ኢየሱስ ነጋዴዎችን ከቤተ መቅደስ አባረረ (ዮሐ. 2፡12-25)

ኢየሱስ ሦስት አስፈላጊ ሃይማኖታዊ በዓሎች ላይ ለመገኘት ወደ ኢየሩሳሌም የሄደ ይመስላል። ዮሐንስ የሚያቀርባቸው ቀጣዮቹ ታሪኮችም በእነዚያ በዓላት ሰሞን የተካሄዱ ነበሩ። የመጀመሪያው በዓል ፋሲካ ነው። ከሦስት ዓመት በኋላ ኢየሱስ በዚህ ዕለት ይሞታል። ኢየሱስ በዚህ ዕለት በቤተ መቅደስ ውስጥ የነበረውን አምልኮ በተመለከተ ጊዜ ስግብግብ ነጋዴዎች አምላኪዎቹን ይበዘብዙና የአምልኮውም መንፈስ በእንስሳት ግዢውና በገንዘብ ልውውጡ ምክንያት በተፈጠረው ጩኸት ታውኮ ነበርና ልቡ በቁጣ ተሞላ። የገመድ ጅራፍ አበጅቶ እንስሳቱን እና ነጋዴዎቹን ከመቅደሱ አባረራቸው።

ተመሳሳዮቹ ወንጌላት ኢየሱስ ነጋዴዎቹን ያባረረው በምድር ያለውን አገልግሎቱን ጨርሶ ከመምጣቱ ጥቂት ቀደም ብሎ እንደሆነ ሊያሳዩ፥ ዮሐንስ ግን በመጀመሪያው ላይ እንደሆነ አድርጎ ያቀርበዋል። ምናልባትም ኢየሱስ ሁለት ጊዜ፥ ማለትም በምድር አገልግሎቱ መጀመሪያና መጨረሻ ላይ፥ አድርጎት ሊሆን ይችላል።

ይህ የኢየሱስ ድርጊት ሁለት ተቃራኒ ውጤቶችን አስከትሏል። አንደኛው፥ ለኢየሱስ ተከታዮች ከፍተኛ እምነትና መረዳት አስገኝቶላቸዋል። በዚህ ውስጥ በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ላይ መሲሑ ለእግዚአብሔር ቤት ስለሚኖረው ቅናት የተገለጸው ሲፈጸም አዩ። ሁለተኛ፥ ለማመን ያልፈለጉት ሰዎች፥ ኢየሱስ ይህንን ለማድረግ ሥልጣን እንዳለው የሚያረጋግጥ ልዩ ምልክት ከእግዚአብሔር እንዲሰጣቸው ጠየቁ። ምንም እንኳ ኢየሱስ ብዙ ተአምራትን ቢሠራም፥ የትኞቹም ቢሆኑ የሃይማኖት መሪዎቹን ለማሳመን በቂ አልነበሩም። ስለዚህ ኢየሱስ እርሱ መሲሑ መሆኑን ለማሳየት ወደ ሞቱና ትንሣኤው ብቻ አመለከታቸው ኢየሱስ ወደ ፈውስ ተአምራቱና አጋንንትን ወደ ማውጣቱ ተአምር አልጠቆማቸውም። ኢየሱስ ከሚፈጽማቸው ተአምራት ውስጥ በጣም ታላቁና የመሲሕነቱ የመጨረሻ ማረጋገጫ (ምልክት) ሞቱና ትንሣኤው ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- እኛ እንዴት ነው አንዳንድ ጊዜ ኢየሱስ ከሞት በመነሣቱ ተአምር ይበልጥ ከመደሰት ይልቅ በፈውስ ተአምር ልንደሰት የምንችለው?

ዮሐንስ የሕዝቡንም ምላሽ ገልጾአል። እነርሱ «በስሙ አመኑ።» «ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፤ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና» (ዮሐ 2፡24-25) ተብሎ ተነግሮናል። በዚህም ዮሐንስ ከሁለት ዓይነት እምነት ጋር አስተዋውቆናል። አሁን እንደተገለጸው ዓይነት ጥልቅ ያልሆነ፥ እኔነት የሞላበት እምነት አለ። በዚህ ዓይነቱ እምነት ሰዎች ኢየሱስን የሚከተሉት ከእርሱ ስለሚያገኙት ነገር ብለው ነው። ኢየሱስ እነርሱ የሚፈልጉትን ነገር እስካደረገ ድረስ፥ ሊከተሉት ፈቃደኞች ናቸው። ነገር ግን የጠበቁትን ወይም ስግብግብ ፍላጎታቸውን ካላሟላላቸው፥ እንዲህ ዓይነት እምነት ያላቸው ሰዎች ፈጥነው ኢየሱስን ይከዳሉ። ለዚህ ነው ኢየሱስ ስለ እምነታቸው ያልተደሰተው። ወደ በኋላ የምናየው ሌላ ዓይነት እምነትም አለ፥ በኢየሱስ ማንነት ላይ እርግጠኛ ሆኖ የተደላደለ እምነት። ይህም ምድራዊ በረከቶች ቢኖሩም ባይኖሩም በስደት ውስጥም እንኳ ቢሆን፥ የግለሰቡ እምነት ጽኑ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያናችሁ ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች የትኛው ዓይነት እምነት አላቸው ብለህ ነው የምታስበው? ለ) ትክክለኛው ዓይነት እምነት እንዳለን ለማረጋገጥ እንዲረዳን ልባችንን እና ኢየሱስን የምንከተልበትን ምክንያት መመርመሩ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading