የሮሜ መልእክት መዋቅርና እና አስተዋጽኦ

፩. የሮሜ መልእክት መዋቅር

የውይይት ጥያቄ፡– ይህን የሮሜ መልእክት እቀራረፅ በጥንቃቄ ካጠናህ፥ በሮሜ ውስጥ የጳውሎስን ትምህርት ፍሰት በሚገባ ልትገነዘብ ትችላለህ። ከዚህ በታች የቀረቡት ሰባት ነጥቦች ወንጌል ለሚያካትታቸው ነገሮች መልካም ማጠቃለያ የሚሆኑት እንዴት ነው?

ጳውሎስ ስለ ወንጌልና እግዚአብሔር ሰዎችን ስለሚያጸድቅበት ሁኔታ የጻፈውን አሳብ ጠቅለል ባለ መልክ (ርዕሰ-ጉዳይ) ማስቀመጡ የሮሜን መልእክት ለመረዳት ይረዳናል። ከሮሜ ውስጥ አንድ ክፍል ሳይገባህ ቢቀር በዚያ ክፍል የተጠቀሰው ዋና ርእሰ ጉዳይ ምን እንደሆነ መለስ ብለህ ብትከልስ መልካም ነው። ብዙውን ጊዜ ጳውሎስ ለማስተላለፍ የሚፈልገውን አሳብ በዚህ ዓይነት መረዳት ይቻላል። ከዚህ በታች የቀረበው ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር የድነት (ደኅንነት) መንገድ ያቀረበው መልእክት ማጠቃለያ ነው።

የመጀመሪያው ነጥብ፡ ጳውሎስ በመግቢያው ውስጥ እግዚአብሔር እንዲሰብክ ያዘዘው ወንጌል ለአሕዛብም ሆነ ለአይሁድ ብቸኛው የድነት (ደኅንነት) መንገድ እንደሆነ ገልጾአል (ሮሜ 1፡1-17)። ኃጢአተኞች እንዴት ሊድኑና የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሊያገኙ እንደሚችሉ የሚያስረዳው የሮሜ መልእክት ጭብጥ በ1፡16-17 ውስጥ ተጠቅሷል።

ሁለተኛ ነጥብ፡– ብሉይ ኪዳንን የሚከተሉ አይሁዶችም ሆኑ ይህንኑ ዕድል ያላገኙ አሕዛብ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኞች ናቸው። ስለሆነም፥ ሁለቱም እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን ድነት (ደኅንነት) በእኩል ደረጃ መቀበል ይኖርባቸዋል (ሮሜ 1፡183፡20)።

ሦስተኛ ነጥብ፡ ሰዎች ለኃጢአተኝነታቸው ከሚቀበሉት ቅጣት ሊያመልጡ የሚችሉበት ብቸኛው መንገድ ድነት (ደኅንነት) ወይም በጳውሎስ አገላለጽ «ጽድቅ» (በእግዚአብሔር ጥፋተኛ አይደለህም መባል) ነው። ስዎች የተወሰኑ ሕግጋትን በመጠበቅ ሳይሆን እግዚአብሔር በሰጠው የክርስቶስ አዳኝነት ላይ እምነታቸውን በሚያሳርፉበት ጊዜ ድነት (ደኅንነት) ያገኛሉ። በዚህም ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ይታረቃሉ። ከዚህ በኋላ የወደፊት ተስፋ፥ ሰላም፥ ደስታና መንፈስ ቅዱስ ሕይወታቸውን ይሞላዋል (ሮሜ 3፡21-5፡21)።

አራተኛው ነጥብ፡ ከድነት (ደኅንነት) ዐበይት ፍሬዎች አንዱ የተቀደሰ ሕይወት ነው። በክርስቶስ በምናምንበት ጊዜ የኃጢአት ተፈጥሯችን ተወግዶ እግዚአብሔርን ለመታዘዝና ለእርሱ ለመኖር ነፃ እንሆናለን። የተቀደሰ ሕይወት የምንኖረው ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት ሳይሆን፥ ስለዳንንና ከኃጢአት እስራት ስለተፈታን እግዚአብሔርን ለማስደሰት ስለምንፈልግ ነው (ሮሜ 6-8)።

አምስተኛ ነጥብ፡ አይሁዶችንም ሆነ አሕዛብን የሚያድነው የክርስቶስ ወንጌል እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ለአይሁዶች የሰጠውን የተስፋ ቃል አያጥፍም። ምንም እንኳ አሕዛብ በክርስቶስ በማመን በብሉይ ኪዳን ለአይሁዶች የተሰጠውን የተስፋ ቃል ቢቀበሉም፥ አይሁዶች እንደ ሕዝብ ወንጌሉን ተቀብለው በእግዚአብሔር በረከቶች ደስ የሚሰኙበት ዘመን ይመጣል (ሮሜ 9-11)።

ስድስተኛ ነጥብ፡– ከዳንን ሕይወታችን ይለወጣል። ድነት (ደኅንነት) የሕይወታችንን ገጽታዎች ሁሉ ይዳስሳል። ከመንግሥት፥ ከእኛ የተለየ እምነትና ልምምድ ካላቸው ሌሎች ክርስቲያኖች፥ ወዘተ… ጋር የምናደርገውን ግንኙነት በሙሉ ያካትታል (ሮሜ 12፡14)።

ሰባተኛ ነጥብ፡– ጳውሎስ በማጠቃለያው የእርሱ ጥሪ ወንጌሉን ላልሰሙ ሰዎች ይህንኑ መልካም ዜና ማብሰር እንደሆነ ይገልጻል። ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ሲመለስ ወደ ሮም፥ ከዚያም ወደ ስፔይን የመሄድ ዕቅድ እንዳለው ተናግሯል። የሮም ክርስቲያኖች ወንጌሉን ወዳልደረሰበት ስፍራ ለመውሰድ በሚያደርገው ጥረት እንዲተባበሩት ይጠይቃል። ጳውሎስ ለሚያውቃቸው የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ሰላምታ በማቅረብ መልእክቱን ይደመድማል (ሮሜ 15-16)።

፪. የሮሜ መልእክት አስተዋጽኦ

  1. መግቢያ (ሮሜ 1፡1-17)
  2. ሰዎች ሁሉ በቅዱሱ አምላክ ፊት ኃጢአትን ስላደረጉ ወንጌል የግድ ያስፈልጋቸዋል (ሮሜ 1፡18፤ 3፡20)።

ሀ. አሕዛብ ኃጢአትን ሠርተዋል (ሮሜ 1፡18-32)።

ለ. አይሁዶች ኃጢአትን ሠርተዋል (ሮሜ 2፡1-3፡8)።

ሐ. ማጠቃለያ፡- ሁሉም ሰው በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአትን ስላደረገ ድነት (ደኅንነት) የግድ ያስፈልገዋል (ሮሜ 3፡9-20)።

  1. ወንጌሉ በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች በእግዚአብሔር እንደ ጸደቁ ያስተምራል (ሮሜ 3፡21-5፡21)።

ሀ. የድነት (ደኅንነት) መሠረት፡- የክርስቶስ ስለ እኛ መሞት ነው (ሮሜ 3፡21-26)።

ለ. የእግዚአብሔርን የድነት (ደኅንነት) ስጦታ የምንቀበለው በሥራ ሳይሆን ክርስቶስ በእኛ ምትክ እንደሞተ በማመን ነው (ሮሜ 3፡27-31)።

ሐ. የእኛ ሥራ ሳይሆን እምነት እንዴት እንደሚያድነን የሚያሳዩ የብሉይ ኪዳን ማስረጃ ዎች (ሮሜ 4)።

መ. ኃጢአተኛው በእግዚአብሔር ከጸደቀ በኋላ የሚያገኛቸው በረከቶች (ሮሜ 5፡1-11)።

ሠ. ኃጢአትንና ሞትን ወደ ዓለም ያመጣው የመጀመሪያው አዳም ሕይወትንና ጽድቅን ካመጣው ከሁለተኛው አዳም ጋር ሲነጻጸር (ሮሜ 5፡12-21)።

  1. ወንጌሉ የተቀደሰ ሕይወት እንድንኖር ይረዳናል (ሮሜ 6፡1-8፡39)።

ሀ. ከኃጢአት ባሕርያችን ጋር ያለን ሕብረትና እግዚአብሔር በሕይወታችን ኃጢአትን እንድናሸንፍ እንዴት እንደሚረዳን መገንዘብ (ሮሜ 6፡1-7፡6)።

ለ. ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕግጋት ለመታዘዝ የሚያደርጉት ጥረት ወደ ውድቀት ሲመራቸው፥ እኛ ግን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እግዚአብሔርን መታዘዝና የተቀደሰ ሕይወት መምራት ችለናል (ሮሜ 7፡7-8፡39)።

  1. ወንጌሉ፥ አሕዛብና አይሁዶች (ሮሜ 9፡11)።

ሀ. አይሁዶች ላለማመን የተጋለጡት የእግዚአብሔርን ጽድቅ ከመቀበል ይልቅ በራሳቸው ጥረት ለመጽደቅ ስለሞከሩ ነው (ሮሜ 9-10)።

ለ. ምንም እንኳ ሁልጊዜም ለድነት (ደኅንነት) በክርስቶስ የሚያምኑ ቅሬታዎች የሚኖሩ ቢሆንም፥ አይሁዶች ሁሉ የሚድኑበት ቀን ይመጣል (ሮሜ 11)።

  1. ወንጌሉ አማኞች ለእግዚአብሔር የሚኖሩትን ኑሮ ይወስናል (ሮሜ 12፡1-15፡13)።

ሀ. አማኞች ሕይወታቸውን ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገው ያቀርባሉ (ሮሜ 12፡1-2)።

ለ. አማኞች እግዚአብሔር በሰጣቸው ጸጋዎች አማካኝነት ቤተ ክርስቲያንን ያገለግላሉ (ሮሜ 12፡3-8)።

ሐ. አማኞች ከሌሎች የቤተ ክርስቲያናቱ አባላት ጋር በፍቅር ይዛመዳሉ (ሮሜ 12፡14-21)።

መ. አማኞች ከክርስቲያኖችም ሆነ ክርስቲያኖች ካልሆኑት ሰዎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ያደርጋሉ (ሮሜ 12፡14-22)።

ሠ. አማኞች ለሰብዓዊ መንግሥታቸው ይጸልያሉ፥ ይታዘዛሉም (ሮሜ 13፡1-7)።

ረ. የአማኞች ሕይወት ቶሎ በሚሆነው የክርስቶስ መመለስ ብርሃን ሲታይ (ሮሜ 13፡8–13)።

ሰ. ክርስቲያኖች የተለየ አመለካከት ያላቸውን ክርስቲያኖች የሚያሳዝኑ ተግባራት ባለመፈጸም ፍቅራቸውን ያሳያሉ (ሮሜ 13፡14-15፡13)።

  1. መደምደሚያ (ሮሜ 15፡14-16፡27)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “የሮሜ መልእክት መዋቅርና እና አስተዋጽኦ”

  1. Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply

%d bloggers like this: