መልእክቶችና አተረጓጎማቸው

ብዙዎቻችን ከጓደኞቻችን ደብዳቤዎችን እናገኛለን። ወዳጆቻችን በደብዳቤዎቻቸው አማካኝነት ስለ ሕይወታቸው ይነግሩናል። ምናልባትም አንዳንድ ጥያቄዎችን ይጠይቁናል። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ሦስተኛና አራተኛ ዐበይት የአዲስ ኪዳን ክፍሎች ደብዳቤዎች ናቸው። በአሁኑ የደብዳቤ አጻጻፍ መጀመሪያ የምንጽፍለትን ግለሰብ ስም በመግለጽ አሳባችንን ካሰፈርን በኋላ በመጨረሻው ላይ የራሳችንን ስም እንጠቅሳለን። የጥንት ዘመን ደብዳቤዎች ግን ብዙውን ጊዜ የጸሐፊውን ስም (ለምሳሌ፥ ጳውሎስ ወይም ዮሐንስ) በመጥቀስ ይጀምሩና በመቀጠልም የደብዳቤውን ተቀባይ (ለምሳሌ፥ የሮም ቤተ ክርስቲያን፥ ቆሮንቶስ፥ ጢሞቴዎስ፥ ወይም የተበተኑ አይሁዶች) ያስከትላሉ።

ከ49-100 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት የተጻፉት እነዚህ መልእክቶች ለአያሌ ምክንያቶች ጠቃሚዎች ናቸው። በመጀመሪያ፥ እነዚህ መልእክቶች የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ትጋፈጣቸው ስለነበሩት ጉዳዮች ጥርት ያለ ምስል ከመስጠታቸውም በላይ፥ እጅግ ጠቃሚዎች ተደርገው ይቆጠሩ የነበሩትን አስተምህሮዎች ያሳዩናል። በወንጌላትና የሐዋርያት ሥራ ውስጥ ትምህርት የተሰጠባቸው ክፍሎች ቢኖሩም፥ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ክርስትናን እንዴት እንደተረዳች፥ ክርስቶስ ጥሩ ሰው ብቻ ሳይሆን አምላክም ጭምር እንደሆነ ለይተው ማወቃቸውን፥ ወዘተ… የምናነበው ከመልእክቶች ነው። እንደ መንፈሳዊ ስጦታዎች፥ በቤተ ክርስቲያን የወንዶችና የሴቶች ሚና፥ የክርስቶስ ምጽአት በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ለቀረቡት የተሳሳቱ ትምህርቶች የተሰጡትን ማረሚያዎችና ማብራሪያዎች የምናነበው ከመልእክቶች ነው።

ሁለተኛ፥ እነዚህ መልእክቶች በክርስትና ሃይማኖት ጠቃሚ ስለሆነው ጉዳይ ግልጽ ማብራሪያዎች ናቸው። ወንጌላትና የሐዋርያት ሥራ ታሪካዊ መዛግብት በመሆናቸው፥ ክርስቶስና ሐዋርያቱ ያደረጓቸውንና የተናገሯቸውን ነገሮች ይገልጻሉ። ነገር ግን የገለጹአቸው ነገሮች ታሪካዊ ጠቀሜታ ብቻ ይኑራቸው ወይም ለዛሬው ሕይወታችን በምሳሌነት የሚያገለግሉ ይሁኑ የምናውቀው ነገር የለም። ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ አሠራር ላይ የአቋም ልዩነት ከሚያንጸባርቁባቸው ምክንያቶች አንዱ ይሄ ነው። መልእክቶች ግን ክርስቶስ ማን እንደሆነና እግዚአብሔር ከልጆቹ ምን እንደሚፈልግ በግልጽ ያስተምራሉ። ስለሆነም፥ እነዚህ መልእክቶች ለእምነታችን መሠረት የሆኑትን ነገሮች ይገልጹልናል። በመልእክቶች ውስጥ በግልጽ የተብራሩት ነገሮች ዛሬ ልንከተላቸው የሚገቡን እውነቶች በመሆናቸው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ነገር ግን በመልእክቶች ውስጥ በግልጽ ያልተብራሩትን ነገሮች አስመልክቶ የጠበቀ አቋም መያዙ አስፈላጊ አይሆንም።

ከወዳጃችን ደብዳቤ ሲደርሰን ግልጹን መልእክት እንጂ ሰምና ወርቅ (ቅኔ) አንጠብቅም። ምናልባት ወዳጃችን እስር ቤት ውስጥ ሆኖ ምሥጢራዊ መልእክቶችን ለማስተላለፍ ካልተገደደ በቀር። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ መንፈስ ቅዱስ የጳውሎስንና የሌሎችንም ደራሲያን ልብ እንዲጽፉ ባነሣሣ ጊዜ፥ መልእክቱን አልደበቀውም። ነገር ግን ልጆቹ የተጻፈውን ተረድተው ተግባራዊ ያደርጉት ዘንድ እግዚአብሔር ግልጽ እውነት ለማስተላለፍ ፈልጓል። ስለሆነም፥ መልእክቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ ግልጽ እውነቶች የሚመደቡና በቀላሉ ተረድተን ዛሬም ከሕይወታችን ጋር ልናዛምዳቸው የምንችላቸው ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር በቅኔ መልክ ስውር መልእክት ከማስተላለፍ ይልቅ መልእክቱን ግልጽ ያደረገልን ለምን ይመስልሃል?

ስለሆነም፥ መልእክቶችን ለመተርጎም የሚከተሉትን ደረጃዎች መከተል ያሻል።

ሀ) ደራሲው መልእክቱን እንዲጽፍ ያነሣሣውን ታሪካዊ ሁኔታ መመልከት

ለ) ደራሲው ለዚያ ሁኔታ የሰጣቸውን መልሶችና የመጀመሪያዎቹን አማኞች ለመምራት ያስተማራቸውን እውነቶች ማጥናት። ለሁሉም ትውልዶች የሚሆኑና ደራሲው ለጠቀሳቸው የተወሰኑ አንባቢያን የሚሆኑ እውነቶች የትኞቹ ናቸው? መልእክቶች እውነትን የሚያስተምሩት በተምሳሌት ሳይሆን በቀጥታ ስለሆነ፥ የተሰወረ ምሥጢር ፈልፍሎ ለማውጣት መጣሩ አስፈላጊ አይሆንም።

ሐ) በዘመናችን የመልእክቶች መርሆች ወይም እውነቶች ተግባራዊ የሚሆኑባቸውን ተመሳሳይ ሁኔታዎች መፈለግ። ከመልእክቶች በምናገኛቸው እውነቶችና ዛሬ በምናዛምዳቸው ነገሮች መካከል ግልጽ ግንኙነቶች ሊኖሩ ይገባል።

መ) አተረጓጎምህ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው አጠቃላይ አሳብ ጋር መስማማቱን ለማወቅ በአንድ መልእክት ውስጥ የተገለጹትን እውነቶች በሌሎች የአዲስ ኪዳን ምንባቦች ውስጥ ከሚገኙ ተመሳሳይ እውነቶች ጋር አነጻጽር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “መልእክቶችና አተረጓጎማቸው”

  1. Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply

%d bloggers like this: