የሮሜ መልእክት መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፡- የሐዋርያት ሥራ 16፡30 እንብብ። ሀ) የወኅኒ ቤቱ ጠባቂ ጳውሎስን ምን ጠየቀው? ለ) ይህ የሰው ልጆች ሊጠይቁ የሚገባው ከሁሉም የላቀ ጥያቄ የሆነው ለምንድን ነው? ሐ) በኢትዮጵያ የተለያዩ የሃይማኖት ክፍሎች ይህን ጥያቄ የሚመልሱባቸውን የተለያዩ መንገዶች ዘርዝር። መ) እግዚአብሔር በአንተ ሕይወት ይህን ጥያቄ የመለሰው እንዴት ነው?

የወኅኒ ቤት ጠባቂው፥ «እድን ዘንድ ምን ላድርግ?» ሲል የሰው ልጅ ሊጠይቅ የሚገባውን ወሳኝ ጥያቄ ነበር ያነሣው። ሁላችንም ብዙ ዓይነት ፍላጎቶች አሉን። ምግብ ከየት እናገኛለን፥ የት እንኖራለን፥ ማንን እናገባለን፥ ሥራ ከየት እናገኛለን? እነዚህ ነገሮች አስፈላጊዎች ቢመስሉም ከጊዜያዊነት አያልፉም። ምላሽ የሚሰጡት ለምድራዊ ሕይወታችን ብቻ ነው። ነገር ግን፥ «እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?» ብለን እግዚአብሔርን ስንጠይቅ ዘላለማዊ ዘለቄታ ያለው ጥያቄ ማንሣታችን ነው። ይሄ ደግሞ አሁን ከእግዚአብሔር ጋር የምናደርገውን ግንኙነት ብቻ ሳይሆን፥ ዘላለምንም የት እንደምናሳልፍ የሚወስን ነው።

ነገር ግን የዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚገኘው ከየት ነው? ሁለት አማራጭ ምንጮች አሉ። በመጀመሪያ፥ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጡ ሰው ሠራሽ ምላሾች አሉ። በዓለም ላይ አብዛኞቹ ሕዝብ ይህን ጥያቄ ስለሚጠይቁ፥ የሚያገኟቸውም ምላሾች የተለያዩ ናቸው። አንዳንዶች፥ «ዘላለማዊ ሕይወትም ሆነ ድነት (ደኅንነት) የሚባል ነገር የለም። ስለሆነም፥ በመብላት፥ በመጠጣትና በመደሰት ራሳችንን ከማዝናናት የተሻለ ነገር የለም» ይላሉ» (1ኛ ቆሮ. 5፥2)። ሌሎች ደግሞ የሕይወታቸውን ክፍተት ለመሙላት ወደ ሌሎች ሃይማኖቶች ይገባሉ። የምሥራቃውያንን ቡድሂዝም ወይም ሂንዱይዝም፥ እስልምናን ወይም የሐሰት ክርስትናን የሚከተሉ ሰዎች አሉ። እነዚህ የሐሰት ሃይማኖቶች በአመዛኙ ሰዎች የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት የተወሰነ ተግባር ሊያከናውኑ እንደሚችሉ የሚያስተምሩ በመሆናቸው ተመሳሳይነት አላቸው።

ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸ የተለየ ዓይነት ድነት (ደኅንነት) አለ። ክርስቶስ፥ «እኔ መንገድና ሕይወት እውነትም ነኝ» በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለምና» ብሏል (ዮሐ. 14፡6)። ለሰማሪያዊቷ ሴት እንደተናገረው። እግዚአብሔርን ለማምለክ የሚፈልግ ማንም ሰው በመንፈስ ብቻ ሳይሆን በእውነትም ሲሰግድለት ይገባል (ዮሐ 4፡21-24)። ጴጥሮስ ስለ ክርስቶስ ሲናገር፥ «እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና» ብሏል (የሐዋ. 4፡12)። ስለሆነም፥ አዲስ ኪዳን «እድን ዘንድ ምን ላድርግ?» የሚለውን ጥያቄ በትክክል ሊመልስ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ ይገልጻል። መልሱም ግልጽ ነው- «በክርስቶስ እመንና ዳን» የሚል ነው (የሐዋ. 168)።

ሰይጣን ይህ ጥያቄ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ስለሚያውቅ፥ ጥያቄውን አንሥተን የእግዚአብሔርን ትክክለኛ መልስ እንዳናገኝ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። በብዙ ነገሮች እንድንዳከምና የተለያዩ ምቾቶችን እንድናሳድድ በማድረግ ጥድፊያ ያበዛብናል። በጥድፊያችን ምክንያት ይህን ጥያቄ አንሥተን የእግዚአብሔርን መልስ እንደማናገኝም ተስፋ ያደርጋል። ወይም ደግሞ ሰዎች በሃይማኖት ጥላ ሥር እንዲሆኑና ድነት (ደኅንነት)ን በተመለከተ ግን የተሳሳተ ምላሽ እንዲያገኙ ያደርጋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች፥ «እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?» የሚለውን ጥያቄ እንሥተው ትክክለኛ ምላሽ እንዳያገኙ ለማድረግ ሰይጣን የተለያዩ መንገዶችን ሲጠቀም የተመለከትህበትን ሁኔታ ግለጽ ። ለ) እግዚአብሔር የሰጠውን የድነት (ደኅንነት)ን መንገድ በግልጽ ማወቅ ለምን የሚያስፈልግ ይመስልሃል? ሐ) የወኅኒ ቤቱ ጠባቂ የጠየቀውን ጥያቄ እንዴት እንደምትመልስ በመግለጽ የእግዚአብሔርን የድነት (ደኅንነት) መንገድ በ100 ቃላት ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።

ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ብቸኛ የድነት (ደኅንነት) መንገድ ጥርት አድርጎ የገለጸው በሮሜ መልእክቱ ነው። ጳውሎስ የየትኛውም ዘር (አይሁዳዊ ወይም አሕዛብ) ወይም ሃይማኖት ተከታይ ቢሆን፥ እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያድንበት ብቸኛው መንገድ በክርስቶስ ላይ በሆነ እምነት እንደሆነ በጥንቃቄ አብራርቷል።

ብዙ ክርስቲያኖች አሳቡን ለመረዳት ሲቸገሩም (ጴጥሮስም እንኳ የጳውሎስን አንዳንድ ጽሑፎች ለመረዳት ተቸግሮ ነበር [2ኛ ጴጥ. 3፡15-16]፥ በታሪክ ሁሉ እግዚአብሔር በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመለወጥ የሮሜን መልእክት ሲጠቀም ቆይቷል። ይህንንም ያደረገው በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት ሰዎች ስለ እግዚአብሔር መንገድ ግልጽ ግንዛቤ እንዲያገኙ በማድረግ ነው። ለምሳሌ ያህል፥ በ15ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ዓመታት ማርቲን ሉተር የተባለው መነኩሴ የተነሣው፥ ካህናት ለመዳን ብለው ልዩ ልዩ የተሳሳቱ ነገሮችን አጽንተው ያዝዙ በነበረበት ወቅት ነው። ይህ ሰው የሮሜን መልእክት በጥንቃቄ በሚያጠናበት ጊዜ እግዚአብሔር በክርስቶስ በማመን የሚገኘውን ብቸኛ መዳን እንዲመለከት ዓይኖቹን ከፈተለት። ከሰዎች ተቃውሞ በተቃራኒ፥ ማርቲን ሉተር እምነቱን በክርስቶስ ላይ በመጣል፥ «የፕሮቴስታንት ክርስትና» የተባለ እንቅስቃሴ ጀመረ። ይህም ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር የድነት (ደኅንነት) መንገድ የሚመልስ እንቅስቃሴ ነበር። ይህ ሰው በኢትዮጵያ የሚገኙ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አባት ነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

2 thoughts on “የሮሜ መልእክት መግቢያ”

  1. Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

  2. በጣም ጠቃሚና ሰዎች በቀላሉ የእግዚአብሔርን ቃል የሚያጠኑበትና ሒዎታቸውን የሚለውጡበት መንገድ ነው!!!

Leave a Reply

%d bloggers like this: