የጳውሎስና በርናባስ አገልግሎት በቆጵሮስ፣ ጲስዲያ እና አንጾኪያ (ሐዋ. 13፡1-52)

ተመስገን ወጣት ክርስቲያን ነው። አባቱ የቤተ ክርስቲያን መሪ ነበሩ። ተመስገን በትምህርቱ ጎበዝ ስላልነበረ የማትሪክ ውጤቱ ሳይሰምርለት ቀረ። ይህም ቀጣይ የትምህርት ዕድሉን አበላሸበት። ሥራ የማግኘት ዕድሉም የመነመነ ሆነ። «የማደርገውን አውቃለሁ። ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ ገብቼ ወንጌላዊ እሆናለሁ። በዚህ ዓይነት እግዚአብሔርን እያገለገልሁ፥ ክፍያም አገኛለሁ። ከዚህም በላይ በቤተ ክርስቲያኔ ውስጥ በሌሎች የተከበርሁ እሆናለሁ» ሲል አሰበ። ይህንንም አሳብ ለአባቱ አቅርቦ አባቱ ሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱን ሽማግሌዎችn አግባብተው ልጃቸውን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እንዲሰድዱላቸውና ሲመለስም በወንጌላዊነት እንዲቀጥሩት አደረጉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ ሰዎች የቤተ ክርስቲያን ወንጌላዊ የሚሆኑት ለምን ይመስልሃል? ለ) አንድ ሰው ወንጌላዊ እንዲሆን ወይም እንዳይሆን ከእግዚአብሔር የሚመጣ ግልጽ ጥሪ አስፈላጊ የሚሆነው እንዴት ነው? ሐ) ለሥራ ወይም ለክብር ብሎ ወንጌላዊ በሆነ ሰውና፥ እግዚአብሔር ጠርቶኛል ብሎ ወንጌላዊ በሆነ አገልጋይ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

ዛሬ ጳውሎስ ወንጌላዊ ለመሆን እንዴት እንደ ተጠራ እናጠናለን። ጳውሎስ አገሩንና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑን ጥሎ በወንጌላዊነት ስም ዓለምን ለመዞር አሳብ አልነበረውም። ቤተ ክርስቲያንም ጳውሎስን በወንጌላዊነት ለመቅጠር አሳብ አልነበራትም። ነገር ግን እግዚአብሔር ለሥራው በግልጽ ጠራው። መንፈስ ቅዱስ በጳውሎስና በቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች ልብ ውስጥ በመሥራት፥ በርናባስና ጳውሎስ የእነርሱ ተጠሪዎች በመሆን ወንጌልን በዓለም ሁሉ እንዲያደርሱ በግልጽ ነገራቸው። በእግዚአብሔር ያልተጠሩ በጣም ብዙ ወንጌላውያን አሉ። እነዚህ ሰዎች ወደ ወንጌላዊነት አገልግሎት የመጡት በራሳቸው ወይም በሌላ ሰው ፍላጎት ነው። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ግልጽ የሆነ ጥሪ ካልተቀበሉ፥ ሰዎችም ሆኑ ቤተ ክርስቲያን በአገልግሎቱ እምብዛም ደስ አይሰኙም።

ከሐዋርያት ሥራ 13-28 ጀምሮ፣ የመጽሐፉ ትረካ ትኩረቱን ይቀይራል። ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ምዕ. 9 ላይ ጳውሎስን ካስተዋወቀን በኋላ፥ ከ9-11 ስለ ጳውሎስ ብዙ ነገር አይነግረንም። የነገረን ነገር ቢኖር ጳውሎስ በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ለማገልገል መምጣቱን ብቻ ነው። ሉቃስ ስለ ጴጥሮስ፥ እስጢፋኖስና ፊልጶስ ሲነግረን ከቆየ በኋላ፥ አሁን ደግሞ ስለ ጳውሎስ ይናገራል። ሉቃስ ከወዳጁ ጋር ብዙ ጊዜ ስለሚያሳልፍና አብሮትም ስለሚጓዝ፥ እነዚህን ታሪኮች በሚገባ ያውቃቸዋል። ወንጌሉ ወደ አሕዛብ አገሮች እንዲደርስ እግዚአብሔር በጳውሎስ ስለ ተገለገለ፥ ሉቃስ እግዚአብሔር በጳውሎስ አማካይነት ባከናወናቸው ተግባራት ላይ ያተኩራል።

  1. በርናባስና ጳውሎስ ወንጌልን ወደ ቆጵሮስ አደረሱ (የሐዋ.13፡1-12)

እግዚአብሔር የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ወደ ምድር ዳርቻ እንድታደርስ አዝዟት ነበር። ይህ ትእዛዝ ከተሰጠ 14 ዓመት ቢሆነውም፥ ወንጌሉ መድረስ የቻለው እስከ አንጾኪያ ድረስ ብቻ ነበር። በመሆኑም እግዚአብሔር የቀረውን የዓለም ክፍል ለመድረስ፥ ቤተ ክርስቲያንን የሚቀሰቅስበት ጊዜ ደረሰ። እግዚአብሔር ይህንን ታላቅ ተግባር ለማከናወን የኢየሩሳሌሟን እናት ቤተ ክርስቲያንን ሳይሆን፥ የአንጾኪያዋን ቤተ ክርስቲያን መምረጡ አስገራሚ ነበር። ሥራውን ለማከናወን ከ12ቱ ሐዋርያት አንደኛውን ስመ ጥር ሐዋርያ አልጠራም። ነገር ግን እግዚአብሔር የአሕዛቡን ዓለም በወንጌል ለመድረስ የሚያስችል ብቃት ያለውን ግለሰብ ነበር የጠራው። እግዚአብሔር ልዑል አምላክ በመሆኑ ሥራውን ለማከናወን ማንኛውንም ግለሰብ ወይም ቤተ እምነት መጠቀም ይችላል። ስለሆነም፥ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቤተ እምነት፥ ለእግዚአብሔር በሚያከናውነው ተግባር መመካት የለበትም። ነገር ግን ለእግዚአብሔር ታማኞች በመሆን፥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ሕያዋን መሆናችንን ማረጋገጥ አለብን። ይህ ሲሆን፥ እግዚአብሔር ለአገልግሎቱ በመረጠን ጊዜ ዝግጁ መሣሪያዎቹ መሆን እንችላለን።

የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን በርካታ የሆኑ ብርቱ መሪዎች ነበሯት። እነዚህም መሪዎች «ነቢያት» እና «አስተማሪዎች» ይባሉ ነበር። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ነቢያት ሁልጊዜ ከሐዋርያት ቀጥለው ይጠቀሱ ነበር። አዲስ ኪዳን ከመጻፉ በፊት እግዚአብሔር ፈቃዱንና አሳቡን ለሕዝቡ የሚያስታውቀው በነቢያቱ በኩል ነበር (1ኛ ቆሮ. 12፡28-29፤ ኤፌ. 2፡20)። ነቢያቱ የሚናገሯቸው ቃሎች መጻኢውን ወይም የወደፊቱን ዘመን የሚያመለክቱ ነበሩ። ይሁንና በአብዛኛው እንደምንገነዘበው ነቢያቱ ይናገሩ የነበረው ለዚያው ዘመን ሕዝብ ነበር። ይህ አገልግሎት በተለይ አዲስ ኪዳን ከመጻፉ በፊት በጣም ይሠራበት ነበር። አስተማሪ በጽሑፍ የሰፈረውን የእግዚአብሔርን ቃል ሰዎች መረዳትና መታዘዝ እንዲችሉ የማብራራት ስጦታ ያለው ሰው ነበር። አስተማሪዎችም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እጅግ አስፈላጊ መሪዎች ነበሩ (ኤፌ. 4፡11-13)።

ሉቃስ የአንኪያን ቤተ ክርስቲያን ዋና መሪዎች ስም የጠቀሰው፥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ምን ያህል ትልቅ እንደ ነበረች ለማመልከት ነው። በርናባስ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋነኛ መሪ በመሆኑ በቀዳሚነት የተጠቀሰው በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። «ኒገር» (ጥቁር) ተብሎ የአይሁድ ስም የተሰጠው ስምዖን አፍሪካዊ ሳይሆን አይቀርም። አንዳንድ ምሑራን ይህ ክርስቲያን የክርስቶስን መስቀል የተሸከመው የቀሬናው ስምዖን ይሆናል ይላሉ። ሉክዮስ (የላቲን ስም ሲሆን፥ ምናልባት ሮማዊ ስምም ሊሆን ይችላል) በሰሜን አፍሪካ ውስጥ የሚገኘው የቀሬና ሰው ነበር። መናሔ ምናልባትም አይሁዳዊ ሲሆን፥ የሄሮድስ አግሪጳ ጉዲፈቻ (ማደጎ) የነበረ ወንድም ሳይሆን አይቀርም። አይሁዳዊው ጳውሎስ የአሕዛብ ከተማ በሆነችው በተርሴስ ነበር ያደገው። የተለያዩ ዘሮች ወይም ጎሣዎች በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚኖሩበት ጊዜ፥ ሁሉም የጎሣ ቡድኖች በአመራሩ ውስጥ በሚገባ መወከላቸው አስፈላጊ ነው።

የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች በጊዜው ለምን ለጸሎትና ለጾም እንደ ተሰበሰቡ አናውቅም። ሆኖም እግዚአብሔር በርናባስና ጳውሎስን ለተለየ ሥራ የመረጠው እየጸለዩ ሳለ ነበር። ከዚህ አራት ዐበይት ነገሮችን ልንመለከት እንችላለን።

ሀ. በርናባስና ጳውሎስ ራሳቸውን አልመረጡም። እግዚአብሔር እነዚህን ሰዎች በመምረጥ ወንጌላውያን ሆነው መሄድ እንዳለባቸው ለመሪዎቹ ገልጾላቸዋል።

ለ. እግዚአብሔር ወንጌል ወዳልደረሰበት ስፍራ፥ ወንጌልን እንዲያደርሱ ተራ ሰዎችን አልመረጠም፤ የመረጠው ግን እንደ በርናባስና ጳውሎስ ያሉ ታዋቂ መሪዎችን ነው። አብያተ ክርስቲያናት ብዙውን ጊዜ ሰዎችን በወንጌላዊነት ለመላክ ፈቃደኞች ናቸው። ነገር ግን በስጦታቸው የተመሰከረላቸውን ለራሳቸው አስቀርተው፥ ስጦታ የሌላቸውን ወንጌላውያን አድርገው ለመላክ ይፈልጋሉ። ይህ ግን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ተቃራኒ ነው። እግዚአብሔር የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ምርጥ መሪዎቿን እንድትልክ ፈልጎ ነበር። በጳውሎስና በበርናባስ ፊት የተደቀነው ሥራ እጅግ ታላቅና ከባድ ስለነበር፥ እግዚአብሔርም የፈለገው ከፍተኛ ስጦታ ያላቸውን መሪዎች እንዲልኩ ነበር።

ሐ. በርናባስ እንደ ሽማግሌ መሪ፥ ጳውሎስ ደግሞ እርሱ እንደሚመራው ሰው ይታዩ ስለነበር በርናባስ ከጳውሎስ በፊት ተጠቅሷል። በመጀመሪያው የወንጌል አገልግሎት አጋማሽ ላይ ግን ይህ ቅደም ተከተል ተለውጦ፥ ጳውሎስ የቡድኑ መሪ ሆኗል።

መ. ከዚህ በኋላ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሽማግሌዎች በረከቶቻቸውን በመስጠትና እጆቻቸውን ጭነው በመጸለይ ለእግዚአብሔር ሥራ ላኳቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ወንጌላውያንን ስለ መምረጥ፥ ማሠልጠንና መላክ ከዚህ ምን እንማራለን? ለ) ይህ አሁን እኛ ከምናከናውነው ተግባር የሚለየውና የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ቤተ ክርስቲያንህ ወንጌላውያንን የምትመርጥበትና የምትልበትን መንገድ በተመለከተ ምን ልትለውጥ ይገባል?

በርናባስና ጳውሎስ ለመጀመሪያው የወንጌል አገልግሎት ሲሄዱ ዮሐንስ ማርቆስ የተባለ ወጣትን ይዘው ሄደዋል። ዮሐንስ ማርቆስ ከበርናባስ ጋር የመጣው፥ በርናባስና ጳውሎስ የእርዳታውን ገንዘብ አድረስው ከኢየሩሳሌም ሲመለሱ ነበር። ምናልባትም እንደ ረዳት እንዲያገለላቸው በማሰብ፥ ዮሐንስ ማርቆስ አብሯቸው እንዲሄድ የወሰነው በርናባስ ሳይሆን አይቀርም። እግዚአብሔር እንዲህ እንዲያደርጉ ያዘዛቸው ነገር ስለመኖሩ ምንም አናገኝም፡፡ ይህ ረዳት ይሆነናል ብለው የወሰዱት ሰው፥ የኋላ ኋላ በበርናባስና በጳውሎስ መካከል መቃቃርንና መከፋፈልን እንደሚያስከትል ሁለቱም ያጤኑት አይመስልም፡፡

በርናባስና ጳውሎስ መጀመሪያ የሄዱት ወደ ቆጵሮስ ደሴት ነበር። በርናባስ ያደገው በቆጵሮስ ስለነበር፥ መንፈስ ቅዱስ የወንጌል አገልግሎታቸውን በዚያ እንዲጀምሩ መራቸው። ወንጌሉን እየሰበኩ በደሴቲቱ መሀል በሚጓዙበት ወቅት፥ ሰርግዮስ ጳውሎስ የተባለ የሮም ባለሥልጣን ወንጌልን እንዲሰብኩለት ጠየቃቸው። ሰርግዮስ ጳውሎስ ጠንቋይ የነበረ አይሁዳዊ አማካሪ ነበረው። ይህ ሰው የበርናባስንና የጳውሎስን አገልግሎት ተቃወመ። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ በጠንቋዩ ኤልማስ ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ በማወጅ ዓይኑ እንዲታወር አደረገ። ሰርግዮስ ጳውሎስም በክርስቶስ አመነ ሉቃስ ይህን አስመልክቶ ሁለት ለውጦችን ዘግቦአል።

ሀ. እዚህ ላይ ሉቃስ ሳውልን በሮማዊ ስሙ ጳውሎስ እያለ መጥራት ይጀምራል። በዚህ ጊዜ የነበሩት በአሕዛብ ክልል ውስጥ በመሆኑ፣ ሉቃስ ከአይሁዳዊ ስሙ (ሳውል) ይልቅ የአሕዛብ ስሙን ለመጠቀም መርጧል።

ለ. የቡድኑን መሪነት ስፍራ ጳውሎስ ወሰደ። ከዚህ በኋላ በመጀመሪያ የወንጌል መልእክተኛነት አገልግሎት ወቅት በሙሉ ጳውሎስ መጀመሪያ ይጠቀሳል። እንዲያውም፥ በሐዋርያት ሥራ 13፡13 የበርናባስ ስም ሳይጠቀስ፥ ቡድኑ «ጳውሎስና ተባባሪዎቹ ተብሎ ተጠቅሷል። ምናልባትም በርናባስ ከአሕዛብ መሪዎች ጋር ለመሥራት ልምዱ አልነበረውም ይሆናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በዚህ ሁኔታ አንዱ ከሌላው በላይ ታዋቂ በሚሆንበት ጊዜ፥ በአብዛኛው ቅናት እንዴት በመሪዎች ውስጥ በቀላሉ ሰርጎ እንደሚገባ ግለጽ፡፡ ለ) በዚህ ጊዜ በበርናባስና በጳውሎስ መካከል በቀላሉ ቅናት ሊከሰት ይችል የነበረው እንዴት ነበር?

  1. ጳውሎስና በርናባስ በጲስዲያና በአንጾኪያ አገለገሉ (ሐዋ. 13፡13-52)

የወንጌል ልዑካኑ ቡድኑ ከቆጵሮስ ደሴት በስተ ሰሜን ወደሚገኘው የገላትያ ክፍለ ግዛት ተጓዘ። የባሕር ዳርቻ ከተማ ወደ ሆነችው ጴርጋን ሲደርሱ፣ ዮሐንስ ማርቆስ ተለይቷቸው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። ዮሐንስ ለምን ይህን እርምጃ እንደ ወሰደ አናውቅም፡፡ ምናልባት በዚህ ጊዜ ጳውሎስ በጠና ታሞ ስለነበር፥ (ገላ 4፡13-14)፥ እርሱም እንዳይታመም ፈርቶ ይሆናል። አንዳንድ ምሑራን ዮሐንስ ማርቆስ የአጎቱ (አክስቱ) ልጅ የሆነው በርናባስ መሪነቱን ለጳውሎስ በመልቀቁ ተበሳጭቶ ነበር ይላሉ። ሌሎች ደሞ ዮሐንስ ማርቆስ የተናደደው የጳውሎስ አገልግሎት ከአይሁዶች ይልቅ በአሕዛብ ላይ እያተኮረ በመሄዱ ምክንያት ነው ይላሉ። ምናልባት የተመለሰው አገሩን ስለናፈቀ ወይም የወንጌላዊነት ሥራ ከባድ ስለሆነበት ሊሆን ይችላል። ዮሐንስ ማርቆስ ለምን ወደ ኢየሩሳሌም እንደ ተመለሰ ባናውቅም፥ ጳውሎስ ግን ዮሐንስ ከእነርሱ በመለየቱ በጣም አዝኖ ነበር።

የውይይት ጥያቄ:- ሀ) የምናምነው ሰው እጅግ በምንፈልገው ሰዓት ትቶን ሲለይ በጣም የምንጎዳው እንዴት ነው? ለ) አንተ በጳውሎስ ስፍራ ብትሆን ኖሮ፥ ከቡድኑ አባላት መካከል አንዱ አገልግሎቱን ቢያቆም ምን ይሰማሃል?

ጳውሎስና በርናባስ ከጴርጋን ተነሥተው ከአንጾኪያ በስተ ሰሜን 90 ኪሎ ሜትር ተጓዙ። አንጾኪያ በገላትያ አውራጃ ውስጥ ወሳኝ ከተማ ነበረች። ከተማይቱ የሮም ቅኝ ግዛት ስለነበረች ብዙ ጡረታ የወጡ የሮም ወታደሮች ይኖሩባት ነበር። በርካታ የአይሁድ ሕዝብም ይኖርባት ነበር። ከተማዋ የተቆረቆረችው በርካታ መንገዶች በሚገናኙበት ስፍራ በመሆኑ፥ ወንጌልን ለማሰራጨት ምቹ ስፍራ ነበረች። ስለዚህ ወንጌል ከአንጾኪያ ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች ሊሠራጭ ይችል ነበር።

ጳውሎስና በርናባስ ምስክርነታቸውን በምኩራብ የመጀመር ልማድ ነበራቸው። ብሉይ ኪዳንን ይከተሉ የነበሩ አይሁድና አሕዛብ ከአረማዊው ሕዝብ ይልቅ የወንጌልን እውነት በቀላሉ ለመረዳት ይችሉ ነበር። አይሁዶች በእግዚአብሔር የተመረጡ ሕዝቦች በመሆናቸው፥ ንስሐ ገብተው በክርስቶስ እንዲያምኑ ሁልጊዜ የመጀመሪያ ዕድል ይሰጣቸው ነበር። በአይሁድ ባሕል ከሌላ ስፍራ የሚመጡ እንግዳ መምህራን፥ ከአምልኮው ፍጻሜ በኋላ የጽሞና መልእክቶችን እንዲያካፍሉ ይጋበዙ ነበር። ስለሆነም፥ የምኩራቡ መሪዎች ጳውሎስና በርናባስ የጽሞና መልእክቶችን እንዲያካፍሉ ጋበዟቸው። ስለዚህ የቡድኑ ቃል አቀባይ የነበረው ጳውሎስ ወንጌልን ማካፈል ጀመረ። ጳውሎስ የሚናገረው ለአይሁዶች በመሆኑ፥ መልእክቱ ቀደም ሲል በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ከተመለከትናቸው የጴጥሮስና የእስጢፋኖስ ስብከቶች ጋር ተመሳሳይ ነበር። ጳውሎስ ያተኮረው በብሉይ ኪዳንና በእግዚአብሔር አሠራር ላይ ነበር። ከዚያም ስለ መጥምቁ ዮሐንስና ስለሚመጣው መሢሕ የተናገረውን ትንቢት ገለጸ። በመቀጠልም ጳውሎስ የተሰቀለውንና ከሞት የተነሣውን ክርስቶስን አስተዋወቃቸው። ጳውሎስ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን በመጥቀስ፥ ክርስቶስ ይመጣል ተብሎ የተነገረለት መሢሕ መሆኑን በሚገባ አብራራላቸው። ከዚያም ሕዝቡ ንስሐ ገብተው በክርስቶስ እንዲያምኑና የኃጢአታቸውን ይቅርታ እንዲያገኙ አጠመቃቸው። በመጨረሻም አይሁዶች እንደ ቀደሙት አባቶቻቸው ወንጌሉን ቸል እንዳይሉ በማስጠንቀቅ ስብከቱን ደመደመ።

አይሁዶችና ፈሪሃ እግዚአብሔር የነበራቸው አሕዛብ፥ ጳውሎስ ባሰማቸው ቃል ስለተደነቁ በቀጣዩ ሰንበት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ፈለጉ። በጳውሎስ መልእክት ደስ የሚያሰኝ ነገር ስለ ሰሙ፥ በመጪው ሰንበት ብዙ አሕዛብ ሊሰሙት ተሰበሰቡ። ይህም ወንጌል ለእኛ ብቻ ነው ብለው ያስቡ የነበሩትን አይሁዶችና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ጥቂት አሕዛብን አስቆጣ። ስለዚህ አይሁዶች በጳውሎስና በርናባስ ላይ በቅናት ተነሣሡ።

በዚህ ጊዜ ጳውሎስና በርናባስ ወደ አሕዛብ ዘወር አሉ። ጳውሎስና በርናባስ እግዚአብሔር አይሁዶችን ብቻ ሳይሆን አሕዛብንም እንደሚፈልግ ሲናገሩ፥ አሕዛብ ደስ ተሰኙ። አሕዛብ በአይሁድ እምነት ውስጥ ብዙ የሚወዷቸው ነገሮች ነበሩ። በሰዎች እጅ ያልተሠራ ንጹሕና ቅዱስ አምላክ በማምለካቸው ደስተኞች ነበሩ። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ለማድረና በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት መገረዙንና አይሁድ መሆኑን አይወዱትም ነበር። አይሁድ መሆን ሳያስፈልጋቸው የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆን እንደሚችሉ ሲነገራቸው፥ ብዙ አሕዛብ አመኑ። ከዚህ ምቹ ከተማ ወንጌሉ ወደ ገላትያ አውራጃ ተሰራጨ።

ሉቃስ፥ የሐዋርያት ሥራን ከጻፈባቸው ዓላማዎች አንዱ ክርስቲያኖችን የሚያሳድዱት ሮማውያን ሳይሆኑ አይሁዶች እንደ ነበሩ ለማሳየት ነበር፡፡ የሮም ባለ ሥልጣን የሆነው ሰርግዮስ ጳውሎስ፥ የጳውሎስንና የክርስቲያኖችን ትምህርት ሲቀበል፥ አይሁዶች ግን ሁከት አስነሡ። በአንጾኪያ አይሁዶች በከተማይቱ ውስጥ ከነበሩት ታላላቅ ባለሥልጣናት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በመጠቀም ጳውሎስና በርናባስ ከተማይቱን እንዲለቅቁ አደረጉ። ጳውሎስና በርናባስ ወደ ኢቆንዮን ሄዱ። በአንጾኪያ ግን ደስታና መንፈስ ቅዱስ የሞላባቸውን ደቀ መዛሙርት አፍርተው ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: