የጳውሎስ ስብከት በተሰሎንቄ፣ በቤሪያ፣ እና በአቴና (የሐዋ. 17፡1-34)

  1. ጳውሎስ በተሰሎንቄ ሰበከ (የሐዋ. 17፡1-9)

ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ወንጌልን የሰበከበት ትልቋ ከተማ ከፊልጵስዩስ 120 ኪሎ ሜትር ርቃ ትገኝ የነበረችው ተሰሎንቄ ናት። በተሰሎንቄ ብዙ አይሁዶች ስለነበሩ ጳውሎስ ምስክርነቱን ለመጀመር ወደ ምኵራብ ሄደ። በሦስት ተከታታይ ሰንበት ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን ተስፋ የተገባለት መሢሕ እንደሆነ አስተማረ። በዚህ ጊዜ አንዳንድ አይሁዶችና ሕያው የሆነውን ፈጣሪ ለማምለክ ሲሉ ከጣዖት የተመለሱ ብዙ አሕዛብ በክርስቶስ አመኑ። ይህም አንዳንድ አይሁዶችን በማስቆጣቱ፥ በጳውሎስና በሲላስ ላይ ሁክት አስነሡ፡፡ ጳውሎስንና ሲላስን ለማግኘት ባለመቻላቸው ጳውሎስን አስጠልሎ የነበረውን ኢያሶንን ወደ ባለሥልጣናት ጎትተው ወሰዱት። ከዚያም ጳውሎለና ሲላለ ሕገ ወጥ ሃይማኖት አስተምረዋል ብለው ከሰሷቸው። ኢያሶን ጳውሎስና ሲላስ የከተማይቱን ጸጥታ እንዳያውኩ ዋስትና እንዲሰጥና ይህ ካልሆነ ቀን የንብረት መወረስና እስራት እንደሚጠብቀው ተነገረው።

ከጳውሎስ የመጀመሪያ መልእክቶች መካከል ሁለቱ ለተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን የተጻፉ ናቸው። እነዚህ መልእክቶች የመከራ ውጤቶች በመሆናቸውና ጳውሎስ በእነዚህ መልእክቶች ውስጥ ካስተማራቸው እውነቶች መካከል አንዱ ክርስቶስ በቶሎ ይመለሳል የሚል ነበር፡፡ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ ሳይወስደን ይቀር ይሆን እያሉ ለሚጨነቁት የተሰሎንቄ ሰዎች፥ ጳውሎስ ክርስቶስ ገና እንዳልተመለሰና ቢመለስ ኖር ወደ ሰማይ ይወስዳቸው እንደነበር ገልጾላቸዋል፡፡

  1. ጳውሎስ ለቤሪያ ሰዎች ወንጌልን ሰበከ (የሐዋ. 17፡10-15)

በዚያን ሌሊት የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ጳውሎስና ሲላስ ከተሰሎንቄ 80 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ቤሪያ እንዲሄዱ መከሯቸው። በቤሪያም ብዙ አይሁዶች ስለነበሩ፥ ምስክርነታቸውን በምኩራብ ጀመሩ፡ ነገር ግን እነዚህ አይሁዶች ጳውሎስን ካጋጠሙት አይሁዶች ሁሉ የተለዩ ነበሩ፡፡ አዲስ በመሆኑ ብቻ ትምህርቱን ላለመቀበል ከማንገራገር ወይም ትውፊትን ከማጣቀስ ይልቅ፥ ጳውሎስ የተናገረውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያነጻጽሩ ጀመር፡፡

ዛሬ በአስተማሪዎች፥ ካሴቶች፣ ቪዲዮዎችና በሌሎችም መንገዶች ብዙ እንግዳ ትምህርቶች ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ናቸው፡ ምን ማድረግ አለብን? የሚያስተምሩት እውነት ይሁን አይሁን እንዴት እናውቃለን? ጥሩ ስለሚመስሉ ብቻ ልንቀበላቸው ይገባል? ሉቃስ ለክርስቲያኖች እውነትን ከሐሰት፥ ከእግዚአብሔር የሆነውን እንደ የብርሃን መልአክ መስሎ ራሱን ከሚለውጠው ከሰይጣን አሳብ ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል አንድ ፍጹም መመዘኛ ብቻ እንዳለ ገልጾአል። ይህም መመዘኛ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንተና ቤተ ክርስቲያንህ የሚቀርበውን ትምህርት፥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጻፈው አሳብ ጋር በጥንቃቄ የምትገመግሙት እንዴት ነው? ለ) የምንሰማውና የምናየው ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው ብሎ መደምደሙ አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው?

ቤተ ክርስቲያን በቤርያ ተወልዳ አደገች። ብዙም ሳይቆይ ታዲያ አይሁዶች ሁከት አስነሡ። (ማስታወሻ፡- ሉቃስ በእነዚህ ስፍራዎች ሁሉ ጳውሎስና ሲላስ ሁከት አለመቀስቀሳቸውን ለማመልከት ይፈልጋል። ሁከት የሚያስነሡት አይሁዶች ነበሩ። የሐዋርያት ሥራ በተጻፈበት ጊዜ እስር ቤት ውስጥ የነበረው ጳውሎስ ለአይሁዶች ተግባር በኃላፊነት መጠየቅ አልነበረበትም። ይልቁንም አይሁዶች በራሳቸው ሥራ መጠየቅ ነበረባቸው።) ስደቱ ያተኮረው በጳውሎስ ላይ ስለሆነ፥ ከተማይቱን ለቅቆ መውጣት ነበረበት፡፡ ሲላስና ጢሞቴዎስ ግን ከፊልጵስዩስ ስለመጡ፥ አጻዲስ አማኞችን ማስተማር ጀመሩ።

  1. ጳውሎስ ወንጌልን በአቴና ሰበከ (የሐዋ. 17፡16-34)

ጳውሎስ ከደቡብ ቤሪያ 300 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ወደምትገኘው ወደ አቴና በመርከብ ተጓዘ። አቴና ከ500 ዓመታት በፊት የምዕራቡ ዓለም የሥልጣኔ ማዕከል ነበረች። የትምህርት፥ የሥነ ጥበብ፥ የፍልስፍናና የሥነ ጽሑፍ ማዕከል ነበረች፡፡ የግሪክ ሥልጣኔ ወደ ጥንቱ ዓለም የተስፋፋው ከአቴንስ ነበር። በጳውሎስ ዘመን የአቴና ክብር ገና ያልደበዘዘ ስለነበር፥ እንደ ወትሮው የትምህርትና የፍልስፍና ማዕከል ነበረች።

ሉቃስ፥ ጳውሎስ ወደ ምኩራብ ገብቶ እንዳስተማረ ቢናገርም፥ ታሪኩ ያተኮረው ጳውሎስ አረማዊ ፈላስፎችን በማስተማሩ ላይ ነው። ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የሚያቀርበው ትንተና ለእነርሱ ፍጹም አዲስ እውነት ስለነበር፥ ፈላስፎቹ ለመስማትና ለመገምገም ፈቀዱ። ምሑራን ተሰብስበው ወደሚወያዩበት አርዮስፋጎስ ወደ ተባለ ስፍራ ወሰዱት። ጳውሎስ ለእነዚህ አሕዛብ ምሑራን ወንጌልን የመሰከረበት መንገድ ብሉይ ኪዳንን ለማያውቁ አሕዛብ ይመሰክርበት የነበረው ዘዴ ሳይሆን አይቀርም።

ጳውሎስ የተነሣው እነዚህ አሕዛብ ምሑራን ከማያውቁት አሳብ ነበር፡፡ የብሉይ ኪዳኑን ፈጣሪ አምላክን ስለማያውቁ፥ ጳውሎስ በሚገባቸው መንገድ ወንጌሉን ማብራራት ነበረበት። የግሪክ ሰዎች አንድን አምላክ ሳያውቁና ሳያከብሩ ቀርተው እንዳያስቀይሙት ይፈሩ ነበር። ስለሆነም፥ «ለማይታወቅ አምላክ» መሠዊያ ሠርተው ነበር። ጳውሎስ ይህ እነርሱ የማያውቁት አምላክ ማን እንደሆነ በመግለጽ ስብከቱን ጀመረ።

ሀ. እርሱ የሰዎች ሁሉ ፈጣሪ ነው። እርሱ የሕይወት ሁሉ ምንጭ ነው። ጳውሎስ አሳቡን ለማስደገፍ የግሪክ ፈላስፎችን ጠቅሷል። (ይህ ጳውሎስ በአይሁድ ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን በግሪክ ትምህርትም የገፋ ምሑር እንደነበር ያሳያል።)

ለ. እውነተኛው አምላክ በእጅ የተሠራ ሳይሆን፥ በዓይን የማይታይ ነው።

ሐ. እግዚአብሔር ሰዎችን ከእርሱ ጋር ባላቸው ግንኙነት መሠረት በኃላፊነት ይጠይቃቸዋል። እርሱ ፈራጃቸው ስለሆነ፥ ለሚሠሩት ሥራ ሁሉ ለእርሱ ተጠያቂነት አለባቸው።

ጳውሎስ ለእነዚህ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ብዙም ሊያብራራላቸው አልቻለም። ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ መናገር ሲጀምር፥ በሙታን ትንሣኤ የማያምኑት ግሪኮች ይስቁበት ጀመር። .

በአቴና ጥቂቶች በከርስቶስ ቢያምኑም፥ በዚያ ግን ቤተ ክርስቲያን ልትመሠረት አልቻለችም፡፡ አንዳንድ ምሑራን ከተማሩ ሰዎች ጋር መከራከሩ ውጤት እንደማያስገኝ ከአቴና ተሞክሮ በመገንዘቡ፥ ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ በሄደ ጊዜ ለመዳን የእግዚአብሔር ኃይል በሆነው የክርስቶስ መስቀል ላይ ብቻ እንዳተኮረ ይናገራሉ (1ኛ ቆሮ. 1፡18)። ጳውሎስ በኋላ እግዚአብሔር ብዙ የተማሩ ሰዎችን እንዳልጠራ ገልጾአል። (1ኛ ቆሮ. 1፡18-2፡16 አንብብ።) ይህ የሆነው ክርስቶስ ሊያድናቸው ስላልፈለገ ሳይሆን፥ በትምህርታቸው በመኩራራት «የመስቀሉን ሞኝነት» ለማመን ባለመፈለጋቸው ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ የተማሩ፥ ሀብታሞች፥ ኃያላንና ታላላቅ ሰዎች በክርስቶስ ያለማመናቸው እውነታ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚታየው እንዴት ነው? ለ) ለእነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ክርስቶስንና የድነት (የደኅንነት) መንገዱን መቀበል የሚከብዳቸው ለምን ይመስልሃል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: