፩. አማኞች ለሰብአዊ መንግሥታቸው ይጸልያሉ፥ ይታዘዛሉ (ሮሜ 13፡1-7)
እንደ ወንጌላዊያን ክርስቲያኖች ከመንግሥትና ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የቀረበ ግንኙነት የለንም። በቀደመው ሥርዓት የስደት ምንጮች ሆነው እሠቃይተውናል። አሁን ድምፅ የመስጠት ዕድል ሲሰጠን ደግሞ ብዙ አማኞች ድምፅ ለመስጠት ፈቃደኞች አይደሉም። ለአገልግሎት ሲጠይቁንም አዎንታዊ ምላሽ አንሰጥም። ከመንግሥት በመራቃችን ደስ የምንሰኝ ይመስላል።
ጳውሎስ ግን ከመንግሥት ጋር የጠበቀ ግንኙነት ሊኖረን እንደሚገባ ይመክራል። ጳውሎስ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ብዙ ጊዜ ስደት እንደደረሰበት አስታውስ። በሮሜ መንግሥት ለአራት ዓመታት ታስሮ ወደ ሚቆይበት የወኅኒ ቤት ይገባ ነበር። ጳውሎስ የሮሜን መልእክት ከጻፈ ከአሥር ዓመታት ያህል በኋላ የሮም ንጉሥ የሞት ቅጣት ፈርዶበታል። ይህም ሆኖ፥ ጳውሎስ ክርስቲያኖች ለመንግሥት መልካም አመለካከት እንዲኖራቸው አስተምሯል። ለምን? ምክንያቱም ኮሚኒስትም ይሁን እንደ የኔሮ ዓይነት ክፉ መንግሥት ይሁን ወይም ጥሩ መንግሥት የትኛውም መንግሥት በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር ነው። ስለሆነም መንግሥትን መቃወም ማለት የእግዚአብሔርን ፈቃድ መቃወም ማለት ነው። እንግዲህ፥ ክርስቲያኖች ከመንግሥት ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል? ጳውሎስ አያሌ ነገሮችን ጠቃቅሷል።
ሀ. ለመንግሥት ባለሥልጣናት መገዛት አለብን። እነዚህ ባለሥልጣናት መጽሐፍ ቅዱስን በቀጥታ እስካልተቃወሙ ድረስ (የሐዋ. 5፡27-29ን አንብብ።)፥ ሕግጋቱን ባንወዳቸውም እንኳ መፈጸም አለብን። መንግሥት እግዚአብሔር ሕግንና ሥርዓትን ለማስከበር፥ የማኅበረሰቡ እንቅስቃሴ እንዳይደናቀፍ ለማገዝና የክፋትን ስርጭት ለመቋቋም ሲል የመሠረተው ተቋም ነው። ለመንግሥት አለመታዘዝ ማኅበረሰቡን ወደ ሁከት፥ ውድመትና ክፋት ይመራል።
ለ. ቀረጥ መክፈል አለብን። ብዙ ክርስቲያን ነጋዴዎች ለመንግሥት ቀረጥ አይከፍሉም። ጳውሎስ ግን ይህ ስሕተት እንደሆነ ያስረዳል። ሁላችንም መንግሥት የሚያሠራቸውን መንገዶች፥ ትምህርት ቤቶች፥ ሆስፒታሎች፥ ወዘተ… ስለምንጠቀም፥ ለእነዚህ ወጭዎች መሸፈኛ የሚያግዝ ቀረጥ መክፈል አለብን።
ሐ. ክርስቲያኖች መሪዎቻቸውን ማክበር አለባቸው። ጳውሎስ የሚናገረው ስለ ክርስቲያን የመንግሥት መሪዎች ወይም ስለ ጥሩ መሪዎች አይደለም። እርሱ የሚናገረው ብዙውን ጊዜ የራስ ወዳድነት አመለካከት ስላላቸው ክርስቲያን ያልሆኑ መሪዎች ነው። ጳውሎስ ሰዎቹ ጥሩ ናቸው ብለን በማሰባችን ሳይሆን እግዚአብሔር ለመሪነት እንዳስነሣቸው በመገንዘባችን ሁልጊዜም ልናከብራቸው እንደሚገባን ያብራራል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ ለመንግሥት መሪዎች ያለውን አመለካከት ከእኛ አመለካከት ጋር አነጻጽር። ለ) በ1ኛ ጢሞቴዎስ 2፡1-2 ለባለሥልጣናት እንድንጸልይ ተነግሮናል። ቤተ ክርስቲያንህ ይህንን የምታደርገውና ክርስቲያኖች በቀዳሚነት ለመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲጸልዩ የምታበረታታው እንዴት ነው? ሐ) በቀበሌህ፡ በወረዳህ፥ በክልልህና በፌዴራል ደረጃ ሥልጣን ላይ ያሉትን መሪዎች ስም ዘርዝር። አሁን ጊዜ ወስደህ ለእነዚህ ሰዎች ጸልይላቸው።
፪. የአማኙ ሕይወት በቅርብ በሚሆነው የኢየሱስ መመለስ ብርሃን ሊታይ (ሮሜ 13፡8-13)
ድነት (ደኅንነት) በምናገኘበት ጊዜ የሕይወታችን ክፍሎች በሙሉ መለወጥ አለባቸው። ጳውሎስ የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን ምክንያት የሚለወጡትን ነገሮች ዘርዝሯል።
ሀ. ክርስቲያኖች የተበደሩትን ገንዘብ ሁሉ ሊክፍሉና በተቻለ መጠን ከብድር የጸዳ ሕይወት መምራት አለባቸው። ከሰው ገንዘብም ሆነ ሌላ ነገር ተበድሮ ለመክፈል እየቻሉ ቸል ማለቱ የክርስቲያናዊ ፍቅር ምልክት አይደለም። ይህ ዓለም በሰዎች ትከሻ ላይ ሆኖ ለመጠቀም የምትከተለው አሠራር ነው።
ለ. ከሕግጋት ዝርዝሮች ይልቅ በአመለካከታችን ላይ ልናተኩር ይገባል። አመለካከቶቻችንም አጠቃላይ ግንኙነቶቻችንን፥ ማለትም ባልንጀራን መውደድ (ክርስቲያኖችንም ሆነ ክርስቲያኖች ያልሆኑትን)፥ ለራሳችን የምናደርገውን ያህልና ሌሎችም እንዲያደርጉልን የምንፈልገውን ጥንቃቄ ለእነዚህ ወገኖች ማድረግ፥ ወዘተ… ያጠቃልላሉ።
ሐ. ክርስቲያኖች ክርስቶስ ዛሬ እንደሚመለስ እያሰቡ ይኖራሉ። ስለሆነም፥ ሕይወታችን ክርስቶስ ሊያጠፋው የመጣበትን የዓለምን ክፋት ከሚያንጸባርቁ ነገሮች ሁሉ ተለይቶ በንጽሕና ሊያዝ ይገባል። ጳውሎስ ክርስቶስን እንድንለብስ አዞናል። ጳውሎስ ይህን ሲል በአመለካከታችንም ሆነ በተግባራችን ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እንድናደርጋቸው የሚፈልገውን ነገሮች ብቻ እንድናደርግ መጠየቁ ነው። አሁንም ጳውሎስ የምናስባቸውን ነገሮች እንድንቆጣጠር ማሳሰቡን አስተውል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ እንደ አማኝ ስለመመላለስ ባስተማረው መሠረት፥ አዳዲስ ክርስቲያኖችን ማስተማር የሚያስፈልገው ስለ ምንድን ነው? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ ለአዳዲስ አማኞች የምታስተምረው ምንድን ነው? ይህንን ጳውሎስ ካስተማረው ጋር አነጻጽር። ጳውሎስ ለክርስቲያን ሕይወት አስፈላጊ ነው ብሎ ያስተማረውን ሃሳብ ለመከተል ይቻል ዘንድ የቤተ ክርስቲያንህን ትምህርት ለመለወጥ ምን ሊደረግ ይገባል?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)
Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት