የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ምርጫ (ሮሜ 9፡1-29)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ «ድነት (ደኅንነት)» የሚለው ቃል የሚያስተላልፋቸውን ፍቺዎች በሙሉ ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር አንተን ያደነባቸውን የተለያዩ መንገዶች ዘርዝር።

ድነት (ደኅንነት)፡- በሁሉም ቋንቋዎች ውስጥ ከሚገኙ ውድ ቃላት አንዱ ድነት (ደኅንነት) ነው። ቃሉ በብዙ የተለያዩ መንገዶች ያገለግላል። አንድ ሰው ከአደጋ በሚተርፍበት ጊዜ ድኗል እንላለን። አንዲት ሴት በጠና በታመመች ጊዜ የታዘዘላት መድኃኒት ካሻላት አድኖአታል ማለት ነው። ይህን ቃል ባለማቋረጥ ከምንጠቀምባቸው መንገዶች ጥቂቶቹ እነዚህ ሁለቱ ናቸው።

ነገር ግን ከሌሎች ሁሉ የበለጠ ጠቀሜታ ያለው አንድ የድነት (ደኅንነት) ዓይነት አለ። ይህም እግዚአብሔር እኛን ከኃጢአታችን የሚያድንበት ነው። (ጳውሎስ ዛሬ ብዙ ሰዎች አጽንኦት በሚሰጡበት ከበሽታ ወይም ከድህነት የመዳን ጉዳይ ላይ ምን ያህል አነስተኛ ትኩረት እንደሰጠ ተመልከት።) በሮሜ መጽሐፍ ውስጥ፥ ጳውሎስ ስለ ድነት ሲያብራራ ነበር። ጳውሎስ ድነት አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት በመግለጽ ነበር የጀመረው። ሰዎች፥ የየትኛውም ነገድ አባል ይሁኑ፥ ሃይማኖተኞች ይሁኑ ወይም አይሁኑ፥ ጥሩ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት ይኑራቸው ወይም አይኑራቸው፥ በቅዱስ አምላክ ፊት ኃጢአትን ስለፈጸሙ ጥፋተኛ ናቸው። ይህም ማለት ከእግዚአብሔር ቁጣ ሥር በመሆናቸው እግዚአብሔር በሞት ይቀጣቸዋል ማለት ነው። በኃጢአታችን ምክንያት የእግዚአብሔር የሞት ቅጣት እንደሚገባን እስካላወቅን ድረስ የድነትን ትርጉም እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ልንረዳው አንችልም።

ጳውሎስ ሰዎች ወደ ክርስቶስ ተመልሰው በመስቀል ላይ እንደሞተላቸው ሲያምኑ እግዚአብሔር ስለሚሰጣቸው ድነት አብራርቷል። ጳውሎስ ማብራሪያውን የጀመረው ከኃላፊ ጊዜ ነው። በሰው ልጆች ሁሉ ላይ የተወሰነው የኃጢአት ጥፋተኝነት «ጥፋተኛ አይደለህም» በሚል እንዲለውጥ እግዚአብሔር ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስን የኃጢአት መሥዋዕት ወይም የቁጣው ማብረጃ አድርጎ መላኩ ብቻ በቂ አይሆንም። እያንዳንዱ ግለሰብ በክርስቶስ ለማመን የግል ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። ያንን የእምነት ውሳኔ ካደረገ በኋላ፥ ጻድቅ የሆነው አምላክ «ጥፋተኛ አይደለህም» ወይም «ጻድቅ ነህ» ሲል ወደ ቤተሰቡ ይቀበለዋል። ይህ የአንድ ጊዜ ውሳኔ ሰዎችን ከዘላለማዊ የሲዖል ፍርድ ያድናቸዋል።

ጳውሎስ በመቀጠል ስለ አሁኑ የድነት ገጽታ ያብራራል። ይህም ከኃጢአት ቁጥጥር ነፃ ወጥተን ክርስቶስን ለመምሰል በየቀኑ በቅድስና የምናድግበት ነው። የክርስቶስ መስቀል ከአማኞች ሕይወት የኃጢአትን ተፈጥሮ እጥፍቷል። በሕይወታችን ውስጥ ባለው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ምክንያት ከኃጢአት ርቀን ለእግዚአብሔር ሕግጋት ልንታዘዝ እንችላለን።

ከዚያም ጳውሎስ ስለ ወደፊቱ የድነት ገጽታ ያብራራል። ጳውሎስ እያንዳንዱ አማኝ ከክርስቶስ ጋር የሚከብርበትን የወደፊት ዘመን አሻግሮ ያያል። ሕይወት በምድር ላይ ብዙ ኀዘንና መከራ የሚበዛበት ሊሆን ይችላል። ሆኖም ምንም ነገር ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንደማይችል ክርስቲያኖች ሊገነዘቡ ይገባል። ሁሉም ነገር ለልጆቹ ጥቅም ይውል ዘንድ እግዚአብሔር ወደ መንግሥተ ሰማይ ሊያደርሰንና ሙሉ ለሙሉ በሕይወታችን ዙሪያ የሚከሰቱትን ነገሮች ለመቆጣጠር ቆርጧል።

ጳውሎስ የወደፊቱን የድነት ገጽታ በሚመለከትበት ጊዜ እያንዳንዱ ክርስቲያን የሚያገኘውን ድነትና ክብር ብቻ አይጠቅስም። ነገር ግን ድነት ሌሎች ሁለት ዐበይት ነገሮችን እንደሚያጠቃልል ያስረዳል። በአዳምና ሔዋን ኃጢአት የተጀመረው ጥፋት (ረሃብ፥ በሽታ፥ የመሬት መንቀጥቀጥ፥ ድርቅ) ይወገድና ፍጥረት ሁሉ ይድናል። እግዚአብሔር መጀመሪያ ሲፈጥር የነበረውንም መልክ ይይዛል። የመጨረሻው ድነት የብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የነበሩትን አይሁዶችም ይነካል። በዚያን ጊዜ እነርሱም ድነትን ያገኛሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በዚህ የወደፊት ድነት (ደኅንነት) እግዚአብሔር ፍጥረትንና ዓለምን በሚያድንበት ጊዜ ይለወጣሉ የምትላቸው አንዳንድ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? ለ) ዛሬ በኃጢአት በቆሸሸች ዓለም ውስጥ በምንሠቃይበት ጊዜ ወደፊት የሚለወጡትን ነገሮች በትክክል መገንዘባችን የሚያጽናናን እንዴት ነው?

የእስራኤላውያን ያለማመናቸው መሠረቱ የእግዚአብሔርን ጽድቅ ከመቀበል ይልቅ በራሳቸው ጥረት ሊጸድቁ ስለፈለጉ ነው (ሮሜ 9-10)።

የውይይት ጥያቄ፡– ሮሜ 9-10 አንብብ። ሀ) ጳውሎስ አይሁዶች ወደ ክርስቶስ እንዲመለሱ የነበረውን ጥልቅ ፍላጎት የገለጸው እንዴት ነው? ለ) አይሁዶች የተቀበሏቸው በረከቶች ምን ምንድን ናቸው? ሐ) በእነዚህ በረከቶች አሁን የማይደሰቱበት ለምንድን ነው? መ) ጳውሎስ ከአይሁድ ዘር መወለድ በቂ እንዳልሆነና ሰዎች የአብርሃም መንፈሳዊ ልጆች ሆነው መወለድ እንዳለባቸው የሚያስረዳው እንዴት ነው? መ) ጳውሎስ አይሁዶችንና ያልዳኑበትን ምክንያት የገለጸው እንዴት ነው? ረ) ለሰዎች ሁሉ የተዘጋጀውን የድነት (ደኅንነት) መንገድ ጠቅለል አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው? ሰ) ሮሜ 10፡9-10ን በቃልህ አጥና። ይህ ክፍል ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች የሚሆኑበትን መንገድ በአጭሩ የገለጸው እንዴት ነው?

የሥነ መለኮት ምሁራንን ከሚያስቸግራቸው ጥያቄዎች አንዱ የእግዚአብሔር ታሪካዊ ሕዝብ የሆኑት አይሁዶች ስፍራ ምን ይሆን? የሚለው ነው። አሁን በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ምን ድርሻ አላቸው? በብሉይ ኪዳን ዘመን በምድር ላይ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ መካከል እግዚአብሔር የራሱ ልዩ ሕዝብ አድርጎ መርጧቸው ነበር። ልዩ ቃል ኪዳኖችንና የተስፋ ቃሎችንም ሰጥቷቸዋል። የሰጣቸውን ሕግጋት በማይታዘዙበት ጊዜም ባለማቋረጥ ይቀጣቸው ነበር። እንግዲህ እግዚአብሔር ከአይሁዶች ጋር የነበረውን ግንኙነት አጠናቅቆ ወደ ቤተ ክርስቲያን ፊቱን መልሷል ማለት ነው? በሮም የነበሩት አይሁዳውያን ክርስቲያኖችም በዚህ አሳብ ግራ ሳይጋቡ አልቀሩም። አይሁዶችና አሕዛብ አሁን እኩል ከሆኑና ወደ እግዚአብሔር መንፈሳዊ ቤተሰብ የሚመጡት በክርስቶስ በማመን ብቻ ከሆነ፥ አይሁዳዊ መሆን ምን ታሪካዊ ጥቅም አለው? የአይሁዶች የወደፊት ተስፋስ ምንድን ነው? እግዚአብሔር ለአይሁዶች የሰጣቸው የብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃሎችስ? ከእንግዲህ በሥጋ አይሁዳውያን ለሆኑት ወገኖች አያገለግሉም ማለት ነው?

ብዙ ክርስቲያኖች ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልስ እግዚአብሔር ከእንግዲህ ወዲህ ለአይሁዶች የተለየ ትኩረት አይሰጥም የሚል ነው። አሁን የእግዚአብሔር ዕቅድ የአብርሃም መንፈሳዊ ዝርያዎች በሆኑት ክርስቲያኖች ላይ ነው፥ የብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃሎችም በተምሳሌታዊ መልኩ በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸሙ እንጂ እግዚአብሔር በሆነ መንገድ ወደፊት ከአይሁዶች ጋር የሚካሄደውን ተግባር የሚያሳዩ አይደሉም ይላሉ። ነገር ግን እግዚአብሔር ለእስራኤልና ለአይሁድ ሕዝብ አሁንም የተለየ ዕቅድ እንዳለው የሚያምኑ ክርስቲያኖች ደግሞ አሉ። እግዚአብሔር ለአይሁዶች የሰጣቸው የተስፋ ቃሎች በብሉይ ኪዳን ውስጥ በተጠቀሰው መልክ ይፈጸማሉ። በዮሐንስ ራእይ ጥናታችን፥ ለዚህ ጥያቄ በምንሰጠው መልስ የትንቢትና የመጨረሻው ዘመን ግንዛቤያችንን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚለውጥ እንመለከታለን።

በሮሜ 9-11፥ ጳውሎስ የአይሁድ ክርስቲያኖች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክሯል። ጳውሎስ ፀረ አይሁዳዊ ነው የሚል ክስ ቀርቦበት ነበር። ጳውሎስ ይህን መልእክት ጽፎ ከጨረሰ ከጥቂት ወራት በኋላ ኢየሩሳሌም ውስጥ ነበር። በዚያም የአይሁድ ክርስቲያኖች በሐዋርያት መሪነት ጳውሎስ ወደ ቤተ መቅደሱ ገብቶ አንዳንድ የአይሁድ የመንጻት ሥርዓቶችን በመፈጸም ፀረ-አይሁዳዊ አቋም እንደሌለው እንዲያረጋግጥ ጠይቀውታል። ጳውሎስ ራሱን ዝቅ አድርጎ የተጠየቀውን ሁሉ በመፈጸም ለአይሁዶች የነበረውን ፍቅር አሳይቷል (የሐዋ. 21፡21-26)። ከዚህም የተነሣ ወደ እስር ቤት ወርዶ ለአራት ዓመታት ማቅቋል። በሮሜ 9-11፥ ጳውሎስ የብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃሎች በአይሁዶች መካከል ስላልተፈጸሙበት ምክንያት፥ በአሕዛብና አይሁዶች መካከል ስላለው ግንኙነትና እግዚአብሔር ለአይሁዶች ያለው የመጨረሻ ዕቅድ ምን እንደሚሆን በማብራራት ለእነርሱ የነበረውን ፍቅር ገልጧል።

 1. ጳውሎስ ለአይሁዶች የነበረውን ጥልቅ ፍቅር ገለጠ (ሮሜ 9፡1-3)። እጅግ የምንወዳቸው የቤተሰባችን አባላት በክርስቶስ ለማመን በማይፈልጉበት ጊዜ ምን ያህል እንደምንጨነቅ ሁላችንም እናውቃለን። ወደ ሲዖል እንደሚሄዱ ስለምናውቅ እንጨነቃለን። በሰማይ እናገኛቸው ዘንድ ዘመዶቻችን በክርስቶስ የሚያምኑበትን ጊዜ በናፍቆት እንጠብቃለን። ጳውሎስም ወገኖቹ ስለሆኑት አይሁዶች ባሰበ ጊዜ እንዲህ ዓይነት የጭንቀት ስሜት ተሰምቶታል። ጳውሎስ የአይሁድን ሕዝብ ወደ ድነት (ደኅንነት) ለማምጣት የሚችል ቢሆን የራሱን ድነት (ደኅንነት) አጥቶ ስለ እነርሱ ወደ ሲዖል ቢወርድ ፈቃደኛ እንደሆነ ገልጾአል። ጳውሎስ አይሁዶችን በጣም ይወዳቸው ነበር እንጂ ፀረ-አይሁዳዊ አቋም አልነበረውም።
 2. ጳውሎስ አይሁዶች ያገኟቸውን ብዙ በረከቶች ይዘረዝራል (ሮሜ 9፡4-5)። እግዚአብሔር አይሁዶችንና አሕዛብን በእኩል ሁኔታ ነበር ያስተናገደው? ጳውሎስ እግዚአብሔር ከአይሁዶች ጋር ታሪካዊ ግንኙነት ስለነበረው፥ አሕዛብ ያላገኟቸውን በረከቶች እንዳገኙ አብራርቷል።

ሀ. አይሁዶች ከእግዚአብሔር ጋር የአባትና የልጅ ዓይነት ልዩ ግንኙነት ነበራቸው። (ዘዳግ. 4፡22-23 አንብብ።)

ለ. «መለኮታዊ ክብር» ነበራቸው። ጳውሎስ ይህን ሲል በምድረ በዳ የነበረውን የክብር ደመና ለመግለጽ ብቻ ሳይሆን በቤተ መቅደስ ውስጥ የተገለጠውንም ለማመልከት ነበር (ዘጸ. 16፡7፤ 1ኛ ነገ 8፡10-10።

ሐ. አይሁዶች ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ ቃል ኪዳኖችን አድርገዋል። በሲና ተራራ ላይ ከተሰጣቸው ቃል ኪዳን በተጨማሪ፥ ለሌዊ፥ ለዳዊት፥ ወዘተ… የተሰጡት ቃል ኪዳኖች ነበሯቸው።

መ. በሲና ተራራ የእግዚአብሔርን ሕግ ተቀብለዋል። ይህም እግዚአብሔር እንዴት ሊኖሩና እርሱን ሊያክብሩ እንደሚገባቸው የገለጠበት መመሪያ ነበር። በዚህ መልኩ የእግዚአብሔርን ቃል የተቀበለ ሌላ ነገድ የለም።

ሠ. አይሁዶች በእግዚአብሔር የተሠራ የቤተ መቅደስ አምልኮ ያካሂዱ ነበር። ይህም በሰዎች አሳብ ሳይሆን በእግዚአብሔር የታቀደ ነበር።

ረ. እግዚአብሔር በቃሉ ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር። ከእነዚህ የተስፋ ቃሎች አብዛኛዎቹ በትንቢት መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፥ ከአይሁዶች የወደፊት በረከቶች ጋር የሚያያዙ ነበሩ።

ሰ. እንደ አብርሃም፥ ያዕቆብና ይስሐቅ ያሉት የአይሁድ የእምነት አባቶች ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ ግንኙነት የነበራቸው ሲሆን፥ እግዚአብሔር በእነርሱ ተጠቅሞ ልዩ የሆነውን የአይሁድ ሕዝብ መሥርቷል።

ሸ. እግዚአብሔር መሢሑ ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ዓለም ያመጣው በአይሁዶች በኩል ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ አይሁዳዊነት ከፍተኛ ታሪካዊ ጠቀሜታ እንደነበረው አስረድቷል። የቀድሞ ታሪካቸው ሊዘከር የሚገባው ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- የሚያምኑ ሰዎች ያላገኟቸውንና አንተ እንደ እግዚአብሔር ልጅ የምትደሰትባቸውን አንዳንድ በረከቶች ዘርዝር። እግዚአብሔርን ስለ እነዚህ በረከቶች ለማመስገን ጥቂት ጊዜ ውሰድ።

 1. ጳውሎስ እግዚአብሔር አጽንኦት የሚሰጠው ከሥጋዊ አይሁዳዊነት ይልቅ ለመንፈሳዊ አይሁዳዊነት እንደሆነ ገልጾአል (ሮሜ 9፡6-29)።

በዚያን ጊዜ የአይሁድ ክርስቲያኖች ጳውሎስን የሚጠይቁት ሌላም ጥያቄ ነበራቸው። ክርስቶስ የአይሁዶችን የኃጢአት ችግር የሚቀርፍና የብሉይ ኪዳን ተስፋዎች ፍጻሜ የሆነው መሢሕ ከሆነ፥ ብዙ አይሁዶች ያላመኑበት ለምንድን ነው? ይህ ክርስቶስ መሢሕ አለመሆኑን አያረጋግጥም? ጳውሎስ ለዚህ ጥያቄ በሰጠው ምላሽ የሚከተሉትን አሳቦች ትኩረት ሰጥቶ አብራርቷል።

ሀ. በትውልድ አይሁዳዊ የሆነ ሁሉ እውነተኛ አይሁዳዊ አይደለም (ሮሜ 9፡6-13)። እስማኤልንና ሌሎችንም ጨምሮ አብርሃም ብዙ ልጆች ነበሩት (ዘፍጥ. 25፡1-4)። ከእነዚህ ልጆች መካከል የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚያመለክተውና የተስፋ ቃል ፍጻሜ የሆነው ይስሐቅ ብቻ ነበር። ርብቃ ሁለት ልጆች ወልዳለች። ዔሣው ታላቅ በመሆኑ፥ እንደ ደንቡ ከሆነ በአይሁዶችና በያዕቆብ የዘር ሐረግ ውስጥ መግባት ነበረበት። ነገር ግን አንዱ የተሻለ ወይም የከፋ በመሆኑ ሳይሆን እግዚአብሔር በሉዓላዊነቱ ስለመረጠው ያዕቆብ የተስፋ ልጅ ሆኗል። በተመሳሳይ መንገድ፥ ሥጋዊ አይሁዳዊ የሆነ ሁሉ መንፈሳዊ አይሁዳዊ አይደለም። ምክንያቱም የአብርሃምን ዓይነት መንፈሳዊ እምነት ያልያዙ አይሁዶች ሁሉ እውነተኛ አይሁዶች ስላይደሉ እነዚህ እንደ ይስሐቅና እንደ ያዕቆብ ላይሆኑ፥ እንደ እስማኤልና ዔሣው ነበሩ።

ለ. ድነት (ደኅንነት) የሚወሰነው በእግዚአብሔር ምርጫ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመረዳት እጅግ ከሚያስቸግሩ አሳቦች እንዱ እግዚአብሔር ለድነት (ደኅንነት) ሰውን በሚመርጥበትና ሰው እግዚአብሔርን በሚመርጥበት ተግባር መካከል ያለው ግንኙነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር የሚድኑትን እንደሚመርጥ፥ የእግዚአብሔር የድነት (ደኅንነት) ስጦታ ለሰዎች ሁሉ ክፍት እንደሆነና ምላሽ የሚሰጡት እንደሚቀበሉ ያስተምራል። በሰብአዊ ደረጃ እነዚህ ሁለት እውነቶች እንዴት አብረው እንደሚሠሩ አናውቅም። በዚህ ስፍራ ጳውሎስ እግዚአብሔር የሚድኑትን እንደሚመርጥና እንደሚወስን ገልጾአል። ይህ እውነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚከተለው መልኩ ቀርቧል።

 1. እግዚአብሔር ሁለቱም ከመወለዳቸው በፊት ዔሳውን ሳይሆን ያዕቆብን መርጦታል።
 2. እግዚአብሔር ለወደደው ምሕረቱን እንደሚያሳይና በጠላው ላይ ደግሞ ፍርዱን እንደሚያወርድ ለሙሴ ነግሮታል።
 3. እግዚአብሔር ፈርዖንን ወደ ሥልጣን እንዳመጣውና አይሁዶችን ላለመልቀቅ እንዲወስን እንዳደረገው ገልጾአል። ይህንንም ያደረገው በአሥሩ መቅሠፍቶችና በአይሁዶች ነፃ መውጣት ክብሩ በዓለም ላይ እንዲገን በመፈለጉ ነበር።

ሐ. እግዚአብሔር አንዳንዶችን ለድነት (ደኅንነት) በመምረጡ አድልዎ አልፈጸምም (ሮሜ 9፡19-29)። እግዚአብሔር አንዳንዶችን ለድነት (ደኅንነት) መምረጡና ሌሎችን መተዉ ፍትሐዊ አይደለም ብለን ከማጉረምረማችን በፊት፥ ጳውሎስ በሮሜ 1-3 የገለጸውን አሳብ ማስታወስ አለብን። ይህ አንዳንድ ሰዎች ለመዳን ጥረት እያደረጉ ሳለ እግዚአብሔር በሰማይ ላይ ተቀምጦ ዕጣ እያወጣ «አትድንም» ሲል የከለከለበትን ሁኔታ የሚያሳይ አይደለም። ወይም ደግሞ አንዳንዶች ለመዳን ሳይፈልጉ እግዚአብሔር አስገድዶ እንዳሳመናቸው የሚያሳይ አይደለም። ይልቁንስ ጳውሎስ ሰዎች ሁሉ ኃጢአተኞች ሆነው በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፁ አብራርቷል። ሰዎች ሊድኑ የሚችሉበት ብቸኛው መንገድ በእግዚአብሔር ምሕረት አማካኝነት ነው። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር ለአንድ ሰው ምሕረትንና ድነትን (ደኅንነትን) ለመስጠት መምረጡና ይህንኑ ተመሳሳይ ተግባር ለሌላው ሰው አለመፈጸሙ አድልዎአዊ ነው አያስብለውም።

ጳውሎስ እግዚአብሔር አንድን ሰው እየመረጠ ሌላውን መተዉ ፍትሐዊ አይደለም ለሚሉ ሰዎች በሰጠው ምላሽ፥ የሚከተሉትን እውነቶች እንዲገነዘቡ ያሳስባቸዋል።

 1. እግዚአብሔር እግዚአብሔር ነው፥ እኛ ሰዎች ግን ማንን ሊመርጥ እንደሚችልና እንደማይችል የመናገር መብት የለንም። እንዲህ ዓይነቱ ጥያቄ እግዚአብሔር ሊሆን የሚገባውንና የማይገባውን፥ ፍትሐዊ የሆነውንና ያልሆነውን የሚወስን የመጨረሻው ባለሥልጣን መሆኑን እንደዘነጋን ያሳያል።
 2. አንድ ሸክላ ሠሪ የተለያዩ ዓይነት የሸክላ ዕቃዎችን የመሥራት መብት አለው። አንዳንድ ዕቃዎች (ወጭቶች) ለምግብ ማቅረቢያ አምረው ሲሠሩ፥ ሌሎች ደግሞ ለውኃ ማምጫ ይውላሉ። እነዚህ ሸክላዎች የማጉረምረም መብት እንደሌላቸው ሁሉ፥ መለኮታዊ ሸክላ ሠሪ የፈጠራቸው ሰዎችም በእግዚአብሔር ውሳኔዎች ላይ የማጉረምረም መብት የላቸውም።
 3. ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ቁጣ የሚገባቸው ኃጢአተኞች ናቸው። የማናችንም ድነት (ደኅንነት) የእግዚአብሔርን ምሕረት እንጂ እኛ ከሌሎች ሰዎች የተሻልን መሆናችንን የሚያሳይ አይደለም። እግዚአብሔር ደግሞ አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ እንዲድኑና በመንግሥተ ሰማይ እንዲከብሩ መርጧቸዋል። የሰው ልጆች ማን እንደተመረጠና እንዳልተመረጠ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታ እንደሌላቸው መገንዘቡ ጠቃሚ ነው። አንድ ሰው «እኔ በክርስቶስ ለማመን ብፈልግም፥ እግዚአብሔር አልጠራኝም» ሊል አይችልም። ወይም ደግሞ «እገሌ ክርስቲያን ያልሆነው እግዚአብሔር ስላልመረጠው ነው» ልንል አንችልም። ልናውቅ የምንችለው ነገር ቢኖር፥ ሀ) የእግዚአብሔር የድነት (ደኅንነት) ስጦታ ለማመን ለሚፈልጉ ሁሉ ክፍት እንደሆነና «በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን ትድንማለህ» ብሎ የመስበክ ኃላፊነት ነው ያለብን። ለ) ከልባቸው የሚያምኑ ሰዎች በእግዚአብሔር እንደተመረጡ ነው። ይህ ግን የግል ውሳኔያቸው ብቻ አይደለም።
 4. በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር፥ ) በታሪክ ሕዝቡ ያልነበሩትን እንደሚመርጥ፥ ለ) የአይሁድን ቅሬታ ብቻ እንደሚያድንና በሌሎቹ ላይ እንደሚፈርድ፥ ሐ) እግዚአብሔር ከምሕረቱ የተነሣ ሁሉንም እንደ ሰዶምና ገሞራ ከማጥፋት ይልቅ አንዳንዶችን እንዳዳነ ተናግሯል።

የውይይት ጥያቄ፡- ጳውሎስ ድነት (ደኅንነት) የእግዚአብሔርም የሰውም ምርጫ እንደሆነ ያብራራበትን ሁኔታ በራስህ አገላለጽ ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ምርጫ (ሮሜ 9፡1-29)”

 1. Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply

%d