ጳውሎስ የሮሜን መልእክት ለማን ጻፈ? መልእክቱስ የተጻፈው መቼና የት ነው?

ጥያቄ፡ ሮሜ 1፡7 አንብብ። ሀ) ጳውሎስ የመልእክቱ ተቀባዮች እነማን ናቸው ይላል? ለ) የመልእክቱን ተቀባዮች እንዴት ገለጻቸው? ሐ) የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት በመጠቀም፥ ስለ ሮም ከተማና ቤተ ክርስቲያን ጻፍ።

የጥንት ዘመን ደብዳቤዎች መግቢያ ሁለተኛው ዐቢይ ክፍል ደብዳቤው ለማን እንደተጻፈ መግለጽ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ “በሮሜ ላላችሁት ሁሉ” ብሏል። ጳውሎስ ይህንን መልእክት የጻፈው በታላቁ የሮም ግዛት መዲና ለነበሩትና በብዙ የተለያዩ ቤቶች ውስጥ ለሚሰባሰቡት ክርስቲያኖች ሁሉ ነበር። «የሮሜ መልእክት» የሚለው የመጽሐፍ ርእስ የተወሰደው የመልእክቱ ተቀባዮች ከመሆናቸው እውነታ ነው።

ጳውሎስ እነዚህን የሮሜ ክርስቲያኖች በሁለት መንገዶች ይገልጻቸዋል። በመጀመሪያ፥ በእግዚአብሔር የተወደዱ መሆናቸውን ይገልጻል። እግዚአብሔር እጅግ ስለወደዳቸው ክርስቶስ እንዲሞትላቸው ላከው። አጥብቆ ስለወደዳቸው ወንጌሉን እንዲሰሙ አደረገ። ይህ የእግዚአብሔር ፍቅርና ድነት (ደኅንነት) የጳውሎስን ሕይወት ስለተቆጣጠረው፥ ምንም ነገር ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንደማይችል የሚገልጽ መዝሙር ተቀኝቷል (ሮሜ 8፡31-39)። ጳውሎስ እግዚአብሔርን ምን ያህል እንደሚወደን ከተገነዘብን፥ በፍጹም ከእርሱ እንደማንለይ ያውቅ ነበር።

ሁለተኛ፥ ጳውሎስ የሮሜ ክርስቲያኖች ቅዱሳን ለመሆን እንደተጠሩ ገልጾአል። ጳውሎስ በተለየ ሁኔታ እንደተመረጠ ሁሉ፥ እያንዳንዱም የሮም ክርስቲያን በእግዚአብሔር ለተወሰነ ዓላማ ነበር የተመረጠው። ጳውሎስ ቅዱሳን ለመሆን የተለዩ እንደሆኑ ተናግሮአል፡፡ በአዲስ ኪዳን ቅዱሳን የሚለው ቃል በሁለት መንገዶች ይተረጎማል፡፡ ምንም ሥጋዊነት ያልለቀቃቸው ቢሆኑም ወይም መንፈሳዊ ሕይወታቸው የበሰለም ቢሆኑ ሁሉም ክርስቲያኖች ቅዱሳን ተብለው ይጠራሉ (ምክንያቱም የተለዩ በመሆናቸው ነው)። ማለትም በድነት (ደኅንነት) አማካኝነት የማያምኑ ሰዎች ከሚገኙበት ዓለም ተለይተን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናል። የቃሉ ትርጉም ሙሉ በሙሉ ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር ክብር የሚኖሩትንም ሰዎች ያመለክታል። ጳውሎስ በዚህ ስፍራ ይህን ቃል የተጠቀመው በሁለተኛው ትርጉሙ ነው። እግዚአብሔር የመረጠን ድነትን (ደኅንነትን) ካገኘን በኋላ እንዳሻን እንድንኖር አይደለም። እርሱ የመረጠን ሕይወታችን ሁሉ ለእርሱ ክብር እንዲውል ነው። ከኃጢአት ተለይተን በሁለንተናችን እግዚአብሔርን እንድናገለግል መርጦናል።

የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር «ቅዱስ» እንድትሆን መርጦሃል? ዓላማው ተግባራዊ ይሆን ዘንድ በሕይወትህ ውስጥ ሊለወጡ የሚገባቸው ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?

ጳውሎስ የሮሜን መልእክት በጻፈበት ወቅት ሮምን አይቷት አያውቅም ነበር። ስለ ሮም ክርስቲያኖች ያገኘውን መረጃ ያቀበሉት እንደ አቂላና ጵርስቅላ ያሉ ሌሎች ክርስቲያኖች ነበሩ። ነገር ግን ይህች ቤተ ክርስቲያን በክርስትና ታሪክ እጅግ ጠቃሚ ቤተ ክርስቲያን እንደምትሆን ተገንዝቦ ነበር። ስለሆነም፥ ይህች ቤተ ክርስቲያን የክርስትናን መሠረተ አሳብ፥ በተለይም የድነትን (ደኅንነትን) እውነተኛ ትርጉም እንድታውቅ አጥብቆ ይሻ ነበር። ጳውሎስ ለዚህች አስፈላጊ ለነበረች ቤተ ክርስቲያን በጣም ጠቃሚ መልእክት ጻፈ።

የሮም ከተማ የሰፊው የሮም ግዛት መዲና ነበረች። በእግዚአብሔር ዕቅድ መሠረት፥ ይህች የሮም ግዛት ወንጌሉና ክርስትና ሥር ሰድደው በዓለም ታላቅ ሃይማኖት የሚበቅልበት ስፍራ ነበረች። ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት፥ ከብሪታኒያ እስከ ኢራንና ከዚያም እስከ ግብጽ በሚዘልቀው የሮም ግዛት ውስጥ 100 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ይኖሩ እንደነበር ይገመታል። ለ1000 ዓመታት ያህል ይህ ግዛት የዓለም ዐቢይ የፖለቲካ ኃይል ነበር። በሮም ከተማ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ይኖሩ የነበሩ ሲሆን፥ ምናልባትም ከተማዪቱ ከየትኛዎቹም የጥንት ዘመን ከተማዎች በላይ የሠለጠነች ነበረች። በሮም ከሚኖሩ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ምናልባትም እብዛኞቹ ባሮች ላይሆኑ አይቀሩም። ብዙውን ጊዜ ወንጌሉ በፍጥነት ሥር ሰድዶ የሚስፋፋው በባሮች መካከል ነበር። ምናልባትም ጳውሎስ ራሱን «የክርስቶስ ባሪያ» ብሎ ከጠራባቸው ምክንያቶች አንዱ፥ ምንም እንኳ እንደ እነርሱ ሥጋዊ ጌቶች ባይኖሩትም መንፈሳዊ ጌታ እንዳለው ለማመልከት ይሆናል።

በሐዋርያት ሥራም ሆነ በጥንታዊ የታሪክ መጻሕፍት ውስጥ ሰፊ ትንታኔ ስለማናገኝ ስለ ሮም ቤተ ክርስቲያን አጀማመር የምናውቀው አሳብ የተወሰነ ነው። ይህች ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደተመሠረተች የሚያወሱ የተለያዩ ንድፈ አሳቦች አሉ። አንዳንድ ምሁራን ከበዓለ ኀምሳው የመንፈስ ቅዱስ መውረድ በኋላ አይሁዶች ክርስትናን ወደ ሮም እንደወሰዱ ይገምታሉ (የሐዋ. 2፡10)። በክርስቶስ ያመኑት አይሁዶች በሮም ምኩራቦች እምነታቸውን ለሌሎች አይሁዶች አስፋፉ። ከበዓለ ኀምሳ 16 ዓመታት በኋላ፥ በ49 ዓ.ም በከተማዪቱ ውስጥ ክርስቲያኖች ያልሆኑትን አይሁዶች የሚያሰጋ የክርስቲያኖች ቁጥር ሊገኝ ችሏል። የሮም የታሪክ ጸሐፊዎች «ክረስተስ» (Chrestus) በተባለ ሰው ምክንያት አይሁዶች በከተማዪቱ ውስጥ ሁከት መቀስቀሳቸውን ጽፈዋል። በዚህ የክርስቶስን ስም በሌሎች ሆሄያት እንደጻፉት እንገምታለን። በሁከቱ ሳቢያ ንጉሡ አይሁዶችን ከከተማዪቱ አስወጣ (የሐዋ. 18፡2)።

ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሐዋርያው ጳውሎስ ከሮም ክርስቲያኖች ጋር ግንኙነት አደረገ በሁለተኛ የሚሲዮናዊነት ጉዞው ከሮም ተባርረው ወደ ቆሮንቶስ ለመኖር ከሄዱት ከአቂላና ከጵርስቅላ ጋር ተገናኘ (የሐዋ. 18፡2)። ጳውሎስ በቆሮንቶስና በኋላም በኤፌሶን አብሯቸው በመቆየት አቂላንና ጵርስቅላን በሚገባ አወቃቸው። በሚሲዮናዊ ጉዞው ሁሉ፥ ጳውሎስ ከብዙ ክርስቲያኖች ጋር ሳይገናኝና ሳይዛመድ አልቀረም። እነዚህም ክርስቲያኖች በኋላ ወደ ሮም ተጉዘው የሮም ቤተ ክርስቲያን አካል ሆነዋል።

ሌላው ንድፈ አሳብ በ30ዎቹ መጀመሪያ ወይም በ50ዎቹ መካከል ጴጥሮስ ለአያሌ ዓመታት በሮም ሲያገለግል እንደቆየ ያስረዳል። ነገር ግን ይህንን አሳብ የሚደግፍ ብዙ መረጃ ማግኘት አልተቻለም። በዚህ ወቅት ከሮም ወይም ወደ ሮም የተጻፉ ደብዳቤዎች ጴጥሮስ በከተማዪቱ ውስጥ እንደነበረ አያመለክቱም።

ሌላው ንድፈ አሳብ በበኩሉ ጳውሎስ በግሪክና እስያ ባካሄደው አገልግሎት ያመኑ እንደ አቂላና ጵርስቅላ ያሉ ክርስቲያኖች ወደ ሮም እንደሄዱ ያስረዳል። እነዚህ ሰዎች ሮም በደረሱ ጊዜ እግዚአብሔር ስለተጠቀመባቸው ብዙ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ለማምጣትና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለመሆን ቻሉ። ጳውሎስ ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን በማወቅ በምዕራፍ 16 ስማቸውን እየጠራ ሰላምታ ያቀረበውም በዚህ ምክንያት ነው። እነዚህ ምሁራን ጳውሎስ ለሮም ቤተ ክርስቲያን የኃላፊነት ስሜት የተሰማው መንፈሳዊ ልጆቹ ስለመሠረቷትና እርሱም መንፈሳዊ «አያት» በመሆኑ ነው ይላሉ። ስለሆነም፥መንፈሳዊ የልጅ ልጆቹን ለመጎብኘት፥ በእምነታቸው ለማበረታታት (ሮሜ 1፡11) እና ወደ ስፔይን ለመሄድ ፈለገ።

በሶስተኛው የሚሲዮናዊነት ጉዞው ጳውሎስ የሮምን ክርስቲያኖች ጎብኝቶ ወደ ስፔይን የመሄድ ፍላጎት ነበረው (ሮሜ 15፡24-28)። ምናልባትም በሚቀጥሉት ክፍለ ዘመናት ይህች የሮም ቤተ ክርስቲያን የምትጫወተውን ሚና መንፈስ ቅዱስ እያሳየው ይሆናል። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ለመጭው ጉብኝቱ ያዘጋጃቸው ዘንድ ይህን መልእክት ጻፈላቸው።

ጳውሎስ የሮሜ መልእክትን የጻፈበት ዘመንና ስፍራ

አብዛኞቹ ምሁራን ጳውሎስ በሦስተኛው የሚሲዮናዊነት ጉዞው ወቅት ለሦስት ወራት ግሪክ በቆየበት ወቅት የሮሜን መልእክት እንደጻፈው ያስባሉ (የሐዋ. 20፡2-3 አንብብ)። ምናልባትም ከቆሮንቶስ ከተማ ይሆናል የጻፈው። የጳውሎስን ደብዳቤ ለሮም ቤተ ክርስቲያን ያደረሰችው ፌቤን የክንክራኦስ ተወላጅ ነበረች። ክንክራኦስ ከቆሮንቶስ ስምንት ማይሎች ርቃ የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ነበረች (ሮሜ 16፡1)።

ይህም ጳውሎስ 1ኛና 2ኛ ቆሮንቶስን ከጻፈ በኋላ በ57 ዓ.ም አካባቢ የሮሜን መልእክት እንደጻፈ ያስረዳል። ጊዜው ከጳውሎስ ሦስተኛ የሚሲዮናዊነት ጉዞ በኋላ ሲሆን፥ ጳውሎስ የእስያና የአውሮፓ ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም ለሚገኙ ድሀ ክርስቲያኖች ያዋጡትን ገንዘብ ለማድረስ በመዘጋጀት ላይ ነበር። በዚህ ጊዜ ለሌላ የሚሲዮናዊነት ጉዞ ዕቅድ በማውጣት ላይ ነበር። ከኢየሩሳሌም ወደ ሮም፥ ከዚያም ከሮም በስተምዕራብ ጫፍ ወደምትገኘው ስፔይን የመሄድ ዕቅድ ነበረው። ወንጌሉ እስከ ሮም ድረስ ስለተጓዘ፥ ጳውሎስ ወንጌሉ ባልደረሰባቸው ስፍራዎች ለማገልገል ፈልጎ ነበር (ሮሜ 15፡20)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “ጳውሎስ የሮሜን መልእክት ለማን ጻፈ? መልእክቱስ የተጻፈው መቼና የት ነው?”

  1. Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply

%d bloggers like this: