የሐዋርያት ሥራ ዓላማ

  1. የሐዋርያት ሥራ ዋነኛ ዓላማ በሉቃስ የተጀመረውን ታሪክ መቀጠል ነው። ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ 1፡1 ላይ እንደሚለው የመጀመሪያ መጽሐፉ ኢየሱስ “ያደርገውና ያስተምረው ዘንድ ስለ ጀመረው” ነገር እንደሚያወሳ ገልጾአል። ይህ መጽሐፍ የክርስትናን ሥራ አጀማመር ያስረዳል። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ደግሞ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን መሪዎችና በመንፈስ ቅዱስ የክርስቶስ ሥራና ትምህርት እንዴት እንደ ቀጠለ ያስረዳል። ሉቃስ ትንሿ ቤተ ክርስቲያን በፍጥነት አድጋ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሮም ግዛት ከነበሩት ዐበይት ሃይማኖቶች አንዷ ልትሆን የበቃችበትን ሁኔታ ያብራራል። ብዙ ምሑራን በሐዋርያት ሥራ 1፡4 ላይ ለቴዎፍሎስ «የተማርኸውን ነገር ታውቅ ዘንድ” ተብሎ የተገለጸው አሳብ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ዓላማ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ። እንዲሁም ሉቃስ የአጻጻፍ ስልቱና የዓይን ምስክሮች ጥንቅሩ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ያሉትን መረጃዎች እንዴት በጥንቃቄ እንደ መረጠ ያሳያሉ ይላሉ።

የውይይት ጥያቄ:- የሐዋ. 1፡8 አንብበህ በቃልህ አጥና፡፡ ሀ) ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠው አገልግሎት ምንድን ነው? ለ) በዚህ ትእዛዝ ውስጥ የተጠቀሱት አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው?

  1. ወንጌሉ እንዴት ከኢየሩሳሌም እንደ ጀመረና ከዚያም ወደ ሰማርያና እስከ ምድር ዳርቻ ሁሉ እንዴት እንደ ተስፋፋ ለማብራራት፥ የጴጥሮስንና የጳውሎስን ታሪኮች በመጠቀም፥ ሉቃስ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ክርስቶስ የሰጣትን ትእዛዝ መፈጸም እንደ ጀመረች ያሳያል።
  2. ከአይሁዶችና ሮማውያን ክርስትናን ለመከላከል፡- ሉቃስ የጴጥሮስንና ጳውሎስን ስብከቶች በመጠቀም ክርስትና አዲስ ሃይማኖት ሳይሆን እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን የተነበያቸው ዓላማዎች ፍጻሜ እንደሆነ አመልክቷል። ስለሆነም፥ አይሁዶች ክርስትና የተስፋዎቻቸውና የሕልሞቻቸው ፍጻሜ እንደሆነ አምነው መቀበል ያስፈልጋቸው ነበር።

ሉቃስ ክርስትና ከይሁዲነት መምጣቱን ለሮማውያንም ያብራራላቸዋል። ይህ ሮምን ለመገልበጥ የተደረገ የፖለቲካ ንቅናቄ ሳይሆን፥ የሰዎችን ልብ ለመለወጥ የሚሻ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ እንደሆነ ያብራራላቸዋል። ብጥብጥን የሚቀሰቅሱት ክርስቲያኖች ላይሆኑ፥ ክርስቲያኖችን ለማሳደድ የሚጥሩት አይሁዶች ነበሩ። በዚህ ወቅት በሮም እስር ቤት ውስጥ የነበረው ጳውሎስም ሲሆን የሮምን መንግሥት የሚያሰጋ ሰው አልነበረም። ምንም በደል አለመፈጸሙን የሮም ገዢ ሳይቀር መስክሮለታል (የሐዋ. 26፡31-32)። ስለሆነም፥ ጳውሎስን መፍታትና ክርስቲያኖችን ከማሳደድ መቆጠብ ተገቢ እንደሆነ ሉቃስ በመጽሐፉ ያሳስባል።

  1. ክርስቶስ በዘመናት ሁሉ ከሚኖሩት አብያተ ክርስቲያናት ምን እንደሚፈልግ የሚያሳይ ምሳሌ ለመስጠት፡- በአንድ በኩል፥ ሉቃስ ስለ ጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ዝርዝር ጉዳዮችን አይሰጠንም። ስለ እምነት መግለጫቸው፥ የጋብቻ ሥርዓቶቻቸው፥ የእሑድ አምልኮአቸው፥ በጥምቀት ወይም በጌታ እራት ጊዜ ስለሚደግሙት ቃሎች፥ ስለ ቀብር ሥርዓቶቻቸው፥ መሪዎች ስለሚመረጡባትና ቤተ ክርስቲያንም ስለምትደራጅበት መንገዶች የምናውቀው ነገር የለም። ይህም በየትኛውም ዘመንና ስፍራ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ራሳቸውን ለማደራጀትና አገልግሎታቸውን ለማካሄድ ብዙ ነጻነት እንዳላቸው ያሳያል። ይህም ሆኖ፥ ሉቃስ በየትኛውም ዘመን የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በምሳሌነት ሊከተሉአቸው የሚገቡ ነገሮችን ዘርዝሯል።

ሀ. እርስ በርስ መደጋገፍና ድሆችን መርዳት እንደሚያስፈልግ ጠቅሷል።

ለ. የመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሚገለጠው በተለወጠ ሕይወትና በተአምራት መሆኑን አስረድቷል።

ሐ. ሰዎች እንደ እግዚአብሔር ልጆች እንዴት መኖር እንዳለባቸውና የእግዚአብሔርንም ቃል ለተከታዩ የማስተላለፍ አደራ እንዳለባቸው ጠቅሷል።

መ. ለቤተ ክርስቲያን ሥራ፥ የኃይል ምንጭ ጸሎት መሆኑን ተናግሯል።

ሠ. የምስክርነት አስፈላጊነት፡- ይህም ሁሉም ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ፥ እንደ ወንጌላውያንና የወንጌል ልዑካን ያሉ የሙሉ ጊዜ አገልግሎቶች ምእመናን ሊደርሱ ወደማይችሉባቸው ስፍራዎች ወንጌሉን ማሰራጨት እንደሚገባቸው ያመለክታል።

ረ. በክርስቲያኖች መካከል የጠበቀ ኅብረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሷል።

ሰ. ስደት የክርስቲያኖችና የቤተ ክርስቲያን ሕይወት አካል መሆኑን ገልጾአል።

ሸ. «የጌታን እራት» ሥርዓት መፈጸም የአምልኮ ዋናው ነገር አድርጎ አቅርቦታል።

ቀ. በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ መሪዎች አስፈላጊ እንደሆኑ ጠቅሷል። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎትን ሲመሩ፥ ሌሎች ደግሞ ምንም የሌላቸውን ወገኖች ሥጋዊ ፍላጎት ያሟሉ እንደነበረ ጽፎአል።

የውይይት ጥያቄ፡- አንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ጠንካራ ሆና ለመገኘት፥ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ማሟላት ያለባት ለምንድን ነው?

  1. የቤተ ክርስቲያንን የዕድገት ሂደት ለማሳየት፡- ከአይሁዶችና ከአሕዛብ ከሚሰነዘርባት ስደት ባሻገር፥ የቤተ ክርስቲያንን ዕድገት የሚገታ ኃይል የለም። ቤተ ክርስቲያንን እግዚአብሔር በክርስቶስ አማካይነት መሥርቷታል። የክርስቶስ ሥልጣንና ኃይል ለቤተ ክርስቲያን ተሰጥተዋል (የሐዋ. 1፡8)። መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥና በቤተ ክርስቲያን አማካይነት ለመሥራት ራሱን ሰጥቷል። ስለሆነም «የገሃነም ደጆች» ወይም የሮም መንግሥት እንኳ ሊያሸንፉአት አይችሉም።

የውይይት ጥያቄ፡- ከመንፈስ ቅዱስ መገኘት የተነሣ፥ የቤተ ክርስቲያን ኃይል በኢትዮጵያ ውስጥ ሊገለጥ ያየሽው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading