የሮሜ መልእክት ልዩ ገጽታዎች

  1. ከቆላስይስ በስተቀር አብዛኞቹ የጳውሎስ ደብዳቤዎች በተወሰኑ ጉዳዮችና የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች ላይ ሲያተኩሩ፥ የሮሜ መልእክት በአብዛኛው አጠቃላይ የሆኑና ነገረ መለኮታዊ ጉዳዮችንም ያነሣል። አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ የሮምን ቤተ ክርስቲያን ስላልጎበኘ፥ ስለ ሮም ቤተ ክርስቲያን ዝርዝር ጉዳዮች የሚያውቀው እንዳልነበረው ይገምታሉ። ስለሆነም፥ በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ክርስቲያኖች በሚጋፈጧቸው አጠቃላይ ጉዳዮች ላይ አተኮረ። በተጨማሪም፥ አማኞች ሊያውቋቸው ስለሚገቧቸው መሠረታዊ አስተምህሮዎች አስተምሮአል።
  2. የሮሜ መልእክት ከጳውሎስ መልእክቶች ሁሉ ረዥሙ ነው። ከሌሎች ሁሉ በበለጠ ሁኔታም የተቀነባበረም ነው። ምሁራን መልእክቱ ከግል ደብዳቤነቱ ይልቅ ነገረ መለኮታዊ ሐተታው እንደሚያመዝን ይናገራሉ።
  3. ጳውሎስ ከሌሎች መልእክቶቹ በተለየ ሁኔታ የክርስትና መሠረት በሆኑት ነገረ መለኮታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። በዚህ መልእክት ውስጥ እንደ ኃጢአት፥ ድነት (ደኅንነት)፥ ጸጋ፥ እምነት፥ ጽድቅ፥ ቅድስና፥ ቤዛነት፥ ሞትና ትንሣኤ ያሉ ዐበይት ሥነ መለኮታዊ ትምህርቶች ተብራርተዋል።
  4. ምንም እንኳን ጳውሎስ በመልእክቶቹ ውስጥ ብሉይ ኪዳንን በመጥቀስ የጻፈ ቢሆንም፥ በሮሜ መልእክት ውስጥ የተጠቀመባቸው የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች ከሌሎች መልእክቶቹ ሁሉ በቁጥር የበረከቱ ናቸው። ትምህርቱን ለማብራራት መሠረት የጣሉለት እነዚህ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች ናቸው። ጳውሎስ አንድ ሰው ብሉይ ኪዳንንና እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ ያከናወነውን ተግባር ሊረዳ የሚችለው ስለ ክርስቶስና በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ስላለው ድርሻ ተገቢውን ግንዛቤ ሲጨብጥ እንደሆነ ያስረዳል።
  5. ጳውሎስ በሮሜ ውስጥ ከሌሎች ደብዳቤዎቹ በበለጠ ሁኔታ ስለ እስራኤልና እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ስለወጠናቸው ዕቅዶች ይገልጻል። አብዛኞቹ ሌሎች ደብዳቤዎቹ በአይሁድና በአሕዛብ መካከል የነበረው ግድግዳ እንደፈረሰና የአሕዛብ ክርስቲያኖች የአብርሃምና የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸው ላይ ያተኩራሉ። ጳውሎስ በአሁኑ የእግዚአብሔር ዕቅድ የአሕዛብ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን አጽንቶ ቢገልጽም፥ እግዚአብሔር አንድ ቀን አይሁዶችን ወደ ራሱ እንደሚመልስና እንደሚያድን ያስተምራል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “የሮሜ መልእክት ልዩ ገጽታዎች”

  1. Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply

%d bloggers like this: