- ክርስቶስ የወይን ግንድ ማለትም የተከታዮቹ መንፈሳዊ ሕይወትና ፍሬያማነት ምንጭ ነው (ዮሐ. 15፡1-17)
መንፈሳውያን ለመሆናችን ትልቁ መረጃው ምንድን ነው? በልሳን መናገራችን? ሌሎችን መፈወሳችን? ምስክርነት? ወይስ አምልኮ? መንፈሳውያን ለመሆናችን ትልቁ ምልከት ፍቅር መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ገልጾአል። ይህን በሕይወታችን ለመፈጸም ከሁሉም የከበደ መሆኑ ግልጽ ነው። ልንዘምር፥ ልንመሰክር፥ በልሳን ልንናገር እንችላለን። ለሰዎች ሁሉ ከራስ ወዳድነት መንፈስ የጸዳ ፍቅር ከመስጠት ጋር ሲነጻጸር እነዚህ ሁሉ ቀላል ናቸው።
ነገር ግን ፍቅርን የሕይወታችን አካል ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው? በዮሐንስ 15፡1-17 ላይ እንደምናነበው ፍቅር ከክርስቶስ ጋር ካለን ኅብረት የሚመነጭ ፍሬ ነው። በእስራኤል አገር በብዛት የሚገኘውን የወይን ተክል በምሳሌነት በመውሰድ፥ ክርስቶስ ምንም እንኳ በመካከላቸው በአካል ባይገኝም ደቀ መዛሙርቱ በፍቅሩ እንዲኖሩ አስተምሯቸዋል። በክርስቶስ መኖር አካላዊ ስፍራን የሚያመለክት ሳይሆን፥ ከእርሱ ጋር ሕያው የሆነ ኅብረት እንድናደርግ የሚያሳስበን ነው። ከክርስቶስ ጋር ሕያው የሆነ ኅብረት እስካለን ድረስ፥ ክርስቶስን መምሰላችን ተፈጥሯዊ ይሆናል። ክርስቶስ ፍቅር ስለሆነ፥ ሌሎችን በልዕለ ተፈጥሯዊ መንገድ እናፈቅራለን። የወይንን ተክል ምሳሌ አድርጎ በመውሰድ፥ ክርስቶስ ከእርሱ ጋር ተጣብቆ መኖር ምን እንደ ሆነ ገልጾአል።
ሀ. የወይኑ ባለቤትና ተካይ እግዚአብሔር አብ ነው። ወይን በኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ ስፍራዎች አይበቅልም። ወይን ከአንድ ግንድ ብዙ ቅርንጫፎች ያሉት ተክል ነው። ከሌሎች ተክሎች በተቃራኒ፥ ወይን በሚገባ የሚያድገው ሲገረዝ ነው። እንግዲህ ክርስቶስ በወይን ምሳሌ እግዚአብሔር አብ በሕይወታችን ውስጥ ምን ያህል እንደሚሠራ እየነገረን ነው። ሕይወታችን ፍሬያማ እንዲሆን ስለሚፈልግ፥ ያለማቋረጥ ይንከባከበናል።
ለ. ክርስቶስ የወይን ግንድ ነው። ሰባተኛው የክርስቶስ «እኔ ነኝ» ዓረፍተ ነገር «እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ» የሚለው ነው (ዮሐ 15፡1)። ከእግዚአብሔር ጋር የተለየ ኅብረት እንዳላቸው የሚናገሩ ሌሎች ሃይማኖቶችና አስተማሪዎች አሉ። ነገር ግን የትኞቹም እውነተኛ ወይን አይደሉም። ቅርንጫፎቹ (የክርስቶስ ተከታዮች) ሁሉ ከእርሱ ጋር የተጣበቁ ናቸው። መንፈሳዊ ሕይወታችን የሚፈሰው ከእርሱ ነው። ቅርንጫፍ እንደ መሆናችን ፍሬ ልንሰጥ የምንችለው ከክርስቶስ ጋር እውነተኛ ኅብረት ሲኖረን ብቻ ነው።
ሐ. ክርስቲያኖች ሁሉ ልዩ ልዩ ቅርንጫፎች ናቸው። እንደ ቅርንጫፍ፥ ዓላማችን እንዲሁ መኖር ሳይሆን፥ ፍሬ ማፍራት ነው። ፍሬ ልንሰጥ የምንችለው ደግሞ መንፈሳዊ ሕይወታችን ጤናማ ከሆነና መንፈሳዊ ሕይወታችን ከክርስቶስ ጋር ካለን ኅብረት የተነሣ የሚፈስስ ሲሆን ብቻ ነው። ይህም የብርቱካን ተክል ሕይወት ከሥሩና ከግንዱ ወደ ቅርንጫፎች በማለፍ ፍሬ ከሚሰጥበት መንገድ ጋር ተመሳሳይ ነው።
መ. እግዚአብሔር አብ (የተክሉ ባለቤትና ገበሬ) እኛን ፍሬያማ ለማድረግ የሚጠቀምባችው ሁለት ዐበይት መሣሪያዎች አሉት። ከእነዚህም፥ አንደኛው መግረዝ ነው። መግረዝ ማለት ዛፉ እንዲያድግና የተሻለ ፍሬ እንዲሰጥ ለማድረግ አንዳንድ አላስፈላጊ ነገሮችን ማስወገድ ነው። በተመሳሳይ መንገድ፥ እግዚአብሔር አብም መንፈሳዊ ፍሬ እንዳናፈራ የሚያደርጉንን ባሕርያት፥ ልማዶችና አመለካከቶችን ከእኛ ያስወግዳል። ይህ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ቅጣት ተብሎ ተጠቅሷል። የዕብራውያን ጸሐፊ እግዚአብሔር ልጆቹ ስለሆንን ይበልጥ ልጆቹን እንድንመስል እንደሚቀጣን ገልጾአል (ዕብ. 12፡4-10)። እርግጥ ነው ቅጣት ለጊዜው ያምማል፤ ዓላማው ግን ይበልጥ ፍሬያማ እንድንሆን ማድረግ ነው። ሁለተኛው፥ መቁረጥ ነው። እግዚአብሔር አብ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ቆርጦ ያስወግደዋል። ከዚያም እግዚአብሔር አብ በፍርድ እንደሚያቃጥላቸው ገልጾአል። ምሑራን ይህን በተመለከተ አንድ ዓይነት አቋም የላቸውም። ይህ ክርስቶስን ያልተከተሉና እግዚአብሔርም በሕይወታቸው እንዲሠራ ያልፈቀዱ ሰዎች በዘላለማዊ ሞት እንደሚቀጡ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ክርስቶስን እንከተላለን እያሉ ነገር ግን ይህንኑ የማያደርጉትን እግዚአብሔር እንደሚያስወግዳቸው የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። በሕይወታቸው የክርስቶስ ተከታዮች አለመሆናቸውን በማሳየታቸው እግዚአብሔር ፍርድን ያመጣባቸዋል። ወይም ደግሞ ክርስቶስ የሚናገረው ከኃጢአታቸው ንስሐ ለመግባት ያልፈለጉ ሰዎች በሥጋ የሚሞቱት ሞት ይሆናል (የሐዋ. 5፡1-11፤ 1ኛ ቆሮ. 11፡27-30)።
ሠ. እግዚአብሔር አብ የሚፈልገው ትልቁ ፍሬ ነገር ፍቅር ነው። እግዚአብሔርን ልንወድና ከእርሱ ጋር የቅርብ ኅብረት ልናደርግ ይገባል። (እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም አሳብህ፥ በፍጹም ሰውነትህ ውደድ። ማር. 12፡29-30)። እርስ በርሳችንም ልንዋደድ ይገባል። ኢየሱስ ወደ መስቀል ሞቱ ሊሄድ ሲል፥ በተደጋጋሚ የተናገረው ትልቁ ትእዛዝ ይህ ነበር። የክርስቶስ ተከታዮች ለመሆናችን ዋነኛው መረጃ ይሄ ነው። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ይሞት ዘንድ ከሰማይ ወደ ምድር ያመጣው ፍቅር ነው። ማፍቀር ማለት ሌሎችን በትሕትና ማገልገልና ካስፈለገም ስለ እነርሱ መሞት ማለት ነው።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያን ከሆንህበት ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር ሕይወትህን ሲገርዝ (ሲያስተካከል) የቆየው እንዴት ነው? ለ) ከክርስቶስ ጋር ያለህ ግንኙነት በተግባር የሚታየው እንዴት ነው? ሐ) የአንድ ክርስቲያን ትልቁ መረጃ (መለያ) ፍቅር ነው። ብዙ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን ፍቅር ለባልንጀሮቻቸውም ሆነ ለዓለም የማያላዩት ለምን ይመስልሃል? መ) ከሚስትህ፥ ከልጆችህ፥ ከቤተ ክርስቲያንህ ምእመናን፥ በማኅበረሰቡ ውስጥ ካሉ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለህን ግንኙነት መርምር። ሕይወትህን የሚመለከት ሰው በእነዚህ ሁሉ ላይ ፍቅርን እያሳየህ ነው ብሎ የሚመሰክርልህ ይመስልሃል? ካልሆነ ለምን? ሠ) የክርቶስን ፍቅር በእነዚህ የሕይወትህ ክፍሎች ሁሉ ልታሳይ የምትችልበትን መንገዶች በምሳሌ ዘርዝር።
- ዓለም ደቀ መዛሙርትን መጥላቱ (ዮሐ 15፡18-27)
ምንም ይሁን ምን እግዚአብሔር ከእኛ የሚጠብቀው ፍሬ ፍቅር ነው። ይህ ማለት ግን ሌሎች እኛን ይወዱናል ማለት አይደለም። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ከማያምኑ ሰዎች ፍቅርን ሳይሆን ጥላቻን መጠበቅ እንዳለባቸው አሳስቧል። ኃጢአት የሌለበት የእግዚአብሔር ልጅ ከሰማይ ወደ ምድር የመጣው በፍቅር ምክንያት ነው። ነገር ግን ተጠላ፥ በመስቀልም ላይ ተሰቅሎ እንዲሞት ተደረገ። የእግዚአብሔር ልጆችም ተመሳሳይ ዕጣ ይጠብቃቸዋል። ለሌሎች ፍቅር ለማሳየት ብንፈልግም እንኳ፥ መጠላታችን የማይቀር ነው። በዓለም መጠላታችን ዓለም ከእግዚአብሔር አብ ወይም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት እንደሌለው ያረጋግጣል። ክርስቶስ ወደ ዓለም ከመጣ፥ በሰዎች መካከል ከኖረና ወደ እግዚአብሔር አብ መድረስ የምንችልበትን መንገድ ካሳየን በኋላ፥ የሰው ልጆች በእግዚአብሔር ላይ እንዳመጹ ለመኖር ምንም ማመኻኛ የላቸውም።
ነገር ግን በሚጠላን ዓለም ውስጥ እንዴት መኖር አለብን? ምንስ ማድረግ አለብን? ዝም እንበል ወይስ ክርስቲያናዊ ማኅበረሰብ እንመሥርት? እንዲህ ማድረግ አንችልም። ትልቁ ሥራችን ለዓለም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መመስከር ነው። ይህንን የምናደርገው ብቻችንን ነው? አይደለም። አጽናኝና የእውነት መንፈስ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር ይሆናል። መንፈስ ቅዱስ በምንመሰክርበት ጊዜ ኃይልን መስጠት ብቻ ሳይሆን፥ እርሱ ራሱም ለዓለም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይመሰክራል። መንፈስ ቅዱስ ከዳኑት ጋር ከመሥራቱም በተጨማሪ፥ ያልዳኑትን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ለማምጣት ስለ ኃጢአታቸው ይወቅሳል። መንፈስ ቅዱስ የሰዎችን ትኩረት ወደ ራሱ አይሰብም። ይልቁንም ትልቁ ዓላማው እንደ ብርሃን የሰዎችን ትኩረትን ወደ ክርስቶስ መሳብ ነው። ያላመኑት በክርስቶስ እንዲያምኑ፥ ያመኑት ደግሞ እርሱን እንዲመስሉና እንዲያመልኩ ያደርጋል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዓለም በክርስቲያኖች ላይ የምታደርሰውን በቃላት ሊገለጽ የማይቻል ጥላቻ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ስጥ። ለ) መንፈስ ቅዱስ፥ ሰው በክርስቶስ እንዲያምን ለማድረግ በልቡ ውስጥ ሲሠራ ያየኸው እንዴት ነው?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)