እግዚአብሔር ብርሃን ሲመለስ ብቻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዮሐንስ 3፡16ን በቃልህ አጥና። ለ) ይህንን ጥቅስ መሠረት አድርገህ ወንጌል ምን እንደሆነ ከ50 በማይበልጡ ቃላት ጻፍ። ለአንድ ሰው ስለ ኢየሱስ ለመናገር 3 ደቂቃ ብቻ ቢሰጥህ፥ በኢየሱስ አምነው ለመዳን እንዲችሉ ምን ትነግራቸዋለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: