እግዚአብሔር ጳውሎስ ወንጌልን ወደ ሮም እንደሚያደርስ ተናግሮ ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ይህንን ለማድረግ የተጠቀመበት መንገድ ጳውሎስን ጨምር ብዙ ክርስቲያኖችን ሳያስገርም አይቀርም፡፡ ጳውሎስ እንደ ነጻ ሰው ሳይሆን ታስሮ ወደ ሮም ለመሄድ ተገደደ። ይህ እስረኛ ሆኖ የጀመረው ጉዞ ራሱ በችግር የተሞላና የሞት አደጋ ያንዣበበበት ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ጳውሎስን ሮም ለማድረስ ወስኖ ነበር። ስለሆነም፥ ማዕበልና የመስጠም አደጋ ቢደርስበትም፥ እግዚአብሔር ግን ባሪያውን ወደ ሮም ወስዶታል።
የውይይት ጥያቄ፡- የሐዋ. 27-28 አንብብ። ሀ) ከእነዚህ ምዕራፎች ስለ እግዚአብሔር መንገዶች ምን እንማራለን? ለ) ስለ ጳውሎስ ምን እንማራለን?
- ጳውሎስ ወደ ሮም ሄደ (የሐዋ. 27፡1-28፡16)።
ከጳውሎስ ጋር ወደ ሮም የተጓዘው ሉቃስ (ሉቃስ «እኛ» እያለ መጻፉን ልብ በላ) ስለ አስቸጋሪው ጉዞ በዝርዝር ጽፎአል። በጥንት ጊዜ ጀልባዎች በነፋስ እየተነዱ በሜድትራኒያን ባሕር ይጓዙ ነበር። እንደ ዛሬዎቹ መርከቦች ሞተር አልነበራቸውም። በተወሰኑ ወቅቶች ተደጋጋሚ ማዕበል ስለሚያጋጥም፥ ብልህ የሆኑ ሰዎች የማይጓዙባቸው ብዙ ወራት ነበሩ።
ነገር ግን ፊስጦስ፥ ጳውሎስ በፍጥነት ከእጁ እንዲመጣ ስለፈለገ ቶሎ ወደ ሮም ሊልከው ወሰነ። ስለሆነም፥ ወደ ሮም የሚሄድ መርከብ እንዳገኘ ጳውሎስን በሮም የመቶ አለቃ አስጠብቆ ላከው። ያለ ምንም ችግር እስከ ቀርጤስ ደሴት ድረስ ተጓዙ። ጳውሎስ ቀጣዩ ጉዟቸው አደገኛ እንደሚሆን ቢያስጠነቅቃቸውም፥ የመቶ አለቃው ወደ ሮም ቀረብ ብሎ የተሻለ ዳርቻ ለማግኘት ስለ ፈለገ፥ ወደፊት እንዲቀጥሉ አስገደዳቸው፡፡ ከዚህ ውሳኔው የተነሣ መርከቧ ስትሰጥም የተጓዦቹም ሕይወት ከአደጋ ላይ ወደቀ። ከብርቱው ማዕበል የተነሣ መርከቧ ተጋጭታ ተሰበረች። ነገር ግን እግዚአብሔር ለጳውሎስ እንደ ተናገረው ሕዝቡ ሁሉ ወደ ዳርቻው በሰላም ደረሱ።
ጳውሎስ እስረኛ ቢሆንም እንኳ፥ እግዚአብሔር ምናልባትም ወንጌል ተሰብኮ በማያውቅባት በዚህች ደሴት ሥራ አዘጋጅቶለት ነበር። እፉኝት እባብ ቢነድፈውም እግዚአብሔር ስላዳነው፥ ለደሴቲቱ መሪና ለብዙ ሕዝብ ለመስበክ ቻለ። ሉቃስ፣ ጳውሎስ ባደረገው ተአምር ላይ ቢያተኩርም፥ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ይመሰክር እንደነበር ጥርጥር የለውም።
እግዚአብሔር እኛን ከሚያበረታታበት ዐበይት መንገዶች አንዱ፥ ክርስቲያኖችን በመጠቀም ነው። የማዕበሉ ጊዜ እስኪያልፍ ድረስ ለሦስት ወራት ከጠበቀ በኋላ፥ ጳውሎስ ወደ ሮም ተጓዘ። በኢጣሊያ ወደ ፑቲዮሉስ ከተማ (የሮም ዋነኛ የወደብ ከተማ) ሲደርሱ፥ እግዚአብሔር ጳውሎስን ለማጽናናት ክርስቲያኖችን ተጠቀመ።
- ጳውሎስ በሮም ሰነበተ (የሐዋ. 28፡17-3)
እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ረዥም ጊዜ ቢፈጅም፥ ጳውሎስን ሮም አድርሶታል፡፡ እግዚአብሔር እኛ በምንጠብቀው መንገድ ባይሆንም፥ የሰጠውን የተስፋ ቃል ይፈጽማል፡፡ ጳውሎስ እስረኛ ቢሆንም፥ አገልግሎቱን አላቆመም፡፡ ሉቃስ፥ ጳውሎስ በሮም ስላሳለፈው ሕይወት ዝርዝር ጉዳዮችን ባይነግረንም፥ ከአይሁድ መሪዎች ጋር ስለመገናኘቱ ገልጾአል። ጳውሎስ ሮም እንደ ደረሰ፥ ታሪኩን ለማብራራት የአይሁድ መሪዎችን ሰበሰበ። ስለ እርሱ በኢየሩሳሌም የነበሩ ሊቀ ካህናት የሐሰት መረጃ እንዳስተላለፉ ገምቶ ነበር። ነገር ግን እነዚህ የአይሁድ መሪዎች ከኢየሩሳሌም የደረሳቸው መረጃ ስለነበር ከጳውሎስ ጋር ለመነጋገር ፈቃደኞች ነበሩ። ጳውሎስ ለእነዚህ ሰዎች ክርስቶስ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን የፈጸመ መሢሕ እንደሆነ አብራራላቸው። ጥቂት አይሁዶች ጳውሎስ የተናገረውን አሳብ ሲቀበሉ፣ ብዙዎቹ ግን ሳያምኑ ቀርተዋል። ጳውሎስ ያለማመን ዝንባሌአቸውን ሲመለከትም ባለማመናቸው የብሉይ ኪዳንን ቃል እየፈጸሙ እንደሆነ አስጠነቀቃቸው። እግዚአብሔር ወንጌሉን ለአሕዛብ እንደሚሰጥ አሳሰባቸው።
ሉቃስ የጳውሎስን ታሪክ ሳይደመድም ትቶታል። ስለ ጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ሌላ መጽሐፍ ለመጻፍ እያቀደ ነበር? ጳውሎስ ከእስር በመፈታቱ ሉቃስ ታሪኩን ከመቀጠሉ በፊት ተጨማሪ መረጃ እየጠበቀ ነበር? ወይስ ሉቃስ ወንጌል ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ወደ ሮም እንደ ተስፋፋ ለማሳየት የተነሣበት ዓላማ ከተሳካ በኋላ ሌላ ነገር ለመጨመር ባለመፈለጉ ይሆን? ምሑራን ብዙ የተለያዩ አሳቦችን ቢሰነዝሩም ምክንያቱን አናውቅም። ከሉቃስ ማጠቃለያ ለመረዳት የሚቻለው ነገር ቢኖር ጳውሎስ በሮም ለሁለት ዓመት እንደ ታሰረና በእስር ቤት ሆኖ እንኳ ወንጌሉን ለብዙ ሰዎች ይመሰክር እንደ ነበር ነው፡ በፊልጵ. 1፡13 ጳውሎስ ለንጉሥ ዘበኞች ወንጌልን እንደ መሰከረ ገልጾአል።
ጳውሎስ ምን ሆነ? በዚህ ጊዜ ተገድሎ ይሆን? ወይስ ተለቅቆ? በፊልጵ. 2፡24 ላይ ጳውሎስ ከእስራቱ በቶሎ ለመለቀቅ ተስፋ እንደሚያደርግ የሚያመለክት አሳብ ስላለ፥ በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ሳይፈታ አይቀርም፡፡ ከ1ኛ ና 2ኛ ጢሞቴዎስ፥ እንዲሁም ከቲቶ መልእክቶች ለመረዳት እንደሚቻለው፥ እንደገና በትንሹ እስያ፥ ቀርጤስ፥ ግሪክና ምናልባትም እስከ ስፔይን ሳይጓዝ አይቀርም፡፡ ከዚያ በኋላ ተይዞ ወደ ሮም ተላከ። በዚህ ጊዜ የሮም መንግሥት ከፍተኛ ፀረ-ክርስቲያናዊ አቋም ስለነበረው በ67/68 ዓ.ም. የጳውሎስን አንገት በሰይፍ እንዲቀላ በማድረግ ገደሉት።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከጳውሎስ ሕይወት ክርስቶስን ስለመከተል የተማርካቸውን ነገሮች ዘርዝር፡፡ ለ) እነዚህን ትምህርቶች እንዴት ከሕይወትህ ጋር ልታዛምድ እንደምትችል ተግባራዊ ምሳሌዎችን ዘርዝር።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)