ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች ያቀረበው ሰላምታና የመልእክቱ ዓላማ (ሮሜ 1፡1-17)

፩. ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች ያቀረበው ሰላምታ (ሮሜ 1፡1-7)

ምንም እንኳ የሮሜ መልእክት ከደብዳቤነቱ ይልቅ ወደ ትምህርታዊ ሐተታነቱ የሚያደላ በመሆኑ ለየት ያለ ቢሆንም፥ ጳውሎስ በመግቢያው ጥንታዊ የደብዳቤ አጻጻፍን ይከተላል። ሁሉም የጳውሎስ መልእክቶች መግቢያ ቢኖራቸውም፥ የሮሜ መልእክት መግቢያ ረዘም ያለና ከሌሎቹ ሁሉ ያነሰ ግላዊ ጉዳዮች ያሉበት ነው።

የጥንት ሰዎች መጀመሪያ የሚያነሡት ጥያቄ፥ «የዚህ መልእክት ጸሐፊ ማን ነው?» የሚል ነበር። በተለይም ጸሐፊውን ወይም መልእክቱን ያመጣውን ሰው ካላወቁት ይህንኑ ጥያቄ አጥብቀው ያነሣሉ። ስለሆነም ጳውሎስ ራሱን በማስተዋወቅና ወንጌሉን ለመጻፍ ሥልጣን ያገኘበትን መሠረት በመግለጽ የሮሜን መልእክት ይጀምራል። ራሱን በአሕዛብ ስሙ ጳውሎስ ብሎ ካስተዋወቀ በኋላ ማንነቱን ለመግለጽ ሦስት ዐበይት ሃሳቦችን ያስቀምጣል።

  1. የክርስቶስ አገልጋይ ነበር። ጳውሎስ አብዛኞቹ ባሪያዎች ከሆኑት የሮሜ ክርስቲያኖች ጋር ራሱን እያመሳሰለ ነበር። እርሱም ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመታዘዝ የኖረ ባሪያ ነበር። የሕይወት ዓላማው ኢየሱስ ክርስቶስን ማገልገል ነበር።
  2. ሐዋርያው ለመሆን ተጠርቷል። እግዚአብሔር ጳውሎስ ከ12ቱ ሐዋርያት እኩል ሥልጣን እንዲኖረው አድርጎ ጠርቶታል። ስለሆነም፥ መልእክቱ ሥልጣን ያለውና ሊደመጥ የሚገባው ነበር። የጳውሎስን መልእክት አለማመን ማለት የክርስቶስን መልእክት እንደ አለማመን ማለት ነበር።
  3. የጳውሎስ ልዩ ዓላማና በእግዚአብሔር የተጠራበት ምክንያት የእግዚአብሔርን ወንጌል እንዲሰብክ ነበር። በሚቀጥሉት ዝርዝሮች ውስጥ ጳውሎስ በቀሪዎቹ የመጽሐፍ ገጾች ስለሚጽፈው ወንጌል ያብራራል።

ሀ) ወንጌሉ ከእግዚአብሔር የመጣ እንጂ ሰዎች የፈጠሩት አይደለም። ስለሆነም፥ የጳውሎስ ትምህርት እግዚአብሔርን ለማስደሰት የሚደረግ ሌላው ጥረት ወይም ሃይማኖት አልነበረም። ይህ እግዚአብሔር ለሰዎች ሁሉ የገለጠው መልካም የምሥራች ነበር።

ለ) ወንጌሉ በብሉይ ኪዳን የተተነበየ እንጂ አዲስ ክስተት አይደለም።

ሐ) የወንጌሉ እውነት በክርስቶስ ላይ ያማክላል። የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ፍጻሜ የሆነው ክርስቶስ መሢሑ የዳዊት ልጅ ነው። ነገር ግን በትንሣኤው እንደተረጋገጠው፥ እርሱ ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅም ነው። ክርስቶስ ለሰዎች ሁሉ እግዚአብሔር ድነትን (ደኅንነትን) ያመጣበት መንገድ ነው። ስለሆነም፥ ክርስቶስ “ስለ ስሙ” ክብርን ይቀበላል። ጳውሎስ በክርስቶስ በማመን የሚገኘውን ድነት (ደኅንነት) ለአሕዛብ የመስበክ ሥልጣን ተሰጥቶታል። ይህም ድነት (ደኅንነት) ለእርሱ በመታዘዝ ይረጋገጣል።

ጳውሎስ የጥንቱን ዘመን የደብዳቤ አጻጻፍ ስልት በመከተል መልእክቱን ለማን እንደጻፈ ይገልጻል። መልእክቱን የጻፈው በሮሜ ላሉት ሁሉ ነበር። ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው በሮሜ ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ሳይሆን በአነስተኛ የቤት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚሰባሰቡ ክርስቲያኖች መሆኑ ግልጽ ነው። ሁሉም የድነት ምንጭ የሆነው እግዚአብሔር ወደ ክርስቶስ ኅብረት የጠራቸው ሰዎች ነበሩ። ሁሉም በእግዚአብሔር የተወደዱና ድነትን አግኝተው ወደ ቤተሰቡ የተቀላቀሉ ነበሩ። የተጠሩትም «ቅዱሳን ለመሆን» እና ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የታዛዥነት ሕይወት ለመኖር ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡– በዚህ የሮሜ መልእክት መግቢያ ውስጥ ስለ ወንጌሉ የተገለጹ ምን ዐበይት እውነቶችን ታያለህ?

ጳውሎስ ከመጀመሪያው ጀምሮ ስለ ድነታችን አያሌ ነገሮችን በአጽንኦት ይጠቅሳል። ጳውሎስ ድነት ከእግዚአብሔር ፍቅርና ጥሪ እንደሚመነጭ ያስተምራል። የወንጌሉ እምብርት መልካም ተግባር ለማከናወን መጣር ወይም ሕይወታችንን መለወጥ አይደለም። ነገር ግን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገር ነው። ድነት ከእግዚአብሔር ፍርድ ማምለጥ ብቻ አይደለም። ነገር ግን የዳንበት ዓላማ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕይወት ለመኖር ነው።

፪. ጳውሎስ ይህን መልእክት የጻፈበት ዓላማ (ሮሜ 1፡8-17)፡- ጳውሎስ ብዙዎቹ የሮሜ ክርስቲያኖች ከእርሱ ጋር ባይተዋወቁም ለረዥም ጊዜ በአእምሮው ውስጥ እንደኖሩ ገልጾአል። ጳውሎስ ስለ እምነታቸው በሰማ ጊዜ በክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነት የሚታወቁ ሰዎች በመሆናቸው ደስ ተሰኝቷል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ባለማቋረጥ ለእነዚህ ሰዎች በመጸለይ በግሉ እንደ ወደዳቸው አረጋግጧል። ነገር ግን ለእነርሱ የነበረው በጎ ስሜት ከመጸለይ ያለፈ ነበር። ከረዥም ጊዜ በፊት ሄዶ ሊጎበኛቸው ፈልጎ ነበር። ነገር ግን ሊሄድ ባቀደ ጊዜ ሁሉ መሰናክሎች ይገጥሙት ጀመር። በዚህ ጊዜ ግን ጳውሎስ ወደ ሮም ሄዶ እንደሚያያቸው እርግጠኛ ሆኗል።

ወደ ሮም የሚሄደው ለምን ነበር? በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት በእምነታቸው እንዲያድጉ ለማገዝ በመፈለግ ነበር። ጳውሎስ «መንፈሳዊ ስጦታዎች» ሲል በ1ኛ ቆሮንቶስ 12 የጠቀሳቸውን ዓይነት የጸጋ ስጦታዎች ማለቱ አይመስልም። ነገር ግን ይህ መንፈሳዊ እውነቶችን ለምእመናን ማስተላለፍን የሚያመለክት ይመስላል። ጳውሎስ በዚህ ክፍል ስለ ማስተማር፥ ማበረታታትና በእምነታቸው እንዲያድጉ ማገዝን ያሳያል። ሁለተኛ፥ ጳውሎስ በሮም ከእነርሱ ጋር «መከር» ለመሰብሰብ ይፈልግ ነበር። ይህም በአብዛኛው አሕዛብ ከሆኑት የሮም ክርስቲያኖች ጋር በመሥራት ወንጌሉን በሮም ለማካፈልና ሰዎች ሲያምኑ ለማየት እንደሚፈልግ ያሳያል። በኋላ ጳውሎስ ወደ ሮም ለመሄድ የፈለገበትን ሌላ ምክንያት ይገልጻል። ይህም ወደ ስፔይን ወንጌሉን ይዞ እንዲሄድ የሮሜ ክርስቲያኖች እንዲረዱት ነበር (ሮሜ 15፡23-33)።

ጳውሎስ በሮም ወንጌሉን ለማካፈል አጥብቆ የፈለገው ለምን ነበር? «ግዴታ» ነበረበት። እግዚአብሔር ለሰዎች ሁሉ ወንጌል እንዲሰብክ አዞታል። ጳውሎስ ለአሕዛብ ወንጌልን ካልሰበከ እግዚአብሔር በኃላፊነት እንደሚጠይቀው ያውቅ ነበር። ወንጌሉን ያልመሰከረላቸው ሰዎች የደም ዕዳ ይኖርበታል። የሮሜን መልእክት ከጻፈ ከአያሌ ወራት በኋላ ለኤፌሶን ሽማግሌዎች ከሰዎች ሁሉ ደም ንጹሕ መሆኑን የተናገረው ለዚህ ነበር (የሐዋ. 20፡26)። በብዙ አገሮች መድኃኒት እያለው ለመርዳት የማይፈልግ ሐኪም ለበሽተኛው ሕይወት ተጠያቂ ይሆናል። ጳውሎስም ለሰው ልጆች ችግር መፍትሔ የሚሰጥ መድኃኒት (ወንጌል) እንዳለውና ይህንኑ መድኃኒት ካላሰራጨ እግዚአብሔር እንደሚፈርድበት ያውቅ ነበር።

ወንጌሉ የሚያስፈልገው ለማን ነው? ጳውሎስ ወንጌሉ ለሰዎች ሁሉ እንደሚያስፈልግ ገልጾአል። «ግሪኮች» የሚባሉት በግሪክ ቋንቋ አፋቸውን የፈቱ ሰዎች ነበሩ። «ግሪክ ያልሆኑት» ደግሞ በግሪክ ቋንቋ አፋቸውን ያልፈቱ የተቀሩት የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ነበሩ። «ጠቢባን» የሚባሉት የተማሩ ሰዎች ሲሆኑ፥ «ሞኞች» የሚባሉት ደግሞ ያልተማሩት ነበሩ።

እግዚአብሔር ስብከቱን እንደሚያከብርለት ጳውሎስ እንዴት እርግጠኛ ሆነ? ሌሎች ሰዎች እያፌዙበት ምስክርነቱን ይፋ እንዲያደርግ ያገዘው ነገር ምን ነበር? ምክንያቱም የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የእግዚአብሔር ኃይል ስላለው ነው። ወንጌል ለሰው ልጅ ችግር ብቸኛው መፍትሔ ነው። ትምህርት፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፥ ገንዘብ፥ ልማት የሰውን ልጅ ጥልቅ ፍላጎቶች ሊያሟሉ አይችሉም። የሰው ልጅ ለሚጋፈጣቸው ችግሮች ሁሉ መልስና ቁልፍ መፍትሔ ያለው ወንጌል ነው። ታሪካዊ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑት አይሁዶችና አይሁዳውያን ያልሆኑት አሕዛብ ሁሉ ይህ ወንጌል ያስፈልጋቸዋል።

በአጭሩ፥ ወንጌል ምንድን ነው? ጳውሎስ በሮሜ 1፡7 «ከእግዚአብሔር የሆነ ጽድቅ» በማለት ጠቅለል ባለ መልኩ ይገልጸዋል። ሁለት ዓይነት ጽድቆች አሉ። እነዚህም በሰው ሥራዎችና ሃይማኖቶች የሚገኝ የሰው ጽድቅና በኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝ የእግዚአብሔር ጽድቅ ናቸው። የሰው ጽድቅ ድነትን (ደኅንነትን) አያመጣም። በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኛውን ወንጀለኛ የማያደርገውና ተቀባይነትን እንዲያገኝ የሚያደርገው የእግዚአብሔር ጽድቅ ብቻ ነው። ሰው የእግዚአብሔርን ጽድቅ ወይም ደኅንነት ሊያገኝ የሚችለው እንዴት ነው? በእምነት ብቻ ነው። ይህም መንፈሳዊ እጁን ወደ እግዚአብሔር ዘርግቶ ነፃ የጽድቅ ስጦታ ሲቀበል ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እያንዳንዳችን በአካባቢያችን ለሚገኙ ከድነት (ከደኅንነት) ለራቁ ሰዎች እንድንመሰክር ተጠርተናል። (የሐዋ. 1፡8 አንብብ።) ጳውሎስ ስለ ወንጌል ምስክርነት ካሳየው ሁኔታ አንጻር ስናይ እያንዳንዳችን ስላለብን ግዴታ ምን እንማራለን? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ የሚገኙት አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ይህንን ግዴታ የሚፈጽሙ ይመስልሃል? መልስህን አብራራ። ሐ) እግዚአብሔር ይህንን ግዴታ እየፈጸምህ መሆንህን ወይም አለመሆንህን እንዲያሳይህና በዚህ ሳምንት የምትመሰክርለት ሰው እንዲጠቁምህ በጸሎት ጠይቅ። ስማቸውን በወረቀት ላይ ጽፈህ እየጸለይህ በዚህ ሳምንት ውስጥ እንዴት እንደምትመሰክርላቸው ዕቅድ አውጣ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች ያቀረበው ሰላምታና የመልእክቱ ዓላማ (ሮሜ 1፡1-17)”

  1. Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply

%d bloggers like this: