የሮሜ መልእክት ዓላማ

የውይይት ጥያቄ፡- ሮሜ 1፡1-17 አንብብ። «ወንጌል» የሚለው ቃል ስንት ጊዜ እንደተጠቀሰ ቁጠር። ይህ ጳውሎስን ስላሳሰበው ዋንኛ ጉዳይ ምን ይነግረናል?

የሮሜን መልእክት በጥንቃቄ በምናጠናበት ጊዜ ጳውሎስ ይህን መልእክት ለመጻፍ ያነሣውት አያሌ ዓላማዎች እንደነበሩት እንረዳለን።

  1. በታሪክ ሁሉ ክርስቲያኖች፥ የሮሜ መልእክት የእግዚአብሔርን የድነት (የድኅንነት) መንገድ የሚያሳይና እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ድነትን (ደኅንነትን) ለመስጠት በወጠነው ዕቅድ ውስጥ ክርስቶስ ምን ዓይነት ስፍራ እንዳለው የሚያመለክት የጳውሎስ ዐቢይ ነገረ መለኮታዊ መጽሐፍ እንደሆነ ሲገነዘቡ ኖረዋል። በመጽሐፉ ውስጥ ተደጋግመው ከተጠቀሱት ቃላት አንዱ «ወንጌል» ሲሆን፥ 12 ጊዜያት ያህል ተጠቅሷል። እንደ ጽድቅ፥ የእግዚአብሔር ጽድቅ፥ ድነት (ደኅንነት) ወዘተ…. ያሉ ቁልፍ ቃላት፥ ጳውሎስ ወንጌሉ በክርስቶስ ላይ እንደሚማከልና ድነት (ደኅንነት) እያንዳንዱ ሰው ከእርሱ ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ላይ እንደሚወሰን ለማሳየት መሻቱን ያሳያሉ። ሰው ለመዳን ምን ማድረግ አለበት? በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት እንዴት ጻድቅ ሊሆን ይችላል? የዳኑ ሰዎች እንዴት ሊመላለሱ ይገባል? እነዚህ ጳውሎስ በመጽሐፉ ውስጥ ለማብራራት ከሚፈልጋቸው ዐበይት ሥነ መለኮታዊ ጥያቄዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው።
  2. ጳውሎስ በጉብኝቱ ወቅት የሮሜ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ወደ ስፔይን ለመውሰድ በወጠነው ዕቅድ እንድትተባበረው እያዘጋጃት ነበር።
  3. ብዙ ምሁራን ጳውሎስ የሮሜ ክርስቲያኖች በአይሁዶችና በአሕዛብ መካከል ስላለው ግንኙነት፥ ብሎም ከሮም መንግሥት ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነትና ስለ ሌሎችም ጉዳዮች ያነሡዋቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ እንደ ሞከረ ያስባሉ። ጳውሎስ አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ በክርስቶስ በማመን ብቻ የሚድኑ መሆናቸውን በመግለጽ ጥያቄዎቻቸውን መልሷል። የክርስቶስ ወንጌል የመጣው አረማውያን ለነበሩት አሕዛብ ብቻ አልነበረም። ረዥም የብሉይ ኪዳን ትውፊት የነበራቸው አይሁዶችም በክርስቶስ ማመን ያስፈልጋቸው ነበር (ሮሜ 1-3)። ምንም እንኳ እግዚአብሔር አሕዛብ ክርስቲያኖችን ወደ ቤተሰቡ ቢያመጣም፥ ይህ እግዚአብሔር ለአይሁዶች የነበረውን ልዩ ዕቅድ አይሰርዘውም። እነዚህ በሥጋ የአብርሃም ልጆች የሆኑት አንድ ቀን ታላቅ መንፈሳዊ መነቃቃትን የሚያገኙ ናቸው (ሮሜ 9-11)። በተጨማሪም፥ ጳውሎስ ለጣዖት የተሠዋን ሥጋ እንደ መብላት ባሉት ባሕላዊ ልምምዶች የሚለያዩ አይሁዶችና አሕዛብ እንዴት ተስማምተው ሊኖሩ እንደሚችሉም አስረድቷል።
  4. በሚሲዮናዊነት አገልግሎቱ ሁሉ፥ የአይሁድ ክርስቲያኖች የጳውሎስን ትምህርት ሲቃወሙ ቆይተዋል። እነዚህ አይሁዶች፥ የአሕዛብ ክርስቲያኖች የሕግን ትምህርት በመከተል እንደ ግርዛት ያሉትን ሥርዓቶች ካልፈጸሙ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንደማይኖራቸው በመግለጽ ተቃውመውታል። የገላትያ መልእክት፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 3 እና 10-13 ይህንን ትግል ያንጸባርቃሉ። በተጨማሪም ጳውሎስ በእምነት ስለ መዳን የሚሰጠው ትምህርት ክርስቲያኖች ኃጢአት እንዲሠሩ ስለሚያበረታታ አደገኛ ነው የሚል አሳብ ለነበራቸው ሰዎች ምላሽ እየሰጠ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ የሮሜን መልእክት ከጻፈባቸው ምክንያቶች አንዱ ስለ ድነት (ደኅንነት) የነበረውን መረዳት ግልጽ ማድረግ ነበር። ድነት (ደኅንነት) ማለት ምን ማለት እንደሆነ፥ ሰው እንዴት ሊድን እንደሚችልና ከብሉይ ኪዳን ሕግጋት ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት እንዳለው አስረድቷል። ጳውሎስ በቅርቡ ወደ ሮም ለመሄድ ተስፋ ስላደረገ፥ እርሱ ወይም ሌላ የአይሁድ ክርስቲያን ደርሶ ክርክር ከመነሣቱ በፊት የሮም ክርስቲያኖች ስለ ድነት (ደኅንነት) በግልጽ እንዲገነዘቡ ፈለገ።
  1. አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ ገንዘብ ሰብስቦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርስ የሚናገረውን አሳብ በሮሜ መልእክት ውስጥ እንዳሰፈረ ይናገራሉ። እነዚህ ምሁራን በአይሁድና በአሕዛብ ክርስቲያኖች መካከል የተጠናከረ ክፍፍል ሲደረግ እንደነበረ ያስባሉ። የአይሁድ ክርስቲያኖች፥ አሕዛብ የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን መከተል አለባቸው በሚለው አቋማቸው ሲጸኑ፥ የአሕዛብ ክርስቲያኖች በቁጥር ከአይሁድ ክርስቲያኖች በመላቃቸው ይኩራሩ ነበር። ጳውሎስ ከዚህ ክፍፍል የተነሣ የአይሁድ ክርስቲያኖች ከአሕዛብ የሚመጣውን ስጦታ ላለመቀበል እንዳይወስኑ ፈርቶ ነበር (ሮሜ 15፡31)። ጳውሎስ ይህ ክፍፍል እንዳይባባስ ይፈልግ ነበር። ስለሆነም፥ አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ ኃጢአትን በመሥራታቸው በእኩል ደረጃ በደለኞች እንደሆኑ በማሳየት በእምነት ድነትን (ደኅንነትን) እንዲቀበሉ ያስገነዝባቸዋል። ሁለቱም የኃጢአት አመለካከቶቻቸውን አሸንፈው በፍቅርና በመቻቻል የሚከፋፍሏቸውን ጉዳዮች (ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ መብላት፥ ወዘተ…) መቆጣጠር ያስፈልጋቸው ነበር።
  2. ጳውሎስ አንዳንዶች እንደሚሉት አይሁዶችንና የብሉይ ኪዳንን እንደማይቃወም ለማሳየት ፈልጎ ነበር (የሐዋ. 21፡20-21)። ምንም እንኳ ጳውሎስ ድነት (ደኅንነት) አይሁዳዊ በመሆን ሳይሆን በእምነት እንደሚገኝ ቢያስተምርም፥ እግዚአብሔር በታሪክም ሆነ ገና ወደፊት ለአይሁዶች የተለየ ዓላማ እንዳለው አመልክቷል። አይሁዶች የእግዚአብሔር የፍሬ ዛፍ ሲሆኑ፥ አሕዛብም እዚያው ላይ ተተክለዋል። አንድ ቀን ግን የጥንቱ ሕዝቡ የሆኑት አይሁዶች ስፍራቸውን ይይዛሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- በእነዚህ ዓላማዎች ውስጥ የታዩት እውነቶች ዛሬ ለአብያተ ክርስቲያኖቻችን የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “የሮሜ መልእክት ዓላማ”

  1. Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply

%d bloggers like this: