ወንጌል በኤፌሶን ተሰበከ (የሐዋ. 18፡23-19፡41)

ሉቃስ ከ53-57 ዓ.ም. ስለ ተካሄደው ሦስተኛው የወንጌል ተልእኮ ጉዞ ብዙም መረጃ አይሰጠንም። ሮሜ 1ኛና 2ኛ ቆሮንቶስን ጨምሮ፥ ከጳውሎስ እጅግ ወሳኝ ደብዳቤዎች መካከል አንዳንዶቹ የተጻፉት በዚህ ጊዜ ነበር። ሉቃስ ያተኮረው በሦስተኛው የጳውሎስ የወንጌል ጉዞ ወቅት ትልቅ የአገልግሎት ስፍራ በነበረችው የኤፌሶን ከተማ ላይ ነበር።

ወንጌል በኤፌሶን ተሰበከ (የሐዋ. 18፡23-19፡41)

ሀ. አጵሎስ በኤፌሶን አስተማረ (የሐዋ. 18፡23-28)። ጳውሎስ ሦስተኛውን የወንጌል ጉዞ የጀመረው በመጀመሪያው የወንጌል ተልእኮ ጉዞ የተከላቸውን የገላትያ አብያተ ክርስቲያናት በመጎብኘት ነበር። ነገር ግን በእንጾኪያ በነበረበትና ወደ ኤፌሶን በሚሄድበት ጊዜ እግዚአብሔር የሕዝቡን ልብ እዘጋጅቶ ነበር፡፡ በግብጽ እስክንድርያ ያደገውና ከፍተኛ ትምህርት የነበረው አጵሎስ (አይሁዳዊ)፥ ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን የተነገሩትን የተስፋ ቃሎች የፈጸመ መሢሕ እንደሆነ በመግለጽ አይሁዶችን ያስተምር ነበር። ነገር ግን አጵሎስ ስለ ክርስቶስ የሚያውቀው በዮሐንስ እስከተጠመቀበት ጊዜ ድረስ ነበር፡፡ ስለሆነም፥ ዮሐንስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር በግ እንደሆነ ማመልከቱን ያውቅ ነበር። ዮሐንስ ክርስቶስ በእሳትና በመንፈስ ቅዱስ እንደሚያጠምቅ በመግለጽ የሰጠውን ምስክርነት ያውቅ ነበር። ነገር ግን ስለ ክርስቶስ ሕይወት፥ ሞት፥ ትንሣኤና ዕርገት አያውቅም ነበር። ጵርስቅላና አቂላ የቀረውን የወንጌል ክፍል በማብራራት ይበልጥ ትክክለኛ መልእክት እንዲያቀርብ ረዱት። ሉቃስ ይህንን ታሪክ የጠቀሰው ለሁለት ምክንያቶች ነበር፡

 1. ሉቃስ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ከፊል እውቀት መያዝ አደገኛ መሆኑን ለማሳየት ይፈልጋል። ከእግዚአብሔር ቃል እውነት ከፊሉን ብቻ በታላቅ ቅንዓት ማስተማሩ በቂ አይደለም። እንዲያውም፥ ይህ የሰዎችን የእውቀት ሚዛናዊነት በማዛባት አደገኛ ውጤት ሊያስከትል ይችላል። አንድ ሰው ስለ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ሳያውቅ፥ በክርስቶስ ሊያምን ይችላል? ይህ የማይመስል ነገር ነው። ዛሬ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ከፊሉን ብቻ የሚያውቁ ብዙ ሰባኪዎች አሉ። ተገቢውን ሥልጠና ለማግኘት ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ በሙሉ ለማጥናት በቂ ጊዜ አይወስዱም። እነዚህ አስተማሪዎች የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ሚዛናዊ ባሕርይ እንዳላቸው አልተገነዘቡም። እንዲያውም አንድ ሰው በአንድ እውነት ላይ ብቻ ካተኮረ፥ አደገኛነቱ ይብሳል። ምክንያቱም የሰዎች እምነት ሚዛናዊ ባልሆነ ነገር ላይ እንዲመሠረት አድርጓል። ከፍተኛ መንፈሳዊ ቅንዓት ያላቸው መልካም ክርስቲያኖች፥ «በልሳን ካልተናገራችሁ ሙሉ ክርስቲያኖች አይደላችሁም» ሊሉ ይችላሉ። ወይም «እግዚአብሔር ከማንኛውም ዓይነት በሽታ ይፈውሳችኋል። ከታመምህ ምክንያቱ ኃጢአት መሥራትህ ነው ወይም የእምነትህ ማነስ ነው» ሊሉ ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ፥ «እግዚአብሔር ሊባርክህ ቃል ስለ ገባልህ እግዚአብሔርን በመታዘዝ ብትመላለስ ሀብታም ትሆናለህ» ይላሉ። እነዚህ ሁሉ ከፊል እውነቶች ናቸው። ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር ካልተመላከሩና ሚዛናዊነታቸው ካልተጠበቀ ሐሰት ይሆናሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህን የሚያስተምሩና የሚሰብኩ ሰዎች በሚገባ ሠልጥነው የእግዚአብሔርን ቃል በሙላት ማወቅ አለባቸው ስለሚለው ነጥብ ምን ያስተምረናል? ለ) የሚሰብኩ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል በብቃት እንዲያውቁ ለማድረግ ቤተ ክርስቲያንህ ምን እያደረገች ነው? ሐ) ቤተ ክርስቲያንህ ከፊል እውነት ብቻ ካላቸው ክርስቲያኖች ጋር በምትገናኝበት ጊዜ ምን ታደርጋለች? ቤተ ክርስቲያንህ እንደ ጵርስቅላና አቂላ ሌሎችን በእግዚአብሔር ቃል እውቀት ዕድገታቸው ልትረዳቸው የምትችለው እንዴት ነው?

 1. ሉቃስ በተጨማሪም የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር መሆን ብቻ በቂ እንዳልሆነና የክርስቶስ ተከታይ መሆን እንደሚያሻ አሳይቷል። ብዙ ምሑራን ከጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ችግሮች አንዱ የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ጉዳይ እንደሆነ ያስረዳሉ። እንደ አጵሎስና በሐዋርያት ሥራ 19 ውስጥ እንደሚገኙ ሌሎች ደቀ መዛሙርት ያሉት፥ ስለ ክርስቶስ ከፊል እውቀት ብቻ ነበራቸው። እነዚህ ሰዎች እውነተኛ አማኞች ነበሩ? ወይስ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ተጨማሪ እውቀት ያስፈልጋቸው ነበር? ከአጵሎስ ታሪክና ጳውሎስ ለዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ከመሰከረላቸው ቃል እንደምንረዳው፥ የክርስቶስን ሙሉ ምስል (ሞቱን፥ መቀበሩንና መነሣቱን) እስካልተረዱ ድረስ እውነተኛ አማኞች አይደሉም።

በኤፌሶን ለተወሰነ ጊዜ ካገለገለ በኋላ፥ እግዚአብሔር አጵሎስን ወደ ቆሮንቶስ መራው። በዚያው እግዚአብሔር ክርስቲያኖችን እንዲያስተምርና በክርስቶስ መሢሕነት የሚያምኑትን አይሁዶች እንዲያሳምን ተጠቀመበት። እግዚአብሔር የአጵሎስን ትምህርተ መለኮት እውቀትና ርቱዕ ተናጋሪነቱን ለመንግሥቱ መስፋፋት ተጠቅሞበታል። የሚያሳዝነው ሰይጣን በኋላ በቆርንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መከፋፈል ያስነሣ ነበር። የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ይልቅ ሰብአዊ መሪዎችን መምረጥ ጀመረች። ስለሆነም አንዳንዶች ጴጥሮስን፥ ሌሎች ጳውሎስን፥ የተቀሩት ደግሞ የንግግር ችሎታ የነበረውን አጵሎስን እንደሚከተሉ አስታወቁ። በ1ኛ ቆርንቶስ ውስጥ ጳውሎስ እግዚአብሔር የተለያየ ስጦታ ያላቸውን ሰዎች እንደሚጠቀም፥ እነዚህ አገልጋዮች ግን መሣሪያ ብቻ እንደሆኑ አብራርቷል። ቤተ ክርስቲያንን የሚተከለውና የሚያሳድገው እግዚአብሔር ነው (1ኛ ቆሮ.1፡10-17፤ 3፡1-5)።

ለ. ጳውሎስ በኤፈሶን የመጥምቁ ዮሐንስን ደቀ መዛሙርት አገለገለ ( የሐዋ. 19፡1-7)፡፡ ጳውሎስ ኤፌሶን ከተማ ሲደርስ አጵሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሄደ፡፡ ጳውሎስ በኤፌሶን አንድ አስገራሚ ነገር ተመለከተ። እንደ አጵሎስ ሁሉ የመጥምቁ ዮሐንስ ተከታይ የሆኑ ሰዎች በኤፌሶን ከተማ ነበሩ። ጳውሎስ ከእነዚህ ሰዎች ሕይወት ውስጥ አንድ የጎደለ ነገር ስለ ተመለከተ፥ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው እንደሆነ ጠየቃቸው። የሚያውቁት ለመሢሑ መምጣ በመዘጋጀት በዮሐንስ መጠመቃቸውን ብቻ በመሆኑ፥ ጳውሎስ ስለ ምን ጉዳይ እንደሚያወራ እንኳ አልገባቸውም ነበር። ክርስቶስ መጥቶ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት በትንሹ እስያ ውስጥ ወደምትገኘው ከተማቸው ተመልሰው ነበር። ከመጥምቁ ዮሐንስ ባገኙት አነስተኛ ትምህርትና መንፈሳዊ ቅንዓት በስተቀር እነዚህ ሰዎች በክርስቶስ ለማመን የሚያስችል መረጃ አልነበራቸውም። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ባቀረበላቸው ማብራሪያ መሠረት በክርስቶስ አምነው ተጠመቁ። ከዚያም ጳውሎስ በዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ላይ እጁን ሲጭንባቸው በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው በልሳንና በትንቢት ተናገሩ።

አንዳንድ ክርስቲያኖች ከድነት (ከደኅንነት) በኋላ በጸሎትና እጅን በመጫን መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ላይ እንደሚወርድ ለማስተማር ይህን ክፍል ይጠቅሳሉ፡፡ ነገር ግን ሉቃስ ይህን ሁልጊዜ የሚፈጸም ክርስቲያናዊ ልምምድ እንደሆነ ለማስተማር የፈለገ አይመስልም፡፡ ከዚህ ታሪክ ውስጥ የሚከተሉትን ነገሮች አጢን፡፡

 1. እነዚህ የዮሐንስ ተከታዮች በአዲስ ኪዳን ትምህርት መሠረት ድነትን (ደኅንነትን) እግኝተው ነበር? የሐዋርያት ሥራ ከዳር እስከ ዳር እንደሚያስተምረው፥ ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በኋላ ድነት (ደኅንነት) የሚገኘው በክርስቶስ በማመን ብቻ ነው። ለዚህም ነው ጴጥሮስ በሐዋ. 4፡12 ላይ ከሰማይ በታች ድነትን (ደኅንነትን) ለማስገኘት የሚችለው የክርስቶስ ስም ብቻ እንደሆነ የገለጸው። ሉቃስ አይሁዶች በብሉይ ኪዳን ላይ ያላቸው እምነት ከእንግዲህ ሊያድናቸው እንደማይችል አመልክቷል። ለመዳን በሞተውና ከምት በተነሣው በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ ስለሆነም፥ በአዲስ ኪዳን ግንዛቤ እነዚህ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ጳውሎስ እስካብራራላቸው ጊዜ ድረስ ክርስቲያኖች አልነበሩም ማለት ነው። እንደ ጵርስቅላና አቂላ በኤፈሶን የነበሩ ክርስቲያኖች ለእነዚህ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ድነትን (ደኅንነትን) ለምን እንዳላብራሩላቸው የምናውቀው ነገር የለም። ነገር ግን ስለ መንፈስ ቅዱስ የሚያውቁት ነገር ስላልነበረ፥ የወንጌሉንም እውነት በሚገባ አያውቁም ነበር።
 2. ጳውሎስ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲጠመቁ አድርጓል። ከኃጢአታቸው ንስሐ መግባታቸውንና ለእግዚአብሔር መንግሥት መዘጋጀታቸውን በመግለጽ የዮሐንስን ጥምቀት ተቀብለዋል። አሁን ደግሞ ለድነታቸው (ለደኅንነታቸው) በክርስቶስ ብቻ እንደሚታመኑ እርሱም መሢሐቸው እንደሆነ አምነው እንደሚከተሉት በመግለጽ የክርስቶስን ጥምቀት ተቀብለዋል።
 3. እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ለመስጠት ጳውሎስን መሣሪያ አድርጎ ተጠቅሞበታል፡፡ ጴጥሮስ በሳምራውያን ላይ እጁን በጫነ ጊዜ፥ መንፈስ ቅዱስን እንደ ተቀበሉ ሁሉ፥ በጳውሎስም አገልግሎት ተመሳሳይ ተግባር ተከናውኗል። ሉቃስ ይህ መንፈስ ቅዱስ ሁልጊዜ የሚመጣበት መንገድ ነው ብሎ እንዳስተማረ የሚያመለክት መረጃ የለም። ምክንያቱም ሉቃስ የጠቀሰው ይህ ያልተለመደ የመንፈስ ቅዱስ መውረድ/መምጣት በመሆኑ ነው። ምናልባትም ሉቃስ የጳውሎስ ኃይልና ሥልጣን አሁን ከጴጥርስ ጋር እኩል እንደሆነና ጳውሎስ ሐዋርያዊ ሥልጣን እንዳለው እንዲታወቅለት ፈልጎ ይሆናል። በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ቢያንስ በሌሎች ሁለት አጋጣሚዎች (ለአይሁዶች በሐዋርያት ሥራ 2 እና ለቆርኔሌዎስና ጓደኞቹ በሐዋርያት ሥራ 10) እጅ መጫን አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም ነበር፡፡
 4. እነዚህ ደቀ መዛሙርት በልሳንና በትንቢት ተናግረዋል። በዚህ ድርጊታቸው በሐዋርያት ሥራ 2 ከተጠቀሱት የአይሁድ ደቀ መዛሙርትና በሐዋርያት ሥራ 10 ከተጠቀሱት የመጀመሪያዎቹ የአሕዛብ አማኞች ጋር ይመሳሰላሉ። የመጀመሪያዎቹ የሰማርያ ሰዎች ባመኑ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በመካከላቸው መገኘቱ፥ በምን መረጃ እንደ ታወቅ አልተጠቀሰም (የሐዋ 8፡17)። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት በተመሳሳይ ገጠመኝ ውስጥ በማለፋቸው ሰዎች የእግዚአብሔርን በረከትና የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ማገኘት የሚችሉት በክርስቶስ በማመን ብቻ እንደሆነ ያመለክታል። ይህ የዮሐንስ ጥምቀት ብቻ በቂ እንዳልሆነ የሚያመላክት ውጫዊ ምልክት ነበር፡፡ (ማስታወሻ፡- እንዲያውም በትንቢት መናገራቸውን ስለሚያሳይ የበለጠ ልምድ እግኝተዋል። ይህ መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ላይ ባልተለመደ መንገድ በወረደ ጊዜ ያልተገለጸ ነው።)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን በመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ላይ እንዲህ ባለ አስደናቂ ሁኔታ ያወረደው ለምን ይመስልሃል? ለ) ሉቃስ ይህንን ታሪክ የጻፈው ሁልጊዜ ድነትና (ደኅንነትንና) መንፈስ ቅዱስን የምንቀበለው በዚህ መንገድ ብቻ መሆኑን ለማስተማር ይመስልሃል፥ ወይስ እግዚአብሔር ለተለየ ዓላማ መንፈስ ቅዱስን ስላወረደበት ሁኔታ ለመግለጽ? ለምን?

ሐ. ጳውሎስ በኤፌሶን የነበረው አገልግሎት (ሐዋ. 19፡8-41)። ጳውሎስ በኤፈሶን ከሁለት ዓመት በላይ አገልግሏል። ይህም በወንጌል አገልግሎቱ ወቅት በየትም ስፍራ ከቆየበት ጊዜ የሚበልጥ ነው። ሉቃስ ስለዚህ ጊዜ ብዙ ታሪኮችን ሊነግረን ሲችል፥ ጥቂቶቹን ብቻ መርጧል።

 1. ጳውሎስ አገልግሎቱን የጀመረው በአይሁዶች ምኩራብ ነበር። አይሁድ ወንጌሉን ለመቀበል ባለመፈለጋቸው ወደ አሕዛብ ዘወር አለ።
 2. ጳውሎስ ሲያስተምር ሰፊ የስብሰባ አዳራሽ ይጠቀም ነበር። በየዕለቱ ወደ አዳራሹ የሚመጡትን ክርስቲያኖችና ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች ያስተምር ነበር። አገልግሎቱ በጣም ውጤታማ በመሆኑ፥ በእስያ አውራጃ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሁሉ እየመጡ ይሰሙት ነበር። ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ወንጌልን ይዘው ይሄዳሉ። ሉቃስ እንዳለው፥ «በእስያም የሚኖሩ ሁሉ አይሁድም የግሪክ ሰዎችም የጌታን ቃል እስኪሰሙ ድረስ ሁለት ዓመት ያህል እንዲህ ሆነ” (የሐዋ. 19፡10)።
 3. እግዚአብሔር ቀደም ሲል በጴጥሮስ በኩል ታላላቅ ተአምራትን እንዳደረገ ሁሉ፥ የጳውሎስንም አገልግሎት በሚያስደንቁ ተአምራት አጽንቶለታል (የሐዋ. 5፡12-16)።
 4. ምናልባትም በኢየሩሳሌም ከአይሁድ ሊቀ ካህናት ጋር ዝምድና የነበራቸው የሚያምኑ የአስቄዋ ልጆች እንደ ምትሐት የክርስቶስን ስም ተጠቅመው፥ አጋንንት ለማውጣት ሲሞክሩ፥ አጋንንቱ በእነርሱ ላይ ተነሥተው መቷቸው። አጋንንትን ለማውጣት የሚያስችል ሥልጣንና ኃይል የሚገኘው ከክርስቶስ ጋር ባለን ግንኙነት እንጂ፥ እንደ ምትሐት የክርስቶስን ስም በመጥራት አይደለም። አጋንንት የሚወጡት የእግዚአብሔር ልጆች በክርስቶስ ላይ በጽኑ ሲደገፉ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠቀም የሚችሉትም በዚህ መንገድ ብቻ ነው።
 5. ክርስቲያኖች ከአሮጌው ሕይወታቸውና ከአምልኮተ ጣዖት በግልጽ ተለዩ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች ከአሮጌ ሕይወታቸው ተለይተው ክርስቶስን ለመከተል ይፈልጋሉ። ተብትቦ የያዛቸውን ነገር አሽቀንጥረው አይጥሉም፡፡ ወይም ደግም በሚታመሙበት ጊዜ በሰይጣን ኃይል ወደሚሠሩ ጠንቋዮች ይሄዳሉ። ሉቃስ የጣዖት አምልኮና የጥንቆላ ማዕከል በሆነችው ኤፈሶን ከጣዖት አምልኮና ከሰይጣን ጋር የተገናኘ ነገር ሁሉ እንደተወገደ ገልጾአል። የምትሐት መጽሐፎቻቸው 50,000 የሥራ ቀናት ደመወዝ ያህል ቢያመጡም፥ አማኞቹ ከማቃጠል አልተመለሱም። ሰይጣን እኛን ለመቆጣጠር የሚጠቀምባቸውን ነገሮች እስካላስወገድን ድረስ፥ ሰይጣን በሕይወታችን ላይ ያለውን ኃይል ሙሉ በሙሉ ልናፈርስ አንችልም። እነዚህም የቀድሞ አምልኮ ምትሐታዊ ነገሮች፥ መጥፎ መጻሕፍትና ቪዲዮዎች፥ ወደ ክፋት የሚመራ ጓደኝነትና የመሳሰሉት ሊሆኑ ይችላሉ።
 6. በኤፌሶን የወንጌሉ ኃይል ታላቅ በመሆኑ፥ አርጤምስ የምትባል ጣዖት የሚያመልኩ ሰዎች ስጋት ያዛቸው። አርጤምስ የሴቶችን ማኅፀን በማለምለም ልጆችን እንዲወልዱ ታደርጋለች የምትባል የኤፌሶን ሰዎች ትልቋ ጣዖት ነበረች፡፡ የአርጤምስ አምልኮ ብዙ ወሲባዊ ርኩሰቶችን ያካትት ነበር። የወርቅና የሌላም ጌጣጌጥ ሠሪዎች በአርጤምስ አምላኪዎች ላይ ጥገኞች ነበሩ። ሰዎች ትናንሽ የአርጤምስ ምስሎችን እየገዙ ወደ ቤታቸው ይወስዱ ነበር፡፡ ስለሆነም፥ ብዙ ሰዎች ክርስቲያኖች እየሆኑ ሲመጡ ገበያቸው እየቀነሰ መጣ። በዚህ ጉዳይ የተጨነቀው ድሜጥሮስ የተባለ ጌጣጌጥ ሠራተኛ በክርስቲያኖች ላይ ሁከት የሚያስከትሉ ሰዎችን አደራጀ። ነገር ግን ክርስቲያኖቹ በገዥው ፊት ሲቀርቡ ብጥብጥ እንዳላስነሱና የአርጤምስን ቤተ መቅደስ በቀጥታ እንዳላጠቁ ስላረጋገጠ፥ በነፃ አሰናበታቸው። ምናልባትም ሉቃስ ሮማውያን ይህንን ሁኔታ እንዲገነዘቡ ፈልጎ ይሆናል። ምንም እንኳ ክርስቲያኖች ጣዖትን ወይም ቄሣርን እንደማያመልኩ ቢታወቅም፥ የጣዖት አምልኮን በመቃወም፥ ቤተ ጣዖቶችን በማፈራረስ ተግባር አይሳተፉም ነበር። ስለሆነም፥ ክርስቲያኖች በሰላም የሚኖሩ እንጂ የሌሎችን ሃይማኖት ለማውደም የሚታገሉ አልነበሩም።

የእግዚአብሔር መንግሥት የሰይጣንን መንግሥት ድል የሚነሣው በሥጋዊ ውጊያ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ የጠንቋዮችን ቤቶች፥ የጥንቆላ ዕቃዎችና ዛፎች እንድናቃጥል አላዘዘንም። ነገር ግን ወንጌሉን በመስበክ መንፈስ ቅዱስ የራሳቸውን ነገሮች እንዲያቃጥሉ እንዲያነሣሣቸው፥ ለእርሱ አሳልፈን እንሰጣለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለኤፌሶን ክርስቲያኖች የጥንቆላ ዕቃዎቻቸውን ማቃጠል ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው? ለምን አይሸጧቸውም ነበር? ለ) ይህ አዳዲስ ክርስቲያኖች ቀደም ሲል የተጠቀሙባቸውን የአምልኮ ዕቃዎች ምን ሊያደርጉ እንደሚገባ ያስተምረናል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: