ክርስቶስ የሕይወት እንጀራ ነው (ዮሐ. 6፡25-71)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች ለሕይወት ወሳኝ ናቸው የሚሏቸውን ነገሮች ዘርዝር። ለ) እነዚህን ነገሮች ባለማግኘትህ ምክንያት የምታጣቸውን ነገሮች ዝርዝር። ሐ) የምንፈልጋቸው ወይም የምናጣቸው ነገሮች ለእኛ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች መሆናቸውን የሚያሳዩት እንዴት ነው?

የምንፈልጋቸው ነገሮች ልባችን የት እንዳለና ለምንስ ነገር ትልቅ ዋጋ እንደምንሰጥ ያመለክታሉ። ቤተሰብ አስፈላጊ በመሆኑ፥ ለጋብቻና ለልጆች ትልቅ ግምት እንሰጣለን። ገንዘብ ጠቃሚ በመሆኑ ለጥሩ ሥራ ትልቅ ግምት እንሰጣለን። ትምህርት ጠቃሚ በመሆኑ ለራሳችንና ለልጆቻችን ጥሩ ትምህርት ለማግኘት የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። ጤንነትም ጠቃሚ በመሆኑ፥ የተሟላ ጤንነት ለማግኘት እንጥራለን። ከእነዚህ ነገሮች ምንም የማይጠቅም የለም። ሁሉም አስፈላጊዎች ናቸው። ችግሩ ብዙ ጊዜ ሰይጣን ለእነዚህ ነገሮች ከመጠን ያለፈ ትኩረት እንድንሰጥ በማድረግ ራስ ወዳዶች ያደርገናል። ራስ ወዳድነት ለክርስቶስ ያለንን አምልኮ ጭምር ሊጎዳ ይችላል። ጸሎታችን ስለ ቤተሰባችን፥ ገንዘባችን፥ ትምህርታችንና ከጤና ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ብቻ ሆኖ ይቀራል። የምንፈልገውን የጸሎት መልስ ሳናገኝ ስንቀር ደግሞ በክርስቶስ ላይ የነበረን እምነት ይመናመናል። ካልተጠነቀቅን ክርስቶስን ስለ ማንነቱ ሳይሆን ስለሚሰጠን ነገር መከተል እንጀምራለን። ክርስቶስ ፈጣሪያችን፥ አዳኛችንና ጌታችን ነው። ክርስቶስ በሕይወታችን የምንፈልገውን በረከት ባይሰጠን እንኳ፥ በእርሱ ለማመን ማንነቱ በቂ ምክንያት ነው። ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጦ፥ «እግዚአብሔር ሆይ፤ ከፈወስኸኝ፥ ሥራ ከሰጠኸኝ፥ የትምህርት ስር ከከፈትህልኝ፥ እከተልሃለሁ።» የሚል እምነት ራስ ወዳድነት የተጠናወተው እምነት ነው። የራስ ወዳድነት እምነት ደግሞ በሕይወታችን ላይ የማንፈልገው ነገር ሲደርስ ይናዳል።

ብዙ አይሁዶች ኢየሱስን የሚከተሉት ለጥቅም ነበር። ምክንያቱም ኢየሱስ ተአምር እንዲያደርግ የሚፈልጉት ከፈውሱና ከምግቡ ለመቋደስ ብቻ ነበር። ስለዚህ የሚበልጠውን የመንፈሳዊ ጤንነት አስፈላጊነት ዘነጉ። ስለሆነም፥ በዚህ ምድር ሲኖሩ እጅግ አስፈላጊው ነገር እነርሱ የፈለጉት ጊዜያዊ በረከት ሳይሆን፥ እርሱ የሚሰጣቸው የዘላለም በረከት እንደሆነ ክርስቶስ አስገንዝቧቸዋል። እኛም የአይሁዶችንና የክርስቶስን ውይይት በመገንዘብ ራሳችንን ልንመረምርና ለምን ምክንያት ክርስቶስን እንደምንከተልና እንደምናመልክ መገንዘብ ይኖርብናል።

ሀ. እግዚአብሔር በእርሱ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ብዙ መልካም ሥራዎችን እንድንሠራ አይጠብቅብንም። ይህ የብዙ አይሁዶች አሳብ የነበረ ሲሆን፥ እያሌ ክርስቲያኖችና ሙስሊሞችም የሚጋሩት ነው። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ለመመሥረት ልናከናውነው የሚገባን አንድ ዐቢይ ሥራ አለ። ይኽውም ክርስቶስ በመስቀል ላይ በእኛ ምትክ በመሞት ባስገኘልን ስጦታ ላይ እምነታችንን ሙሉ ለሙሉ ማሳረፍ ነው።

ለ. የአይሁድ መሪዎች የኢየሱስን መሢሕነት የሚያመለክት ሌላ መረጃ ፈለጉ። እነዚህ ሰዎች በጥቂት ዓሣና እንጀራ አምስት ሺህ ሰዎችን ሲመግብ ከጥቂት ቀናት በፊት አይተው ነበር። ያዩት ግን ለእነርሱ በቂ አልነበረም። «አንተ ለአንድ ቀን ብቻ እንጀራ ሰጠኸን፤ ሙሴ ግን ለ40 ዓመታት መናን ሰጠን። እናም ከሙሴ እንደምትበልጥ አረጋግጥልን» ሲሉ ጠየቁት። መጀመሪያ ክርስቶስ ሙሴ መናን ሰጠን ማለታቸው ትክክል እንዳልሆነ አመለከተ። መናው የመጣው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነበር። አሁንም እግዚአብሔር አብ የተለየ መና እየሰጣቸው ነበር። ክርስቶስ ከሰማይ የመጣው ለዓለም የዘላለም ሕይወትን ለመስጠት ነው። መናው የዘላለም ሕይወትን ለመስጠት ካለመቻሉ ባሻገር ይህን መና የበሉ ሰዎች ሞተዋል። ኢየሱስ የሚሰጠው መንፈሳዊ እንጀራ ግን የዘላለም ሕይወትን ይሰጣል።

ሐ. አይሁዶች ክርስቶስ ከሰማይ የማያቋርጥ እንጀራ እንዲያዘንብላቸው በመፈለጋቸው፥ እርሱ የተናገረውን አሳብ በትክክል ሳይረዱ ቀሩ። ስለሆነም፥ ክርስቶስ አሳባቸውን ከሥጋዊ እንጀራ ወደ መንፈሳዊ እንጀራ መለሰ። ክርስቶስ የመጀመሪያውን «እኔ ነኝ» ቀመር ተናገረ (ዮሐ 6፡35)። እርሱ የሕይወት እንጀራ ነው። እርሱ የሚሰጠው መንፈሳዊ እንጀራ፥ የሰዎችን ጥልቅ ይኸውም መንፈሳዊ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ የሚያሟላ ነው። በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወትን መንፈሳዊ እንጀራና መንፈሳዊ ውኃ ተመግበው ይረካሉ።

መ. በክርስቶስ ማመን የግለሰብ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርም ሥራ ነው። ብዙ ክርስቲያኖች ስለ ድነት (ደኅንነት) ሁለት ዓይነት የተለያዩ አመለካከቶች አሏቸው። አንዳንዶች ድነት (ደኅንነት) የግለሰቡ ተግባር መሆኑን በመግለጽ፥ አንድ ሰው በኢየሱስ ሲያምን ይድናል ይላሉ። ከፈለገም ክርስቶስን በመተው ድነቱን (ደኅንነቱን) እንደሚያጣ ይናገራሉ፤ ይህ የብዙ ኢትዮጵያውያን አመለካከት ነው፤ በድነት (ደኅንነት) ሥራ ውስጥ የሰዎች ምርጫና ድርሻ ትልቅ እንደ ሆነ ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ በድነት (ደኅንነት) ሥራ ውስጥ የእግዚአብሔር ድርሻ ትልቁን ስፍራ ይይዛል ይላሉ። ግለሰቡ እንዲያምን የሚያደርገው እግዚአብሔር ስለሆነ፥ እርሱ ብዙም ምርጫ የለውም ይላሉ። ግለሰቡ ካመነ በኋላ የእግዚአብሔር ልጅ ይሆናል። ይህ ሰው በኃጢአት ሊወድቅና ክርስቶስን ሊክድ ቢችልም፥ ደኅንነቱን ሊያጣ ግን አይችልም ይላሉ። ይህም «የዘላለም ዋስትና» (eternal security) የሚባለው አመለካከት ሲሆን፥ አንድ ሰው በክርስቶስ እጅ ውስጥ ከገባ በኋላ ራሱ ግለሰቡን ጨምሮ ማንም ከክርስቶስ እጅ ሊያስወጣው እንደማይችል ያስረዳል (ዮሐ. 10፡28-29)።

ሁለቱም አመለካከቶች በከፊል እውነትነት አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሁለቱም አመለካከቶች ይናገራል። እግዚአብሔር ለሰዎች የመምረጥና የመተው መብት ሲሰጥ እንመለከታለን። በተጨማሪም፥ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች እምነታቸውን እንዳይጥሉ፤ ይህን ቢያደርጉ ግን ለዘላለም ኩነኔ እንደሚዳረጉ ሲያስጠነቅቅ እንመለከታለን። በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ የሚያምኑትን እግዚአብሔር ለእርሱ እንደ ሰጠና ከመካከላቸው አንድ እንኳ እንደማይጠፋ የተናገረውን ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦች እናገኛለን። ድነት (ደኅንነት) ካገኘንበት ቀን ጀምሮ እስከ ሙታን ትንሣኤ ድረስ ክርስቶስ እንደሚጠብቀንና የዘላለም ሕይወትን እንደሚሰጠን እሙን ነው። በተለይ ብዙ ሰዎች እምነታቸውን ክደው ወደ ዓለም እየተመለሱ እያየን፥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለቀረቡት ለእነዚህ ሁለት አመለካከቶች በቀላሉ መፍትሔ ልንሰጥ አንችልም። ነገር ግን በራሳችን ሥራ ላይ ከመጠን በላይ እንዳንደገፍ ልንጠነቀቅ ይገባል። (ጳውሎስ መፈለግንም ማድረግንም በእኛ የሚሠራው እግዚአብሔር እንደሆነ ገልጾአል። ፊልጵ. 2፡13 አንብብ።) እንዲሁም በእግዚአብሔር ምርጫና ጥበቃ ላይ ከመጠን ያለፈ ትኩረት በመስጠት ምርጫችን ዘላለማዊ መዘዞችን እንደሚያስከትል ልንዘነጋ አይገባም። ከቶውንም፥ «እንግዲህ ድኛለሁ። ምንም ባደርግ ክርስቶስ ይጠብቀኛል። ስለሆነም፥ እንዳሻኝ መኖር እችላለሁ» የሚል አመለካከት መያዝ የለብንም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንተ ክርስቶስን መርጠህ ሳለ ክርስቶስ ግን እግዚአብሔር አንተን ለእርሱ እንደ ሰጠህ መናገሩን እንዴት ትረዳዋለህ? ለ) ድነትን (ደኅንነትን) በተመለከተ በአማኙ ወይም በእግዚአብሔር ድርሻ ላይ ከመጠን በላይ ትኩረት መስጠቱ ምን ዓይነት ችግሮችን የሚያስከትል ይመስልሃል?

ሠ. አይሁዶች ክርስቶስ አምላክና ከሰማይ የመጣ መሆኑን ሲናገር ሊቀበሉት አልቻሉም። ወላጆቹንም እንደሚያውቁ ገለጹ (ዮሴፍ እውነተኛ አባቱ መስሏቸው ነበር።) እንጀራው አይሁዶች ሊበሉት የሚገባቸው ሥጋው እንደሆነ ሲናገር ደግሞ ጭራሽ ግራ ተጋቡ። ቁሳዊ እንጀራን ስለመብላት ያስቡ ነበርና፤ ክርስቶስ እርሱን በመብላት የራሱ ሰው እንድንሆን እየጠየቀን ነው? ሲሉ ተገረሙ። አይሁዶች ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ ስለሚሞተው ሞት እንደሚናገር አልገባቸውም ነበር፤ የሞቱ ምሳሌ የሆነውንና ለደቀ መዛሙርቱ እንዲበሉት ስለሰጣቸው እንጀራ እየተናገረ እንደሆነ አልተገነዘቡም።

ብዙ ክርስቲያኖች ይህን የክርስቶስን ትምህርት በትክክል አልተረዱትም። በቅዱስ ቁርባን ጊዜ የምንወስደው እንጀራና ወይን ወደ እውነተኛው የክርስቶስ ሥጋና ደም ይለወጣሉ ብለው የሚያስቡ ክርስቲያኖች አሉ። እነዚህ ወገኖች፥ የጌታን እራት በምንወስድበት ጊዜ የኢየሱስን ሥጋ እየበላንና ደሙንም እየጠጣን ነው ይላሉ። አንዳንዶች እንዲያውም አንድ ሰው ቅዱስ ቁርባን በሚወስድበት ጊዜ ይድናል ብለው ያስባሉ። ለዚህም ነው አንድ ሰው ሊሞት ሲል ቄስ ጠርተው ቅዱስ ቁርባን እንዲቀበል የሚያደርጉት ነገር ግን ኢየሱስ በዚህ ስፍራ በተምሳሌታዊ አገላለጽ የሚናገር ይመስላል። ክርስቶስ ሐሙስ ምሽት፥ ለደቀ መዛሙርቱ ሞቱን የሚዘክሩበትን ተምሳሌት ሰጣቸው። እንጀራው ጸጋውን፥ ወይኑ ደግሞ ደሙን ይወክላሉ። ሁለቱም በአንድነት ክርስቶስ ለዓለም ኃጢአት መሞቱን ያመለክታሉ። የጌታ እራት በሕይወታችን ውስጥ ለተፈጸመው ነገር ውጫዊ መገለጫ ነው። ሆዳችን እንጀራውንና ወይኑን እንደሚቀበል ሁሉ፥ በክርስቶስ በምናምንበት ጊዜ የክርስቶስ ሞት ሥጋውና ደሙ) የዘላለም ሕይወትን ለመስጠት በሕይወታችን ውስጥ ይሠራል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ወደ አንድ የመካነ ኢየሱስ ቄስ ዘንድ ሂድና በቅዱስ ቁርባን ጊዜ ኅብስቱና ወይኑ ምን እንደሚሆኑ ጠይቅ። የእርሱ አመለካከት ከአንተ እንዴት እንደሚለይ አብራራ።

ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የተከተሉት ሰዎች የኢየሱስን ትምህርት በትክክል ለመረዳት ሲቸገሩ ይታያል። ክርስቶስ ትተውት ሊሄዱ መዘጋጀታቸውን ስለተገነዘበ ሁለት ዋና አሳቦችን ተናገረ። አንደኛው፥ የዘላለም ሕይወትን የሚያገኙት በእርሱ በኩል ብቻ እንደሆነ አስጠነቀቃቸው። ክርስቶስ ከሚሰጠው የዘላለም ሕይወት ጋር ሲነጻጸሩ ሥጋዊ ምግቦችና የራስ ወዳድነት ፍላጎቶች ከቁም ነገር የሚገቡ አይደሉም። ክርስቶስን ትቶ መሄድ ማለት ከዘላለም ሕይወት ተቆርጦ መጥፋት ማለት ነው። ኢየሱስ የተናገራቸው ከባድ አሳቦች እርሱን ትተው እንዲሄዱ ከሚያስፈራሯቸው ይልቅ፥ ሁሉንም ነገር ለማወቅ እንደማይችሉ ተገንዝበው በትሕትና እርሱን መቀበል ያስፈልጋቸው ነበር። ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ በክርስቶስ ለማመን መሞከሩ ይበልጥ አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። ከዚያ በኋላ ክርስቲያኖች እርሱን ለማየት፥ ተአምራትን ሲሠራ በአካል ለመመልከት ወይም ሲያስተምር በአካል ተገኝተው ለመስማት አልቻሉም።

ሁለተኛው፥ ክርስቶስ ድነት (ደኅንነት) የእግዚአብሔር ሥራ እንደሆነ እንደገና አረጋገጠ። ክርስቶስ ልባቸውን ያውቅ ስለነበር፤ እምነታቸው በራስ ወዳድነት ላይ እንደተመሠረተና ትተውት እንደሚሄዱ ያውቅ ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር እንደ አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት፥ ዘላቂ እምነት ያላቸውን ሰዎች እንደሰጠው ያውቅ ነበር።

ሕዝቡ ትቶት ሲሄድ ደቀ መዛሙርቱ ብቻ ከክርስቶስ ጋር ቀሩ። ክርስቶስ እምነታቸውን ለመፈተን ፈልጎ እነርሱም ለመሄድ ይፈልጉ እንደሆነ ጠየቃቸው። በጴጥሮስ ቃል አቀባይነት ደቀ መዛሙርቱ እምነታቸው ክርስቶስ በሚያደርግላቸው ነገር ላይ ሳይሆን በመንፈሳዊ ቁም ነገሮች ላይ እንደተመሠረተ ገለጹለት። ጴጥሮስ፥ «ክርስቶስ ሆይ፥ አንተ አምላክ (‘ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ’ (የአይሁዶች አገላለጽ ነው) ነህ። አንተ የዘላለም ሕይወትን የሚሰጥ እውነት አለህ። ስለሆነም፥ ምንም ቢሆን ምን አንተን እናምንሃለን» አለ። ክርስቶስ በሚያደርግልን ጊዜያዊ ነገሮች ላይ እምነታችንን ከምንመሠርተው ከብዙዎቻችን በተቃራኒ፥ ጴጥሮስ በዋነኞቹ መንፈሳዊ ነገሮች ላይ ትኩረት መስጠትን ተምሮ ነበር።

ምንም እንኳ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሚሞትበት ጊዜ ሩቅ ቢሆንም፤ ክርስቶስ ይሁዳ አሳልፎ እንደሚሰጠው ያውቅ ነበር። ስለሆነም፥ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ‘ዲያብሎስ’ እንደሆነ እስጠነቀቀ። ይህንንም ያደረገው ይሁዳ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ውሎ ክርስቶስን አሳልፎ ስለሚሰጥ ነበር። አምላክ እንደ መሆኑ፥ ክርስቶስ የሰዎችን ልብ ያውቃል። ማን እንደሚክደው፥ ማን በእምነቱ ጸንቶ እንደሚቆምና አሳልፎ የሚሰጠውም ደቀ መዝሙር ማን እንደሆነ ያውቅ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ላለፉት ሦስት ወራት በቤተ ክርስቲያንህ የቀረቡትን ስብከቶች አስታውስ። ትኩረት የተሰጠው ክርስቶስ ለሰዎች በሚሰጣቸው ሥጋዊ ነገሮች ላይ ነው ወይስ መንፈሳዊ ነገሮች? ለ) ለዘላለም ከሚዘልቁ መንፈሳዊ ነገሮች ይልቅ በሥጋዊ ነገሮች (ቁሳቁስ፥ ፈውስ) ላይ የበለጠ ትኩረት ማድረግ አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: