ከኃጢአት ተፈጥሯችን ጋር ያለን ግንኙነትና እግዚአብሔር ኃጢአትን እንድናሸንፍ እንዴት እንደሚረዳን መገንዘብ (ሮሜ 6፡1-7፡6)

ዘሪሁን ወደ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት የታወቀ ኃጢአተኛ ነበር። ብዙውን ጊዜ ጠጥቶ የሚሰክር ሲሆን፥ ወደ ሴተኛ አዳሪዎች ይሄድ፥ ዕጽ ይወስድና መጥፎ ዐመሉን ለማስታመም ገንዘብ ይሰርቅ ነበር። አንድ ሰው በክርስቶስ ካመነ እግዚአብሔር ኃጢአቶችን ይቅር እንደሚል ሲገለጽለት፥ ዘሪሁን በክርስቶስ አመነ። በዚህ ጊዜ የክርስቶስ ፍቅርና ጸጋ አስደነቀው፥ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ልጅ ሊመራ ስለሚገባው ሕይወት ያስተማረው ሰው አልነበረም። ዘሪሁን ኃጢአቱን እየፈጸመ የክርስቶስን ይቅርታ ከመጠየቅ የተለየ ነገር እንደማይጠበቅበት አስቦ ነበር። እግዚአብሔር ቸር ስለሆነ ኃጢአታችንን ይቅር እንደሚል እውነት ነው። ዘሪሁን ግን እግዚአብሔር የጠራው የተቀደሰ አኗኗር እንዲኖር እንደነበረ አያውቅም ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዘሪሁን ስለ እግዚአብሔር ጸጋ የተሳሳተ ግንዛቤ መያዙ ወደ ተሳሳተ ክርስቲያናዊ አኗኗር እንዴት እንደመራው ግለጽ። ለ) በሕይወትህ አሁንም ከኃጢአት ጋር እንዴት እንደምትታገል አብራራ። ገላ. 5፡16-26 አንብብና ይህ መንፈሳዊ ትግል በሕይወትህ ውስጥ እንዴት እንደታየ ግለጽ።

«የእኔ ኃጢአት የእግዚአብሔርን የይቅርታ ኃይል ካሳየ፥ ይህ የእግዚአብሔር ጸጋ በሕይወቴ የበለጠ እንዲገለጥ የበለጠ ኃጢአት መሥራት አለብኝ ማለት ነውን? ድነት (ደኅንነት) ንጹሕ ሕይወት በመኖር ሳይሆን በእምነት

ብቻ የሚገኝ የእግዚአብሔር ነፃ ስጦታ ከሆነ፥ የተቀደሰ አኗኗር የመኖር ትርጉሙ ምንድን ነው?» ጳውሎስ ስለ ድነት (ደኅንነት) የሰጠውን ትምህርት ለመረዳት በሚሞክሩበት ጊዜ የአይሁድ ክርስቲያኖች ያስቸገሯቸው ጥያቄዎች እነዚህ ነበሩ። «ብዙ ኃጢአት በሚኖርበት ጊዜ የእግዚአብሔር ጸጋ በብዛት ይገለጣል የሚለው እምነት ክርስቲያኖችን ወደ በለጠ ኃጢአት አይመራምን? ሲሉ አሰቡ (ሮሜ 5፡20)። ብዙዎቹም ግራ ተጋቡ። አንዳንድ ክርስቲያኖች የጳውሎስን ትምህርት በተሳሳተ መንገድ በመረዳታቸው ብዙ ኃጢአት በሠራን ቁጥር እግዚአብሔር ጸጋውንና ይቅርታውን እንዲያሳይ የበለጠ ዕድል እንሰጠዋለን ወደሚል አቅጣጫ ያዘመሙ ይመስላል። ስለሆነም፥ አንድ ሰው የእግዚአብሔርን ይቅርታ እስከጠየቀ ድረስ ብዙ ኃጢአት መሥራቱ አሳሳቢ አይደለም ብለው ደመደሙ። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከአባቱ ሚስት ጋር ግልጽ ኃጢአት የሚያደርግ ግለሰብ በመካከላቸው እንዲኖር በፈቀዱ ጊዜ እግዚአብሔር ለኃጢአት የሚያሳየውን ጸጋና ይቅርታ እያሳየን ነው ብለው አስበው ነበር (1ኛ ቆሮ. 5፡1-13)።

ሰዎች እግዚአብሔርን ለማስደሰት ብዙ ሰው ሠራሽ ደንቦችን መከተላቸው ትክክል እንዳልሆነ ሁሉ፥ ክርስቲያኖች የተቀደሰ ሕይወት መምራት የለብንም ብለው በኃጢአት መመላለሳቸውም አደገኛ ነው። ጳውሎስ ወንጌሉንና በመስቀል ላይ የተፈጸመውን ነገር በትክክል መገንዘቡ በንጽሕና እንድንኖር የሚያግዝ መሆኑን አመልክቷል። የእግዚአብሔር ጸጋና የኃጢአት ይቅርታው የኃጢአት ሕይወት ለመምራት ማመካኛ አይሆነንም።

የውይይት ጥያቄ፡– ሮሜ 6—7 አንብብ። ሀ) እንደ ዘሪሁን ላሉ ክርስቲያኖች ለኃጢአት አነስተኛ ግምት መስጠትና እግዚአብሔር ይቅር ይለኛል በሚል አሳብ በኃጢአት መቀጠሉ ስሕተት የሆነበትን ምክንያት ጠቅለል አድርገህ ግለጽ። ለ) ይህ ክፍል ስለ አማኝና ስለ ኃጢአት ምን ያስተምራል?

በ ሮሜ 6፡1-8፡39 ውስጥ ጳውሎስ ወንጌሉ የተቀደሰ ሕይወት እንድንኖር እንዴት እንደሚረዳን ያብራራል፡፡ ሮሜ 1-5፥ «አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ሕይወቱን የሚያስተካክለው እንዴት ነው? እንዴትስ እርሷ ልትድን ወይም ሊድን ይችላል?» ለሚለው ጥያቄ ጳውሎስ መልስ በመስጠት ላይ ነበር። አሁን በሮሜ 6-8 ጳውሎስ፥ «ከዳንሁ በኋላ፥ ከኃጢአት ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ይኖረኛል?» የሚለውን ጥያቄ ሲመልስ፥ በሦስት እውነቶች ላይ አተኩሯል። አንድ ሰው በክርስቶስ ላይ እውነተኛ እምነት ሲኖረው የሚከተሉት ነገሮች ተግባራዊ ይሆናሉ።

1) በክርስቲያኖች ላይ የሚኖረው የኃጢአት ኃይል ስለተሰበረ እንደ ቀድሞው ኃጢአትን ለመፈጸም አንገደድም። ከኃጢአት ቁጥጥር ነፃ ነን።

2) አሁን ክርስቶስን ለማስከበር በመሻት ባሪያዎቹ ሆነን እንመላለሳለን። የተቀደሰ ሕይወት በመኖር ክርስቶስን እናስከብራለን።

3) እግዚአብሔር የሚሰጠን መንፈስ ቅዱስ የተቀደሰ ሕይወት የምኖርበትን ኃይል ይሰጠናል። ከእንግዲህ ኃይል አጥተን በኃጢአታችን አንቀጥልም። በሕይወታችን ኃጢአትን አሸንፈን በቅድስናና ክርስቶስን በመምሰል ልናድግ እንችላለን።

ከኃጢአት ተፈጥሯችን ጋር ያለን ግንኙነትና እግዚአብሔር ኃጢአትን እንድናሸንፍ እንዴት እንደሚረዳን መገንዘብ (ሮሜ 6፡1-7፡6)

ጳውሎስ የሚከተሉትን ዐበይት ነጥቦች በማቅረብ ለምን በኃጢአት ሕይወታችን ልንቀጥል እንደማንችል የሚከራከርበት መንገድ ውስብስብ ነው።)

ሀ. በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት፥ በክርስቶስ ባመንህ ጊዜ ከእርሱ ጋር ተዋህደሃል። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ አንተም ለአሮጌው የኃጢአት ሕይወትህ ሞተሃል። ክርስቶስ ለአዲስ ሕይወት በተነሣ ጊዜ፥ አንተም እግዚአብሔርን ለምትታዘዝበት አዲስ ሕይወት ተነሥተሃል (ሮሜ 6፡1-11)። ክርስቶስ በመስቀል ላይ እንደ ሞተ ሁሉ፥ አንተም በክርስቶስ ላይ ባለህ እምነት ለአሮጌው ሕይወትህ ሞተሃል (ተሰቅለሃል)። በዚያን ጊዜ በሕይወትህ ላይ የነበረው የኃጢአት ኃይልና የበላይነትም ሞቷል። ከእንግዲህ፥ «የኃጢአት ባሪያ» አይደለህም። ክርስቶስ የሞትን ኃይል አሸንፎ ከሞት እንደ ተነሣ ሁሉ፥ አንተም ኃጢአት ጨርሶ ለተደመሰሰበት ለአዲስ ሕይወት ከሞት ተነሥተሃል። አሁን ሕይወትህን ለእግዚአብሔር እየታዘዝህ የመኖር ነጻነት አለህ።

ጳውሎስ ይህንን አማኙ ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጋር የሚተባበርበትን ሁኔታ «በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ መጠመቅ» ሲል ይጠራዋል። ይህ አገላለጽ የሚያሳየው የአማኙን የመጀመሪያ የድነት (ደኅንነት) ልምምድ እንጂ የውኃ ጥምቀት አይደለም። አሁን በአብያተ ክርስቲያናችን አንድ ሰው በክርስቶስ ካመነ በኋላ እስኪጠመቅ ድረስ ለስድስት ወራት ወይም ለአንድ ዓመት የክትትል ትምህርት እንዲወስድ ይደረጋል። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ግን ከዚያ በተቃራኒ ያመኑትን ወዲያውኑ ታጠምቅ ነበር። ስለሆነም፥ አዲስ ኪዳን ብዙውን ጊዜ እምነትንና ጥምቀትን አንዳንድ ክስተት አጠቃልሎ ድነት (ደኅንነት) ሲል ይጠራዋል (የሐዋ. 2፡38)።

ጳውሎስ በእምነት ወደ ክርስቶስ በተመለስን ጊዜ የተከሰተውን ሁኔታ ለመግለጽ የድርጊት ፈጻሚ የኃላፊ ጊዜ መግለጫ ግሥ ይጠቀማል። ብናስተውለውም ባናስተውለውም፥ በሕይወታችን ተግባራዊ ብናደርገውም ባናደርገውም፥ በሞቱና በትንሣኤው ከክርስቶስ ጋር ተባብረናል። በመሆኑም፥ አሁን የኃጢአት ተፈጥሯችን ስለማይቆጣጠረንና ለመታዘዝ ልንመርጥ ስለምንችል፥ ኃጢአትን መፈጸም የለብንም።

በሕይወታችን ኃጢአትን ድል የምናደርግበት የመጀመሪያው እርምጃ ኃጢአት የመፈጸም ግዴታ እንደሌለብን ማወቅ ነው። ጳውሎስ ለኃጢአት ሞተን በክርስቶስ በኩል ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደሆንን እንድንቆጥር መክሮናል (ሮሜ 6፡11)። ለእግዚአብሔር ንጹሕ ሕይወት ለመኖር አንችልም ብለን ካሰብን፥ ሰይጣንና የኃጢአት ተፈጥሯችን በቀላሉ ያሸንፉናል። ነገር ግን እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ልንመርጥ እንደምንችል ካወቅን፥ ኃጢአትን ለማሸነፍና በቅድስና ለማደግ የመጀመሪያውን እርምጃ ወስደናል ማለት ነው።

ለ. አማኞች ከኃጢአት ቁጥጥር ነፃ ስለሆንን፥ እግዚአብሔርን ለመታዘዝ፥ የተቀደሰ ሕይወት ለመምረጥና የጽድቅ ባሪያዎች ለመሆን የመምረጥ ብቃት አለን (ሮሜ 6፡12-23)። ጳውሎስ ከኃላፊ የጊዜ መግለጫ ጊዜ ወደ ቀጣይ የአሁን ጊዜ መግለጫ ግሥ መሸጋገሩን ማጤኑ ጠቃሚ ነው። ይህም ባለማቋረጥ ልንፈጽመው የሚገባን ቀጣይነት ያለው ትእዛዝ እንደ ሰጠን ያሳያል። በሕይወታችን ላይ ያለውን የኃጢአት ኃይል የመግደል ኃላፊነት ባይኖርብንም (ባመንን ጊዜ እግዚአብሔር ይህንኑ ስላደረገ)፥ በሕይወታችን ኃጢአትን ስለምናስተናግድበት ሁኔታ ግን ኃላፊነት አለብን። ጳውሎስ በኃጢአት ላይ ድል ማግኘታችን የሚወሰነው በምርጫችን እንደሆነ ያስረዳል። መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ትእዛዝ በሚሰጠን ጊዜ ሁሉ ምርጫ ልናደርግና የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንድናበረክት ያዘናል። ጳውሎስ አማኞች ባለማቋረጥ ሊፈጽሟቸው የሚገሷቸውን ሦስት ተግባራት ዘርዝሯል።

  1. መሻቱን ታሟሉለት ዘንድ ኃጢአት በሰውነታችሁ አይንገሥ። በጥንት ዘመን ሁለት ዓይነት ባሪያዎች ነበሩ። እነዚህም ያለ ምርጫቸው በትውልድ ባሪያዎች የሆኑና ለሚወዱት ሰው በራሳቸው ምርጫ ባሪያዎች የሆኑ ነበሩ። ጳውሎስ እግዚአብሔር በክርስቶስ ባመንን ጊዜ ለክፉ የኃጢአት ተፈጥሯችን በግድ ከምንገዛበት ሁኔታ እንዳወጣን ያስረዳናል። አሁን በፈቃዳችን የጽድቅ ባሪያዎች መሆን አለብን። እንደገና ለዚያ ክፉ የኃጢአት ተፈጥሮ ባሪያ መሆን ሞኝነት ነው። የኃጢአት ተፈጥሯችን ወደ ኃጢአት እንዲወስደን በምንፈቅድበት ጊዜ ሁሉ ባሪያዎቹ ለመሆን ፈቅደናል ማለት ነው።
  2. ብልቶቻችሁን ለኃጢአት አታቅርቡ። ሰይጣንም ሆነ የኃጢአት ተፈጥሯችን ኃጢአትን እንድናደርግ ከመፈተን አልፈው ሊያስገድዱን አይችሉም። ኃጢአትን የምንፈጽመው በምርጫችን ነው። ይህ ከአይጥ ወጥመድ ጋር ተመሳሳይ ነው። አይጥ ወደ ወጥመዱ እንድትገባ የሚፈትናት ምግብ እንጭምራለን እንጂ አይጧን በግድ በወጥመዱ እንድትያዝ ልናስገድዳት አንችልም። አይጧ ልትያዝ የምትችለው በፈተናው የተሸነፈች እንደሆነ ብቻ ነው። ጳውሎስ በፈተናው ወድቀን ሰውነታችንን ለኃጢአት እንዳናስገዛ ይመክራል። ምናልባትም ጳውሎስ የሚያስበው ብዙ ክርስቲያኖችን ስለሚፈትነው የወሲብ ኃጢአት ይሆናል።

በኃጢአት ላይ ድልን ለመቀዳጀት የሚያስችል ሁለተኛው እርምጃ እንደገና የኃጢአት ባሪያ ላለመሆን መወሰን ነው።

  1. ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ። ኃጢአት በባርነት እንዲገዛን ከማድረግ ይልቅ እንደ ጻድቅ ባሪያዎች ራሳችንን ለእግዚአብሔር ማቅረብ ይኖርብናል። ለእርሱ ካለን ፍቅር የተነሣ በፈቃዳችን ለእግዚአብሔር ባሪያዎች መሆን ይኖርብናል። ይህንንም የምናደርገው እንድ ባሪያ ጌታውን ለማስደሰት እንደሚኖር ሁሉ በየቀኑ እግዚአብሔር የሚፈልገውን በመፈጸም ነው። የኃጢአት ተፈጥሮ ከሚመራን መንገድ እየራቅን፥ እግዚአብሔር የሚፈልጋቸውን ነገሮች ማከናወን አለብን። ኃጢአት ሁልጊዜም ጥፋትን ያስከትላል። ለምሳሌ ያህል፥ ግንኙነቶችን፥ ባሕርይን፥ ቤተሰብን ያጠፋል።) ስለሆነም፥ ወደ ሕይወትና ቅድስና የሚወስደውን እግዚአብሔርን የመታዘዝ አቅጣጫ ልንከተል ይገባል። በኃጢአት ላይ ድልን ለመቀዳጀት የሚያስችለን ሦስተኛው እርምጃ እግዚአብሔርን ለመታዘዝና እርሱን ለማክበር ሕይወታችንን አሳልፎ መስጠት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ወሲባዊ ኃጢአት ለመፈጸም ተፈትነሃል እንበል። ጳውሎስ የገለጻቸውን ሦስት ደረጃዎች በመከተል፥ ይህን ፈተና እንዴት ትቋቋመዋለህ?

ጳውሎስ አማኞች በክርስቶስ በማመናቸው ምክንያት ያገኙትን ሕይወት ካገባች ሴት ጋር ያነጻጽረዋል። ባሏ በሕይወት እስካለ ድረስ ሴቲቱ በታማኝነት አብራው ልትኖር ይገባል። እርሷም ሆነች እርሱ ወሲባዊ ታማኝነት ሊኖራቸው እንደሚገባ «የጋብቻ ሕግ» ያዛል። ነገር ግን ባለቤቷ በሚሞትበት ጊዜ ወሲባዊ ግንኙነቱን የሚቆጣጠረው የጋብቻ ሕግ ይለወጣል። ባሏም ከእንግዲህ በእርሷ ላይ ቁጥጥር አይኖረውም። በዚህ ጊዜ ሌላ ባል ብታገባ አመንዝራ አትባልም።

በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ከመዳናችን በፊት በኃጢአት ተፈጥሯችን «ሕግ» እንገዛ ነበር። (በዚህ ስፍራ «ሕግ» የሚያመለክተው ብሉይ ኪዳንን ሳይሆን፥ የክፉ ተፈጥሯችንን ኃይልና ፍላጎት ነው።) በዳንን ጊዜ ግን ከዚያ የኃጢአት ተፈጥሮ ቁጥጥር ነፃ ወጥተናል። ምክንያቱም በእኛ ላይ የነበረው ኃይሉ ሞቷልና። አሁን አዲሱ ባላችን የሆነውን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በማስደሰት ልንመላለስ እንችላለን።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “ከኃጢአት ተፈጥሯችን ጋር ያለን ግንኙነትና እግዚአብሔር ኃጢአትን እንድናሸንፍ እንዴት እንደሚረዳን መገንዘብ (ሮሜ 6፡1-7፡6)”

  1. Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading