የአዲስ ኪዳን ቅኝት

የኢትዮጵያን ፕሬዚዳንት ከሚያህል ትልቅ ሰው የግል ደብዳቤ ደርሶሃል እንበል። ይህንን ደብዳቤ ምን ታደርገዋለህ? ሳትከፍተው ለብዙ ቀናት ትቆያለህ? አትቆይም። ደብዳቤው እንደደረሰህ በፍጥነት ከፍትህ ታነብበዋለህ። የደብዳቤውን መልእክት ለመረዳት ቀጥተኛውን መንገድ ትከተላለህ ወይስ እንደ ሰምና ወርቅ ቅኔያዊ ፍች ትፈልጋለህ? ፕሬዚዳንቱ ለአንተ ስውር መልእክት የሚጽፉበት ምክንያት እንዳለ ካላሰብህ በቀር፥ ቃላቱን በጻፉበት መንገድ በመመልከት ግልጽ ፍች መሻትህ የማይቀር ነው።

አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ለልጆቹ የጻፈው ደብዳቤ እንደሆነ ገልጾአል። መጽሐፍ ቅዱስ ልታውቃቸው በሚያስፈልጉ ጠቃሚ መልእክቶች የተሞላ እግዚአብሔር ለአንተ የላከው ደብዳቤ ነው። ለዚህም ነው እግዚአብሔር የላከልህን ደብዳቤ መደርደሪያ ላይ ከማስቀመጥ ወይም ወደ ቤተ ክርስቲያን ይዞ ከመሄድ በላይ በጥንቃቄ ማንበብ የሚኖርብህ። ከእግዚአብሔር በላይ ታላቅ አካል ስለሌለ፥ እርሱ የላከልህ መልእክት ለሕይወትህ ወሳኝ ነው። እግዚአብሔር ቃሉን ሲሰጥ ትርጉሙን ደብቆ በፍለጋ እንድናገኘው አላደረገም። ይልቁንም በግልጽ በምንረዳቸው ቃላት አማካኝነት መልእክቱን አስተላልፎአል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የደብዳቤ አተረጓጎም ከቅኔ (ሰምና ወርቅ) የሚለየው እንዴት ነው? ለ) መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ቅኔ ወይም እንደ አንድ ጠቃሚ ደብዳቤ መመልከቱ በአተረጓጎምህ ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?

አዲስ ኪዳን የተባለው የእግዚአብሔር መልእክት ክፍል እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በጹሑፍ ያስተላለፈው የመጨረሻው መልእክት ነው። ብሉይና አዲስ ኪዳን ስለ እግዚአብሔርና እርሱን ስለመከተል ልናውቃቸው የሚገቡንን ነገሮች በሙሉ ያብራሩልናል። እግዚአብሔር ያስተላለፈልንን መልእክት ለመረዳት ልንጠይቃቸው የሚገቡን ሁለት ጥያቄዎች አሉ።

  1. የእግዚአብሔር መልእክት መጀመሪያ ለተቀበሉት ሰዎች ምን ዓይነት ትርጉም ነበረው? ምንም እንኳ የእግዚአብሔር ቃል በሁሉም ዘመን ለሚኖሩ ሰዎች የታቀደ ቢሆንም፥ መጀመሪያ በተወሰነ ጊዜ ለነበሩት ሰዎች ነበር የተሰጠው። ለአዲስ ኪዳን ይህ ጊዜ ከ50–100 ዓ.ም ነበር። በዚያን ጊዜ ስለነበሩት ክርስቲያኖች ሁኔታ የተሻለ ግንዛቤ በምናገኝበት ጊዜ፥ የእግዚአብሔር መልእክት መጀመሪያ ለእነርሱ ምን ፍች እንደነበረው ልንረዳ እንችላለን።

በመጀመሪያው ምእተ ዓመት ውስጥ አይሁዶች በአሕዛብ አገሮች ተገዝተው ከቆዩ በኋላ ጊዜያዊ ነጻነት አግኝተው ነበር። በታላቁ ሄሮድስ ዘመን የአይሁድ ሕዝብ በዳዊትና በሰሎሞን ዘመን የነበረውን ያህል የበረከተ ቁጥር ነበረው። ብዙም ሳይቆይ ይህንኑ የነጻነት ጊዜ ስለተነጠቁ፥ አይሁዶች በኃይለኛው የሮም አገዛዝ ሥር ወደቁ። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ከጠላቶቻቸው እንደሚያድናቸው ተስፋ የሰጣቸውን መሢሕ ናፈቁ። በመጀመሪያው ምእተ ዓመት የመጀመሪያ ዓመታት ብዙ የፖለቲካና የወታደራዊ መሪዎች ነጻነታቸውን መልሰው ለመቀዳጀት በሮም ላይ ያምፁ ጀመረ። ነገር ግን ክርስቶስ መንፈሳዊ ንጉሣቸው ሆኖ ሲመጣ አሳዳጆች ሊቀበሉት ባለመፈለጋቸው ሰቀሉት። ክርስቶስ የተወለደው፥ የኖረው፤ የሞተውና ቤተ ክርስቲያኑን የመሠረተው በዚሁ ቀውጢ ወቅት ነበር። በአይሁዶች መካከል የተወለደችው ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ በሕዝባቸው ላይ እንዲገዛ በፈለጉት ታማኝ የእግዚአብሔር ተከታዮች የተገነባች ነበረች። በመጨረሻም፥ በአይሁዶች የዓመፅ ተግባር የተበሳጩት ሮማውያን በ70 ዓ.ም ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሱን አወደሙ። ይህም ልዩውን የአይሁድን መንግሥትና የአምልኮ ስፍራ ከፍጻሜ አደረሰው።

አሕዛብም ቢሆኑ የፍልስፍናና የሃይማኖት ውጣ ውረድ ለመጋፈጥ ተገድደው ነበር። ብዙዎች የአያት የቅድመ አያቶቻቸውን የጣዖት አምልኮ መከተል ሰልችቷቸው ነበር። አምልኳቸው ስሜትን በሚያነሣሡ ነገሮች የተሞላ ቢሆንም፥ ሕይወታቸውን የመለወጥ አቅም ግን አልነበረውም። ስለሆነም፥ እነዚህ አሕዛብ ሌላ የተሻለ ነገር ይፈልጉ ነበር። በመጀመሪያ፥ ስለ አንድ አምልኮና ቀጥተኛ የግብረገባዊነት ትምህርት የሚሰጥበትን የአይሁዶች ሃይማኖት ለመከተል ይፈልጉ ነበር። በአዲስ ኪዳን ዘመን እንዲህ ዓይነት አሕዛብ «እግዚአብሔርን የሚፈሩ» ተብለው ይጠሩ ነበር። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር ለመዛመድ ወደ አይሁድነት መለወጥ እንዳለባቸው የሚያስረዳውን አሳብ ለመቀበል ፈቃደኛች አልነበሩም። ስለሆነም ክርስቲያኖች ስለ አንድ አምላክና ለኃጢአታቸው ስለሞተው ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምሩ፥ አሕዛብ ከልባቸው ያዳምጡ ጀመር። ወደ አይሁድነት መለወጥ ሳያስፈልጋቸው የክርስቶስን ስጦታ በእምነት ተቀብለው የእግዚአብሔር ልጆች ሊሆኑ እንደሚችሉ ሲነገራቸው፥ ብዙዎች እመኑ። ቤተ ክርስቲያን ከፓለስታይን ውጭ ስትስፋፋ ብዙ አሕዛብ አመኑ።

ይህ ቤተ ክርስቲያን በፍጥነት ያደገችበት ጊዜ ነበረ። ክርስቶስ ወደ ሰማይ ባረገበት ወቅት 120 የቅርብ ተከታዮች ነበሩት። ከ 30–70 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ከኢየሩሳሌም ወደ ትንሹ እስያና አውሮፓ እንዲሁም እስከ ሮም ድረስ ተስፋፋች። (በአሁኗ እስራኤል፥ ሶርያ፥ ሊባኖስ፥ ቱርክ፥ ግሪክ፥ ኢጣሊያ፥ የቀድሞዪቱ ዩጎዝላቪያና አልባኒያ ቤተ ክርስቲያን ተስፋፍታለች።) በግብጽና ምናልባትም እስከ ስፔይን ድረስ አብያተ ክርስቲያናት እንደነበሩ አያጠራጥርም።

ለአይሁዶችም ሆነ ለአሕዛብ ይህ ከፍተኛ የስደት ጊዜ ነበር። ብዙውን ጊዜ በክርስቶስ ያመኑ ሰዎች ከኖሩባቸው ማኅበረሰቦች ይባረሩ ነበር። ስለሆነም አንዳንዶች በክርስቶስ ላይ የነበራቸውን እምነት ለመሸሸግ ወይም ወደ አሮጌው አኗኗራቸው ለመመለስ ይፈተኑ ነበር። ሐዋርያት እነዚህ ክርስቲያኖች ስደትን እንዳይፈሩና እስከ ሞት ድረስ መስቀላቸውን ተሸክመው በመዝለቅ መዳናቸውን እንዲፈጽሙ አስጠንቅቀዋቸዋል።

ይህ ወቅት የሥነ መለኮታዊ ጥያቄዎችም ጊዜ ነበር። «ኢየሱስ ማን ነበር? ምን ነበር ያስተማረው? ሰው ድነትን (ደኅንነትን) ሊያገኝ የሚችለው እንዴት ነው? እንደ ክርስቶስ ተከታዮች አኗኗራችን ምን ሊመስል ይገባል? ስለ ክርስቶስና የድነት (የደኅንነት) መንገድን በተመለከተ የተሳሳተ ትምህርት የሚያስተምሩትን ሰዎች እንዴት እናድርጋቸው?» በእነዚህ የእምነት መመሥረቻ ጊዜያት የቀድሞዎቹ አማኞች አስተምህሮን ሲያብራሩና የሐሰት ትምህርቶችን ሲቃወሙ እንደኖሩ ሁሉ፥ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን የምትጋፈጣቸውን ችግሮች የሚፈቱ መጻሕፍትን የተለያዩ ሰዎች እንዲጽፉ መርቷቸዋል። እነዚህም መጻሕፍት በኋላ ተሰብስበው አዲስ ኪዳን ሊባሉ በቅተዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 11፡2-16 አንብብ። የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን ዳራና እነዚህን ጥያቄዎች ለጳውሎስ ያቀረቡባቸውን ምክንያቶች ማወቅ፥ መልሱን በተሻለ ሁኔታ እንድንረዳ የሚያደርገን እንዴት ነው?

  1. የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል ከሕይወታችን ጋር ለማዛመድ ከፈለግን፥ «ይህ የእግዚአብሔር ቃል ዛሬ ለእኛ ምን ትርጉም ይሰጣል?» ብለንም መጠየቅ አለብን። ብዙ ሰዎች ይህንኑ ጥያቄ ብቻ ስለሚያነሡ፥ የእግዚአብሔርን መልእክት በተሳሳተ መንገድ ይተረጉሙታል። ለምሳሌ፥ ጳውሎስ ሴቶች ራሳቸውን እንዲሸፍኑ ያዘዘበትን ሁኔታ አስመልክቶ በጳውሎስ ዘመን የነበረውን ባሕላዊ ልምምድ ለመረዳት ሳይሞክሩ በዘመናችን ተግባራዊ ለማድረግ ይጥራሉ። ምንም እንኳ ትእዛዙ ተግባራዊ ሊሆን ቢችልም፥ ተግባራዊ ልናደርግ የምንችልበትን መንገድ የምናውቀው በጳውሎስ ዘመን የነበረውን ባሕልና እንዲህ ዓይነት ትእዛዛት የሰጠባቸውን ምክንያቶች ስናውቅ ብቻ ነው። እግዚአብሔር የጻፈልንን ደብዳቤ በትክክል ለመተርጎም፥ እግዚአብሔር መልእክቱን ለመጀመሪያዎቹ አንባቢዎች በሰጠበት ወቀት ምን ለማለት እንደፈለገ መረዳት አለብን። እግዚአብሔር በዚያን ዘመን ያስተላለፈውን መልእክት በአግባቡ ስንረዳ፥ ዛሬ መልእክቱ እንዴት ከሕይወታችን ጋር እንደሚዛመድ ልናስተውል እንችላለን። በአዲስ ኪዳን ዘመን ለተወሰኑ አብያተ ክርስቲያናት ወይም ግለሰቦች የተጻፉ አብዛኞቹ ጉዳዮች ወይም አስተምህሮዎች ዛሬም ለቤተ ክርስቲያኖቻችን የሚያስፈልጉ ናቸው። በቀጥተኛ ትእዛዝም ሆነ በተዘዋዋሪ መርሆዎች የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ፥ ልብንም ለማቅናት፥ በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል” (2ኛ ጢሞ3፡16-17)።

አዲስ ኪዳን በአምስት ዐቢይ ክፍሎች ሊከፈል ይችላል። የመጀመሪያው ክፍል አራቱ ወንጌላት የሚገኙበት ሲሆን፥ ስለ ክርስቶስ ምድራዊ ሕይወት ይነግሩናል። ምንም እንኳ ወንጌላት ታሪካዊ እውነቶች ቢሆኑም፥ ለሁለት ዓላማዎች እንደተጻፉ በቀደመው የአዲስ ኪዳን አሰሳ ትምህርት ተመልክተናል። እያንዳንዱ ወንጌል የተጻፈው የማያምኑ ሰዎች በክርስቶስ ማመን እንደሚያስፈልጋቸው ለመንገርና፥ ከርስቲያኖች ደግሞ ክርስቶስን መከተል ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንዲረዱ ጭምር ነበር።

ሁለተኛው የአዲስ ኪዳን ክፍል የሐዋርያት ሥራ ነው። የሐዋርያት ሥራ ስለ ቤተ ክርስቲያን አጀማመርና ወንጌሉ በሮም ግዛቶች ስለተስፋፋበት ሁኔታ ይተርካል። ምንም እንኳን ታሪካዊ ክስተቶችን ያካተተ ቢሆንም፥ የማስተማሪያ መሣሪያም ሆኖ አገልግሏል። ይህ መጽሐፍ ክርስቲያኖች የሮም ጠላቶች ስላልሆኑ ሊሰደዱ እንደማይገባቸው ለማያምኑ ሰዎች የሚያስረዳ ሲሆን፥ ለክርስቲያኖች ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ምን ዓይነት መሆን እንዳለባት ያስተምራል። በእያንዳንዱ አማኝ ውስጥ ባለው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል አማካኝነት፥ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ማመን እንዳለባቸው የምትመሰክር ማኅበረሰብ ልትሆን ይገባል። በተጨማሪም፥ እግዚአብሔርንና ክርስቶስን የምታመሰግን የአምልኮ ማኅበረሰብ፥ የእግዚአብሔርን ቃል የምታጠናና የምትማር ማኅበረሰብ፥ ለታላላቅ ነገሮች በእግዚአብሔር የምትታመን የጸሎት ማኅበረሰብ፣ ሰዎች በቅርብ ኅብረት እርስ በርሳቸው ለመረዳዳት በፍቅር የተሞሉበት የኅብረት ማኅበረሰብ ልትሆን ይገባል (የሐዋ. 2፡44-47)።

የውይይት ጥያቄ:- ዛሬ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ወደሚፈልገው የዕድገት ደረጃ ይደርሱ ዘንድ እነዚህን ሁለት የአዲስ ኪዳን ክፍሎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዴት ልንጠቀም እንደምንችል በምሳሌ አስረዳ?

የመጀመሪያዎቹ ሁለት የአዲስ ኪዳን ክፍሎች ለቀሪው የአዲስ ኪዳን ክፍል ታሪካዊ መሠረት ይጥላሉ። የክርስቶስን ማንነት፥ የኖረበትንና የሞተበትን ሁኔታ እስካላወቅን ድረስ፥ በቀሪው የአዲስ ኪዳን ክፍል ስለ ክርስቶስ የተሰጠውን ትምህርት ልንረዳ አንችልም። እንዲሁም በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የሚገኘውን ታሪክ እስካላወቅን ድረስ፥ ጳውሎስና ሌሎችም አገልጋዮች መልእክቶቻቸውን የጻፉላቸውን አብያተ ክርስቲያናት ሁኔታ ልንረዳ እንችልም። ስለሆነም፥ ወንጌላትና የሐዋርያት ሥራ የመልእክቶች መሠረቶች ናቸው ማለት እንችላለን።

በአንጻሩ ደግሞ፥ መልእክቶች ወንጌላትና የሐዋርያት ሥራ ውስጥ የቀረበውን ትምህርት እንድንረዳ የሚያግዙን የማብራሪያ መጻሕፍት ዓይነት ናቸው። የክርስቶስ ሕይወት ዛሬ ለእምነታችንና ለአኗኗራችን ምን ዓይነት ትምህር (ተዛምዶ) እንዳሉት ያሳያሉ። መልእክቶች በቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ኃይል ስለሠራው መንፈስ ቅዱስ ጠቃሚ እውነቶችን እንድናውቅ ይረዱናል። ስለ መንፈስ ቅዱስም ሆነ ስለ ክርስቶስ የሚናገሩትን መሠረታዊ ሃሳቦች ሁሉ በመልእክቶች ማብራሪያ መሠረት ልንረዳቸው ይገባል። አንድ ትምህርት በወንጌላት ወይም በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ብቻ የሚገኝ ከሆነ ዛሬ ከሕይወታችን ጋር እንዴት እንደምናዛምድ መጠንቀቅ አለብን። ለዚህም ምክንያቱ ጸሐፊው የተከሰተውን ጉዳይ ብቻ ለማብራራት ወይም የክርስቶስ ተከታዮች በዚህ መንገድ መመላለስ እንዳለባቸው ለመግለጽ መፈለጉን ስለማናውቅ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- በሐዋርያት ሥራና በዕብራውያን መልእክት መካከል ያሉትን 13 መጻሕፍት ዘርዝር። የእነዚህ መጻሕፍት ጸሐፊ ማን ነው?

ሦስተኛውና አራተኛው ክፍሎች ለተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትና ግለሰቦች የተጻፉትን ደብዳቤዎች ያካትታሉ። ሦስተኛው ክፍል ጳውሎስ የጻፋቸውን አሥራ ሦስት መጻሕፍት ያጠቃልላል። የቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች እግዚአብሔር ጳውሎስን ቤተ ክርስቲያኑን ለመመሥረት እንደተጠቀመበት በማመናቸው መልእክቶቹን በቀዳሚነት ዘርዝረዋል። መልእክቶቹ የተዘረዘሩት ጳውሎስ በጻፋቸው ቅደም ተከተል ሳይሆን ከትልቁ ወደ ትንሹ ነው። ጳውሎስ ስለ ድነት (ደኅንነት) ዝርዝር ማብራሪያ ያቀረበበት የሮሜ መጽሐፍ መጀመሪያ ላይ ሲጻፍ፥ አጭሩ የፊልሞና መጽሐፍ መጨረሻ ላይ እንዲገባ ተደርጓል። ጳውሎስ በእነዚህ መልእክቶች ስለ ክርስቶስ ማንነትና በደቀ መዝሙርነት እርሱን መከተል ማለት ምን ማለት እንደሆነ አስተምሯል። ብዙውን ጊዜ እነዚህ መልእክቶች አንዲት ቤተ ክርስቲያን ልትረዳቸው የሚገቧትን የተወሰኑ ዶክትሪኖች በማቅረብ፥ የተወሰኑ ችግሮችን በመፍታት ወይም ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትጋፈጣቸውን ጥያቄዎች በማንሣት ምላሽ ይሰጣሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- በፊልሞናና በራእይ መካከል ያሉትን መጻሕፍት ዘርዝር። የእነዚህ መጻሕፍት ጸሐፊ ማን ነው?

አራተኛው ክፍል ስምንት መልእክቶችን የያዘ ሲሆን፥ እንደ ዮሐንስ፥ ጴጥሮስና ይሁዳን የመሳሰሉ የተለያዩ ጸሐፊያን ጽፈውታል። እነዚህ መልእክቶች አብዛኞቹ ለአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ወይም ግለሰብ ሳይሆን፥ ለአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተላኩ ነበሩ። ስለሆነም፥ ምሁራን «አጠቃላይ መልእክቶች» ብለው ይጠሯቸዋል። እነዚህ መጻሕፍት በየአብያተ ክርስቲያናቱ በመስፋፋት ላይ ስለነበሩት የሐሰት ትምህርቶች ከማስጠንቀቃቸውም በላይ እንዴት እግዚአብሔርን በሚያስከብር ሁኔታ መመላለስ እንዳለብን ያስተምሩናል።

አምስተኛው ክፍል የዮሐንስ ራእይ ነው። የዮሐንስ ራእይ በአሁኑ ዘመን ያልተለመደ «ሥዕለ ራእያዊ ሥነ ጽሑፍ» በመባል የሚታወቅ ነው። ይህ አይሁዶች በብሉይ ኪዳን ዘመን ፍጻሜና በብሉይና አዲስ ኪዳናት መካከል በነበሩት 400 ዓመታት ውስጥ የተጠቀሙበት የሥነ ጽሑፍ ዓይነት ነው። የራእይ መጽሐፍ በአንድ በኩል በመጀመሪያው ምእተ ዓመት መጨረሻ በስደት ውስጥ ስለነበሩት ክርስቲያኖች ጠቃሚ እውነቶችን ያስተላልፋል። በተጨማሪም፥ ክርስቶስ ለዘላለም ለመንገሥ ከመመለሱ በፊት የሚከሰተውንም የመጨረሻውን ዘመን ሁኔታ ያመለክታል። ዐቢይ ጭብጡ «እግዚአብሔር የታሪክ ሁሉ ተቆጣጣሪ ነው» የሚል ሲሆን፥ ክርስቲያኖች ተስፋ አስቆራጭ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ሳይቀር ተበራትተው እንዲኖሩ ያበረታታል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አምስቱን የአዲስ ኪዳን ክፍሎችና የያዛቸውን መጻሕፍት ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “የአዲስ ኪዳን ቅኝት”

  1. Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply

%d bloggers like this: