ወንጌል የሚለው ቃል መልካም የምሥራች ማለት ነው። ይህ እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ሁሉ ይቅር ብሎ በነፃ እንደሚያሰናብተን የሚያረጋግጥ አዋጅ ነው። በቤተሰቡ ውስጥ ተቀባይነትን አግኝተን ለዘላለም ልንድን እንችላለን። ሌላኛው የወንጌሉ ገጽታ «የእግዚአብሔር ቁጣ» ነው። ይህ ቁጣ ባልዳኑት ሰዎች ላይ እግዚአብሔር የሚያሳየው የጥላቻ ስሜት እይደለም። እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ እንደሚወድ እናውቃለን (ዮሐ. 3፡16)። ነገር ግን ይህ ቁጣ እግዚአብሔር ዐመፃን በሚያደርጉት ላይ የሚያመጣው ቅዱስ ፍርድና ቅጣት ነው። እግዚአብሔር ቅዱስና ኃጢአትን የሚቀጣ አምላክ በመሆኑ፥ ኃጢአትን ዝም ብሎ አያልፍም። ጳውሎስ ወንጌሉን በጥድፊያ የሰበከው ይህ ቅጣት ባላመኑት ሰዎች ላይ ዘላለማዊ መዘዝ ስለሚያስከትል ነው። የእግዚአብሔር ቁጣ የማያምኑትን ሰዎች የሚያጋጥም የሲኦል ፍርድ ብቻ ሳይሆን፥ አሁንም መንፈሳዊ ሕይወት በማይኖሩ ሰዎችም ላይ የሚደርስ እንደሆነ ጳውሎስ ገልጾአል።
ጳውሎስ የአሕዛብ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብ ሁኔታ የሚያመለክትበትን መንገድ እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል። ሰዎች ወንጌልን ባለመስማታቸው ምክንያት ከእግዚአብሔር ፍርድ ያመልጣሉ ብሎ መገመት እንደማያስፈልግ ክርስቲያኖች ቢገነዘቡ መልካም ነው። ሰዎች ወንጌልን አለመስማታቸው ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት ምክንያት ሊሆን አይችልም። ሮማውያን በከተማዪቱ ውስጥ ለተለያዩ ጣዖታት ቤተ መቅደሶችን ሠርተው የሚያመልኩ ሃይማኖታዊ ሰዎች ነበሩ። ነገር ግን ጳውሎስ ሃይማኖተኛነታቸውንና ኃጢአተኝነታቸውን ከእግዚአብሔር እይታ አንጻር ሲመለከት ከዓመፀኝነትና ከኃጢአት በስተቀር ምንም መልካም ነገር እንዳልነበራቸው ተገንዝቧል። ይህም የሮማውያን ብቻ ሳይሆን የሁሉም ነገዶችና ሕዝቦች ባሕርይ ነው።
የውይይት ጥያቄ፡– ዛሬ የእግዚአብሔር ቁጣ እንዲሁም የሕዝቡ ዓመፀኝነትና ኃጢአተኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው እንዴት ነው?
በብዙ ትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ የአዝጋሚ ለውጥ (ኢቮሉሽን) ንድፈ አሳብን ያስተምራሉ። ይህም ሰዎችና እንስሳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ እንደሚሄዱ የሚያስረዳ ሳይንሳዊ ትምህርት ነው። ጳውሎስ ግን ዓለምን የተመለከተው ለየት ባለ መንገድ ነበር። ጳውሎስ እግዚአብሔርን የማያመልክና ሕግጋቱን የማይታዘዝ የትኛውም ሰው ወይም አገር በጥፋት ጎዳና ላይ እንደሚገኝ ገልጾአል። በዚህ ክፍል፥ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን የተጻፉ ሕግጋት ላያውቁ ቢችሉም በኃጢአተኛ ልባቸው በፈጣሪያቸው ላይ ማመፁን እንደሚመርጡ በመግለጽ የሰው ልጆችን በተለይም የአሕዛብን ውድቀት አስረድቷል። ጳውሎስ የሰው ልጆችን ውድቀት በሚከተሉት ደረጃ ዎች ይዘረዝራል።
ሀ. ሰዎች ሁሉ ስለ እግዚአብሔር የተወሰነ እውቀት አላቸው (ሮሜ 1፡19-20)። ንጉሥ ሰሎሞን ይህን መንፈሳዊ እውቀት «በሰው ልብ ውስጥ ያለ ዘላለማዊነት» ሲል ገልጾታል (መክ 3፡11 አንብብ)። ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ላያውቁ ቢችሉም፥ ከእግዚአብሔር ፍጥረት አንዳንድ ባሕርያቱንና የመፍጠር ኃይሉን ሊገነዘቡ ይችላሉ (መዝ. 19፡ አንብብ።) ለድነት (ለደኅንነት) የሚያበቃ እውቀት ላይኖራቸው ቢችልም፥ ፈጣሪ አምላክ እንዳለ፥ እነርሱም የእርሱ ፍጡራን ስለሆኑ ሊያመልኩትና ሊታዘዙት እንደሚገባ ያውቃሉ።
ለ. ሰዎች ለእግዚአብሔር ለመታዘዝና እርሱን ለማስከበር አይፈልጉም (ሮሜ 1፡21)። በታሪክ ሁሉ በየትኛውም ነገድ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የፍጥረትን ምስክርነት ላለመቀበል ይመርጣሉ። ፈጣሪያቸውን ለማክበርና ደስ የሚሰኙበት መልካም ስጦታ ሁሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚመጣ ተገንዝበው ምስጋና ሊያቀርቡለት ባለመፈለጋቸው በእግዚአብሔር ላይ ያምፃሉ። (ጳውሎስ እግዚአብሔር ለሰጠን ነገር ሁሉ አመስጋኞች እንድንሆን ምን ያህል በአጽንኦት እንደሚገፋፋን አጢን።)
ሐ. ማንነቱን ቢገልጥላቸውም ሰዎች እውነተኛውን አምላክ ለማምለክ አይፈልጉም። ይህም ወደ መንፈሳዊ ዕውርነትና የተሳሳተ አስተሳሰብ ይመራል (ሮሜ 1፡22-23፥ 25)። ይህ ዓመፅ እግዚአብሔርን ለማምለክ ጉልበት እንዳይኖራቸው ያደርጋል። ሰዎች እውነተኛውን አምላክ ለመቀበልና ለማምለክ ስለማይፈልጉ፥ አእምሯቸው ጨልሞ የሞኝነት ውሳኔዎችን ያደርጋሉ። ከሁሉም በላይ ሞኝነት የነገሠበት ውሳኔያቸው ደግሞ የራሳቸውን ሃይማኖት ለመፍጠር መፈለጋቸው ነው። በጳውሎስ ዘመን፥ ይህ ውሳኔ ሰዎችን ወደ ጣዖት አምልኮ መርቷቸዋል። ከእንጨት ወይም ከብረት የቀረጹአቸው ምስሎች አማልክት ሆነው እንደሚያድኗቸው በሞኝነት ያምኑ ነበር። በእኛ ዘመን ደግሞ ይህ የሞኝነት ውሳኔ የሚገለጸው የሐሰት ሃይማኖቶችን በመከተል ነው። ሰዎች ሁሉ በተፈጥሯቸው ሃይማኖተኞች ናቸው። አብዛኞቹ በግልጽ የተብራራ የአምልኮ ሥርዓት ሲኖራቸው፥ ይህም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንገኛለን ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። የእግዚአብሔርን ሕልውና የሚክዱ (athiests) ወይም የአዲሱ ትውልድ (New Age) ተከታዮች እንኳ የሕይወታቸው አምላክ እንደሆኑ በማሰብ ራሳቸውን በማምለክ ላይ ይገኛሉ። ነገር ግን እነዚህ ሃይማኖቶች ድነት (ደኅንነት)ን ስለማያስገኙ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ሞኝነት ብሎ ይጠራዋል።
መ. ትክክለኛ ያልሆነ አምልኮ ወደ ተሳሳተ አኗኗር ይመራል። ይህም ሰዎች በእግዚአብሔር አምሳል እንደተፈጠሩ ሰብአዊ ፍጡራን ሳይሆን እንደ እንስሳት የሚኖሩበት ዓይነት ሕይወት ይሆናል። ሰዎች ለእውነተኛው አምላክ ለመገዛት በማይፈልጉበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር የልባቸውን ፍላጎት እንዲከተሉ በማድረግ ይፈርድባቸዋል። ይህም ተጨማሪ ፍርድን ያስከትልባቸዋል። ጳውሎስ እግዚአብሔር «አሳልፎ ሰጣቸው» እያለ ሦስት ጊዜ ደጋግሞ የጠቀሰውን አስተውል (ሮሜ 1፡24፥ 26፥ 28)። የመጀመሪያው የእግዚአብሔር ፍርድ የሰዎች ሥነ ምግባር እንዲላሽቅና እግዚአብሔር የሰጣቸውን ስጦታ ከአግባብ ውጭ እንዲጠቀሙ አድርጓቸዋል። ይህም አንድ ወንድ ከሚስቱ ጋር፥ አንዲት ሴት ደግሞ ከባሏ ጋር ልታደርግ የሚገባትን ወሲባዊ ግንኙነት በመቃወሙ ነው። በጥንት ዘመን የጣዖት አምልኮ፥ አምላኪዎች በቤተ መቅደስ ከሚገኙ ሴተኛ አዳሪዎች ጋር ከሚፈጽሙት ግብረ ሥጋ ግንኙነት ጋር የተያያዘ ነበር። ነገር ግን ይህ ወሲባዊ ምግባረ ብልሹነት በምድር ላይ በሁሉ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፥ ይህም የእግዚአብሔር ፍርድ ምን ያህል እንደ ተስፋፋ ያሳያል።
ሠ. ባለማቋረጥ የእግዚአብሔርን ሕግጋት አለመታዘዝ ከተፈጥሯዊ ውጭ ወደሆኑት ተግባራት ይመራል። እንስሳት እግዚአብሔር በወንድና ሴት መካከል እንዲፈጸም የወሰነውን ተፈጥሯዊ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሕግጋት ሲያውቁ፥ ሰዎች ግን ከተፈጥሯዊ ደንብ ውጭ ወጥተው የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ያደርጋሉ። በዓለም ዙሪያ ተቀባይነቱ እያደገ የመጣው ግብረሰዶማዊነት የሰዎችን የማስተዋል ዕድገት የሚያመለክት ሳይሆን ፈጽሞ ከእግዚአብሔር የመለየታቸው ምልክት ነው።
ጳውሎስ ከእግዚአብሔር መለየት ቅጣትን እንደሚያስከትል አስረድቷል (ሮሜ 1፡27)። ዛሬ እግዚአብሔር ስለ ወሲባዊ ንጽሕና የሰጠውን ሕግ በማይከተሉ ሰዎች ላይ ፍርድ ማምጣቱን ከምንመለከትባቸው መንገዶች አንዱ የኤድስ ወረርሽኝ ነው። በምዕራቡ ዓለም በኤድስ ወረርሽኝ ከተጠቁት ሰዎች አብዛኛዎቹ ግብረሰዶማውያን ናቸው። በአፍሪካና እስያ ኤድስ እየተስፋፋ ያለው ሰዎች ብዙ ወሲባዊ ግንኙነቶችን ስለሚያደርጉ ነው። ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕግ ጠብቀው ከትዳራቸው ውጭ ወሲብ ባይፈጽሙ የኤድስ በሽታ ይጠፋ ነበር። በኢትዮጵያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የኤድስን በሽታ የሚያስከትለው ቫይረስ አለባቸው። እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ባለመፈለጋቸው ምክንያት በቤተ ክርስቲያንም ሆነ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ብዙ ሰዎች ይሞታሉ። ይህ በጳውሎስ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል በዘመናችን ከሚፈጸምባቸው መንገዶች አንዱ ነው። ሌሎች ብዙ በሽታዎችም ተገቢ ባልሆኑ ወሲባዊ ግንኙነቶች አማካኝነት ይተላለፋሉ።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ትክክለኛ ያልሆነ ግንኙነት ወደ ተሳሳተ ወሲባዊ ባሕርይ እንደሚመራ አመልክቷል። ይህን በኢትዮጵያ ውስጥ በማያምኑ ሰዎች መካከል ያየህበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) ብዙ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር ወሲብ መፈጸም ተገቢ ነው ብለው የሚያስቡት ለምንድን ነው? ሐ) እግዚአብሔር ሰዎች ንጹሕ ወሲባዊ ሕይወት እንዲከተሉ የሰጠውን ሕግ በሚመለከትና ከብዙ ሰዎች ጋር ዝሙት ማድረግ ስለሚያስከትለው ውጤት ጥቂት ሰባኪያን ብቻ ግልጽ ትምህርት የሚሰጡት ለምንድን ነው? መ) ስለ ኤድስ አመጣጥና እንዴት ሊወገድ እንደሚችል ለወጣቶችና ለማኅበረሰቡ ለማስተማር ቤተ ክርስቲያንህ ምን ዓይነት አስተዋጽኦ ልታበረክት ትችላለች?
ረ. ለእግዚአብሔር በቀጣይነት አለመታዘዝ በሰብአዊ ግንኙነቶች ሁሉ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል (ሮሜ 1፡28-32)። እግዚአብሔር የሚያምፁ ሰዎችን ሲቀጣ ለበለጠ ውርደት አሳልፎ የሚሰጣቸው እንደሆነ ለሦስተኛ ጊዜ ማንበባችን ነው። ሰዎች የተበላሹት በወሲባዊ ገጽታዎች ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሕይወት ክፍሎቻቸው ነው። ጳውሎስ በዚህ ስፍራ ሁለት ዓይነት ኃጢአቶችን ዘርዝሯል። እነዚህም «ትልቅ» ናቸው ብለን የምናስባቸውና «ትንሽ» ናቸው የምንላቸው ኃጢአቶች ናቸው። ጳውሎስ የሰዎች አእምሮ በኃጢአት ስለተበላሸ፥ የክፋት ተግባራቸው ገደብ እንዳጣ አመልክቷል። በሂትለር የተፈጸመው ዓይነት የሕዝብ ጭፍጨፋዎች ተካሂደዋል። በሩዋንዳ ክርስቲያኖች ነን የሚሉ ሰዎች የሌላውን ነገድ አባላት ፈጅተዋል። በዓለም ሁሉ ላይ የሚካሄዱት ጦርነቶች በሰዎች ልብ ውስጥ ስግብግብነት፥ አድመኝነት፥ ውድቀት፥ ኃጢአትና ክፋት እንዳለ ያሳያሉ።
በተጨማሪም፥ ጳውሎስ በጣም አሳሳቢ አይደሉም የምንላቸውን አንዳንድ ኃጢአቶችም ይዘረዝራል። በዝርዝሩም ውስጥ እንደ ማታለል፥ መዋሸት፡ ማጭበርበር ሲኖሩ፥ ሐሜት፥ ስድብ፥ ትዕቢትና ለወላጆች አለመታዘዝ እንደ ሌላ ኃጢአቶች ተዘርዝረዋል።
ጳውሎስ በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ ያለውን ጥልቅ ጨለማና ኃጢአት ለመግለጥ ይፈልጋል። ከመካከላችን ያልዋሸ፥ ያላማ፥ በትምህርቱ ወይም በቤተሰቡ ወይም በጎሳው፥ ወዘተ… ያልተኩራራ ማን ነው? አንድን ሰው ስላልገደልን ወይም የወሲብ ኃጢአት ስላልፈጸምን ያንን ያህል ክፉዎች እይደለንም ብለን ልናስብ እንችላለን። ነገር ግን እያንዳንዳችን ከጠለቀው ልባችን ውስጥ ኃጢአት እንዳለብን ልንገነዘብ ይገባል። ጳውሎስ የውድቀት የመጨረሻ ደረጃ የሆኑትን እነዚህን ኃጢአቶች እንዴት እንደሚዘረዝር ተመልከት። በግብረ ሶዶማውያን ወይም ከእኛ በላይ ክፉዎች ናቸው በምንላቸው ሰዎች ላይ ከመፍረድ ይልቅ እያንዳንዳችን የራሳችን ልብ ምን ያህል ክፉ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል።
ጳውሎስ በሮሜ 1 ሊያስተላልፍ የሚፈልገው መልእክት አሕዛብ ሁሉ ኃጢአተኞች እንደሆኑ ነው። ልባችን በኃጢአት የቆሸሸ ነው። አሕዛብ በመጽሐፍ ቅዱስ በተገለጸው መሠረት ስለ እግዚአብሔር በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ባይችልም፤ ከእግዚአብሔር ፍጥረት በቂ እውቀትን ያገኛሉ። መጽሐፍ ቅዱስን አለማወቃቸው ከኃጢአት ነፃ ያደርጋቸዋል ማለት አይደለም። የሰው ልጆች እግዚአብሔር በፍጥረቱ ውስጥ የሰጠውን እውቀትን ባለመቀበላቸው በምርጫቸውና በተግባራቸው ዓመፀኛነታቸውን አሳይተዋል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በኢትዮጵያ ውስጥ ይህን የሰዎችን ጥልቅ ኃጢአተኝነት ያየህባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) ክርስቲያኖች ብንሆንም እንኳ የራሳችንን የልብ ክፋት እንዴት ልንመለከት እንደምንችል አብራራ። ሐ) ይህ ሰዎች ጥሩ በመሆናቸው እግዚአብሔር እንደሚቀበላቸው በመግለጽ ስለሚያቀርቡት ክርክር ምን ያስተምራል?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)
Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት