እምነት እንጂ ሥራችን እንደማያድነን የሚያሳዩ የብሉይ ኪዳን ምሳሌዎች (4:1-25)

የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያጸድቀው በእምነት እንጂ በሥራ እንዳልሆነ ጳውሎስ ያረጋገጠበትን ሁኔታ በአጭሩ አብራራ።

የጳውሎስን መልእክት የሚያነቡ አይሁዶች አዲስ የድነት (የደኅንነት) መንገድ እያቀረበልን ነው የሚል ስጋት አድሮባቸው ነበር። በተለይም እግዚአብሔር ሕግጋቱን የሚታዘዙትን እንደሚቀበል ያስተምራል ብለው ከሚያስቡት የብሉይ ኪዳን ትምህርት ተቃራኒ ስለመሰላቸው ተጨንቀው ነበር። «በእምነት መዳን በብሉይ ኪዳን የተገለጠውን እውነት አይሽረውም ወይ?» ሲሉ ጠየቁ። ጳውሎስ ግን ብሉይ ኪዳን በግልጽ እንደሚያስቀምጠው ከእግዚአብሔር ጋር መልካም ግንኙነት የሚፈጠረው በእምነት እንጂ ትክክለኛ የሆነ ነገር በማድረግ አለመሆኑን በማስገንዘብ መልስ ሰጥቷቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡– ዘፍጥረት 15፡1-6 አንብብ። ሀ) እግዚእብሔር ለአብርሃም የሰጠው የተስፋ ቃል ምን ነበር? ለ) አብርሃም ለእግዚአብሔር የተስፋ ቃል የሰጠው ምላሽ ምን ነበር? ሐ) እግዚአብሔር ለዚህ ምላሹ ለአብርሃም የሰጠው ስጦታ ምን ነበር?

ሀ. የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች (ሮሜ 4፡1-8)

  1. ብሉይ ኪዳን ስለ አብርሃም ምን ይላል? (ሮሜ 4፡1-5) አብርሃም ታላቅ ተግባር በመፈጸሙ ነው እግዚአብሔር ጻድቅ የሚለውን ስያሜ እንደ ሽልማት የሰጠው? አልነበረም። ዘፍጥረት 15፡6 እንደሚያሳየው፥ የአይሁዶች አባት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው የብዙ ሕዝብ አባት እንደሚሆን የተሰጠውን የተስፋ ቃል በማመኑ ምክንያት ነበር። የአብርሃም ጽድቅ እንደ ስጦታ «የተቆጠረ» እንጂ አብርሃም ላከናወነው ተግባር በደመወዝነት የተከፈለው አልነበረም።
  2. ሌላው የአይሁዶች ጀግና የነበረው ዳዊት፥ እግዚአብሔር ሰውን የሚባርከው ሕግን በመጠበቁና አንድን ታላቅ ተግባር በማከናወኑ ምክንያት እንዳልሆነ መስክሯል (ሮሜ 4፡6-8)። አንድ ሰው የሚባረከው እግዚአብሔር በነፃ ኃጢአቱን ይቅር ሲል ነው (መዝ. 32፡1-2)። ዳዊት ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ግንኙነት «በትክክለኛ» ነገር ላይ የተመሠረተ ቢሆን ኖሮ ይሞት እንደነበረ ገልጾአል። እርሱ ነፍሰ ገዳይና አመንዝራ ነበር። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ግንኙነት በአምላኩ ፍቅር፥ ጸጋና የኃጢአት ይቅርታ ላይ እንጂ የሚገባውን ዋጋ በመቀበሉ ላይ የተመሠረተ አልነበረም።

ለ. አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ በእግዚአብሔር ዘንድ በእምነታቸው ምክንያት ተቀባይነት እንደሚያገኙ የሚያሳይ የአብርሃም ምሳሌነት (ሮሜ 4፡9-25)። ጳውሎስ እግዚአብሔር ሁልጊዜም ሰዎችን በእምነታቸው ላይ ተመሥርቶ እንደሚያጸድቅ ከአብርሃም ሕይወት ጠቅሶ አስረድቷል። አይሁዶች አብርሃም አባታችን ነው ይሉ ነበር። እርሱ የአይሁድ ሕዝብ ጅማሬ ነበር። እግዚአብሔር አይሁዶች መሆናቸውንና ከዚህም የተነሣ የተስፋ ሕዝብና የእግዚአብሔር ልዩ ሕዝብ መሆናቸውን ለማመልከት ለአብርሃም ውጫዊ ምልክት የሆነውን የግርዛት ሥርዓት ሰጥቶት ነበር።

እዚህ ላይ የጳውሎስን ትምህርት ለመረዳት በአብርሃም ሕይወት ውስጥ የተከናወኑትን ተግባራት ቅደም ተከተል ማወቅ ይኖርብናል። በዘፍጥረት 12 እግዚአብሔር አብርሃምን ጠርቶ ከዑር ወደ ከነዓን እንዲሄድ አዘዘው። አሕዛብ የነበረው አብርሃም ሕይወቱን ከአደጋ ላይ በመጣል ቤተሰቡን ትቶ ወደ ከነዓን እንዲሄድ ያደረገው በእግዚአብሔር ላይ የነበረው እምነት ነበር።

በዘፍጥረት 15፥ እግዚአብሔር ለአብርሃም እንደ ሰማይ ከዋክብት የበረከተ ዘር እንደሚሰጥ ተስፋ ገባ። አብርሃም የማይቻል የሚመስለውን የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል በማመኑ እግዚአብሔርም እምነቱን እንደ ጽድቅ ቆጠረለት። በዘፍጥረት 17፥ እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዘሩ የግርዛትን ሥርዓት ሰጠ። ይህም አብርሃም አይሁዳዊና ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት የሚያደርግ ሰው መሆኑን የሚያሳየው ምልክት ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር አብራም ይባል የነበረው አሕዛብ አብርሃም የተባለ አይሁዳዊ የሆነው። በዘፍጥረት 21፥ እግዚአብሔር ለአይሁዳዊው አብርሃም ተስፋ የገባለት ይስሕቅ የተባለ ልጅ ተወለደ። ጳውሎስ ከእነዚህ በአብርሃም ሕይወት ውስጥ ከተከሰቱት ነገሮች ቅድም ተከተል በመነሣት የሚከተለውን ገለጻ አድርጓል።

እግዚአብሔር አብርሃምን ጻድቅ ያደረገው በግርዛት ሥርዓት አይሁዳዊ ከመሆኑ በፊት አሕዛብ ሳለ ነበር (ሮሜ 4፡9-15)። ይህም አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ ጽድቅን ለማግኘት አይሁዳዊ መሆንና መገረዝ አስፈላጊው አለመሆኑን ያሳያል። አብርሃም የብሉይ ኪዳንን ሕግ ሳይከተሉ፥ ሳይገረዙና አይሁዳዊ ሳይሆኑ በእግዚአብሔር የሚያምኑ አሕዛብ (ከሕግ ውጭ ያሉት) መንፈሳዊ አባት ነበር። አብርሃም፥ ከሕግ የነበሩት፥ በእግዚአብሔር ላይ እምነት የነበራቸው፥ የብሉይን ሕግ በመጠበቅና በመገረዝም በአካል አይሁዳዊ የነበሩት ሰዎችም አባት ነው። እግዚአብሔር ሰውን “ጥፋተኛ አይደለም” የሚልበት ዋነኛው መስፈርት በእግዚአብሔር ላይ የሆነ እምነት እንጂ አይሁዳዊ መሆን ወይም የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን መከተል አይደለም። ሰውን እውነተኛ የአብርሃም ልጅ የሚያደርገውና ጽድቅን የሚያሰጠው እምነት ነው። ሕግን ለመጠበቅ የሚሞክሩና በራሳቸው ጥረት ድነት (ደኅንነት)ን ሊያገኙ እንደሚችሉ የሚያስቡ ሰዎች የእምነት ፈለጉን ስለማይከተሉ የአብርሃም ልጆች ሊሆኑ አይችሉም። ስለሆነም፥ የእግዚአብሔርን ሕግ ሙሉ ለሙሉ ሊጠብቁ ስለማይችሉ ከእግዚአብሔር ቁጣ ሥር ናቸው።

ሐ. አብርሃም በእግዚአብሔር እውነተኛ እምነት ምን እንደሆነና የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ማግኘት የሚቻለው አንድን ተግባር በማከናወን ሳይሆን በእምነት እንደሆነ በሕይወቱ አሳይቷል (ሮሜ 4፡16-23)። (ማስታወሻ፡- ለአብርሃም የተሰጠው የተስፋ ቃል ልጅ ነበር። ለእኛ የተሰጠን የተስፋ ቃል ድነት (ደኅንነት)ን ማግኘት ነው።) በዘፍጥረት 18፥ እግዚአብሔር ለአብርሃም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እርሱና ሣራ ልጅ እንደሚወልዱ ተስፋ ሰጥቶት ነበር። በሰው ግንዛቤ ይህ የተስፋ ቃል ሊፈጸም የማይችል ነበር። በዕድሜያቸው መግፋት የተነሣ አብርሃም (የ100 ዓመት አረጋዊ) እና ሣራ የ90 ዓመት አረጋዊት) በሥጋ ልጅ ሊወልዱ አይችሉም ነበር። ሣራ በትዳር ዘመናቸው ሁሉ መካን ነበረች። ስለሆነም፥ ልጅ የመውለድ ችሎታቸው ሙት ነበር። አብርሃም ግን እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል አመነ። ሁልጊዜም እምነት የሚነሣው ከእግዚአብሔር የተስፋ ቃል እንጂ ከሰው ተስፋ አይደለም። አብርሃም ልጅ ለመውለድ አለመቻላቸውን ጨምሮ እግዚአብሔር ለሞተው ሕይወትን ሊሰጥ እንደሚችል ያውቅ ነበር። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር የተስፋ ቃሉን እንደሚፈጽም አመነ። እግዚአብሔር የአብርሃምን እምነት ያከበረውና «ጥፋተኛ ያልሆነና» ከእርሱ ጋር ትክክለኛ ግንኙነት እያደረገ መሆኑን ያወጀው ለዚህ ነበር። ይህ ሁሉ የሆነው አብርሃም ከመገረዙና አይሁዳዊ ከመሆኑ በፊት ነበር።

ስለሆነም፥ አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ሊከተሉት የሚገባ ምሳሌ ነው። በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ አማካኝነት ለድነታችን (ለደኅንነታችን) የሚያስፈልገውን ሁሉ እንዳሟላ የሚገልጸውን የእግዚአብሔርን ቃል አምነን እንቀበላለን እንጂ በራሳችን ጥረት ለመዳን አንሞክርም።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “እምነት እንጂ ሥራችን እንደማያድነን የሚያሳዩ የብሉይ ኪዳን ምሳሌዎች (4:1-25)”

  1. Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply

%d bloggers like this: